By | March 20, 2018


የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ

Oromo Liberation Army (OLA)

ክፍል አራት

በክፍል ሦስት ፅሁፍ ውስጥ ባሁኑ ጊዜ በአገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገር የሚገኙትና ከጠላት ነፃ ሆነው የተደራጁት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ ፖለቲካና ትግል ዓላማቸው በሁለት ትላልቅ ቡድኖች ተከፍለው ተብራርቷል። እንዲሁም “የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ዓላማዎች ይፃረራሉ ወይስ ይደጋገፋሉ?” በሚል ርዕስ ስር  የዓላማቸው አንድነትና ነገር ግን የትግላቸው ግብ ልዩነት በዚያው ፅሁፍ ውስጥ ተብራርቷል። ይሁን እንጂ በኦሮሞ የነፃነት ትግል ጎራ የሚታዩ ችግሮች በሌላ መንገድ ሲታዩ፣ ያሉት ችግሮች የትግሉ ዓላማና ግብ ብቻ እንዳልሆኑ መረዳት ይቻላል። ይህንን ጉዳይ በዚህኛው ክፍል ፅሁፍ ውስጥ እናያለን።

አንድ ዓይነት የትግል ዓላማና ግብ ያላቸው የኦሮሞ ድርጅቶች ለምንድነው አንድነት መፍጠር ያልቻሉት?

የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳይግባቡ ከሚያደርጉት ውስጥ ዋንኛው የትግሉ ዓላማና ግብ ልዩነት ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ሲታይ ግን እንዳይግባቡ የሚያደርጋቸው ይህ በቻ እንዳልሆነ ይታወቃል። ለምን ቢባል አንድ ዓይነት ወይንም ተመሳሳይ የትግሉ ዓላማና ግብ ያላቸው እንኳን አንድነት ፈጥረው በጋራ ለመታገል አልቻሉምና። ለምሳሌ ባንድ ቡድን ውስጥ የሚመደቡት አንድ ዓይነት የትግል ዓላማና ግብ ያላቸውን የኦሮሞ የነፃነት ኃይሎች፥

 • በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፤
 • በአቶ ገላሳ ዲልቦ የሚመራው ኦነግ፤
 • የተወሃደ ኦነግ ተብሎ የሚጠራው፤
 • የኦሮሚያ ነፃነት ግንባር ተብሎ የሚታወቅ በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራ፤
 • የኦሮሚያ ነፃነት ኃይልች አንድነት (ULFO) ተብሎ የሚታወቅ ድርጅት

እና የመሳሰሉትን ብናይ፣ ሁሉም ተመሳሳይ የሆነ የትግሉ ዓላማም ሆነ የመጨራሻ ግብ ያላቸው ይመስለኛል። ይህ ሆኖ እያለ እነዚህን ድርጅቶች አንድ መሆን ወይንም የትግል አንድነት እንዳይፈጥሩ የሚያግዳቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ ግን ያስቸግራል።

በነገራችን ላይ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የነፃነት ትግሉ መሪና አንጋፋ አንደመሆኑ መጠን ዛሬ በተለያዩ ድርጅቶች ወይም ቡድኖች ተከፋፍሎ መታየቱ እጅግ ያሳዝናል። ይኼኛው ኦነግ ወይም ያኛው ኦነግ ብሎ መጥራት ራሱ የሚያሳፍር ነው ብል ነገር ማጋነን አይሆንብኝም።

ወደ ዋናው ጉዳይ ለመመለስ፣ በይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህ ድርጅቶች አንድ ዓይነት ግብ እየተመኙ፤ ይህንንም ግብ ለማረጋገጥ ተባብረው በጋራ መስራት ሲጠበቅባቸው፤ በተቃራኒው ጠላትን ትተው አንዱ ሌላው ላይ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲያካሄዱ መታየታቸው ነው። እኔ ነኝ የምበልጠው በማለት፣ ኣንዱ ሌላውን ለማጥፋት ሲጥር ነው የሚታየው እንጂ ኑ እስቲ አብረን ተቀምጠን ተወያይተን፣  ችግሮቻችንን ፈተን ይህንን ትግል ወደፊት እናራምድ ማለታቸው አይታይም አይሰማም። ይህ ጉዳይ ለነፃነት ትግሉ ሌላ ፈተና እንደሚሆን የተገነዘቡ አይመስለኝም።

የኦሮሞ የነፃነትና ዲሞክራሲ ኃይሎች ቡድን ውስጥ ያሉትንም ድርጅቶች ብናይ ለምሳሌ፥

 • የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ – ODF)፤
 • የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ – OFC)

እና ሌሎች ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸውን ድርጅቶች ብንመለከት፣ የነሱ የትግል ዓላማና ግብ አንድ ባይሆንም፣ ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ እነዚህም ቢሆኑ ተቀራርበው ብቻል አንድነት ለመፍጠር ካልተቻለ ደግሞ በጋራ ለመስራት የሚጥሩ አይመስሉኝም። ኦፍኮን ብንወስድ እነሱ ቢያንስ ሁለት በፊት ብቻ ለብቻ ተደራጅተው የነበሩትን የኦሮሞ ፈዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (OFDM) እና የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስን ኦብኮ (ONC) አዋህደው አንድ ድርጅት ኣድርገዋል። እነዚህ ለሌሎች ምሳሌ መሆን ይችሉ ነበር። ኦዲግን ከወሰድን ግን እኔ እስከማስተውለው ድረስ በኦሮሞ የነፃነት ጎራ ውስጥ ከሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር ትብብር (alliance) መፍጠር ትተው ወደ ሌላ ጎራ ሄደው ውጫዊ ትብብር ወይም ጥምረት ሲፈልጉ ይታያሉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ አገራዊ እንቅስቃሴን (Ethiopian National Movement) ማየት በቂ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።

ከዚህ በፊትም በተለያዩ ፅሁፎች ውስጥ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ እንደኔ አመለካከት የኦሮሞ ድርጅቶች ውስጣዊ አንድነት ወይንም ትብብር (internal alliance) ሳይፈጥሩ፣ በተናጠል ውጫዊ ትብብር (external alliance) ፍለጋ መሄድ ውጤቱ ያማረ የሚሆን አይመስለኝም። አደገኛ አካሄድም ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ። በኦሮሞ አንድነት ወይም ትብብር የኦሮሞ ጎራ ኃይል ካልተጠናከረና አስተማማኝ ካልሆነ፣ ከባዕድ ጋር በሚደረገው ድርድርና ስምምነት ላይ መናቅና ከዚህም ጋር ተያይዞ ስህተት ሊሰራ ይችላል። ይህ በኦሮሞ ታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ ሲታይ የነበረ እውነታ ነው። ስለዚህ ከሌሎች ኃይሎች ጋር ማንኛውም ድርድር ሲደረግ በተናጠል ሳይሆን በሁሉም የኦሮሞ ኃይሎች ስምምነት መሆን አለበት። ይህን ለማድረግ ደግሞ በቅድሚያ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች አንድነት ወይም ትብብር መኖር የግድ ይሆናል።

ከውጫዊ ኃይል ጋር ድርድር በሚደረግበት ሁኔታ ውስጥ ውጫዊው ኃይል ከኦሮሞ ኃይል በልጦ ከተገኘና የኦሮሞ ኃይል ደካማ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ በድርድሩ ላይ መሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ የኦሮሞ የነፃነት ትግል እስካሁን ያስመዘገባቸው ድሎች እንኳን አደጋ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ለዚህ ነው የኦሮሞ ኃይል መጠናከር የሚኖርበት። የኦሮሞ ኃይል የሚጠናከረው ደግሞ ውስጣዊ አንድነትና ትብብር ሲኖር ብቻ ነው። ይህ ጉዳይ እንደ ቀላል መታየት የለበትም። የኦሮሞ የነፃነት ጎራ መጠናከር ደግሞ ዛሬ ሕዝባችንን እየገደለ ያለውን የሕወሃት መንግስት ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ ለነገው የኦሮሞና ኦሮሚያ ህልውና ዋስትና ይሆናል። ለዚህ ነው የኦሮሞ አንድነትና ትብብር ወሳኝ የሚሆነው። እጅግ የሚያሳዝነው ግን ይህ እውነታ ምኞት ብቻ ሆኖ መቅረቱና በመሬት ላይ በተግባር የሚታይ መጥፋቱ ነው። አንድነት ፈጥረው የኦሮሞን የትግል ጎራ ማጠናከሩም ቀርቶ፣ ኣንዱ በሌላው ላይ መዝመትን ቢያቆምና ጠላት ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነበር።

አሁንም ደግሜ ደጋግሜ የምለው ትብብርን ወይንም ጥምረትን የማቋቋም ሂደት ደረጃ በደረጃ ካልተከናወነ ትርፍ የሚያመጣ አይመስለኝም። ደረጃ በደረጃ ስል ምን ማለቴ ነው?

 • አንደኛ፥ በቅድሚያ አንድ ዓይነት ወይንም ተመሳሳይ የትግል ዓላማና ግብ ያላቸው ኃይሎች አንድነት መፍጠር፤ ይህ የነፃነት ኃይሎች አንድነት ይሆናል ማለት ነው።
 • ሁለተኛ፥ አንድ ዓይነት የትግል ዓላማ ያላቸው ነገር ግን የተለያዩ ግብ የሚከተሉ ኃይሎች በመተባበር የጋራ የሆነ የትግል ስልትና እስትራቴጂ ለመንደፍ ዓላማዊ ትብብር መፍጠር፤
 • ሦስተኛ፥ አንድ ወይም ተመሳሳይ የትግል ዓላማ ካላቸው ውጫዊ ኃይሎች ጋር የነፃነት ኃይሎች አንድነት ወይም ትብብር መፍጠር፤
 • አራተኛ፥ ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱ ደረጃዎች በሚገባ ከተጠናቀቁ በኋላ ሁሉን አቀፍ ጥምረት ወይም ትብብር (All-Inclusive Alliance) መመስረት

ቢያንስ በነዚህ መንገዶች ደረጃውን ጠብቆ ካልተከናወነ ጠላትን የሚያሸንፍም ሆነ ለነገው ዋስትና የሚሆን ጠንካራና አስተማማኝ ኃይል መገንባት የሚቻል አይመስለኝም። ለየብቻ በተናጠል መሄድ ተለይተው ለብቻ መመታት ካልሆነ በስተቀር፣ አንድ የሚፈልጉትን ነገር ማግኘት አይቻልም የሚል እምነት አለኝ።።

አንድ መረሳት የሌለበት ጉዳይ፣ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ስምምነት መጥፋት በኦሮሞ ማህበረ ሰብ ወስጥ ለሚፈጠሩት አለመግባባቶች መሰረት ይሆናል። ይህንን መሰረት በማድረግ በቡድንም ሆነ በተናጠል አንዱ በሌላው ላይ ይዘምታሉ። ይህ ደግሞ በተለይም በውጭ አገር በሚገኙ በኦሮሞ ማህበረ ሰብ ውስጥ ሲታይ የቆየና አሁንም አልፎ አልፎ እየታየ ያለ ነው። ድርጅቶቻችን በመካከላቸው ያለውን ችግር እስካልፈቱ ድረስ የድርጅቶቹ አባላትም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው አንዱ በሌላው ላይ የሚያደርጉት ዘመቻ ሊቆም አይችልም። የችግራችን መንስዔው ወይም ምንጭ ድርጅቶቻችን ናቸው ማለት ይቻላል። ይህ እውነታ ለሁሉም ግልፅ መሆን አለበት። ጠላት የኦሮሞን ዘር ለማጥፋት ከምንጊዜም በላይ ቆርጦ በተነሳበት ባሁኑ ጊዜ እኛ ግን መግባባት አጥተን ለጠላት ሁኔታን ማመቻቸት ትርጉሙ ምንድነው?

በሌላ በኩል ደግሞ በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የሚፈጠሩት ችግሮች በአባላትና በደጋፊዎቻቸው መሃል  ብቻ አይቀርም። አልቀረምም። የኦሮሞ ሚዲያዎች እንኳን ሳይቀሩ በቡድን በመደራጀት እንደዚሁ ኣንዱ በሌላው ላይ ዘመቻ ሲያካሄድ ይታያል። የኦሮሞ ሚዲያዎች ነፃ ሆነው የቆሙለትን ሕዝብ ማገልገል ግዴታቸው ጭምር ሆኖ እያለ ነገር ግን እነሱም በተመሳሳይ መልኩ አንዱ ሌላውን ሲተች፣ ሲሰድብ፣ ሲረግም ይታያሉ። የኦሮሞ አክቲቪስቶችም እንደዚሁ ነፃ ሆነው ባላቸው ችሎታ ለዚህ ለነፃነት ትግል የራሳቸውን ድርሻ ከመወጣት ይልቅ ኣንዳንድ ጊዜ ተቃራኒ ስራ ሲሰሩ የታያሉ። ስለዚህና ተመሳሳይ ጉዳዮች በሚቀጥለው ፅሁፍ ውስጥ እናያለን።

ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.