በቅማንት ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለዉን ጭፍጨፋ፣ እንግልትና ወከባ አስመልክቶ በቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

በቅማንት ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለዉን ጭፍጨፋ፣ እንግልትና ወከባ አስመልክቶ በቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

Via ቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ – ቅዴፓOctober 4, 2019

የቅማንት ብሄረሰብ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በድሮዉ ሰሜን ጎንደር ዞን በወገራ ፤በላይ አርማጭሆ፣ በጎንደር ዙሪያ፣ በጎንደር ከተማ፣ በደንቢያ፣ በጭልጋ፣ በመተማና ቋራ ወረዳዎች በኩታ ገጠምነት ሰፍሮ የሚገኝ እንዲሁም እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዊ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ጋር ተሰባጥሮ የሚኖር እና እኔ ቅማንትነኝ የሚል አንድ አይነት የሆነ የስነልቦና ባለቤት የሆነ ህዝበ ነዉ፡፡ ይሁን እንጅ በ1983 የደርግ ስርዓት ተገርስሶ የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እኩልነት እንዲሁም ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ የመብት ተጠቃሚነትን እና እስከ መገንጠል ሙሉ መብት ያከበረ ህገመንግስት ከፀደቀ ወዲህ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ህገመንግስቱ ያጎናፀፋቸዉን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት በመጠቀም እራሳቸዉን ያስተዳድራሉ፣ የራሳቸዉን ልማት እራሳቸዉ አቅደዉ እራሳቹ ይፈፅማሉ እንዲሁም ባህል ወግ ቋንቋቸዉን ይጠቀማሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የቅማንት ህዝብ እንደብሄር የመቆጠር መብቱንም ተነጥቆ በባህል እና በቋንቋዉ እንዳይኮራ እንዲሁም በማንነቱ ተሸማቅቆ እንዲኖር የተለያዩ ዘመቻዎች ሲፈራረቁበት ኖረዋል፡፡ ይሁን እንጅ የቅማንት ህዝብ የተነጠቀዉን ቅማንትነቱን ለማስመለስ እና ህገ መንግስቱ ያጎናፀፈዉን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም የማንነት እና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ለበርካታ አመታት ህገ መንግስታዊ ሂደቱን ጠብቆ ምላሽ እንዲያገኝ ለሚመለከተዉ የመንግስት መዋቅር ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ እና ህገመንግስታዊ የትግል ጉዞ ሲያደርግ የቆየ እና አሁንም እያደረገ ያለ መሆኑ ይታዎቃል፡፡ ህገ መንግስታዊ የመብት ጥያቄዉን የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ተቀብሎ ህዝብን በማወያየት ሕጉን ተከትሎ ጥያቄውን ከመፍታት እና ህዝብን የሚያረካ እና ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጥ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የተለያዩ የአፈና ስልቶችን በመጠቀም ጥያቄዉ እንዲጓተት እና አላስፈላጊ መስዋእትነት እንዲከፈል አድርጓል፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-

