By | March 8, 2018


የወታደራዊ አገዛዝ ወይስ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ?

ባይሳ ዋቅወያ – Bitootessa 8, 2018

*****

ያልተጠበቀ ነገር ባይሆንም ባልተጠበቀበት ሰዓት ውድ የመከላከያ ሚንስትራችን በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ “ያገሪቷ ህልውና አደጋ ላይ በመውደቁ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ታውጇል” ብሎ “ጥልቅ ሃዘን በተሞላበት መንፈስ” ለምንወደው ወገኖቹ አሳወቀን። የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ በተለያዩ መንግሥቶቻችን በተለያዩ ጊዜያት “ሲታወጅል(ብ)ን” ስለነበረና ኢህአዴግም በቅርብ ጊዜ ዓውጆት ”አገራችንን ከአደጋ ያዳነበት“ ፍቱን የአገዛዝ ስልት መሆኑን ያወቅነውና የተረዳነው ጉዳይ በመሆኑ ይህኛው የአቶ ሲራጅ መግለጫ ብዙም ባላሳሰበን ነበር። ግን፣ ይህኛው ዙር ዓዋጅ ከበፊቶቹ ሁሉ በቅርጽና በይዘቱ ብቻ ሳይሆን እስከነአስፈላጊነቱ ድረስ አወዛጋቢ ሆኖአል። ከዘመዶቼ ሰሞኑን ከሚደርሰኝ ዜና እንደተረዳሁት ከሆነ ኮማንድ ፖስቱ ውሃና መብራት ቆርጦባቸው በጨለማ ውስጥ እንዳሉና በውሃ ጥም እየተሰቃዩ መሆናቸውን ስሰማ ደግሞ፣ አንዳች ዓይነት እርዳታ ላደርግላቸው ከማልችልበት ባህር ማዶ ሆኜ መጨነቄን ሌሎች ኢትዮጵያውያንም እንዲረዱና በያሉበት ሆነው ይህንን “መከላከያ ሰራዊት” ተብዬው በህዝባችን ላይ ያወጀውን ወረራ ራሳቸውም በጥልቁ ከመረዳት ባሻገር ለሌላውም የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንዲያሳውቁ በማለት ይህንን ከሞላ ጎደል በኦሮሚያ ክልል ላይ ያነጣጠረውን ዓዋጅ ይዘት ብዚች ጽሁፍ አማካይነት ለማቅረብ ወሰንኩ። የዓዋጁን አፈጸፀም በተመለከተ አስተማማኝ መረጃ ላገኝ የቻልኩት ከኦሮሚያ ክልል ብቻ ስለሆነ፣ በሌሎች ክልሎች ውስጥ ያለውን ሁኔታ የተሻለ መረጃ ያላቸው ወገኖቼ መረጃቸውን ቢያጋሩን ደስ ይለኛል።

የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ በአፈጻፀሙ ላይ ብዙ መሰረታዊ የሆኑትን ለምሳሌ የመሰብሰብና የመንቀሳቀስ የመሳሰሉትን የሰው ልጆችን ህገመንግሥታዊና ተፈጥሮያዊ መብት ስለሚጥስ፣ ያገሪቷ ህልውና አደጋ ውስጥ ሊገባና ይህንን አደጋ ደግሞ ለመቀልበስ የመከላከያ ሰራዊቱን ከማሰማራት ሌላ አማራጭ አለመኖሩ ካልተረጋገጠ በስተቀር አይታወጅም። በሌላ አነጋገር የአገሪቷን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል ደጅ የቆመው አስከፊ ክስተት በጸጥታ አስከባሪ ሃይሎችና በህዝቡ ብርታት ሊወገድ የማይቻል መሆኑ ካልተረጋገጠ በስተቀር፣ አገሪቷን ከውጪ ወራሪ ኃይል ለመከላከል የተመሰረተውንና፣ ሥልጠናውም ከባዕድ ጠላት ጋር ጠመንጃ እንዲማዘዝ እንጂ ባዶ እጁን አንከርፍፎ ለሰልፍ በመውጣት ህጋዊ መብቱን በጠየቀው ሲቪል ዜጋ ላይ ለውጪ ጠላት የታለመውን ጥይት ተኩሶ እንዲገድልበት የመከላከያ ሠራዊቱን ማሰማራት ማለት አይደለም ማለት ነው።

የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ/ “የውጪ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የህግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን” የፌዴራል መንግሥቱ የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው” በማለት ሶስት መሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች አስቀምጧል። የሚኒስትሮች ም/ቤትም መስፈርቶቹ በሙሉ ተሟልተዋል በማለት ዓዋጁን ለፓርላማ አቅርቦ “ከተወያዩበት በኋላ” በአፈ ጉባዔው አቆጣጠር መሠረት ሁለት ሶስተኛው አባል ደግፎት ጸድቆአል። ተደርጎ ነበር ስለተባለው ውይይት ብዙ የምናውቀው ነገር ባይኖርም፣ ሾልኮ ከወጣው መረጃ የተገነዘብነው አንድ ተስፋ ሰጪ ክስተት ግን፣ የፓርላማው አባላት እንደወትሮው በአንድ ሞተር የሚዘወር ጭንቅላት ያላቸው ይመስል 547ቱም ባንድ ላይ እጅ የሚያነሱበት ልምድ ተሽሮ፣ በ27 ዓመት የኢህአዴግ አገዛዝ ሥርዓት፣ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ 90 የሚጠጉ የቁርጥ ቀን የኦሮሞ ልጆች “ተገዥነታችንና ታማኝነታችን ለህገ መንግሥቱና ለመረጠን ህዝብ ብቻ ነው” ብለው በአደባባይ ዓዋጁን ተቃውመው ድምጽ መስጠታቸው ነው። በተረፈ፣ የምርጫው ሂደት በአባላት ተደገፈም አልተደገፈም የተለመደው አሰራር “እናንተ ምረጡ፣ እኛ እንቆጥራለን” በሚል ስታሊናዊ መሪህ ስለሚመራ እንኳን 90 ሰው ይቅርና 500ም ሰው ቢቃወመው፣ ዓዋጁ ገና ለፓርላማ ሳይቀርብ ሥራ ላይ ውሎአል።

በኔ ግምት፣ ያሁኑ ዙር “የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ” በታወጀበት ወቅት በኢትዮጵያ የነበረው ሁኔታ፣ የውጭ ወረራ ያልተካሄደበት፣ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱም በምንም መስፈርት አደጋ ላይ ያልነበረና ምንም ነገር ከተለመደው የህግ ማስከበር ሥርዓት አቅም በላይ ያልሆነ ነበረ። ለማንኛውም የነበረውን ሁኔታ በቅደም ተከተል ማስቀመጡ ለሙግቴ መንደርደርያ ይሆናል ብዬ ስለምገምት እንደሚቀጥለው ላቅርብ።

የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአስራ ሰባት ቀናት በዝግ ያካሄደውን ስብሰባውን እንዳጠናቀቀ በአደባባይ ወጥቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ በሰጠው መግለጫ መሰረት፣ ድርጅቱ ዲሞክራሲያዊ አሰራር ስላልነበረውና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ባለመቻሉ ህዝቡን ማስቆጣቱን አምኖ ይቅርታ ጠይቆ ነበር። ጥፋትን አምኖ ይቅርታም ከመጠየቅ አልፎ ለተበደለው ህዝብ ካሳ እንዲሆን ከማሰብ፣ መልካም አስተዳደር እጦትን አስመልክተው ለመብታቸው መከበር በመታገላቸው ብቻ ያላግባብ ታስረው የነበሩትን የፖሊቲካ እስረኞች በሙሉ እፈታለሁ ብሎ ቃል ገባ። ለብዙ ዓመታት “ዲሞክራቲክ ድርጅት ነኝ፣ በመሆኔም ደግሞ ባገሪቷ ላይ ዲሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን ስላሰፈንኩ፣ መንገድ ላይ ወጥተው ለመረበሽ የሞከሩት አንዳንድ ጸረ ሰላም ቡድኖች በቀሰቀሱት ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ እንጂ የፖሊቲካ እስረኞች በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሉም” ብሎ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን መላውን የዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ለማሳመን ይሞክር ስለነበረ፣ የኢህአዴግ እስረኞችን ለመፍታት መወሰኑ ያልተጠበቀ መለኮታዊ ምርቃት የሆነውን ያህል ህዝቡን አስደሰተ። ቃል በተገባውም መሰረት፣ አንዳንድ የፖሊቲካ  መሪዎች ተፈትተው ከዘመዶቻቸው ጋር ተቀላቀሉ። በምድሪቷም ከብዙ ዓመታት በኋላ አንዳች አይነት የደስታ ድባብ ሰፈነ። የተፈቱት የፖሊቲካ እስረኞችም እስር ቤት በነበሩበት ጊዜ የሆነ ስብሰባ አድርገው በጥልቅ ከተነጋገሩበት በኋላ የጋራ አቋም የወሰዱ ይመስል ባንድ ድምጽ “ህዝቡ ትግሉን ፍጹም ሰላማዊ በሆን መንገድ ብቻ መቀጠል አለበት” ብለው በየፊናቸው ለደጋፊዎቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አስታወቁ። በቄሮ ታውጆ የነበረው የሶስት ቀናት የገበያ ማዕቀብ እንዲነሳና ህዝቡ ከተፈቱት መሪዎች ጋር በመሆን የመብት ጥያቄ ትግሉን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ እንዲቀጥሉ ስላሳሰበ ዓድማው ወድያውኑ ቆሞ ሰላም ሰፈነ። ህዝቡ ከዳር እስከዳር የደስታ ጭፈራውንና ቀረርቶውን እያሰማ በተገኘው ድል ተኩራርቶ ሰላማዊ ትግሉን ለመቀጠል ወሰነ። “የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ይታወጅ ይሆናል” በማለት ይናፈስ የነበረውን ወሬ “መሰረተ ቢስ ነው” በማለት የመንግስቱ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር በጉብኝት ከነበረበት ካሜሪካ ባደባባይ ተናገረ። በቅርቡ የተነሳው ዓዋጅ ምንኛ እንደጎዳን እናውቅ ነበርና ሌላ ዙር የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ባለመታወጁ ተደስተን በረጅሙ ተነፈስን፥ ግን ለትንሽ ሰዓታት። በሚቀጥለው ቀን አቶ ሲራጅ መርዶውን በደስታ መንፈስ ተሞልቶ ”አበሰረልን”።

