በኢትዮጵያ የስርዓቱ ሙሉ ለውጥ ነው ወይስ በስርዓቱ ውስጥ የሚደረገው የጥገና ለውጥ ነው የሕዝቦችን ጥያቄ መመለስ የሚችለው??

በኢትዮጵያ የስርዓቱ ሙሉ ለውጥ ነው ወይስ በስርዓቱ ውስጥ የሚደረገው የጥገና ለውጥ ነው የሕዝቦችን ጥያቄ መመለስ የሚችለው??

ብርሃኑ ሁንዴ, February 27, 2018

ከዚህ በፊት “የሕዝቦች ጥያቄ የግለ ሰቦች ሹመት አይደለም” በሚል ርዕስ ባቀርብኩት አንድ አጭር ፅሁፍ ውስጥ የግለሰቦች ሹመት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ እንደማይችል ሀሳቤን ለመግለፅ ሞክሬ ነበር። የጠቅላይ ሚኒስተርነት ጉዳይ አሁንም የመወያያ አጀንዳ ሆኖ እየቀጠለ ስለሆነ፣ ዛሬም እስቲ በዚህ ላይ ሀሳቤን ለመግለፅ አፈልጋለሁ። አንድ መታወቅና ግልፅ መሆን ያለበት፣ ለሕዝብ ተቆርቛሪ የሆኑና ብቃት ያላቸው ግለሰቦች ለውጥ ማምጣት አይችሉም ማለት ሳይሆን፣ እንደኔ አመለካከት በዚህ መንግስት ተብዬውና የተወሰኑ ቡድኖች እንደ ፈለጉ ሀገሪቷን አየተጫወቱባት በሚገኙት የወያኔ ስርዓት ውስጥ የትኛውም ተወዳጅነት ያለው ሰው በጠቅላይ ሚኒስተርነት ተመርጦ አራት ኪሎ ቢገባ፣ ለሕዝቦች ጥያቄ መልስ መስጠት እንደማይችል ሙሉ በሙሉ አምናለሁ።

ለማ መገርሳና አብይ አህመድ ቢያንስ ከአነጋገራቸው ሲታይ ለኦሮሞም ሆነ ለሌሎች የሀገሪቷ ሕዝቦች ቆርጠው ለመስራት የተነሱ ይመስላሉ። የፖለቲካ ሕይወት ታሪካቸው ምንም ቢሆን፣ ቢያንስ ባሁኑ ወቅት ከሕዝባቸው ጋር ለመቆም የወሰኑ ይመስለኛል። የምናገሩትን በስራ የማሳየታቸውን ጉዳይ ግን ወደፊት የምናየው ይሆናል። እንደኔ ሀሳብ ግን ወያኔዎች አራት ኪሎ እስካሉ ድረስ፤ የመንግስት መዋቅሮች በተለይም ቁልፍ ቁልፍ የሆኑት በእጃቸው እስካሉ ድረስ ለማም ሆነ አብይ ለጠቅላይ ሚኒስተርነት ተመርጠው ቢቀርቡም ለሀገሪቷ የተፈለገው ለውጥ መምጣት አይችልም። ነገሮች እኛ አንደምናየውና እንደምናስበው ሳይሆን በጣም የተወሳሰቡ በመሆናቸው፣ ሁሉ ነገሩ የማይሳካ መስሎ ቢታይም እንኳን ለትክክለኛ ለውጥ የተሻል የሚሆነው፣ ወያኔ ላንዴና ለመጨራሻ ጊዜ እንዲትወገድ ትግልን ማፋፋምና፤ ለሽግግር መንግስት መዘጋጀት ነው።

የኦሮሞን የነፃነት ትግልን በተመለከተ፣እውነቱን ለመናገር ምንም ያህል በአዲሱ የነ ለማ መገርሳ አመራር ድርጅታዊ ሪፎርም ለማድረግ ቢሞከርም፤ ኦሕዴድ (OPDO) ሙሉ በሙሉ ከኢሕአዲግ (EPRDF) ካልተላቀቀች ለነፃነት ትግሉ እንቅፋት እንደምትሆን ጥርጥር የለውም። ለምን ቢባል አሁንም ለወያኔዎች መሳሪያ እየሆኑ በሕዝባችን ላይ ጉዳት የሚያደርሱት ግለስቦች በዚህ ድርጅት ውስጥ ተሰግስገው ስላሉ ነው። የOPDO ከEPRDF መላቀቅና ራሱን የቻለ ሕዝባዊ ድርጅት መሆን ለወያኔዎች የመውደቂያ መንገድ ጅምር ነው የሚሆነው። የወያኔ ተላላኪዎች ባይኖሩ ወያኔ በኦሮሚያ ውስጥ አንደ ልቧ ተንቀሳቅሳ ሕዝቦቻችንን ለመጉዳትና ንብረታችንን መዝረፍ ባልቻለች ነበር።

ወደ ጉዳዩ መነሻ ማለትም ወደ ፅሁፌ ርዕስ ለመመለስ፤ የወያኔ ስርዓት እስካለ ድረስ እነዚ ሰው በላ ሰዎች ባሉበት የስርዓቱን ጥገና ለማድረግ መሞከርና የጠቅላይ ሚኒስተርነትን ቦታ በግለስቦች ለማስያዝ መሞከር እንዲሁ ከንቱ የጊዜ ማቃጠያ ሙከራ ነው የሚሆነው እንጂ፤ ለውጥ ለማምጣትም ሆነ ለለውጥ ሽግግር ለማድረግ የሚረዳ መስሎ አይታየኝም። መፍትሄው በሚቻለው መንገድ ሁሉ በመጠቀም ይህንን ሰው በላ ስርዓት መስወገድ ነው። ይህ ደግሞ የሚቻለው በተባበረና በተቀናጀ የሕዝብ ትግል ነው። ይዋል ይደር፣ ይፍጠን ይቆይ እንጂ የሕዝብ ትግል ሁሌም አሸናፊ ነው። ስለዚህ የሕዝባችን ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ከተፈለገ፤ የስርዓት ጥገናና የግለሰቦች ሹመት ሳይሆን የስርዓቱ ሙሉ ለውጥ እንዲመጣ ትግል ማጠናከር ነው። ሌላው የአቅጣጫ ማስቀየሪያ ሙከራ ነው።

ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.