ለሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ኢትዮጵያዊነትና ኦሮሞነት ምንና ምን ናቸው?

ለሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ኢትዮጵያዊነትና ኦሮሞነት ምንና ምን ናቸው?

ፀጋዬ ገብረ መድህን

(BBC Amharic) — ግጥም፣ ተውኔት ሲጽፍ የልቡን ቀለም እየቀባ ያቀርባል። ስለ ሕዝብ፣ ስለ አገር፣ ስለ ወንዝ፣ ስለ ስልጣኔ፣ በአጠቃላይ ያመነበትን እውነት በቅኔ ወደ ብርሃን ያወጣል።

በጥልቁ ያሰላስላል፤ ምናቡም ሩቅ ነው። ሎሬቱን ራሱ በጥበብ ተጠቅልሎ ለትውልድ የተላለፈ ቅርስ ነው እያሉ የሚያሞጋግሱት በቅርብ የሚያውቁት ብቻ ሳይሆን በሥራዎቹ በፍቅር የወደቁ እና በፍቅር ያጣጣሙት ጭምር ናቸው።

. . .የማይድን በሽታ ሳክም

የማያድግ ችግኝ ሳርም

የሰው ሕይወት ስከረክም

እኔ ለእኔ ኖሬ አላውቅም. . .

በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉ ከ30 በላይ ተውኔቶችን ጽፏል።’እሳት ወይ አበባ’ የግጥም መድብሉ ሲሆን፣ ‘ሀሁ በስደት ወር’፣ ‘እናት ዓለም ጠኑ’፣ ‘የከርሞ ሰው’፣ ‘መልዕክተ ወዛደር’፣ ‘ሀሁ ወይንም ፐፑ’፣ ‘የመቅደላ ስንብት’ የተሰኙ ደግሞ ከተውኔቶች መካከል የተወሰኑት ናቸው።

ሐምሌትና ማክቤዝ፣ ደግሞ ከእውቁ ዊሊያም ሼክስፒር ወደ አማርኛ ከመለሳቸው ስራዎቹ መካከል ናቸው።

እነዚህ የጥበብ ሥራዎች ፀጋዬ በአገር፣ በብሔርተኝነትና በማንነት ላይ ያለውን አቋም ያሳዩ ይሆን?

ለዚህ ጥበበኛ ኢትዮጵያዊነትና ኦሮሞነት ምንና ምን ናቸው?

አቶ ሚካኤል ሽፈራው በሙያው ሥነ ሕንጻ ባለሙያ ሲሆን፣ የፀጋዬን በክብር እንደሚወደውና እንደሚያነበው ይናገራል። ከስራዎቹ አንዱንም በመተንተን መጽሐፍ አሳትሟል።

መጽሐፉ ‘ምስጢረኛው ባለቅኔ’ ይሰኛል። ፀጋዬ በቅኔ እና በምሳሌ ስለሚጽፍ ያኔ ሰው አይረዳም ነበር ይላል። አቶ ሚካኤል፣ ፀጋዬ በመጨረሻዎቹ ዘመናት የጻፈውን ‘ሀሁ በስድስት ወር’፣ ምዕራፍ በምዕራፍ ትርጉም ለመስጠት ሞክሯል።

ከዚህም በተጨማሪ በአምቦ ዩኒቨርስቲ ለሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ማስታወሻነት እየተገነባ ያለውን ማዕከል ዲዛይን በማድረግ በነጻ እያገለገለ ነው።

“ማንም የፍፁም እውነት ባለቤት አይደለም”

ሎሬት ፀጋዬ ስለ አንድ ነገር በጭራሽ በእርግጠኝነት አይናገርም። በቡድንም አያስብም። ከኢትዮጵያዊነትም ከኦሮሞነት የሚበልጠውን እውነት ሊያሳየን ይሞክራል ይላል አቶ ሚካኤል።

በዚህ በተነተነው የፀጋዬ ተውኔት ውስጥ፣ ሁለት ሰዎች እግራቸውና እጃቸው አንድ ላይ ተጠፍሮ ነው የሚጀምረው። ይህም የአንድ እናት ልጆች መሆናቸውን ለማሳየት የተጠቀመው ምሰላ (ሲምቦሊዝም) መሆኑን ያስረዳል።

