By | April 15, 2018


የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ, Bitootessa 27, 2018                                        

ክፍል ስድስት

ባለፉት በአምስት ክፍሎች በቀረቡት ተከታታይ ፅሁፎች ውስጥ የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ትላንት የነበሩትና ዛሬ ያሉትን ፈተናዎች በሚመለከት ኣንዳንድ ጉዳዮች በጥቂቱም ቢሆን ለመብራራት ተሞክረዋል። ዛሬ በኦነት ጎራ (camp) የሚታዩ ችግሮች አብዛኞቹ ውጭ አገር በሚገኙት የኦሮሞ ማህበረ ሰብ ውስጥ ናቸው። ለኦነት የዛሬ ፈተና ከሆኑት ጉዳዮች ሳንወጣ፣ በአገራችን ኦሮሚያ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉትን ጉዳዮች ለማየት የሚከተሉት የፅሁፌ ተከታታይ ክፍሎች በነዚህ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ። ከኦሮሞ ሕዝባዊ ንቅናቄ ጋር በተያያዘ የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕድድ) ያለውን ሚናና ድርሻ እንደዚሁም ጠላታችን ወያኔ ምን እየሰራ እንዳለ እናያለን።

የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕድድ – OPDO) የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት)ኣጋር ይሆናል ወይንስ እንቅፋት ይሆንበታል?

ባሁኑ ጊዜ እንደሚሰማው፣ ኦሕድድ የትላንቱ ድርጅት አይደለም፤ የኦሮሞን ሕዝባዊ ንቅናቄ እያገዘ ነው፤ ለኦሮሞ የነፃነት ትግልም ተጨማሪ ኃይል እየሆነ ነው ወዘተ ይባላል። እኔ ግን ከዚህ አባባል ጥርጣሬ አለኝ። ለምን ጥርጣሬ እንዳለኝ ለመግለፅ እስቲ በቅድሚያ ይህ ድርጅት እንዴት እንደተቋቋመ፣ ለምን እንደ ተፈጠረ፣ ምን ሲሰራ እንደ ነበርና እየሰራ እንዳለ ባጭሩ ለማብራራት እሞክራለሁ። እውነት ነው፤ አንድ ነገር ትላንት እንደ ነበረ ዛሬ፣ ዛሬ እንዳለ ነገ ሊኖር እንደማይችል አያከራክርም። ትላንት ዛሬ፤ ዛሬም ነገ ሊሆን አይችልም ማለቴ ነው።

የዚህን ድርጅት ታሪክ ለታሪክ ፀሃፊዎች በመተው፤ ነገር ግን የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ እንደሚያሳየውና እንደሚታወቀው ይህ ድርጅት በኦሮሞ ብሔርተኞች የተቋቋመ ነፃ የፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን፣ የጠላትን ዓላማ ለማሳካት የተመሰረት ድርጅት ነው። የድርጅቱም ዓላማ፥ አንደኛ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እንዲዳከም ለማድረግ ሲሆን፣ ሁለተኛ በዚህ ድርጅት ተጠቅመው ወደ ኦሮሚያና ኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ ለመግባት ወያኔዎች ያዘጋጁትን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ነው። በዚህ የተነሳ ይህ ድርጅት የኦሮሞን ሕዝብ የሚወክል ሳይሆን፣ በኦሮሚያ ወያኔን የሚወክል ድርጅት ሆኖ ተልዕኮውን ሲፈፅም የቆየ ድርጅት ነው።

ይሁን እንጂ ባለፉት 25ne ዓመታት ውስጥ የኦሮሞ ብሔርተኞች በተለያዩ ምክንያቶች ወደዚህ ድርጅት ተቀላቅለዋል። በዚህ ድርጅት ውስጥ ያሉት የኦሮሞ ብሔርተኞች ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሕዝባቸው ያላቸውን ተቆርቋርነትን በተለያዩ መንገዶች ሲያሳዩ ቆይተዋል። በ2015 የኦሮሞ ሕዝባዊ ንቅናቄ ሲጀመር፣ በዚህ ድርጅት ውስጥ ተደብቀውና ታፍነው የቆዩት በይፋ እንዲወጡ እድል ፈጠረ። ይህ ሕዝባዊ ንቅናቄ በዚህ ድርጅት ላይ ከፍተኛ ጫና አደረገ ማለት ነው። በዚህ ምክንያት ወደውም ይሁን ተገደው፤ ፈልገውም ይሁን ሳይፈለጉ ኣንዳንድ  የድርጅቱ አባላት ወጥተው ኦሮሙማንና የኦሮሞ ብሔርተኝነትን የሚያንፀባርቁ ንግግሮችን ማድረግ ጀመሩ። ከነዚህ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚታወቁት ኦቦ ለማ መገርሳ ናቸው።

