አሃዳዊነትን ማውገዝ ጨፍላቂነት መቃወም እንጂ አንድነትን ማጥላላት አይደለም! – ክፍል –2

ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ (PH.D.)

ክፍል –2

የመደመር ‹‹ፍልስፍና›› እንደ ገዳፊነት !

(Ethiopianism_as_Reductionism)

መደመር ወይም አንድነት እጅግ መልካም ነው፣ ግና አንድነት (መደመር) ማለት አንድ ዓይነት መሆን አይደለም! ብዝሃነት ማንም ሰው ልክደው የማይችለው የተፈጥሮ ሕግ ነው። የተለያዩ የባሕል ልዩነቶች መኖራቸው በራሳቸው ችግር ልሆኑ አይችሉም፤ ችግር የሚሆነው እውቅና ያለመስጠት ጉዳይ ነው። በተለይ በሀገራችን ኢትዮጵያ የባሕል ልዩነትን እንደሌለ አድርጎ መመልከት በጣም ስህተት ነው። የባሕልና የቋንቋ ልዩነት የማሕበራዊ ሕይወታችን አንዱ አካል አንደመሆኑ መጠን እንደ ችግር ወይም ሥጋት መታየት የለበትም። በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ወጥ ባሕል (ማለትም አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ የታሪክ አረዳድ፣ አንድ ሃሳብ…ወዘተ) ለማሰረጽ መሞከር በጣም የተሳሳተና ተቀባይነት የሌለው አመለካከት ነው።

ስለዚህ፣ ኢትዮጵያዊነት በሕዝቦቿ ብዝሃነት ላይ የተገነባ መሆን ይኖርበታል። የባሕል ብዝሃነት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን አይቃረንም። የጋራ ኢትዮጵያዊነት ስሜት መፍጠር የሚቻለው ሁሉን የሚያካትትና በጋራ ጥቅም ላይ የወል ተቋማትን መመስረት እና ሁሉን አሳታፊና እኩልነትን የሚያከብር መዋቅር መዘርጋት ሲቻል ነው። የባሕል ብዝሃነት የኢትዮጵያ አንድነትን በተሳትፎ የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ በተቃራኒው የራስን የብሔር የበላይነት ብቻ መጉላት ኢትዮጵያዊ-ብሔርተኝነትን የሚንድ ነው። የሀገር ፍቅር እውን ሊሆን የሚችለው ጥልቅ አንድነትን/መደመርን በልዩነት የሚያከብር ