በይቅርታ የማይታለፍ ጉዳይ

በይቅርታ የማይታለፍ ጉዳይ

ብርሃኑ ሁንዴ , Muddee 13, 2018


በሰው ልጆች ድርጊት ውስጥ በይቅርታ የሚታለፍ ጉዳይ አለ። ይህ የተፈጥሮ ሕግ ነውና። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ በወያኔ ስርዓት ስር በዘጎች ላይ ሲደርስ የነበረው አሰቃቂ ጉዳይ እንዲሁ በቀላሉ በይቅርታ የሚታለፍ አይደለም። ይህንን አጭር ፅሁፍ አንዳቀርብ ያነሳሳኝ “በጌታቸው አሰፋ አሰቃቂ ግፍ የደረሰባቸው የፍትህ ሰቆቃ በሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ የሚያተኩር ዶክመንተሪ” https://www.youtube.com/watch?v=S22CiXZmtOo በሚል ርዕስ ባሁኑ ጊዜ እየታየ ያለው አንድ አሰቃቂ ቪዲዮ ሲሆን፣ ይህም የሚያሳየው ወያኔዎች በገነቡት እስር ቤት ውስጥ በሰዎች ላይ ሲደርስ የነበረውን ድርጊት ነው። በኣካላቸው ላይ ይህ አሰቃቂ ድርጊት የደረሰባቸው ይቅርና ይህንን ፊልም ማየት ራሱ ራስ ያሳምማል። እውነት ለመናገር ይህንን ፊልም ሳይ እንባዬን መቆጣጠር ነበር ያቃተኝ ብል ነገር ማጋነን አይደለም።

የተወሰኑ ሰዎች ይህንን ዕድል አግኝተው ስለደረሰባቸው ድርጊት ተናገሩ እንጂ፣ ያልተሰማና ያልታወቀ ቁጥር እንደሌለው የማይካድ ነው። ይህ በሰው ልጅ ላይ ሲደርስ የነበረው አሰቃቂ ድርጊት በይበልጥ የተፈፀመው ደግሞ በኦሮሞ ልጆች ላይ ነበር። በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሲደርስ የነበረውንና እየደረሰም ያለውን የሚያውቀውና የሚያየው እግዚአብሔር ብቻ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ እስራት፣ እንግልት፣ አፈና፣ ግድያና የመሳሰሉትን ሁሉ ተቋቁሞ፤ ዛሬ ሁሉም የሚደሰትበትን የለውጥ አየር ያምጣ እንጂ የድሉ ባለቤት እንደሆነ የሚገባውን ትርፍ ማግኘት ቀርቶ ዛሬም በሰላም እንኳን ወጥቶ መግባት አልቻለም። ዛሬም እንደ ትላንትናው በኦሮሚያ አዋሳኝ ድንበሮች ላይ ከቀዬው፣ መሬቱና ንብረቱ አየተፈናቀለና እየተገደለም ይገኛል። የትላንትናው ኣንሶት ለምንድነው የዚህ ሕዝብ ስቃይ ዛሬም መቆም ያልቻለው?

የአገሪቷ ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ብዙውን ጊዜ ስናገሩ እንደነበር፣ ጊዜው የፍቅርና የእርቅ ጊዜ ነው ስሉ ነበር። ባጠቃላዩ ሲታይ እንደዚህ ይባል እንጂ ጠ/ሚኒስተሩ በዜጎች ላይ ይህንን አሰቃቂ ድርጊት የፈፀሙትን ወንጀለኞች እንዴት ነው የምያዩት? ይህንን አሰቃቂ ድርጊት የፈፀሙትም ሆኑ ካላይ ትእዛዝ ሲያስተላልፉ የነበሩት ሁሉ ዛሬ በነፃነት እየኖሩ ናቸው። ምንድነው የቀረባቸው? መቸ ነው ለሕግ የሚቀርቡት? ለምንድነው እስከ ዛሬ እንኳን ለሕግ ሳይቀርቡ የቆዩት? ይህ ለውጡን አያመቻቸው ነኝ የሚለው መንግስት ምን እየሰራ ነው ያለው? ዛሬም ከወያኔ እጅ መላቀቅ ኣልቻለም ወይንስ ለምንድነው እነዚህን ወንጀለኞች አሳዶ መያዝና ለፍርድ ማቅረብ ያልቻለው? ለምንድነው የኦሮሞ ሕዝብ ዛሬም ከቀዬው፣ መሬቱና ንብረቱ እየተፈናቀለና እየተገደለ ያለው?

ይህቺን አገር እያስተዳደራት ያለው ኦሮሞ ነው በሚባልበት ወቅት ለኦሮም ሕዝብ የሚደርስለት እንዴት ጠፋ? አብይና ለማ ምን እያሰቡና እየሰሩ ናቸው? ኢትዮጵያዊነት ሱስ ሆኖ ለዚህ ጉዳይ ቅድሚያ መስጠታቸው እንዳለ ቢሆንም፣ የኦሮሞ ሕዝብ የኢትዮጵያ አካል አይደለምና ነው የዚህ ሕዝብ ስቃይ የማይታየው? ኦሮሞ ዛሬም ይህቺን አገር ለማኖር ሲባል መሞት አለበት? ከቀዬውና ከመሬቱ ሲፈናቀል ዝምታ መምርጡ ተገቢ ነው? የዚህ ሕዝብ ጥያቄ መቸ ነው መልስ የሚያገኘው? የፊንፊኔስ ጉዳይ መቸ ነው መፍትሄ የሚያገኘው? በድብቅ ስራ ላይ አየዋለ ያለው የፊንፊኔ ማስተር ፕላን መቸ ነው የሚቆመው? ከፊንፊኔ ዙሪያ እየተፈናቀሉ ያሉት አርሶ አደሮች መፈናቀላቸው መች ነው የሚቆመው? ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተወሰደባቸው መሬትስ መቸ ነው የሚመለስላቸው?

እነዚህ ጉዳዮች ሁሉ በዝምታና በይቅርታ የማይታለፉ በመሆናቸው፣ መንግስትም ሆነ ጉዳዩ የሚመለከተው ማንኛውም አካል አስቸኳይ ምላሽ መስጠት አለበት።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.