የኦቦ ለማ መገርሳ ንግግሮች እውነትም እንደ ማር የሚጣፍጡ ናቸው። ይህ ምንም ጥረጣሬ የለውም። ነገር ግን እነዚህ ጣፋጭ ንግግሮችና ቃል የተገቡት ነገሮች በስራ ወይም በተግባር በግልፅ ኣልታዩም ብል ከሀቅ መራቄ አይሆንም። እውነት ነው በኦቦ ለማ አመራር ስር ኣንዳንድ ጥቃቅን ስራዎች እንደተሰሩ አይካደም።  እነዚህ ጥቃቅን ስራዎች ምን ያህል ለኦነት እንደሚያበረክቱ ግን አከራካሪ ነው። እኔ እንደሚመስለኝ የኦሮሞን ብሔርተኝነት የምያንፃባርቁ ግለሰቦች ናቸው በዚህ ድርጅት ውስጥ የሚታዩት እንጂ ኦሕድድ እንደ ድርጅት እውነት ስር ነቀል ውስጣዊ ተሃድሶ አድርጎ፣ እንደ አንድ ነፃ የሕዝብ ድርጅት ሆኖ ይወጣል ለማለ ት በጣም ያስቸገራል። ድርጅቱ አሁንም የተቋቋመለትን ዓላማ እያሳካ ነው የምል እምነትነው ያለኝ።

ይህ ድርጅት አሁንም ከሕወሃት ተፅዕኖ የተላቀቀ አይመስለኝም። የድርጅቱ አባላት አሁንም የወያኔን ትእዛዝ በመቀበል በሕዝባችን ላይ ጉዳት የሚያመጡ ይመስሉኛል። በሌላ መንገድ ደግሞ ይህ ድርጅት ወያኔን የሚቃወምበት ኃይልም ሆነ ስልጣን ያለው አይመስልም። የኦቦ ለማ አዲሱ አመራርም የሕዝብን ወኔ የሚነካ ንግግር ያድርግ እንጂ በተግባር የሚታይ የለም። ጌቶቻችን ሕዝባችን ብቻ ናቸው እያሉ በየሄዱበት ሲናገሩ ተሰምተዋል። ነገ ግን የሕዝባችንን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ቀርቶ፤ የድርጅቱን አባላትና የአመራሩ አባላቱን ሰላምና ደህንነት እንኳን ማስጠበቅ ኣቅቷቸው፤ ይሀው በዙ ሰዎች ከዚህ ድርጅት ውስጥ እየተለቀሙ ወደ እስር ቤት እየተወረወሩ ናቸው። ታዲያ የድርጅቱ ኃይል የት አለ? የድርጅቱ ስልጣንስ የት አለ?

ድርጅቱ ኃይልና ስልጣን ቢኖረው ኖሮ (እዚህ ላይ ስልጣን ስል በፌዴራሉ ሕገ መንግስት መሰረት እንደ ኣንድ የፌዴራል ክልል መንግስታዊ ድርጅት ማለቴ ነው) በቅድሚያ የድርጅቱንና የአመራር አባላትን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ይችል ነበር። ነገር ግን ይህንን ማድረግ ኣልቻለም። የኦቦ ለማ አመራር ራሱ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው። በአመራር አባላቱ ላይ ምን ሊደርስባቸው እንደሚሄድም አይታወቅም፤ አንድም ዋስትና የለም። ታዲያ የአመራርና የድርጅቱን አባላት ከጥቃት መከላከል ያልቻለ ድርጅት ነው የሰፊውን ሕዝብ ሰላም ማስጠብ የሚችለው? የሕዝቡን ሰላም ማስጠበቅ ያልቻለ ድርጅት ነው ለኦነት አስተዋፅዖ የሚያበረክተው? ስለዚህ ከዚህ እንኳን ተነስተን ካየን፣ ይህ ድርጅት ለኦነት አጋር የሚሆን አይመስለኝም። አጋር መሆን ቀርቶ አሁን ባለው ሁኔታ እንዲያውም እንቅፋት ነው ብዬ አምናለሁ።

