By | August 9, 2018


በሱማሌ ክልል የፌዴራልና የጦር ጄነራሎች ጣልቃ ገብነት

Via Rajo, Hagayya 9, 2018

ፖለቲከኞችና ዳየፐርስ (diapers) የሚያመሳስላቸው አንድ ባህሪ አላቸው፡፡ሁለቱም በየግዜው ለተመሳሳይ ምክንያት መቀየር አለባቸው፡፡ የሱማሌ ክልል ከሌላው በተለየ የነበረብን ዋንኛ ችግር አብዲ ኢሌ ሌሎች አስር የቀደሙት መሪዎች በአማካይ አንድ አመት ሲቆዩ እሱ በፕሬዝዳንትነት 8 ዓመት በፀጥታ ዘርፍ ኃላፊነት ደግሞ 2 ዓመት ቆይቷል፡፡ እነዝያ 10 ፕሬዝዳንቶች የሥልጣን ግዜያቸውን ሳይጨርሱ እንዲነሱ የተደረገበት ዋንኛ ምክንያት የነበረው የፌዴራልና የጦር ጄነራሎች ጣልቃ ገብነት መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ለምን ፌዴራልና የጦር ጄነራሎች በአብዲ ኢሌ ላይ ሊረጋጉ ቻሉ?

በተለይ የጦር ጄነራሎች አብዲ ኢሌ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ሆኖ አብረው በመስራታቸው የሚፈልጉትን አይነት ሰው እንደሆነ ለማመን በቅተዋል፡፡ ከዝያ በኃላ እሱን ሥልጣን ላይ ማቆየትና በትረ-ሥልጣኑን ከሁሉም አካል መጠበቅ ዋንኛ ሥራቸው ሆነ፡፡ የቀድሞ የደህንነት ኃላፊው አቶ ጌታቸው አሰፋ አብዲ ኢሌን ለማንሳት ብዙ ተግተዋል ነገር ግን ከጦር ጄነራሎች በኩል ባገኘው ድጋፍ መሰረት የተነሳበትን ተቃውሞ ሊያከሽፍ መብቃቱ ይነገራል፡፡አቶ ጌታቸው አብዲ ለሀገሪቱ ህልውና ጠንቅ ሊሆን እንደሚችል ያምን ነበር፡፡ ምን ያደርጋል በመጨረሻ ሰዓት ላይ የቄሮዎችና ፋናዎች ትግል ሲበረታበት ግዜ ከአብዲ ኢሌ ጋር በመስማማት ከ1 ሚልዮን በላይ ኦሮሞዎችና ሱማሌዎች እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡

የጦር ኃይሉ ከአብዲ ያገኙት ነገር ቢቆጠር አይዘለቅም፡፡ በደፈናው ምን ያላገኙት ነገር አለ ማለት ይቀላል፡፡ አብዲ ኢሌ ሌላው ቀርቶ መከላከያ መዋጋት ያለበትን ጦርነት እስከ ሶማሊያ ዘልቆ ተዋግቷል፡፡ የአንድ ክልል ፖሊስ እንደሚታወቀው ከክልሉ ያለፈ ተግባር መፈፀም የለበትም፡፡ የኛዎቹ ጉዶች ግን ሶማሊያ ገብተው የተዋጉት አል ሸባብን ብቻ ሳይሆን በዘር ከተጧላቸው ጎሳዎች ጋርም ነው፡፡ የገንዘብ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡ የፀጥታ ዘርፍ በጀት የክልሉን በጀት 60-70 % ይሸፍናል፡፡ ይህ ሂሳብ የሚወራረድበት በጀት አይደለም፡፡ ስለዝህ ሁሉም የፌዴራል ባለስልጣን ጅግጅጋ ከሄደ ዋንኛው ስጦታው ቦርሳ ሙሉ ብር እንደሆነ ሁሉም ይረዳዋል ብለን እናስባለን፡፡ አንዳንዴ ግን አብዲ ኢሌ ሌላም ነገር ያደርጋል፡፡ የቀድሞ ጠ/ሚ ሀማደ ሚስት ጅግጅጋ ሲትመጣ አብዲ ኢሌ የሱማሌ ባህል ነው በማለት 2 ኪ.ግ ወርቅ ጀባ ብሏታል፡፡ እሷም ውለታ ለመመለስ ጠ/ሚ ሀማደ በፓርላማ አብዲ ኢሌ ለሱማሌ ክልል ያመጣውን ለውጥ በተለይ በውሃ ላይ በመግለፅ ሌሎች ክልሎች የሱን ፈለግ እንድከተሉ ጠይቀዋል (ይሄ ቀልድ አይደለም እውነት ነው!) የኮንትራባንድና ሌሎች የዶላር ዝውውር ጉዳዮች ሁሉም ስለሚያውቀው ማንሳት አስፈላጊ አይደለም፡፡

በአጭሩ ለማለት የፈለግነው አብዲ ኢሌ በስልጣን ሲቆይ ክልሉ የራሱ ንብረት አድርጎ ወሰደው፡፡ መግደል፣ ማሰር፣ መዝረፍ፣ ሁሉንም ንግዶች በዘመዶቹ ቁጥጥር ስር ማድረግ፣ ስልጣኑን ለመርሲንና አቅራቢያው ላሉ ሰዎች መስጠት ራሱ ብቻ የሚያዝበት ሆነ፡፡ “የበላ አፍ ያፍራል” ሱማሌዎች እንደሚሉት በሚደረገው ጉዳይም ፌዴራል አላየሁም አልሰማሁም አለ! ህዝቡም ነገን ለመኖር ግማሹ ተሰደደ ሌላውም ዝምታን መረጠ ሌለኛው ደግሞ ይኸው ሄጎ ሆኖ ለዛሬው ጥፋት ዳርጎናል፡፡

የወቅቱ ጥያቄ የሆነው አብዲ ኢሌ የሾመውን ጣቱን የሚጠባ እንድሁም የሄጎዎች የጎበዝ አለቃ በመሆን ላለፉት ቀናት ጦርነት በአገሪቷ ላይ በማወጅ ነፍስ እንድጠፋ፣ ቤተክርስትያናት በውስጣቸው ካሉት ምእምናንና ቀሳውስት ጋር እንድቃጠሉ፣ ንብረት እንዲዘረፍ ያደረገውን ሰው እንዴት አድርገን ፕሬዝደንት ልንለው እንችላለን? የሄጎዎች ጎበዝ አለቃ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ በመሆኑ ለህግ ሊቀርብ ይገባል!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.