By | March 21, 2018


የሰላማዊ ትግል ይዘት!

ከጨዋቃ ከለቾ, የካቲት 2010   

Landscape in Oromia, suburb of Finfinne

Bitootessa 21, 2018

ዛሬ በኢትዮጵያ  ውስጥ ያሉ ጭቁን ሕዝቦች በሰላማዊ መንገድ ለሚያደርጉት የትግል ሂደት ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከፍለዋል።  ወጣት ሽማግሌ፥ ወንድ ሴት ሳይል ሁሉም በያለበት ላደረገው ሰላማዊ ተሳትፎ፥ በገዢው ህወሓት ምላሹ፥ ድብደባ፥ እስር እና ሞት መሆኑ በገሀድ ይታያል።  በተደጋጋሚ በጭቁን ሕዝቦች ላይ የደረሰው ስቃይና በደል ተመሳሳይና አንድ ወጥ ባሕርይ ስላላቸው፥ አጠቃላይ ገጽታውን ለመቃኘት እንሞክር።  በተለይ ያለፈውን የትግል ውጣ ውረድ ማስታወሱ፥ ያለንበትን የትግል ይዘት ጉዞ፥ ለማጠናከር ይረዳናል።  በዚህ አኳያ ትላንት በጨቋኝ ገዢዎች ከተወሰዱት ኢ-ዲሞክራሲያዊ ፀረ-ሕዝብ ድርጊቶች በመነሳት፥ አብይ የሆኑትን መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች እንመልከት።

  1. ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን የተከተለ፥ ነፃ የሕዝብ ምርጫ ሂደት አለመኖር፦
  2. ጭቁን ሕዝቦች፥ በመሬታቸው ላይ፥ የባለቤትነት መብታቸው፥ በግልጽ መደፈር፦
  3. በሐይማኖት ጉዳይ “የመንግሥት” ጣልቃ ገብነት፥ መንፈሳዊ ነፃነትና ሰላም አለመስፈን፦
  4. የብሔር ብሔረሰቦች፥ ራስን በራስ የማስተዳደር፥ ዲሞክራሲያዊ መብት በተግባር

ሥራ ላይ አለመዋል ወዘተ —ናቸው።

ኢትዮጽያ የብዙ ሕዝቦች ሀገር እንደመሆኗ፥ የአያሌ ሕዝቦች ቋንቋ፥ ታሪክ፥ ባሕልና ቅርጽ የሚንፀባረቅባት፥ የታላላቅ ሐይማኖቶች፥ የክርስትና የዋቃና የእስልምና እምነቶች፥ ለብዙ ዘመናት በሕዝቡ መሀከል የኖሩባት ነች።  ያለ መታደል ሆኖ፥ ለረዥም ጊዜ በጭቁን ሕዝቦች ላይ የተፈራረቀው የጭቆና ሥርዓት፥ ለዚህ መራር ትግል አድርሶናል።  ጭቁን ሕዝቦች መብታቸው ተገፎ፥ ቋንቋቸው ተረግጦ፥ ከገዛ መሬታቸው ተፈናቅለው፥ በስቃይ፥ በድህነትና በስደት የኖሩ “ዜጐች” ናቸው።   በሽዎች የምቆጠሩ ደሀ ገበሬዎችና ወጣቶች ያለ ውዴታቸው ተገደው፥ ጨቋኞች በፈጠሩት ጦርነት ውስጥ ተማግደዋል።

አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥ በአምባገነን የህወሓት ገዢ ወገኖች ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት፥ በጭቆና ሰንሰለት ሥር ይገኛሉ።   በገሀድ የታወቀው ሐቅ፥ ከ26ዓመታት በላይ፥ የህወሓት ገዢዎች፥ ጭቁን ሕዝቦችን በመሣሪያ ሃይል፥ ተጭነው ኖሯል።   በዚህ ረዥም የህወሓት የጭቆና ዘመን፥ ብዙ ተቃዋሚ ቡድኖችና ግለሰቦች ታስረዋል፥ ተገድለዋል፥ ከሀገሪቷ የፖለቲካ ሂደት ታግደዋል፥ ከሀገር ተሰደዋል።  ከሞት የተረፉት፥ የነቁና ተራማጅ የሕብረተሰቡ አባላት፥ በየጊዜው በምደርስባቸው ስቃይ፥ እስር ቤታቸው ከሆነ ቆይቷል።

ባለፉት 26 ዓመታት የተፈጸሙትን ፀረ-ሕዝብ ድርጊቶች ለመዘርዘር ባልችልም፥ ከዋነኞቹ የምርጫ ፈተናዎች መሀከል፥ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ለመግለጽ እፈልጋለሁ።