ኦሕድድ ለውጥ ያመጣል በለው የምናገሩ ሰዎች በመሬት ላይ ያለውን እውነታ የተረዱ አይመስለኝም። እነሱ እምነት የጣሉበት ይህ ድርጅት ለውጥ ማምጣት ቀርቶ ራሱን እንኳን የምከላከልበት ኃይል የለውም። ይህ ድርጅት እንደ ድርጅት ለኦነት አጋር ሊሆን አይችልም ካልኩ በኋላ፣ እስቲ ከዚህ ድርጅት ውስጥ ወጥተው ለኦሮሞ ሕዝብ ለመስራት ቆርጠናል የምሉትን እንይ፥ ኦቦ አባ ዱላ ገማዳ ከአፍ ጉባዔነት ስልጣን ለቅቄኣለሁ ብለው በተናገሩበት ወቅት ለኦሮሞ ሕዝብ ለመስራትና ወደ ሕዝባቸው ለመወገን የቆረጡ መስለው ነበር። ይህ ደግሞ በተስፋ እየተጠበቀ እያለ፣ ይሀው ብዙም ሳይቆዩ ወደ ስልጣናቸው ተመልሰው ስሰጡ የነበሩትን አገልግሎት እየሰጡ ናቸው። ያ የተሰራው ድራማ ለምን እንደ ሆነ እስከ ዛሬ የሚታወቅ የለም።

የቀሩትም ሰዎች የሚናገሩትና ቃል የገቡት በተግባር ይታያል ለማለት ምን ዋስትና አለ? ሌላው እጅግ የሚደንቀው ደግሞ የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስተር ምርጫ ነው። የኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስተር ስለ ተመረጠ የኦሮሞ ብሔራዊ ጥያቄ መልስ ማግኘት የሚችል ይመስል፤ ከኦሮሞ ውስጥ በሚወጣው ጠቅላይ ሚኒስተር  የአገሪቷ አንድነት የሚጠበቅ ይመስል፤ ከኦሮሞ ውስጥ በሚወጣው ጠቅላይ ሚኒስተር  ሰላማዊ የሽግግር መንግስት መቋቋም የሚችል ይመስል የማይሳካ ጉዳይ ማውራት ያለውን እውነታ ኣለመረዳት ነው ወይስ ራስን ኣሞኝተው ሌላውንም ለማሞኘት ነው? የወያኔ ስርዓት በቦታው እስካለ ድረስ፣ አንድ ጠቅላይ ሚኒስተር  ይቅርና ሚሊየን ኦሮሞ እዚህ ቦታ ቢቀመጥ የኦሮሞን ብሔራዊ ጥያቄ መመለስ አይችልም። የኦሮሞ መሰረታዊ ጥያቄ የግለሰቦች ሹመት አይደለምና።

እንግዲህ በፅሁፉ ርዕስ ላይ ወደ ተነሳው ጥያቄ ለመመለስ፣ ኦሕድድ ለኦሮሞ የነፃነት ትግል አጋር መሆን የሚችለው የሚያስከፍለውን ማንኛዉንም መስዋዕትነትን በመቀበል ከኢሕአድግ ተላቆ ነፃ የሕዝብ ድርጅት በመሆን ከቀሩት የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር ትብብር ሲያደርግ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ የወያኔ ስርዓት በቦታው እስካለ ድረስ፣ እዚያ ውስጥ እንደ አንድ የኢሕአድግ አባል ድርጅት ቀጥዬ የሕዝብን ትግል እደግፋለሁ የሚል ከሆነ፣ ይህ ትርፍ ማምጣት ቀርቶ ድርጅቱ ራሱ የህልውና ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ መረዳት አለበት። በዚህ መንገድ ከቀጠለ ትንሽ የኦሮሞ ሕዝብ ተቆርቋርነት ያላቸው የድርጅቱ አባላት ኣንድ ባንድ ተለቃቅመው እስር ቤት እንድሚወረወሩ ጥርጥር የለውም። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለኦሮሞ የነፃነት ትግልም ሌላ ፈተና ያመጣል እንጂ ለትግሉ አጋር አይሆንም። በሚቀጥለው ፅሁፍ ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሀሳቤን ይዤ እመለሳለሁ።

ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

Previous Articles:

5. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አምስት
4. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አራት
3. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሦስት
2. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሁለት
1. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አንድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.