መቼም መንግሥት ከህዝብ የተቀበለው አደራ ስላለበትና ያገሪቷን የግዛት አንድነትና የህዝቦቿን በሰላም የማኖር ኃላፊነት ያለበት ተቋም በመሆኑ፣ ዓዋጁ በርግጥም በህገ መንግሥቱ ውስጥ እንደተካተተው፣ ያገሪቷን የህገ መንግሥቱን ምንነት አደጋ ላይ የሚጥል ለኛ ለየዋሁ ህዝብ ያልታየ ግን ደግሞ “ለመንግሥታችን” ብቻ የታየ አንዳች ምክንያት ቢኖር ነው ብለን ራሳችንን ለማሳመንና ከዚህ “ካነጣጠረብን አደጋ” እንዴት አድርገን “ከመንግሥታችን” ጎን ቆመን እንደምንወጣው ማስላት ጀመርን። ግን ልባችን አልፈቀደም። ያገሪቷን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ሊከት የሚችል ”የውጭ ወረራ” መኖሩን የሚያመላክት አንዳች መረጃ አጣን። ኋላ እንደገባን፣ ዓዋጁ በዋናነት ያነጣጠረው በኦሮሞ ቄሮዎች ላይ መሆኑንና፣ የዚህን አኩሪ ትውልድ ለሶስት ዓመታት ያሰሙ የነበረውን የመልካም አስተዳደር እጦትና የመብት ጥሰት ጥያቄ አንስተው ወደ አደባባይ በመውጣታቸው፣ እንደ ውጭ ወራሪ ኃይል መቆጠራቸው ደግሞ በግልጽ አልተነገረንምና!

በግሌ ግን የሚከተሉት ክስተቶች “የመንግሥታችንን” ቅንነት ጥያቄ ውስጥ እንድከት ከማድረጋቸውም በላይ ዓዋጁ ራሱ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ሳይሆን፣ ህገ መንግሥቱን ተመርኩዞ የተተገበረ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ይመስለኛል። ዘርዘር ላርገው።

የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ በመሰረቱ የህዝብን የተፈጥሮያዊና ህገ መንግሥታዊ መብቶችን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ስለሚጥስ፣ ህዝቡም ለዓዋጁ መንስዔ የሆነውን የህልውና ማጣት አደጋ አምኖበትና “ግድ የለም፣ ለጊዜውም ቢሆን የመብቶቼን መጣስ እስማማበታለሁ” ብሎ ከመንግሥት ጎን ሆኖ ያንዣበበውን አደጋ ለመከላከል ዝግጁ እንዲሆን ታስቦ የሚታወጅ ነው። የመብት መጣስ ደግሞ አሳዛኝ በመሆኑና ባገሪቷ ህልውና ላይ ያነጣጠረው አደጋ የዜጎችንም ነፍስ መሰዋት ሊያስከትል ስለሚችል፣ መንግሥት ይህንን ዓይነት ዓዋጅ ሲያውጅ በሃዘን ተሞልቶ መሆን አለበት። ድንኳን ተተክሎ ሙሾ ይወረድ፣ ጥቁር ሱፍና ክራቫት ይለበስ ለማለት ሳይሆን፣ ያገሪቷ መሪ በሃዘን ሙዚቃ ታጅቦ ለኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ ማስተላለፍ ያለበት አገራዊ መርዶ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ይህ ሁኔታ ከክተት ዓዋጅ ጋር ይስተካከላል ማለት ነው። ጥያቄ ውስጥ የገባው የእናት አገር ህልውና ነውና። ያሁኑ ዓዋጅ ግን ለህዝብ የደረሰው ብርዕሰ ብሄሩ ሳይሆን በመልዕክተኛው በሲራጅ በኩል ነበር። ጠ/ሚኒስትሩ ተተኪ እስኪሾም ድረስ ሥልጣን ላይ ስላሉ መልዕክቱ በተላላኪ እንዲደርሰን መደረጉ፣ ወይ ያንዣበበው አደጋ እንደተባለው ያገሪቱን ህልውና የሚያሰጋ ስላልነበረ በርዕሰ ብሄሩ ደረጃ መነገር የለበትም ተብሎ የታሰበ ነው፣ ወይም ደግሞ በኢህአዴግ ውስጥ ህዝቡ ከሚያውቀው የተለየና ድብቅ የሆነ ከዚህ ዓዋጅ አንዳች ዓይነት ጥቅም የሚያገኝ  ወይም ሊያገኝ ያሰበ የፖሊቲካ ኃይል ይኖራል ብዬ እገምታለሁ።

ዓዋጁም የታወጀው ባልታሰብ ሰዓት ብቻ ሳይሆን ለመታወጁም ምንም ምክንያት አይኖርም ተብሎ በመንግሥቱ አፈቀላጤ እየተነገረን እያለና ፓርላማው በሥራ ላይ እንደሌለ እየታወቀ፣ ይህንን ዓዋጅ በአቋራጭ ለማወጅ ምን ዓይነት አስከፊ አደጋ ቢያንዣብብ ነው የሚል ጥያቄ ማንሳትም አግባብ ያለው ይመስለኛል። ዓዋጁ በሁለት ሶስተኛ የፓርላማው አባላት ድጋፍ ካልጸደቀ ሥራ ላይ እንደማይውልና ፓርላማው ደግሞ ተሰብስቦ እስኪወስን አስራ አምስት ቀን እንደሚያስፈልገው እየታወቀ፣ ዓዋጁም ይጽደቅ አይጽደቅ ቁርጡ ሳይታወቅ፣ በታወጀ በማግሥቱ ያገሪቷን መከላከያ ሰራዊት ከተለያየ ቦታ አሰባስቦና በኦሮሚያ ክልል ማሰማራቱ፣ ዓዋጁ የአንድ ትዕይንት መደምደምያ እንጂ መግቢያ እንዳልሆነ ይጠቁማል። የመከላከያ ሰራዊቱ በጊንጪና በአምቦ፣ በነቄምቴና በደምቢ ዶሎ ተሰማርቶ “ያገሪቷን ህልውና አደጋ ላይ ያደረሱትን” ወጣቶችን የመግደል ተልዕኮውን በሥራ ላይ ማዋል የጀመረው አዋጁ በታወጀ በጥቂት ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ነበርና ጥርጣሬዬ ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ። ፓርላማው “ባያጸድቀው” ኖሮ፣ ይህ ሁሉ ወጪ ወጥቶበት የተነሳቀሰውን የመከላከያ ሰራዊት ወደ ካምፑ ለመመለስ ሌላ የሎጂስቲክ ውጣ ውረድና ካዝና ማራቆት ሊጀመር ነበር ማለት ነው። ነገሩ በጥልቅ የተጠና፣ “ፓርላማውም እንደሚያጸድቀው” አስቀድሞ ስለሚታወቅና፣ የመከላከያ ሰራዊቱም በተጠንቀቅ ላይ ሆኖ “ተሰማራ” የምትለዋን ቃል ብቻ ይጠባበቅ ስለነበር፣ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ኦሮሚያን ማጥለቅለቁ የሚደንቅ አልነበረም።

