By | April 15, 2018


የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ

ትግል

ክፍል ሦስት

በክፍል ሁለት ፅሁፍ ውስጥ የኦሮሞ የነፃነት ትግል የውስጥና የውጭ ጠላቶች በተለያዩ ቦታ ወይም ቡድን ተከፍለው ባጭሩ ተብራርተው ነበር። በተጨማሪም ኣንዳንድ የኦሮሞ ድርጅቶች፣ ቡድኖችና ግለስቦች ወይንም አክቲቪስቶች ለኦሮሞ የነፃነት ትግል ዓላማ የተሳሳተ ፍቺ በመስጠት፤ በዚህ የተነሳ የትግሉም ግብ እንደዚሁ በተሳሳተ መንገድ እንዲታይ እያደረጉ መሆናቸውም በዚያው ፅሁፍ ውስጥ ተብራርቷል። በዚህ ክፍል ሦስት ፅሁፍ ውስጥ ክፍል ሁለት ውስጥ በተጠቀሱት የትግሉ የዛሬ ፈተናዎች ላይ ተጨማሪ ጉዳዮችን ማንሳት እሞክራለሁ።

የኦሮሞ የፖላቲካ ድርጅቶች ዓላማዎች ይፃረራሉ ወይስ ይደጋገፋሉ?

ይህ ጥያቄ ከባድና የተወሳሰበ እንደሆነ ይገባኛል። ባሁኑ ጊዜ ይህን ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ አይሆንም የሚሉ ሊኖሩም ይችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ የነፃነት ትግሉ ጠላቶችና አጋሮቻቸው ይህንን ጥያቄ ጠምዝዘው እንደ ፕሮፓጋንዳ ተጠቅመውበት በኦሮሞ መካከል ችግር እንዳይፈጥሩ ይህንን ጉዳይ በጥንቃቄ ማየት በጣም ወሳኝ ነው። በሌላ በኩል ሲታይ ግን ዛሬ ያሉትን ችግሮቻችንን ካልተረዳን፤ ቤታችንን ዛሬውኑ ማፅዳት ካልጀመርን፤ ነገ ሌሎች ችግሮች ውስጥ መግባታችን ስለማይቀር፣ ይህ ጉዳይ መፍትሄ ካላገኘ ወደፊት ኦሮሞና ኦሮሚያን አደገኛ ችግር ውስጥ ሊከት ይችላል። ስለዚህ ፈርተው ያሉትን ችግሮች መደበቅ ወይም መሸፋፈን ሕዝባችንን ይጎዳል እንጂ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም።

ከዚህ በላይ ለተነሳው ጥያቄ መልስ ከመፈለግ በፊት፣ ባሁኑ ጊዜ በአገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገር የሚገኙትን የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በሁለት ትላልቅ ቡድኖች ከፍሎ ማየት ይቻላል። ኦሕዲድ (OPDO) እነዚህ ውስጥ ኣል ወይስ የለም? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። ነገር ግን አዲሱ የዚህ ድርጅት አመራር ሕዝባዊነትን እያሳየ ቢሆንም ይህ ድርጅት ለአሁን ነፃ የሕዝብ ድርጅት ስላልሆነ፣ ይህንን ድርጅት በዚህኛው ማብራራዬ ውስጥ አልከትም። ወደፊት ግን ይህንን ድርጅት በሚመለከት ሀሳቤን ኣቀርባለሁ። ሁለቱ ዋና ዋናዎቹ ቡድኖች፥

  1. የኦሮሞ የነፃነት ኃይሎች – እነዚህ የኦሮሞን ሕዝብና የኦሮሚያን ነፃነት እንደ ትግሉ ዓላማቸው አድርገው የሚታገሉና ግባቸውም ይህንኑን ለማረጋገጥ የሆኑ ኃይሎች ናቸው። እንዴት እየታገሉ እንዳሉ ሌላ ጥያቄ ስለሆነ፣ ይህንን ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።
  2. የኦሮሞ የዲሞክራሲ ኃይሎች እነዚህ ደግሞ ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት እንታገላልን የሚሉ ነገር ግን ግባቸው ከነፃነት ኃይሎቹ ግብ ወዲህ የሚሆን ማለትም የኦሮሞ ሕዝብ ነፃነቱን ካገኘ፣ በዚህች ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ የኦሮሞ ጥያቄ ሊመለስ ይችላል የሚሉ ኃይሎች ናቸው።