 1. የቅማንትን ህዝብ በማሰር እና በማገት እንዲሁም በመግደል ብሄረሰቡ ያቀረበዉን ህጋዊ የመብት ጥያቄን የሚያስቆም የመሰለው የአማራ ክልል መንግስት የክልልን የፀጥታ ሃይል እና የልዪ ሃይል ታጣቂዎችን በመጠቀም ሰኔ 6/2007 ዓ.ም በጭልጋ ወረዳ አይከል ከተማ ጦርነት በማወጅ 6 ንፁሃን በመግደል ሴቶች እና ህፃናትን ማስፈራራት ጀመሩ። የኮሚቴ አባላትን ለ1.ዓመት ከ6ወር ደመወዛቸውን ተነጠቁ ጊዜያቸውን በእስር እንዲያሳልፉ ሆኑ።
 2. በጥቅምት 24/2008 ዓ.ም በጮንጮቅ ከተማ ጦርነት በመፍጠር እና በማስፈራራት በርካቶችን ተገደሉ።
 3. በጥቅምት 25-30/2008 ዓ.ም በላይ አርማጭሆ ወረዳ ማውራ ቀበሌ በክልሉ ልዩ ሀይል በተደረገ ጭፍጨፋ 22 ሰወች ሲገደሉ ህፃናት እናቶች እንዲሁም ወልዳ የተኛች አራስ እናት ሳትቀር ተገድላለች።
 4. በጥቅምት 24/2008 ዓ.ም ህጋዊ ያልሆነ ፀብ አጫሪ የሆኑ መልእክቶች የሚተላለፍበት በክልሉ መንግስት የተደገፈ 7000 ሰልፈኛ የተሳተፈበት ከዚህ ውስጥ 5000 የጦር መሳሪያ የያዘ ሰላማዊ ሰልፍ በአይከል ከተማ የብሄረሰቡን ጥያቄ መቃወም አላማው ያደረገ ሰልፍ ተካሄደ (የሰብአዊ መብት ጥናት ሰኔ 2008)።
 5. ህዳር 29/2008 ዓ.ም በመተማ ወረዳ በሽንፋ ከተማ በክልሉ መንግስት በጀት የተደገፈ ከተለያዩ ዞኖቾ እና ወረዳወች በተወጣጣ የታጠቀ ሃይል (በቁጥር 70,000 ከዚህ ውስጥ 50,000 የጦር መሳሪያ የታጠቀ) በመያዝ የዘር ጭፍጨፋ ተካሄደ። በርካታ ሰዎች ተሰው በርካቶች ለከባድ የአካል ጉዳት ተዳረጉ በርካታ ሃብት ንብረት ተዘረፈ ተቃጠለ በርካቶች ከኑሮ ቀያቸው እና ከስራ ቦታቸው ተፈናቅለዋል። በዚህም ምክንያት 118 ንፁሃን ዜጎች ሲሞቱ 37 ቱ ከፍተኛ የአካል ከጉዳት ደርሶባቸዋል 5 ግለሰቦች እስካሁን የገቡበት አይታወቅም 149 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሃብት ንብረት ተዘርፏል ተቃጥሏል። ይህ ተግባር ህጋዊ ሆኖ የመብት ጥያቄ የጠየቀውን የቅማንትን ህዝብ ልብ የሰበረ እና ግልፅ የሆነ ዘርን የማጥፋት ዘመቻ ነበር።
 6. ይህንን የዘር ማጥፋት ዘመቻ የኢትጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጥናት በማድረግ ክልሉ በቅማንት ህዝብ ላይ የፈፀመዉ ግድያ፤ ጭፍጨፋ እና ማፈናቀል ትክክል ባለመሆኑ በየደረጃዉ ያለዉ የመንግስት አመራር እና የፀጥታ መዋቅር ሀላፊዎች እንዲጠየቁ እና ተጎጅዎች ተገቢዉ ካሳ ተሰጥቷቸዉ ወደ ቀያቸዉ እንዲመለሱ ለኢፌድሪ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ምክረ-ሀሳብ አቅርቦ ቢያፀድቅም የተወካዮች ም/ቤት ያፀደቀዉ ተፈፃሚ ሳይሆን ከመቅረቱ በላይ ለነዚህ ወንጀለኛ አመራሮች የልብ ልብ የሰጠ ሆኖ አልፎዋል፡፡
 7. የቅማንት የራስ አስተዳደር አመሰራረትን አስመልክቶ የኢፌድሪ ጠ/ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ሀምሌ 30/2010ዓ.ም የቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴን እና የሚመለከታቸዉን የመንግስት ሀላፊዎች በጋራ በጠ/ሚኒስትሩ ፅ/ቤት አዎያይተዉ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት አስተዳደሩን ለመመስረት የሚያስችል ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ክልል መስተዳድር ቢሮ ለመሄድ ነሀሴ 28/2010 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ቢሯቸዉ በዉይይት ላይ እንዳሉ የአብክመ መንግስት የቅማንት አስተዳደር እንዲመሰረት ፍላጎት ስላልነበረዉ 26 የኮሚቴ አባላትን በክልሉ የፅጥታ ሀይል አፍኖ ካሰረ በሁዋላ ከ26ቱ መካከል 8ቱን ያለ አግባብ ለሁለት ወራት ያህል በግፍ አስሮ አቆይቷል፡፡