ሌላው የዓዋጁንም ይዘት በተመለከተ፣ ካገሪቱ ህልውና ጋር ያልተያያዙና ኮማንድ ፖስቱ በተግባር ያውላቸዋል የተባሉ የክልል መንግሥታት የሥራ ድርሻ የሆኑ የቢሮክራሲ ሥራዎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ኮማንድ ፖስቱ ይተገብረዋል ተብሎ ከተሰጡት ሥራዎች አንዱ “በየክልሉ የተዛባውን የመሬት ይዞታን ማስተካከል” ነው። ይህ በምንም መልኩ የመከላከያ ሠራዊቱ የሥራ ድርሻ ሊሆን አይችልም። ያገሪቱን ዳር ድንበር ከውጪ ወራሪ ኃይል እንዲጠብቅ የተፈጠረና የሰለጠነን ሠራዊት፣ በሲቪል ቢሮክራሲ ውስጥ ገብቶ የመሬት ስርትን እንዲመረምርና እንዲያስተካከል ማዘዝ አንዳች የተደበቀች ለኢህአዴግ አመራር ብቻ የተገለጠች “ልዩ ነገር“ ብትኖር ነው ብዬ አሰብኩ። ሌላም እንደዚሁ ይዘቱ ግልጽ ያልሆነ “ያላግባብ ሃብት ማንቀሳቀስ” የሚል ተጨማሪ ተልዕኮ ለኮማንድ ፖስቱ የተሰጠ ቢሆንም፣ ምንም ማብራርያ ስላልተሰጠበት በምን መስፈርት “ያገሪቷን ህልውናና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ሊያደርስ” እንዳንዣበበ በግልጽ ቢነግሩንና ተባብረን “ዘምተንባቸው” አገሪቷን ከአደጋ ብናድናት ደግሞ ጥሩ ነበር።

በዓዋጁ አፈጻፀም ረገድ ሌላ ያገሪቷን ህልውና በምንም መልኩ አደጋ ላይ የማይጥልና ከተከሰተም ብዙ ወራት ያለፈውና ችግሩ በኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደር አቀነባባሪነትና ያለፌዴራሉ መንግሥት እርዳታ ጊዜያዊም ቢሆን መፍትሄ የተገኘለትን፣ በኦሮሚያና በሶማልያ ክልል ኗሪዎች መሃል በተፈጠረው “ሰው ሰራሽ” ግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉትን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋውን ተፈናቃይ ኦሮሞዎችን መልሶ የማቋቁም አደራ ለኮማንድ ፖስቱ መሰጠቱ ነው። ከዚያ ሁሉ ወራት በኋላና፣ እንኳን ዕርዳታ ሊያደርግ ይቅርና የተፈናቃዮቹ ወገኖቻችን ሰቆቃ በብሄራዊ ሚዲያ እንኳ እንዳይተላለፍ ሲከለክል የነበረው “መንግሥታችን”፣ አሁን ላይ ቆሞ፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና መላው የኦሮሞ ህዝብ ርብርቦሽ ጊዜያዊ መፍትሄ የተገኘለትን ጉዳይ እንደ አንድ “ያገሪቷን ህልውና ከሚፈታተኑ አደጋዎች” አድርጎ በማቅረብና የኮማንድ ፖስቱ ተጋፍጦት “አገሪቷን ከአደጋ እንዲያድን” ማወጁ፣ ዓዋጁ ከመጀመርያውም የታለመው አገሪቷን ከአደጋ ለማዳን ሳይሆን ለሌላ እኩይ ዓላማ ነው ለማለት እደፍራለሁ።

እንደው ያገሪቷን ህልውና የተፈታተነ አደጋ ስለነበረ ዓዋጁ አስፈላጊ ነበር ብለን ራሳችንን ለማሳመር ብንሞክር እንኳ፣ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 93/5 ውስጥ የተካተተውና በህግ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቋቋም የተደነገገው “የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ” የሚል ሆኖ እያለ፣ ይህ ኢ-ህገመንግሥታዊ የሆነ “ኮማንድ ፖስት” የሚባለው ከማናቸውም የክልል አስተዳደር የበላይ የሆነና፣ የፌዴራል መዋቅሩን የሚጻረር፣ ተጠያቂነቱም በግልጽ ለማን እንደሆነ የማይታወቅ የከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊቱ አባላትን ብቻ ያቀፈ አካል እንዴት ሊፈጠር ቻለ የሚለው ጥያቄም ሌላው የዓዋጁን ወቅታዊነት ብቻ ሳይሆን ቅንነቱንም ትልቅ ጥርጣሬ ውስጥ ይከታል። የሚያሳዝነው ግን የቦርዱን መቋቋምም ሆነ ተቋቁሞም ከሆነ ደግሞ የመከላከያ ሰራዊቱ እስካሁን ድረስ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከደርዘን በላይ የሚሆኑትን ወጣቶችን የገደሉትን የመከላከያ አባላት ለፍርድ ሲያቀርብ አለመታየቱ ነው።