እዚህ ላይ ዲሞክራሲ የሚለውን ቃል የጨመርኩበት ምክንያት፣ የነዚህ B) ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች የትግላቸው ዓላማ እንደነሱ አባባል ኢትዮጵያን የዲሞክራሲ አገር ለማድረግ ስለሆነ ነው እንጂ በ A) ውስጥ የሚገኙ የነፃነት ኃይሎቹ በዲሞክራሲ አያምኑም ለማለት አይደለም።

እንግዲህ ከላይ ባጭሩ እንደ ተገለፀው፣ ሁለቱም ኃይሎች በጋራ ያላቸው ዓላማ የኦሮሞን ሕዝብ ነፃ ለማውጣት ይመስለኛል። ይህንን የጋራ ዓላማ ካላቸው ደግሞ የትግል ዓላማቸው አይፃረርም ማለት ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም ከኦሮሞ ሕዝብ ነው የተፈጠሩት፤ የዚህኑን ሕዝብ ስም ነው ኣንግበውም የተነሱት፤ ለዚሁ ሕዝብ እንቆማለን እያሉም ነው። ታዲያ አንድ የጋራ የሆነ ነገር እንደ አጭር ጊዜ የትግል ዓላማ ይዘው በመተጋገዝ አብረው ከመስራት ይልቅ እርሰ በርስ መተቻቸትና አንዱ ለሌላው እንቅፋት መሆን መጣር ከየት መጣ? ወይንስ የማያግባባቸው ሌላ ምክንያት አለ ማለት ነው? የነዚህ ኃይሎች ኣለመግባባት ደግሞ ለነፃነት ትግሉ ሌላ ፈተና ይሆናል። የራስን ቤት ማፅዳት ከዚህ መጀመር ስላለበት።

በሌላ መንገድ ሲታይ ግን፣ እንደኔ አመለካከትና ግንዛቤ እነዚህ ኃይሎች ዓላማቸው እንዲፃረር የሚያደርገው የነፃነት ትግሉ የመጨረሻ ግብ ነው ብዬ አስባለሁ። A) ውስጥ ያሉት ኃይሎች ስማቸው እንደሚያሳየው የኦሮሞን ሕዝብ ነፃነት ከማስገኘትም ባሻገር፣ የኦሮሚያን የወደፊት ዕጣ ፋንታ በኦሮሞ ሕዝብ እንዲወሰን የሚታገሉ ናቸውብዬ አምናለሁ። የራስን ዕድል በራስ/ለራስ የመወሰን መብትን መሰረት በማድረግ ማለት ነው። በነፃነት ኃይሎቹ አገላለፅ የኦሮሞ መሰረታዊው ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ በመሆኑ፣ በቅኝ ግዛት ስር ያለች አንድ አገር ደግሞ ከቅኝ ግዛት መውጣት አለበት ብለው ስለሚያምኑም ነው። የራሱን ዕድል በራሱ/ለራሱ የመወሰን መብት ደግሞ የማንኛውም ሕዝብ ተፈጥሮአዊ መብት ስለሆነ፣ ይህ አካሄድ ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ ለኦሮሞ ሕዝብ ብቻ የተፈጠረ መብት ስላልሆነ ማለቴ ነው።

ኢትዮጲያ የዲሞክራሲ አገር ከሆነች የኦሮሞ ጥያቄ በዚህ ውስጥ ሊመለስ ይችላል የሚሉት B) ውስጥ ያሉት ኃይሎች ይህንን እንደ ትግላቸው ዓላማና ግብም ለማድረግ መብት ኣላቸው። ይሁን እንጂ የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከኢትዮጲያ አመሰራረት ታሪክ ጋር ተያይዞ ከታየ፣ የኦሮሞ ሕዝብ እየቆሰለ እስከ ዛሬ የደረሰውን ቁስሉን አገሪቷን ዲሞክራሲያዊ አገር በማድረግ የሚድን ይመስላል? የሚለው ሌላ ትልቅ ጥያቄ የሚያነሳ ይመስለኛል። እውነት እንናገር ከተባለ ኢትዮጵያ የምትባል አገር በኃይል ከተመሰረተችበት ጊዜ ኣንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ለራሱ ምንም ፋይዳ ሳያገኝ ይህችን አገር ለማኖር ብሎ እንደ ኦሮሞ ከፍተኛ መስዋዕትነትን የከፈለ ሌላ ብሔርም ሆነ ሕዝብ በዚያች አገር ያለ አይመስለኝም። ይሁን እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ ብድር ይህ ሆኖ፣ ይኸው ዛሬ የዘር ማጥፋት ጦርነት ተክፍቶበት በመላው ኦሮሚያ ሕዝባችን እየደማ ነው ያለው። በመሆኑም ካሁን በኋላ ለኦሮሞ ምን ይመጣል ብለው ራስን መጠየቅ እጅግ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ።