የመጀመሪያው የህወሐት የፖለትካ «ምርጫ ጫወታ» የተጀመረው በሽግግር መንግሥቱ ምስረታ ዋዜማ በ1984/1992 ነበር።  በቻርተሩ ዓላማ መሠረት፥ ለምርጫ የተዘጋጁት ተሳታፊዎች፥ በተለይ የኦሮሞ ድርጅት እጩዎች፥ አብዛኞቹ በህወሓት ሰራዊት ተይዘው እስር ቤት ገቡ።  የታሰሩትን ለማስፈታት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀረ።  በመጨረሻ ነፃ የሆኑት የኦሮሞ ድርጅቶች በሙሉ፥ ከህወሓት የምርጫ ድራማ ራሳቸውን አገለሉ።  ህወሓትና ጭፍሮቹ ብቸኛ የውሸት ምርጫ አሸናፊዎች ሆኑ።   የኦሮሞ ድርጅቶች በሽብርተኝነት ተወንጅለው፥ በጠላትነት ተወገዙ፥ ታሰሩ፥ ተገደሉ፥ ተሰደዱ።

በ1989/1997 ከ5 ዓመታት በኃላ የተቃዋሚ ድርጅቶች በተለይ በቅንጅት አስተባባሪነት፥ ያደረጉት የምርጫ ተሳትፎ፥ በተመሳሳይ ሁኔታ እንደገና በህወሓት ተቀለበሰ።  በብዙ ሽህ የምቆጠሩ የቅንጅት ደጋፊዎች ህወሓትን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ።   በህወሓት ወደ 200 የምጠጉ ሰዎች በአደባባይ ተረሸኑ። በዚሁ ተቃውሞ፥ በወቅቱ የቅንጅት መሪዎች ለእስር ተዳረጉ።  ህወሓት ኢ-ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ፥ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር፥ የተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ፥ ግፊትና ተጽዕኖ በማድረግ፥ ከማንኛውም የሀገሪቷ «የምርጫ ሂደት» አስወግዷል።

የተቃዋሚ ሃይሎች፥ ካለፈው ፀያፍ ታሪክ በመማር፥ በጊዜው አስከፊ ሁኔታ ላይ ትኩረት በማድረግ፥ ለአስተማማኙ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ትግላችንን ማፏፏም ይገባል።  የሕዝቦችን ዘላቂ ነፃነት ለማረጋገጥ፥ የጭቁን ሕዝቦችን የትግል ይዘት፥ የደረሰበትን ደረጃ፥ መለስ ብሎ መዳሰስ ያስፈልጋል።  የትግል ሂደታችንን በይበልጥ ወደፊት ለማራመድ፥ የትግላችንን ጥንካሬና ድክመት በሰፊው በማጤን፥ በጋራ የትግል ዓላማ ሥር መጠናከር አለብን።  ከየት ተነስተን የት እንደምንደርስ ማወቅ ይኖርብናል።  የአጭርና ረዥም ጉዞአችንን ሂደት ግምት ውስጥ በማስገባት፥ መጨረሻው ግባችን ይታውቃል።  በጉዞአችን ውስጥ የሚያጋጥመንን መሰናክል፥ የመጓጓዣ፥ የስንቅ፥ ወዘተ—አጠቃላይ እጥረቶችን በሙሉ፥ በጥያቄ ውስጥ ሳላስገባ ነው።  ለዚህ ሁሉ መሠረታዊ ድጋፍ የሰው ሃይል፥ የገንዘብና የእውቅ ሰዎችን ጠቃሚ ምክር፥ መቀበልና ማስተናገድ ይገባናል።  በትግል ሂደት ውስጥ ከትምህርትና የትግል ልምድ የቀሰምናቸውን መልካም አስተሳሰቦችን፥ እንደ አስፈላጊነቱ በተግባር ሥራ ላይ ማዋል፥ ይጠቅማል እንጅ አይጐዳም።

በሕዝቦች ትግል ሂደት ውስጥ፥ ሁሉም የራሱ የትግል ውጤት መመዘኛ አለው።   የሰላማዊ ትግል ውጤትን፥ ደረጃ በደረጃ አመዛዝኖ፥ ጠለቅ አድርጐ ማየቱ ይጠቅማል።  ያለ ቅጥ፥ በከንቱ፥ የሕዝቦች መስዋዕትነት ከበዛ፥ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል።  መታወቅ ያለበት ዋናው ቁም ነገር፥ የሕዝቡን ልብና አዕምሮ የማረከ፥ የትግል ሂደት፥ ምን ጊዜም አይወድቅም።