ዓዋጁን የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ሳይሆን ህገ መንግሥቱን ከለላ አድርጎ በህዝባችን ላይ የታወጀ ወታደራዊ ዓዋጅ መሆኑን ከሚያሳዩት ባሕርይዎች አንዱ፣ አንዣብቧል የተባለው አደጋ “በተለመደው የህግ ማስከበር ሥርዓት ለማቋቋም የማይቻል” እንዳልሆነ ጉልህ የሆኑ ነባራዊ ሁናቴዎች መኖራቸው ነው። ለምሳሌ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስና ሌሎችም ሰላም አስከባሪ ኃይላት መብታቸውን ለማስከበር በወጡት ቄሮዎች ላይ አንዳችም ዓይነት እርምጃ እንዳይወስዱ የክልሉ መንግሥት ስላዘዘ፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰውም ሆነ በንብረት ላይ አደጋ ሳያደርሱ ለሶስት ዓመታት ተሰልፈው በመውጣት ብሶታቸውን ይገልጹ የነበረ ሲሆን፣ የተቃውሞ ሂደቱ በየትም ቦታ እንኳን ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሊያሰጋ ቀርቶ ከክልሉ ፖሊስ ቁጥጥር ውጭ የሆነበት ጊዜ አልነበረም። በኔ ግምት ይህ በኦሮሞ ህዝብና በኦህዴድ መካከል እየታየ ያለው የመቀራረብና የመግባባት ጉዳይ ለወያኔ ቡድን የተዋጠለት አይመስለኝም። በኔ ግምት፣ ኦህዴድ የወያኔ ፍጡርና ብሎም ፍጹም ታዛዥ በመሆኑ፣ ፈጣሪያቸው ወያኔ በኦሮሚያ መሬት ላይ እንደፈለገ እንዲያዝበት ላለፉት ሃያ አምስት ሙሉ መብት ተሰጥቷቸዋል። ዛሬ የአዲሱ ትውልድ የነለማ መገርሳ ቡድን ግን “የተለመደውን” አጎብዳጅነት መቃወም ሲጀምሩና ለኦሮሞ ህዝብ መብትና ማንነት በአደባባይ መናገር የቀን ተቀን ሥራቸው በማድረጋቸው፣ ጥቅሙ የቀረባቸው የወያኔ ባለሥልጣናትና ጀሌዎቻቸው ይህንን የኦህዴድን አሻፈረኝነትና ከኦሮሞ ህዝብ ጋር የመግባባት ሂደት “ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የተፈታተኑ” መሰላቸው። ይህ ደግሞ በምንም መልኩ የኢትዮጵያን ህልውና የማይፈታተን የማንነት ጥያቄ ብቻ ስለሆነ፣ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ሳይሆን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ነው ለማለት የደፈርኩት። አፍ አውጥተው “መፈንቅለ መንግሥት” ነው እንዳይሉ ደግሞ ሌላው ቢቀር የአፍሪቃ አንድነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባቸውን አገራት ከአባልነት እስከመሰረዝ የደረሰበት ሁኔታ በመኖሩና ኢትዮጵያ ደግሞ  የድርጅቱ መቀመጫም ስለሆነች፣ መፈንቅለ መንግሥት ከማለት “የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ” በማለት በተለመደው አሰራር የተለመደውን ጥቅም ማግኘት ሲያቅታቸው “በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ” ስም ወታደራዊ አገዛዝ አስፍኖ የተለመደው የጥቅም ምንጭ እንዳይዘጋ ለማድረግ ታስቦ የታወጀ ነው ያልኩት። መፈንቅለ መንግሥት ህገ ወጥ ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ግን ህጋዊ ነውና።

ከዚህ በመነሳት ነው እንግዲህ ዓዋጁ ያነጣጠረው በቄሮዎች በተመራውና ላለፉት ሶስት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሲካሄድ የነበረውን የማንነትና የመብት ጥያቄ ላይ ነው የምለው። ቄሮዎች ደግሞ የጠየቁት የማንነትና የመብት መከበር ጥያቄ በሰላም መንገድ እንጂ አንዳችም ቦታ ላይ ህገ መንግሥቱን በመጻረር የትጥቅ ትግል ይቅርና ተራ የጎረምሳ ጉልበት እንኳ የተጠቀሙበት ሁኔታ አልነበረም። ባንዳንድ አገራት ተመሳሳይ ተቃውሞ ለማሳየት በአደባባይ የሚወጡት ወጣቶች የሚፈጽሙትን የጥፋት ተግባራት በቴሌቪዥን መስኮታችን ስናስተውል፣ ቄሮ ምንኛ የነቃና የተደራጀ፣ መብቱን ለማስከበር ደግሞ ሰላማዊ ህዝባዊ ዓመጽ እንጂ እንኳን ጥይት ይቅርና ዱላ ይዞ መውጣት እንደሌለበት መመርያው አድርጎ የተቀበለ የታሪክ ኃላፊነት ያለበት ትውልድ መሆኑን ነው። ለዚህም ደግሞ የህብረተሰቡን ባህል ተከትለው ታሪካዊ ግዴታቸውን በመወጣት፣ ሰላማዊ ትግል ከሁሉም የትግል ዘዴዎች አመርቂ መሆኑን ያለመታከት ያስተምሩ ለነበሩ ለነበቀለ ገርባና ቡድንና ለወጣቱ ትውልድ የኦህዴድ አመራር አባላት ምስጋና ይገባቸዋል። እንግዲህ ይህንን ቄሮን ነው መንግሥት ላገሪቷ ህልውና ያሰጋሉ ብሎ በመፈረጅ በአስቸኳይ አዋጅ ስም ወታደራዊ አገዛዝ ያወጀባቸው። አሁን የማይታየን ወይም ደግሞ እንዲታየን የማንፈቅደው፣ ግን ደግሞ ሊከሰት የሚችል አደጋ ቢኖር፣ ዛሬ ትግሉን መቶ በመቶ በሰላማዊ መንገድ በማካሄድ ላይ ያለው ቄሮ፣ የፌዴራል መንግሥቱና መከላከያ ሰራዊቱ ሰላማዊውን ወጣትና ሌላውንም የኦሮሞ ህዝብ መግደልና ማሰር ከቀጠለበት፣ መቼም የሰው ልጅ ራሱንና ቤተሰቡን ብሎም ማህበረሰቡን ከጅምላ ግድያ ለማዳን ተመጣጣኝ የሆነ የትግል ሥልት ለመቀየስ እንደሚገደድ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል። ጉልበተኛው ሊደፍራት የሚታገላትን ጎረምሳ አርፈሽ ተደፈሪ ማለት ከተፈጥሮ ውጭ ይመስለኛል። ተለማምጣ ከመደፈር መትረፍ ካልተቻላት የተገኘውን አጋጣሚና መሳርያ ተጠቅማ ራሷን ከመከላከል የሚያግዳት ነገር ሊኖር አይችልም።