ይኹን እንጂ እነዚህ ሰዎች ወዲያው መጣላት ይጀምራሉ። አትተያዩም፤ አትደማመጡም እንጂ እውነት አንድ ቦታ የለችም እያለ ያን ዘመን በፖለቲካ አቋማቸው ለሚጣሉ ፖለቲከኞች ይናገራል።

ይሁን እንጂ ፀጋዬ “ይህ ተጎድቷል፤ ያ ጎድቷል በሚል መፍትሄ አይሰጥም” እንደውም ፀጋዬ ለዚህ ሕዝብ መፍትሔ ነው ብሎ የሚያስበው፣ መንቃት፣ አይንን መክፈት እና ማወቅ ነው ይላል አቶ ሚካኤል።

አንዱ ቡድን ስለሌላው ቡድን ማወቅ፣ መመራመር ከቻለ ሁለቱ ብርሃኑ ውስጥ ይገናኛሉ ይላል።

ለእርሱ መንቃት ማለት ታሪካችንን ማወቅ፣ ያወቅነው እውቀት ጎዶሎ መሆኑን መረዳትን ይጨምራል።

ፀጋዬ ገብረ መድህን ማን ነው?

ፀጋዬ አምቦ ቦዳ የሚባል አካባቢ ተወለደ። እናቱ በጣሊያን ጊዜ ሸሽተው ነው ከአባታቸው ጋር ጎረምቲ የምትባል አካባቢ የሄደው።

አባቱ የሜጫ ኦሮሞ ሲሆኑ፣ እናቱ ደግሞ የአንኮበር አካባቢ አማራ ነው።

እናቱ ወ/ሮ በለጠች ታዬ አምቦ ከማህበረሰቡ ጋር በፍቅር ነበር የሚኖሩት፣ ከባላቸው እህት፣ ወ/ሮ አርገቱ ጋር ደግሞ የጠበቀ ወዳጅነት ነበራቸው።

እናቱ ወንድ ልጅ ለማግኘት ለአቦ ቤተክርስትያን ስለት አስገብተው ፀሎት ሲያደርጉ፣ በእምነታቸው ዋቄፈቱ የነበሩት ወ/ሮ አርገቱም ለወዳጅነት ሲሉ አብረው ይፀልዩ ነበር ይላል አቶ ሚካኤል።

ሎሬት ፀጋዬ በኦሮምኛ ነው አፉን የፈታው። በኋላም የጣልያን ወረራ ጊዜ ከአንኮበር ሸሽተው የመጡት የእናታቸው ወንድሞች ግዕዝን አስተማሩት።

አባቱ ደግሞ ዘመናዊ ትምህርት አስገቧቸው።

በኋላ ላይ ነው ጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት የዊሊያም ሼክስፒርን ጠነን ያለ እንግሊዝኛን ነበር የተማረው።

አባቱ ሹመት እናቱ ደግሞ ክህነት ይመኙለት ነበር።

ስለዚህ የዚህ ሰው ማንነት በራሱ ውስጥ አንዴ ሲዋደድ አንዴ ሲጣላ በአገር ደረጃ አይተነዋል።

የእናቱን ፍላጎት ለመሙላት፣ ከካህናት ጋር ይውል ነበር። እነርሱን ደግሞ ይተውና ከሹማምንት ጋር ይሄዳል። በዚያው ቀርቶ አይቀርም ተመልሶ ሲጽፍ ይታሰራል። ስራዎቹም አንዳንዴ ይታገዱበት ነበር ይላል አቶ ሚካኤል ሽፈራው።

ስለ አገር ማወቅ የሚፈልገውን እውነት ፀጋዬ፣ ከውጪ ሳይሆን ከውስጡ ለማግኘት ይለፋ ነበር። ኢትዮጵያን መከፋፈል ደሜን ማፍሰስ ነው ብሎ ያምን ነበር።

ይህ ሰው በኢትዮጵያዊነቱ ልቆ ይሂድ እንጂ የዓለም ዜጋ ነው። የእውቁን ፀሀፊ ዊሊያም ሼክስፒርን፣ ጠነን ያለ እንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ቢተረጉምም፣ ብዙ ጊዜውን ያዋለው ግን ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሥራዎቹ ላይ ነው።

ለእርሱ ኦሮሞነትና አማራነት ፍፁም ተጋጭተውበት አያውቁም። እንዲያውም ወደ ጥናትና ጥበብ ይቀይራቸዋል።

ይኹን እንጂ ፍትህ ሲጎድል ደግሞ ዝም ብሎ የሚመለከት አይደለም። ለምሳሌ ‘ይድረስ ለወንድሜ ለምታውቀኝ ለማላቅህ’ የሚለው ስራ የብሔር ብሔረሰቦች ጭቆና የሚያትት ነበር።

ሎሬቱ ብሔርተኛ ነበሩ?

