By | April 15, 2018


የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ, Bitootessa 21, 2018

ክፍል አምስት

በክፍል አራት ፅሁፍ ውስጥ አንድ ዓይነት የትግል ዓላማ ያላቸው የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ምንም እንኳን የትግሉ ግባቸው አንድ ቢሆንም፣ በመካከላቸው ስምምነት ኖሮ የትግል አንድነት መፍጠር እንዳልቻሉ፤ አንድነት መፍጠርም ቀርቶ እንዲያውም አንዱ በሌላው ላይ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲያደርግ እንደሚታይ፤ በዚህ ምክንያት ደግም በኣባላትና ደጋፊዎቻቸው መካከልም ተመሳሳይ ዘመቻ ሲድረግ እንደሚታይም ተብራርቶ ነበር። በተጨማሪም ከድርጅቶቹ የመነጩት ችግሮች በኦሮሞ ማህበረ ሰቦች መካከልም በተለያየ መልክ እንደሚታዩም በዚያው ፅሁፍ ውስጥ ተብራርቷል። በዚህኛው ፅሁፍ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች የሚታዩትን ሌሎች ችግሮችን  እናያለን።

ፀረ-ኦሮሙማ የሆኑና ለነፃነት ትግሉም እንቅፋት የሚሆኑ የማይድኑ በሽታዎች

በባዕድ የጭቆና አገዛዝ ስር ወድቆ ሁሉንም ቢያጣም፣ የኦሮሞ ሕዝብ እጅግ አኩሪ ባሕልና ታሪክ ያለው፣ ፍቅርና ክብር ያለው፣ እንደዚሁም የዲሞክራሲ መሰረት የሆነ ወግና ስርዓት ያለው ሕዝብ እንደሆነ ዘመድ ቀርቶ ጠላቶቹ እንኳን ማስረጃ እንደሚሆኑለት የማይታበል ሀቅ ነው። ከዚህ ሕዝብ መፈጠር እጅግ የሚያኮራ ነው ብል ነገር ማጋነን አይሆንም። ይሁን እንጂ በዚህ በመራራ የነፃነት ትግል ውስጥ በሺዎቹ የሚቆጠሩ ጀግኖች የተወለዱት ያህል፤ ስርዓት የለሾች፣ ከሃዲዎች፣ ለሆድ አዳሪዎች፣ ደንታ ቢሶች እና የመሳሰሉትም አየተወለዱ እንደሆነ በገሃድ የሚታይ ነው። ይህ ከየት መጣ? የሚለው ጥያቄ ጥልቅ ጥናትና ሰፊ ትንታኔን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ይህንን ጉዳይ ዛሬ እዚህ ኣላነሳም። የነዚህ ምንጭ ምንም ይሁን ምን እነዚህ ጉዳዮች የማይድኑ በሽታዎችና ፀረ ኦሮሙማ በመሆናቸው ለዛሬው ትግል እንቅፋት ከመሆናቸውም ባሻገር ለነጌኣችን አደገኛ የሆኑ ናቸው።

እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ፣ በኦሮሞ ጎራ የሚታዩ በይበልጥ ደግሞ እጅግ አፍራሽና ፀረ አንድነት የሆኑት፥ በቀዬ፣ በክልል፣ በሃይማኖትና በቋንቋ ዲያሌክት እንኳን ሳይቀር እንደዚሁም ደግም በፖለቲካዊ አመለካከት መከፋፈል ነው። ይህ ደግሞ ከሁሉም የበለጠ ትልቅ በሽታና ፀረ-ኦሮሙማና ፀረ-ኦሮሞ አንድነት ነው። እነዚህ አፍራሾች እስካሉ ድረስ፣ የነፃነት ትግሉም የተፈለገው ግብ ሳይደርስ እንደሚቆይ ጥርጥር የለዉም። እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ዛሬ ለነፃነት ትግሉ እንቅፋት ከመሆንም አልፈው፣ ለወደፊታችን ለኦሮሞና ኦሮሚያ አደገኛ መሰረት የሚጥሉ ናቸው። እነዚህ የችግሮቹ ተዋናዮች እየሰሩ ያሉት መጥፎና አፍራሽ ነገር ዛሬ አይታያቸውም ይሆናል። ነገር ግን አንድ ጥፋት ሲደርስ ይገለፅላቸው ይሆናል። እዚህ ላይ አንድ የኦሮሞ ተረት ትዝ ይለኛል። Amma naaf ife jedhe ballaan (jaamaan) mana gubee” የሚል ሲሆን ወደ አማርኛ ሲተረጎም፥ “አንድ ዓይነ ስውር ቤት ያቃጥልና አሁን ነው የበራልኝ፣ የታየኝ አለ” ይባላል።

የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በተለይም አንድ ዓይነት ግብ የሚፈልጉ ዛሬ ተለያይተው ያሉት በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ብቻ ሳይሆን ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች የችግሮቹ ምንጭ በመሆናቸው ነው ማለት ይቻላል። እነሱ ግን የፖለቲካ አመለካከትን፣ የዓላማና ግብ ልዩነትን እንደ ዋንኛ ምክንያት አድርገው ያቀርባሉ እንጂ መንስዔው ሌላ ነው። አንቀው የያዙን ችግሮችና ለትግሉም የውስጥ ጠላት የሆኑት እነዚሁ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ናቸው።  እነዚህ ችግሮች ቶሎ መፍትሄ ካላገኙ ማለትም የዚህ ዓይነት አፍራሽ ስራ የሚሰሩ ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ የሚመጣው ጉዳት ይህ ነው የማይባል በመሆኑ፣ ከዚህ ደግሞ ማንም ማምለጥ አይችልም። ስለዚህ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሳይሆኑ ቢታሰብበት መልካም ነው።

በድርጅቶቻችን በኩል እስቲ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ኦነግን እንደ መሳሌ እንውሰድ፥ የተለያዩ ፖለቲካዊ አመለካከትና ኣይዶሎጂ በድርጅቱ ውስጥ ቢኖርም፣ እኔ እንደሚመስለኝ ከ1991 በፊት ይህ ድርጅት ጠንካራና አንድነት ያለው ግንባር ነበር። ጠንካራነትና አንድነት ባይኖረው ኖሮ ዛሬ ኦሮሞ የሚኮራባቸው ድሎች ባልተገኙ ነበር። ከ1991 በኋላ ግን የትግሉ መሪና አንጋፋ በሆነው በዚህ ድርጅት ውስጥ የተለያዩ መገነጣጠል ሲታዩ ነበር። ለመለያየቱ ምክንያት የሆኑት ግን ኣንዳንዴ እንደምባለው  እውነት የዓላማና ግብ ልዩነት ብቻ አይመስሉኝም። ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች ወሳኝ ሚና እንደ ተጫወቱ ነው የሚታየኝ። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የተፈጠሩት ችግሮች ለሌሎች ችግሮች መፈጠርና መብዛት መሰረት የጣሉ ናቸው። ለተፈጠሩት ችግሮች የጋራ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ኣንዱ በሌላው ላይ ጣት ሲያቀስርና አንዱ በሌላው ላይ ዘመቻ ሲያከሄድ ይታያል። ይህ ደግሞ ለጠላት ጥሩ ሁኔታን ያመቻቻል።