እንግዲህ ወደድንም ጠላንም ዓዋጁ “ባፓርላማው ጸድቆ” ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሥራ ላይ እንዲውል ታውጆአል። በተሰጠውም መሰረት፣ ኮማንድ ፖስቱም መወገድ አለባቸው ብሎ ካመነበት ማንኛውንም ያላንዳች ማመንታት እንዲገድል ሙሉ መብት ተሰጥቶት “ላገሪቷ ህልውና አደገኞች የሆኑ” ደርዘን ቄሮዎችን ገድሏል። በትላልቅ የኦሮሚያ ከተሞች የመገናኛ አውታሮችን፣ የመብራትና የውሃ አገልግሎትን ቆርጧል። ዜጎች እንኳን ወደ ደጅ ይቅርና ከክፍላቸውም እንዳይወጡ በመደረጉ፣ በጨለማ ውስጥ ሆነው በውሃ ጥም እያለቁ መሆናቸውን ከቦታው የሚደርሱን አስተማኝ መረጃዎች ይናገራሉ። በሰላማዊ ዜጎች ላይ ይህን ኢሰብዓዊ ግፍ መፈጸም እውነት ያንድ አገር መከላከያ ሰራዊት በራሱ ዜጎች ሊፈጽማቸው የሚገባቸው ተግባሮች በምንም መስፈርት ትክክል ነው ብሎ የሚሞግተኝ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም።

በኔ ግምት የህገ መንግሥታዊ መብቱን መከበር ብቻ በሰላማዊ መንገድ እየጠየቀ ያለውን ቄሮንና ሙሉ ድጋፍ የሰጠውን የክልሉን መንግሥት፣ ህገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ከሥልጣን ለማውረድና ህዝቡንም በክልሉ በሰላም የመኖር መብቱን ለመጣስ አቅዶ፣ ኮማንድ ፖስት የሚባል ወራሪ የውጭ ኃይል አሰማርቶ የኦሮሚያንና የኦሮሞዎችን ህልውና አደጋ ውስጥ ከቷልና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ውሎ ሳያድር “በኦሮሞ ህዝብ ማንነትና የክልል ህልውና ላይ ያነጣጠረ አደጋ” መኖሩን ለህዝብ አሳውቆ፣ ህዝቡም የተገኘውን ሁሉ የትግል ዘዴ ተጠቅሞ ራሱን፣ ቤተሰቡና ማህበረሰቡን እንዲከላከል” የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ማውጣት አለበት እላለሁ ኦሮሚያ፣ ኮማንድ ፖስት በተባለ ወራሪ ኃይል ስትደፈር፣ ኮማንድ ፖስቱ ደግሞ የመግደል ዓላማውን ካላቆመና ገዳዮችም ለፍርድ የማይቀርቡ ከሆነ፣ ዕድሜ ልኩን ሲገፋ የኖረው ትውልድ ዛሬም እስከ ጫፍ ድረስ ከተገፋ፣ ሳይወድ በግድ ራሱን ለመከላከል ሲል ብቻ ባሩድ ከመንከስ የሚያቆመው ነገር አይኖርም ብዬ እገምታለሁ። ዛሬ ቧንባ ዘግቶ ወገንን በውሃ ጥም የሚቀጣ ወራሪ ኃይሉ ኮማንድ ፖስት፣ ነገ ደግሞ፣ “ላገሪቱ ህልውና የሚያሰጋውን ቄሮን ለማጥፋትና ኢትዮጵያን ለማዳን” በሚል ሰበብ፣ ልክ ጣሊያን እንዳደረገው፣ የውኃው ምንጭ ውስጥ መርዝ ከመጨመር የሚያግደው ያለ አይመስለኝም።