 8. በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የታወጀዉን የእስረኞች የምህረት አዋጅ የቅማንት ብሄረሰብ የመብት ጥያቄ በመጠየቃቸዉ ብቻ የታሰሩ ንፁሀን ዜጎቻችን የምህረት አዋጁ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ተደርጓል፡፡
 9. ከጥቅምት 19/2011 ዓ.ም ጀምሮ በመተማ፣ በቋራ፤በላይ አርማጭሆ፤በታች አርማጭሆ እና በጭልጋ ወረዳዎች በሚገኙ በሁሉም ቀበሌዎች በሚኖሩ ቅማንቶች ላይ ያለምንም ማቋረጥ ኢ-ሰብአዊ እና ከሠው ልጅ የማይጠበቅ ዘግናኝ ወንጀል በክልሉ መንግስት አስተባባሪነት ከተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች የተመለመሉ ታጣቂዎች እና ሽምቆች እንዲሁም በልዩ ሃይል ፖሊስ አማካኝነት እና ከየቦታዉ በተሰባሰቡ ሽፍቶች አማካኝነት የተፈፀመ ሲሆን በዚህም ምክንያት ከ473 በላይ ንጹሃን ቅማንቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣አረጋዉያን እና ህፃናት ከቤት ውስጥ ተቃጥለዋል፤ ሴቶች እህቶቻችንም ተደፍረዋል። ፖሊስ ጣቢያ ዉስጥ በህግ ጥላ ስር የነበሩ 4(አራት) ቅማንቶች ሳይቀር ሽንፋ ፖሊስ ጣቢያ ተገድለዋል፡፡ አሰቃቂ በሆነ መልኩ ጥር 2 እና 3/2011 ዓ.ም በመተማ ከተማ 58 እናቶች እና ህፃናት ቤት ዉስጥ ተቃጥለዋል፡፡ ይህ ሲሆን መከላከያ ከቦታዉ የነበረ ቢሆንም ትዛዝ አልተሰጠኝም በማለት ሲመለከት ከቆየ በሁዋላ 58ቱን ከተቃጠለ ቤት ዉስጥ በማዉጣት በአንድ ጉድጓድ ቀብሯል፣ ከ300 በላይ ንፁሀን ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ 245 ዜጎች ያለምንም የፍርድቤት ትዕዛዝ ከአንድ ዓመት በላይ ታፍነዉ በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች ይገኛሉ፣ ከ4 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ተቃጥሏል፣ ትራክተሮች እና ሌሎች የጭነት ተሸከርካሪዎች በተጨማሪም ትልልቅ የንግድ ድርጅቶች ሰሊጥን፣ጥጥ እና ማሽላን ጨምሮ ተቃጥሏል፣ የመተማ እና የቋራ አርሶ አደሮቻችን እንዳያርሱ ተደርገዋል፣ 91,245 በላይ ቅማንቶች ከመኖሪያ ቀያቸውና ከሥራ ቦታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ ቦታዎች ያለምንም በቂ ሰብዓዊ እርዳታ በመከራና ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይህን ችግር የከፋ የሚያደርገዉ ደግሞ ለተጎጅ እና ለተፈናቃይ ቅማንቶች ምንም አይነት ካሳ ትክ እና መልሶ የማቋቋም ስራ አለመሰራቱ የቅማንትን ህዝብ ሰቆቃ አስከፊ አድርጎታል፡፡
 10. የ2011 ዓመት የትምህርት ዘመን በቅማንት ቀጠና በሚገኙ ትምህር ቤቶች ልዩ ሀይል በማስፈር በጭልጋ ወረዳ እና በመተማ ወረዳ ከ47,757 ተማሪዎች ትምህርታቸዉን እንዲያቋርጡ ተደርጓል፡፡
 11. አንዳንድ የአማራ ክልል አመራሮች ስልጣናቸዉን እና አንዳንድ የሚዲያ ተቁዋማትን በመጠቀም የቅማንትን አርሶ-አደሮች ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቀዋል፣የመተማ የቅማንት ቀበሌዎች ለተከታታይ 4 ዓመታት ጦር ማሰልጠኛ ሆነዉ ቆይተዋል የሚል መግለጫን በማዉጣት እና የዜና ሽፋን በማሰራት እንዲሁም መላዉ የቅማንት ህዝብ ጥያቄየን ሰላማዊ በሆነ መንገድ አቅርብልኝ ብሎ የዎከለዉን ኮሚቴ እና መላዉ የቅማንትን ህዝብ የህወሃት ተላላኪ፣ጥቅመኛ፣ የዉክልና ተዋጊ፣አሸባሪ እና ሌሎችን ፀያፍ የሆኑ ስያሜዎችን በመስጠጥ እና እጃቸዉን እንቆርጣለን የሚል የማስፈራሪያ ዛቻን በመጠቀም ህዝብን ለግጭት እያነሳሱ በቅማንት ህዝብ ላይ ሲያዘምቱበት ቆይተዋል፡፡