ስለዚህ ትልቁ በኦሮሞ የነፃነት ጎራ (camp) ውስጥ ያለው ችግር የዚህችን አገር ሁኔታና የኦሮሞን ታሪክ ጎን ለጎን ይዘው ማይትና መገንዘብ ኣለመቻል ይመስለኛል። የነፃነት ትግሉ መንስዔ ወይም የኦሮሞ ብሔራዊ መሰረታዊ ጥያቄ ምን አንደሆነ በዚህ ላይ መግባባት እስከ ሌለ ድረስ፤ በትግሉ የጋራ ዓላማና ግብ ላይ መስማማት  እስከ ሌለና የጋራ የትግል ስልትና እስትራቴጂ ማውጣት እስካልተቻለ ድረስ የዚህ የነፃነት ትግሉ ፈተናዎች እየበዙና እየሰፉ ነው የሚሄዱት እንጂ የሚቀንሱ አይመስሉም። ይህ የአለመግባባት ችግር እንደዚሁ ከቀጠለ ደግሞ፣ የራሳችንን ቤት ማፅዳት ቀርቶ ያለውም የመፍረስ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል ማለት ነው። በዚህ እጅግ በጣም በተወሳሰበ ሁኔታ ውስጥ ድንገት አንድ ለውጥ እንኋን ቢመጣ፣ ስላልተዘጋጀንበት አሁንም ሌላ ዕድል ሊያመልጠን ይሆናል ማለት ነው። ያዚህች አገር ታሪክ እንደሚያሳየው ሁል ጊዜ አንድ ለውጥ ሲመጣ ያልታሰበና ያልተጠበቀ ኃይል በዚህ አጋጣሚ እንደሚጠቀም ነው።

እውነታው ይህ ስለሆነ ዛሬ ካሉት የነፃነት ትግሉ ፈተናዎች ውስጥ አንዱና ትልቁ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ የሆነ ዓላማና ግብ ማጣታቸው መሆኑ ለሁሉም ግልፅ መሆን አለበት። ድርጅቶቻችን የሚፃረሩ ዓላማና ግብ አንግበው እስከሄዱ ድረስ ለሕዝባችን ውዥንብር የመፍጠሩ ጉዳይ እንዲሁ ይቀጥላል ማለት ነው። በዚህ መንገድ በሚፈጠሩት ሁነታዎች ውስጥ ጥሩ ዕድልና ትርፍ የሚያገኙት የነፃነት ትግሉ ጠላቶች ብቻ ናቸው እንጂ ሕዝባችን ከዚህ የሚያገኘው ፋይዳ የለም። ታዲያ ለምንድነው ይህንን እውነታ የማንገነዘበው? ለምንድነው የራሳችንን ችግር መፍታት ትተን የባዕድ ጎራ ሄደን የሌሎችን እገዛ የምንጠይቀው? የኦሮሞን አቅም ንቀን ነው ወይስ በራሳችን መተማማን ኣንሶን ነው? የኦሮሞ ሕዝብ አንድ ለውጥ ለማምጣት አንድነትም ሆነ አቅም (capacity) አንዳለው ለዓለም እንኳን ባሳየበት ወቅት፤ የዚህን ትልቅ ሕዝብ ኃይል ለራሱ ነፃነት እንዲያውል ከማስቻል ውጭ ለሌሎች ነፃነት ብሎ መስዋዕትነት እንዲከፍል ለምን እናደርጋለን? ኦሮሞ ራስህን ጠይቅ/ራስሽን ጠይቂ!!!

በኦሮሞ የነፃነት ትግል ጎራ ያሉት ችግሮች በሌላ መንገድ ሲታዩ ደግሞ፣ የትግሉ ዓላማና ግብ ልዩነት ብቻ አለመሆኑንም መረዳት ይቻላል። እንዴት ቢባል፣ አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ ዓላማና ግብ ያላቸው የኦሮሞ ድርጅቶችም እኮ አንድነት ፈጥረው ኃይላቸውን ሲያጠናክሩ ኣልታዩም። ይህ ለምን ሊሆን ቻለ? ከኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት የሚበልጥ የግል ፍላጎት ነው ያለው? እነዚህን ጥያቄዎችና እንዲሁም ከዚህ ጋር የሚገናኙትን ጉዳዮች በሚቀጥለው የፅሁፌ ክፍል ውስጥ እናያለን።

ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

2. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሁለት
1. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አንድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.