አንድ በጣም የዘገነኝ ነገር ቢኖር፣ ዓዋጁ ላፓርላማ ቀርቦ “ከተወያዩበትና” “በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ድጋፍ” ካለፈ በኋላ፣ “ያገሪቷን ህልውና አደጋ ላይ ነው እየተባለ” እየተባለ ምኑ አስደስቷቸው ነው “የህዝብ ተወካዮቹ” በደስታና በጭብጨባ አዳራሹን ያናወጡት? አስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ እኮ በተፈጥሮው “የእናት አገር ሞት መቃረቡን” የሚነግር “መርዶ” ስለሆነ ደስታው ምኑ ላይ እንደሆነ አልገባኝም። ሙሶሊኒ ወታደሮቹን በጳጳሱ እያስባረከ ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ወገኖቻችንን እንዲገድሉ ሲልካቸው መለዮአቸውን ወደ ሰማይ እየወረወሩ ያሳዩ የነበረውን ደስታ፣ ዛሬ በመዲናችን “ተወካዮቻችን” ያሳዩ የነበረው የመደሰት ምልክት ምንኛ ከህዝብ እንደተለዩ፣ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያሳድዱና ወገኖችን ለሞት አሳልፎ ከመስጠት የማይመለሱ አረመኔዎች መሆናቸውን ሳስተውል ከነሱ ጋር ያንድ አገር ዜጋ መሆኔ ራሱ ቀፈፈኝ።

ጊዜ ያመጣውን ጊዜ ይመልሰዋል ይላሉ አበው ሲተርቱ። ዛሬ ጉልበት አለኝ ብሎ በሰላማዊው ህዝብ ላይ ዘምቶ አፍላ ወጣቶችን በጥይት የሚያጭዱ የመከላከያው ሰራዊት አባላት፣ ውሎ ይደር እንጂ አንድ ቀን ለፍርድ መቅረባቸው አይቀሬ ነው። እየፈጸሙ ያሉት የግድያ ወንጀል ደግሞ በጦርነት ወቅት በ humanitarian law የሚፈቀደው “የታጠቀ ጠላትን የመግደል መብት” ሳይሆን የይርጋ መብትን በማያስተናግደው በ human right law መሪሆዎች ጥሰት ስለሆነ፣ በዚች ምድር ላይ በሕይወት እስካሉ ድረስ ተጠያቂ ሆነው እንደታደኑ ይኖሯታል። የመብቱን መከበር ብቻ በሰላማዊ መንገድ የሚጠይቀውን ዜጋ መግደል ደግሞ በምድራዊውም ሆነ በሰማያዊው ህግ ወንጀል ስለሆነ ገሃነም ወይም ወህኒ ቤት ከመውረድ አያድንም።

የታፈነ ነገር ጊዜውን ጠብቆ መፈንዳቱ አይቀርም። ይህ ዲያለክቲካዊ ሃቅ ነው። ያ ጊዜ ደግሞ ደርሶ የኦሮሞ ህዝብ ፍርሃትን አሸንፎ ደረቱን ለጥይት ገልጦ ለመብቱ እየተሟገተ ነው። ሌላው ቀርቶ በኦህዴድ ውስጥ ያሉት ኦሮሞዎችና የክልል አመራሮች ሳይቀር የወያኔን አገዛዝ በአደባባይ መቃወምና ከሰፊው ህዝብ ጋር መወገን ከጀመሩ ሰንብተዋል። ዛሬ ያለው የኃይል ሚዛን ለወያኔ/ኢህአዴግ ያደላ ቢሆንም በሂደት ውስጥ ግን ሚዛኑ ወደ ቄሮዎች እንደሚደፋ ዕሙን ነኝ። ከፊታቸው የቆመውን ጎልያድን ለማንበርከክ የሚያስችላቸውን ወንጭፍ አዘጋጅተው በቂ ድቡልቡል ድንጋይ በመሰብሰብ ላይ ስለሆኑ ግዙፉ ጎልያድ ይዋል ይደር እንጂ ከነዚህ ወጣት ትውልድ በሚወረወር ድንጋይ ተመትቶ እንደሚወድቅ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የለኝም። የሚያሳስበኝ ግን፣ ወያኔ ይህንን “የአስተሳሰብ ለውጥና የቄሮዎችን ጥንካሬ” ከግምት ሳይከት ቀርቶ “እንደለመደው” በጉልበት መግዛቱን ከቀጠለበት፣ የግፉ ብዛት ከመጠን በላይ ይሆንና ዛሬ ባዶ እጁን ለሰልፍ የሚወጣው ቄሮ፣ ህገ መንግሥታዊ መብቱን ለማስከበር ሲባል፣ ነገ ደግሞ ጠብመንጃ አንግቶ እንዳይሰለፍ የሚከለክለው ምድራዊ ኃይል ያለ አይመስለኝም። ያንን “በጠብመንጃ ኃይል” ተደግፎ መብትን የማስከበር ልምድን ነው እንግዲህ ካገራችን የፖሊቲካ ህይወት ላንዴና ለመጨረሻ እንዲወገድና፣ ካለጠብመንጃ ሥልጣን መያዝም ሆነ ማቆየት የሚቻል የማይመስለውን ወያኔን፣ ከተቻለ በማሳመን፣ ካልተቻለም በተቀነባበረ ህዝባዊና ሰላማዊ ዓመጽ ለማስወገድ መጣር ያለብን።

ጎልያድን አስወግዶ የጭቆና ቀንበሩን በመስበር ላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች በሙሉ ካልተባበሩ እውነተኛ ነጻነት ሊገኝ ስለማይችል፣ ሁሉም ባንድ ላይ በመነሳት ህገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው መጠየቅ አለባቸው። በሂደት ውስጥ ደግሞ አምቦ ላይ ኦቦ ነጋሳ ሲገደል ባህር ዳር ላይ አቶ ከፍያለው ካልተሰማው፣ ጎልያድን የምናስወግድበትና ባገራችን ሰላም ሰፍኖ የምናይበትን ጊዜ ማራዘም ይሆናል። ዛሬ በዚች ቀውጢ ጊዜ ኃይላችንን በማስተባበር ይህንን ጭራቅ አስወግደን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችለንን መሰረት ለመጣል በጋራ ለመቆም የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን። የተለመደው ድርጅቶችን የመፍጠርና የማባዛት ባህላችን መቆም አለበት። አገሪቷን ከዳር እስከዳር ያዳረሰው አገራዊ አደጋ አንድ ብቻ ሆኖ እያለ፣ ይህንን አደጋ ለመስበር ደግሞ መቶ የተለያዩ ድርጅቶች አቅፈን የምንጓዝበት ምክንያት ሊኖር አይገባም። ለግል የፖሊቲካና ሌላም ማህበረሰባዊ ጥቅም ካልሆነ በስተቀር፣ ዛሬ አገራችን ያለችበትን ሁኔታ በቅንነት ለሚረዳው ሰው፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሮ ከመታገል መታቀብ በታሪክ ፊት በከሃዲነት የሚያስጠይቅ ይመስለኛል።