 12. በተቃጠሉ የቅማንት መኖሪያ ቤቶች አመድ ዉስጥ ከባድ የጦር መሳሪያዎች እንደ ቅንቡላ፣ ብሬን ፣ መትረጊስ፣ የመከላከያ አልባሳት፣ ሀሰተኛ የብር ኖቶች፣ ሀሽሾች እና ሌሎችም ተገኙ በማለት የሀሰት ዉንጀላዎችን የሚዲያ ዘገባ እንዲያገኙ በማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረዉ የሚያደርግ ስራን እየሰሩ ህዝብን ለግጭት ዘነሳስተዋል፡፡
 13. በርካታ የሆኑ የብሄረሰቡን አባላት የመብት ጥያቄ ለምን ጠየቃችሁ በሚል ሰበብ ጋፍፎ ማሰር እና በብሄረሰቡ አማካኝነት ህጋዊ የሆነ ዉክልና ያለዉን እንዲሁም ትልቅ ክብር የሚሰጠዉን አስተባባሪ ኮሚቴ ያለጥፋት መወንጀል እና ማሳደድ ተፈፅሟል፡፡
 14. ነሀሴ 30/2011ዓ.ም በላይ አርማጭሆ ወረዳ እና በጭልጋ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ባሉ የእምነት ተቋማት(ቤተክርስቲያን ዉስጥ) የመንግስት አመራሩ የመከላከያ የሰራዊት አባላትን በመያዝ እና በመግባት አማኝ አርሶ አደሩን ማንገራገር እና ኮሚቴ ነኝ ብሎ የሚንቀሳቀስ አካልን በሙሉ አጋልጡ አልያ እናስራችሁዋለን በማለት ሲያንገራግሩ ቆይተዋል፤
 15. ከጳጉሜ 04/2011ዓ.ም ጀምሮ የክልሉን የልዩ ሀይል እና ፋኖ የሚባል ኢ-መደበኛ የሆነ ታጣቂ ሀይል በጭልጋ ወረዳ በአይከል ከተማ በሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች 100 ሜትር እርቀት እንዲሁም በቀበሌ መስተዳድር ቢሮዎች፣ በወጣት መዝናኛ ቦታዎች፣ ሰፊ ህዝብ በሚበዛባቸዉ የገቢያ መዳረሻዎች ከማስፈር በተጨማሪ የቅማንት ህዝብ የ2012ዓ.ም አዲስ አመትን ለማክበር በዝግጅት ላይ እያለ በጭልጋ ወረዳ በአንጓባ፣ ጮንጮቅ፣ ተንባ እና ቤዛሆ በተሰኙ ቀበሌዎች በመሄድ እና በንፁሀን አርሶ አደሮች ላይ ተኩስ በመክፈት ቀበሌዎች ላይ የሚኖሩ እናቶች እና ህፃናትን ከማሸበር በተጨማሪ 3(ሶስት) አርሶ-አደሮችን ገድለዉ 4(አራት) አርሶ አደሮችን ገድለዉ ተመልሰዋል፣ ትምህርት ቤት ላይ መምህር ተግድሏል፡፡
 16. ከመስከረም 10-12/2012ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንዲሁም ከመስከረም 16/2012ዓ.ም እስከ ዛሬ ድረስ በጭልጋ ወረዳ በሁሉም የደጋማ የገጠር ቀበሌዎች፣ በአይከል ከተማ እንዲሁም በጎንደር ከተማ በቁጥር በርካታ የሆነን ታጣቂ በማሰማራት ከቅማንት አርሶ-አደሮች ጋር መደበኛ እና ተከታታይነት ያለዉ ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ቁጥሩ በዉል ያልታዎቀ በርካታ አዛዉንቶች ፣ህፃናት እና እናቶች አርሶ-አደሮች ተገድለዋል፣ቆስለዋል፣ የቁም እንስሳት ተገድለዋል፣ ጎንደር ከተማ ሰዎች ቤት ዉስጥ በሳት ተቃጥለዋል፣ የንግድ ድርጅቶች እና መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል ተዘርፈዋል፡፡

በመሆኑም የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ቅዴፓ/ በቅማንት ህዝብ ላይ ለተፈጠረዉ የአካል እና የህይዎት ጥፋት የተሰማዉን ከፍተኛ የሆነ ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ እንዲሁም ለወገን ዘመዶቻቸዉ እና ለመላዉ የቅማንት ህዝብ መፅናናትን እየተመኘን፡-ከዚህ በታች የተዘረዘረዉን የአቋም መግለጫ አዉጥቷል፡፡