በቀዬ፣ በክልል፣ በሃይማኖትና በመሳሰሉት ላይ ተመስርተው የተፈጠሩት ችግሮች ዛሬ ወደ ፖለቲካ አመለካከትም ተሻግረው፣ እገሌ ይህ ነው፣ እገሌ ያ ነው፣ እገሌ ኦነግ ነው፣ እገሌ የዚህ ወይም የዚያ ቡድን ኣባል ወይንም ደጋፊ ነው፣ እገሌ ኦሕድድ ነው ወዘተ በማለት ጠላትን ትተው እርሰ በርስ ሲወቃቀሱ ይታያል። ከሁሉ በላይ ደግሞ መርዝ እየረጨ ያለውና ኦሮሙማን (Oromummaa) አደጋ ውስጥ ሊጥል እየተንቀሳቀሰ ያለው የኦሮሞን የጋራ ቋንቋ Afaan Oromooን በዲያሌክት በመካፋፍል ይህ የወለጋ፣ የሸዋ፣ የአርሲ፣ የሀረርጌ ወዘተ ዲያሌክት ነው እያሉ በዚህ በኩል ልዩነት ለመፍጠር የኦሮሞን አንድነት ለማፍረስ የሚደረገው ዘመቻ ነው። ታዲያ በዚህ ዓይነት አካሄድ ነው ጠላትን አሸንፈን፣ያጣነውን ነፃነትና የአገር ባለቤትነትን መልሰን የምናገኘው? የዚህ ዓይነት ዓፍራሽ አመለካከት ይዘን ነው የጋራ አገር ለመመስረት የምንመኘው? በጀግኖቻችን ደምና አጥንት እየቀለድን እንደሆነ ተገንዝበናል? የጀግኖቻችን ነፍስ የዝንቦች ነፍስ ሆነ እንዴ?

እስቲ ዛሬ የኦሮሞ ልጆች በክልል፣ በሀይማኖት፣ በፖለቲካ አመላካካት፣ በምንናገረው የቋንቋችን ዲያሌክት ወዘተ የምንከፋፈልበት ወቅት ነው? ዛሬ ድርጅቶችን ምክንያት አድርገን ይህ በእገሌ የሚመራ ኦነግ ነው፤ ይህ ኦዲግ ነው፤ ያ ኦሕዴድ ነው። ያ ኦፌኮ ነው ወዘተ አያልን ትኩረታችንን ከጠላት የምንቀይርበት ወቅት ነው? ማንኛውም የኦሮሞ ድርጅት አንድ ድንጋይም ትሁን ወደ ጠላት እስከ ወረወረ ደረስ፤ የኦሮሞን ሕዝብ ፍላጎት በማይፃረር መንገድ እስከ ሰራ ድረስ፤ መደጋገፍ ያለብን ወቅት ነው እንጂ የማይሆን ምክንያት እየፈጠርን እርሰ በርስ የምንጣላበት ጊዜ አይደለም። የጠላትን ዕድሜ ማራዘም እንጂ ለሕዝባችን የሚገኝ ፋይዳ የለም። ዛሬ ጠላታችን ወያኔ ከምንጊዜውም የበለጠ ኃይሉን አጠናክሮና አቀናጅቶ የኦሮሞን ዘር ለማጥፋት ቆርጦ በተነሳበት ወቅት፤ ይህንን አደገኛ ጠላት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከነመሰረቱ ለመጣል ያለንን ጉልበትና ኃይል ማቀናጀት ነው እንጂ በኦሮሞ የነፃነት ትግል ጎራ እርሰ በርስ መዋጋት ጊዜ የሚጠይቀው ጉዳይ አይደለም።

እንግዲህ፣ ስለማይድን በሽታችን እዚሁ ላይ በማቆም፤ እስቲ የሆነ ሆኗልና፣ ያለፈውም ኣልፏልና፣ ፈጣሪያችን አእምሮአችንን ወደ ጥሩ ይቀይር እያልን፤ በአገራችን ኦሮሚያ እየተካሄደ ያለውን የዘር ማጥፋት ጦርነት እይተን፤ በየቀኑ እየሞተና እየደማ ያለውን ሕዝባችንን በማስታወስ፤ እርሰ በርስ ከመዋጋት አንድ ድንጋይም ትሁን ወደ ጠላታችን እንወርውር። በምንችለው መንገድ ሁሉ ድርሻችንን እንወጣ። ድርሻችን ደግሞ ኦሮሙማን (Oromummaa) የሚያሳድግ እንጂ የዚህ ፀር መሆን የለበትም። በሚቀጥለው ፅሁፍ ውስጥ ባሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ውስጥ እየሄደ ስላለውና  በተለይም ኦሕዴድን (OPDO) በተመለከተ ሀሳቤን ይዤ እቀርባለሁ።

ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

4. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አራት
3. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሦስት
2. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሁለት
1. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አንድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.