በሌላ አቅጣጫ ሁሉገብ የትግል ስልትን አማራጭ ያደረጉ፥ በተለይ የትጥቅ ትግልን ስልት መርሆ በዋናነት ያስቀመጡ፥ ብቃትና ልምድ ያላቸው ነባር ሃይሎች(ድርጅቶች) ሕቡዕና ግልጽ እንቅስቃሴዎች፥ ጐላ ብሎ በአደባባይ አልታዩም።  እነዚህ ነባር የሕዝብ ሃይሎች የትግሉን ሂደት ጠቀሜታና ተግባራዊነት በመረዳት፥ የሕዝቡን የልብ ትርታ አመዛዝኖ፥ ወሳኝ ሕዝባዊ የድጋፍ እርምጃ እንደምወስዱ ተስፋ አለኝ።

ባለፉት 3 ዓመታት የቄሮና የፋኖ ወጣቶች ሰላማዊ ኒቅናቄ፥ አሁን ለደረስንበት የትግል ደረጃ አድርሶናል።  እነዚህ ታጋይ ወጣቶች ያለ መሣሪያ ሃይል፥ በሰላማዊ መንገድ ያሰሙት ተቃውሞ፥ በሕዝቡ መሀከል ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል።  በዚህ ትግል ሂደት ውስጥ፥ በሽዎች የምቆጠሩ ሕይወታቸውን ሰውተዋል።  የቄሮና የፋኖ የትግል ሂደት፥ በዚህ ከቀጠለ፥ ለጭቁን ሕዝቦች የጋራ ትግል ትብብር፥ ብሩህ የተስፋ አለኝታ ናቸው።  የሕዝቦች የጭቆና ጩኸትና የለውጥ መንፈስ፥ የፈጠረው ሰላማዊ ኒቅናቄ ሳይቀዘቅዝ፥ የሁሉገብ የትግል ስልት ደጋፊዎች፥ በአንድነት በቶሎ አማራጩን ጐዳና ማጠናከር አለባቸው።

በአንፃሩ የሰላማዊ ትግል ይዘት፥ «በዲሞክራሲያዊ መንገድ» በገዢው የህወሓት መንግሥት ላይ የለውጥ ተጽዕኖ ካላመጣ፥ ታሪክ እንደምያሳየን፥ በውግዘትና ሰላማዊ ተቃውሞ ብቻ ለውጥ አይመጣም።  በዚህ ወሳኝ ወቅት ሕዝባዊ ድርጅቶች፥ በጥቃቅን የአመለካከት ልዩነቶች ላይ ከማተኰር ይልቅ፥ ለጋራ ዘላቂ መፍትሔ፥ ጠንካራ ሕብረት መታገል ይገባቸዋል።

የሰላማዊ ትግል ሕዝባዊ ወላፈን ያስከተለው የአስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅ ጋጋታ፥ አዝማሚያው፥ የገዢውን ህወሓት መፍረክረክ ያሳያል።  የሥልጣን ሽኩቻው ዝቃጭ ገጽታ፥ በዲሞክራሲያዊ ሂደት ሕዝባዊ መፍትሔ ካላገኘ፥ ጭቁን ሕዝቦች፥ ለአምባገነን ግለሰቦች የባሰ ፀረ-ሕዝብ ድርጊት ይጋለጣሉ።

በመጨረሻ ጨቋኝ ገዢዎች መውደቂያቸው ስደርስ፥ እርስ በርስ ተከፋፍለው፥ ሥልጣን ላይ መፋጀታቸው የማይቀር ክስተት ነው።  በኢትዮጵያ ይህን የከፋ እልቂት ለማስወገድ፥ የብዙሐኑ ትግል፥ የእያንዳንዳችንን ሙሉ ተሳትፎና ድጋፍ ይጠይቃል።   በተለይ የሁሉገብ ትግል ስልትን ይዘት ያካተተ፥ የተለያዩ ድርጅቶችን የጋራ አመለካከት የያዘና፥ የሰው ሃይልን ጥቅም ያወቀ፥ የተቀናጀ የትግል ትብብር ያስፈልጋል።  በተራማጅ ሃይሎች የተባበረ የትግል ሂደት፥ የጭቁን ሕዝቦችን ሕይወት ለማዳን እንታገል።  የድሉ ባለቤት፥ ምን ጊዜም ሕዝቡ ነውና!!

One thought on “የሰላማዊ ትግል ይዘት!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.