 1. የቅማንት ህዝብ ላነሳዉ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ሳያገኝ፣ የቅማንትን ህዝብ የገደሉ እና ያስገደሉ፣ የቅማንትን ህዝብ ያፈናቀሉ ወንጀለኛ የመንግስት መሪዎች እና የጎበዝ አለቆች በገለልተኛ ቡድን ተጣርቶ በህግ ሳይጠየቁ፣የተፈናቀለ ህዝብ ተገቢዉ የመልሶ ማቋቋም ስራ ተሰርቶ ወደ ቀያቸዉ ሳይመለሱ፣ ለተጎዱ ቅማንቶች ተገቢዉ ካሳ እና ትክ ሳይፈፀም፣ በግፍ ያለጥፋታቸዉ የታገቱ ቅማንቶች የፍርድ ሂደትን አልፈዉ ሳይለቀቁ፣ የቅማንት ህዝብ ዉክልና ያለዉ እና ከ5 ዓመታት በላይ የቅማንትን ህዝብ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሲመራ የቆየዉ የቅማንት የራስ አስተዳደር አስተባባሪ ኮሚቴ የታሰሩት ሳይፈቱ ወደ ጫካ የተሰደዱት ሳይመለሱ እና የቅማንት ህዝብ ያልሾማቸዉ እና የቅማንትን ህዝብ የማይወክሉ መሪዎች እና ተቋማት ህጋዊ እርምት ሳይሰጣቸዉ ቆይቷል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ የአማራ ክልል መንግስት በክልሉ ያለዉን ታጣቂ በማሰባሰብ በጭልጋ ወረዳ አርሶ-አደሮች በአይከል እና ጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ላይ አስከፊ የሆነ ጦርነትን ከፍቷል፡፡ ስለሆነም የቅማንት ህዝብ የሰላም እና የልማት ተጠቃሚ ያደርገኛል ብሎ በመረጠዉ መንግስት አማካኝነት መጨፍጨፍ ስለሌለበት የክልሉ መንግስት የከፈተዉን ጦርነት አቁሞ በቅማንት ቀጠና ያሰማራዉን ታጣቂ ሀይል በአስቸኳይ ሰብስቦ እንዲያስዎጣ እና በሀይል ከማሰብ ይልቅ በሀሳብ ተግባብቶ እንዲሰራ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ ቅዴፓ/ በአንክሮ ያሳስባል፡፡
 2. የአማራ ክልል መንግስት የህዝብ ስልጣንን መከታ በማድረግ በ2008ዓ.ም እና በ2011ዓ.ም ቅማንት በሆነዉ ህዝባቸዉ ላይ ከፈፀሙት ግፍ ሳይማሩ አሁንም አንዳንድ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ድርጊቱን ለመድገም በሚያስመስል መልኩ በተደጋጋሚ ልክ ያልሆነ መግለጫን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ መሪ ተማሪውን እንዲሁም ተመሪ መሪውን ማክበር የተፈጥሮ ግዴታ ነው። ህዝብ በጉልበት አይመራም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቀራረብ የብልህ መሪ ተግባር ነው። በ2008 ዓ.ም የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የአማራ ክልል መንግስት የቅማንትን ህዝብ በድሏል እና በይፋ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት ምክረ ሀሳብ ማቅረቡ ይታዎሳል፡፡ ስለሆነም የአማራ ክልል መንግስት ምክረ ሀሳቡን በማስታዎስ ተግባራዊ ከማድረጉ በተጨማሪ የህዝብ መሪነት ስልጣንን መሰረት በማድረግ ጦር ያዘመቱ እና የዘመቱ የፖለቲካ እና የፀጥታ አመራሮች እና አባላት ከድርጊታቸዉ እንዲታቀቡ እና አሁንም በድጋሜ እንዳይሳሳቱ ከማድረግ ባሻገር ተገቢዉን የማያዳግም እርምት ሊወስድ ይገባል ሲል ቅዴፓ ያሳስባል፡፡