ለማጠቃለል ያህል የተለመደውን ለወያኔ የማቀርበውን ምክር አዘል ማሳሰቢያ እንደገና ልሰንዝር። በጠብመንጃ ብርታት ሥልጣን መያዝ ብቻ ሳይሆን ሥልጣንን ማቆየት እንደሚቻል ለዓለም ህዝብ አስመስክራችኋል። ሥልጣንን በሞኖፖሊ ይዛችሁ በቆያችሁበት በሶስት ምዕት ዓመት ጊዜ ውስጥ የዜጎችን ልብና ቀልብ ለመማረክ አለመቻላችሁን ግን በቅጡ የተረዳችሁት አይመስለኝም። በመሆኑም እንደለመዳችሁ በጠብመንጃ ብርታት መግዛቱን የመፈለጋችሁን ያህል ህዝቡ ደግሞ ከዳር እስከዳር፣ የአገዛዛችሁን ሥርዓት ገርስሶ ለመጣል ተሰልፏል። ታፍኖ የነበረው ህዝብ ፍርሃትን አሸንፎ በአደባባይና በፓርላማችሁ ሳይቀር ተቃውሞውን እያሳያችሁ ነው። አምባገነን መንግሥታት እስከ ግብዓተ መሬታቸው ድረስ ሥልጣንን ማስረከብ እንደማይፈልጉ ባውቅም፣ መቼም ወገኖቻችን ናችሁና ከልምድ ተነስቼ የሚከተለውን አጭር ምክርና ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ።

በፖሊቲካ ሕይወት፣ ከተቃዋሚ ጋር ሥልጣንን በዕኩልነት ለመጋራት መደራደር በራስ የመተማመን እንጂ የመሸነፍ ምልክት አለመሆኑን ተገንዝባችሁ በአስቸኳይ ለድርድር መቅረብ አለባችሁ። የድርድሩም ዓላማ እስከሚቀጥለው መደበኛ የምርጫ ቀን ድረስ አገሪቷን የሚያስተዳድር ከሁሉም ባላድርሻ አካላት በተውጣጡ የድርጅት ተወካዮች የተዋቀረ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ሲሆን፣ በዚህ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የፖሊቲካ ድርጅቶች በምርጫ ቅስቀሳ እንዲሳተፉ ለማድረግ የጸረ ሽብር ዓዋጁንና የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁን ማንሳት አለባችሁ። ይህን ካደረጋችሁ፣ ህዝቡም ለተቃውሞ ሰልፍ መውጣቱን ትቶ ፊቱን ወደ ምርጫው ያዞራል። እናንተም የትግራይ ክልልን ድምጽ በሙሉ አሸንፋችሁ ወደ ፓርላማው መመለሳችሁ ዕሙን ስለሆነ ለወደፊቱ የሚያሰጋችሁ ነገር አይኖርም።  በነዚህ ሁለት ዓመታት የሽግግር ወቅት ደግሞ እስከዛሬ የሰራችሁትን በጎም ሆኑ ክፉ ሥራዎች የመገምገምና የሚስተካከልም ካለ ለማስተካከል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ እስከዛሬ “ለፍታችሁ” ያካበታችሁትን ሃብት “ቦታ ቦታ” ለማስያዝ በቂ ጊዜ ይኖራችኋል። የከዚህ የተሻለ ሥልጣንን በክብር የማስረከብ ዘዴ ስለሌለ በጥብቅ አስቡበት። ለድርድር አንቀርብም የምትሉ ከሆነ ግን፣ ወደዳችሁም ጠላችሁ እንደማንኛውም አምባገነን መንግሥት አንድ ቀን ተገፍታችሁ ትወድቃላችሁ። ያኔ ግን አወዳደቁ በጣም አስቀያሚ ይሆናል። እንደተከበሩ ሥልጣንን በሰላም መልቀቅና ተዋርዶ በመልቀቅ መካከል ያለው ልዩነት ደግሞ ከናንተ የተሰወረ  አይመስለኝም። ባገራችን ሰላም ሰፍኖ እናንተም እንደ ነፍሰ ገዳይ ሳይሆን እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ህገ መንግሥታዊ መብታችሁ ተከብሮላችሁ የምትኖሩባትን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት መሰረት የሚሆነውን የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ታሪካዊ ሚናችሁን ተወጡ። በሥልጣን ወንበሩ ላይ ስለሆናችሁ፣ ተቃዋሚ ኃይሎችን በሙሉ ለድርድር መጋበዝ ደግሞ ታሪካዊ ግዴታችሁ ነው። አገሪቷን ወደማያስፈልግ የርስ በርስ ጦርነት ላለመምራትና፣ ላገርና ለወገን ሰላም ሲባል ብቻ ፈጣሪ ቅን ልቦና ሰጥቷችሁ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ያምጣችሁ። አሜን።

******

ጄኔቫ፣ 3 March 2018

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.