በሚኒሶታ ኖርዝ ዌስተርን ዩኒቨርስቲ የሥነጽሑፍ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ተፈሪ ንጉሤ፣ ፀጋዬ ገብረ መድህን የፓን አፍሪካ ብሔርተኝነት ያቀነቅን ነበር ይላሉ።

እይታውና ፍልስፍናው ከጥቁር ሕዝቦች ማንነት ይመነጫል። ኦሮሞነቱንም ካየነው ኦሮሞ ከኩሽ ሕዝቦች አንዱ ነው ብሎ ስለሚያምን እነርሱ ደግሞ የስልጣኔ ጀማሪዎች ናቸው ይላል።

እርሱ የሚዘምርለት ኢትዮጵያዊነት፣ ኦሮሞ የሚፈልገው አይነት ነው ይላሉ ዶ/ር ተፈሪ።

ይሄንን ደግሞ በጽሑፎቹ ውስጥ በግልጽ ታይቷል።

እሳት ወይ አበባ በሚለው የግጥም መድብል ውስጥ፣

አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ

በኔና በአንቺ መሃል አጉል ስልጣኔ ቆሞ

የሚሉት መስመሮች ተምረናል የሚሉ ሰዎች እንዴት ራሳቸውን እንደሚክዱና ሕዝብን እንደሚበድሉ ይናገራል። በትያትር በኩልም አርሶ አደሩን ባላባቱ (ባለመሬቱ)፣ እንዴት አድርጎ እንደሚበድል በጥልቀት አሳይቷል።

በብዛት በኦሮምኛ አልጻፈም ማለት ብሔርተኛ አይደለም ወይንም በማንነቱ አይኮራም ማለት አይደለም። ምክንያቱም እርሱ ኦሮሞ ለዓለም እንዴት መተዋወቅ አለበት ብሎ የሚያስበው ነው በማንነቱ የሚኮራ የሚያደርገው።

ለምሳሌ በእንግሊዘኛ የተጻፈው ‘ኦዳ ኦፍ ኦራክል’ የሚለው ስራው፣ የኦሮሞ ምልክት የሆነውን ኦዳን መጠቀሙ በራሱ በማንነቱ እንደሚኮራ የሚያሳይ ነው። እርሱ በኖረበት ዘመን የነበሩ መንግሥታት ማነነታቸውን ከሰለሞን ግንድ ቢመዙም እርሱ ግን ሁሌም በጥቁርነቱ እንደ ኮራ ነው።

አድዋና ቴዎድሮስ የሚሉ ሥራዎቹም ሲታዩ በጥቁር ማንነት የተቃኙ ናቸው።

ስለዚህ ፀጋዬ ጥበብን ለጥበብነቱ ብቻ ሳይሆን ለማህበራዊ ለውጥና ባህልን ለማስተዋወቅ ተጠቅሞበታል።

ፀጋዬ ገብረመድህን እኤአ በ1998 ኢትዮጵያ ሪቪው በተባለው መጽሔት ላይ በታተመ ቃለምልልሱ ላይ ኢትዮጵያዊነት ለአንተ ምንድን ነው ተብሎ ተጠይቆ ነበር።

ለሎሬቱ ኢትዮጵያዊነት የአፍሪካን ታሪክ፣ ስልጣኔና ባህል የሚረዳ፤ እንዲሁም የዓለምን ስልጣኔ፣ ባህል እኩልነትና ወንድማማችነት ጠንቅቆ የሚገነዘብ ነው።

ሎሬቱ አክሎም፣ “ስለዚህ እኛ ለትምህርት አሜሪካ እንደምንሔደው፣ እነርሱም [አሜሪካውያን] ግብዝነታቸውን ትተውና ዝቅ ብለው ከቀደምት የሰው ዘሮች ምድር ለመማር መምጣት አለባቸው። ለኔ ኢትዮጵያዊነት ያ ነው” ብሎ ነበር።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.