 3. በ2011ዓ.ም በጭልጋ ወረዳ እና በመተማ ወረዳ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በክልሉ ታጣቂዎች መከበባቸዉን እና ከፍተኛ የሆነ የጥይት ተኩስ የሚተኮስባቸዉ በመሆኑ የተማሪ ወላጆች የልጆቻቸዉን ሀይዎት ለማዳን ሲሉ ልጆቻቸዉን ከትምህርት ቤት አስቀርተዉ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በ2012ዓ.ም የትምህርት ዘመንም ትምህርት ቤቶች ከታጣቂዎች አቅራቢያ በመሆናቸዉ እና መምህራንም የሚገደሉበት ቦታ በመሆናቸዉ ትምህርት ቤቶች እንዳይከፈቱ እና ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት ላለመሄድ ተገድደዋል፡፡ ስለሆነም የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እና የኢ.ፌ.ድ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር ቦታዉ ድረስ ወርዶ በማረጋገጥ እና ተገቢዉን ማስተካከያ በመስጠት ሁሉም ትምህርት ቤቶች ከክልሉ ታጣቂዎች ነፃ እንዲሆኑ በማድረግ የህፃናትን የመማር መብት እንዲያስከብር ቅዴፓ በአንክሮ ያሳስባል፡፡
 4. የቅማንት ህዝብ ያነሳዉን የመብት ጥያቄ እና እየተስተናገደ ያለበትን ሂደት እንዲሁም እየደረሰበት ያለዉን ግፍ እና በደል በተደጋጋሚ ጊዜ ለማእከላዊ መንግስቱ ማሳዎቅ ቢቻልም የማዕከላዊ መንግስቱ የቅማንትን ህዝብ እንደ ኢትዮጵያዊ ህዝብ ቆጥሮ ችግሮችን ከመጋራት ይልቅ በዝምታዉ ተባባሪነቱን እያሳየ ይገኛል፡፡ ስለሆነም የማእከላዊ መንግስቱ ለቅማንት ህዝብ ያለዉን የተንሻፈፈ እይታ በማንሳት የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር እና በአማራ ክልልም ጣልቃ በመግባት የህዝቦችን ሰብዓዊ መብት ከማክበር እና ከማስከበር ባሻገር ህዝቦች ለሚያነሱት ጥያቄ በህገመንግስቱ የዓሰራር ስርዓት መሰረት ምላሽ እንዲሰጥ ቅዴፓ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
 5. የፌደራል መንግስት የሚመራዉን ህዝብ ሰላም እና ደህንነት የማስጠበቅ ህገመንግስታዊ ግዴታ አለበት፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት እራሱን አይነኬ አድርጎ የሚያስበዉን እና በሚመራዉ ህዝብ ላይ የጭፍጨፋ ተግባርን እየፈፀመ ያለዉን የአማራ ክልል መንግስት ጨፍጫፊዎቹን እንዲሰበስብ፣ ተባባሪ እና አደራጅ የሆኑ አንዳንድ የሚዲያ ተቁዋማት እና አክቲቪስቶች፣ አላማቸዉ ህዝብን በማበጣበጥ ደም ማፋሰስ እና ህገመንግስቱን ለመናድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ በተላይ ለቅማንት መጨፍጨፍ ዋና ተዋናይ የሆኑ በመሆናቸዉ ከድርጊታቸዉ በአጭር ጊዜ ዉስጥ እንዲታቀቡ ከማድግም ባለፈ ተገቢዉን የህግ ቅጣት እንዲያገኙ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ቅዴፓ በአንክሮ ይጠይቃል፡፡
 6. የፌደራል መንግስት የቅማንትን ህዝብ መጨፍጨፍ አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ በመሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታዎቅ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈፀም ዝምታን መርጧል፡፡ ስለሆነም ይህ ተግባር ለዜጎቹ ትኩረት አለመስጠት፣ በዜጎቹ ደም መቀለድ ነዉ እና እንደማንኛዉም ጥፋተኛ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የቅማንትን ህዝብ በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ በቅማንት ህዝብ ላይ የደረሰዉን የህይወት እና የንብረት ጥፋት እንዲሁም የስም ማጉደፍ በጥንቃቄ ምርመራ ተደርጎ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሪፖርት በማቅረብ ትክክለኛዉን እዉነታ ለኢትዮጵያዉያን ወንድሞቻችን እንዲያስረዱልን የቅማንት ዶሞክራሲያዊ ፓርቲ/ቅዴፓ/ አጥብቆ ያሳስባል፡፡
 7. የቅማንት ህዝብ የወከለዉ ለዘመናት የቅማንትን ጥያቄ ህገመንግስቱ የሚፈቅደዉን መርህ ተከትሎ ሲያቀርብ የቆየዉ እና ፍፁም ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የቅማንትን ህዝብ ሲመራ የቆየዉን ለኢትዮጵያ መሪዎችም ምሳሌ ሊሆን የሚችለዉ የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላትን አፍኖ የማሰር እና ህይወታቸዉን ለማዳን ሲሉ ወደ ተለያየ ቦታ እንዲሰደዱ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቅማንት ህዝብ ቁማር የሚጫዎቱ ቁማርተኞችን በመሪነት ቦታ በማስቀመጥ የቅማንት ህዝብ ሳይፈልጋቸዉ አሻንጉሊት መሪዎች ተሰይመዋል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት ይህን አስተባባሪ ኮሚቴ በቅማንት ህዝብ በኩል ፍፁም ታማኝ እና እምነት የተጣለበት መሪ መሆኑን በመገንዘብ ከዚህ በፊት ላከናወኑት መልካም የመሪነት ተግባራቸዉ የምስጋና እዉቅና በመስጠት ወደ ቦታቸዉ የመመለስ ስራን እንዲሰራ እና ህዝብ የማይፈልጋቸዉን መሪዎችን በማንሳት፣የቅማንት ብሄረሰብ ዞንን የህዝብ ፍላጎትን እና ተሳትፎን ባገናዘበ መልኩ በማዋቀር፣ በቀጠናዉ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ሰላም እና ፍትህ እንዲሰፍን መንግስት ተግቶ እንዲሰራ እየጠየቅን የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም ሰላም እና ፍትህ የሰፈነበት፤ የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት የቅማንት አካባቢ ብሎም በብሄራዊ አንድነቷ የተጠናከረች ኢትዮጵያን ለማየት ያስችል ዘንድ ተቆራርጠን የምንሰራ ይሆናል፡፡ በተለይ ደግሞ የኢፌድሪ መንግስት የቅማንትን ጥያቄ በመፍታት ሂደት በሚያደርጋቸዉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ከቅማንት ህዝብ እና ከኢፌድር መንግስት ጎን በመሰለፍ ፓርቲያችን የድርሻዉን የሚዎጣ መሆኑን በአንክሮ እንገልፃለን፡፡
 8. የቅማንት ህዝብ በአሁኑ ሰዓት ካነሳዉ ህገመንግስታዊ የመብት ጥያቄ ባሻገር የህልዉና ትግል እያደረገ ይገኛል፡፡ ስለሆነም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ አጋር የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሀገር ዉስጥም ሆነ ከሀገር ዉጭ ያላችሁ የብሄረሰቡ ተወላጆች እና ወዳጆች በቅማንት ህዝብ ላይ የሚፈፀመዉን ጭፍጨፋ፣ እንግልት እና ወከባ በተለመደዉ መልኩ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንድትቃወሙልን እና ከወገናችሁ ከቅማንት ህዝብ ጎን እንድትሰለፉ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ቅዴፓ/ ጥሪዉን ያቀርባል፡፡

የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ቅዴፓ/
መስከረም 23/ 2012 ዓ.ም

1 Comment

 1. Now it is time to pass blood all we Have one of four (A, B, AB or O), serve ethiopia with out any hesitation .

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.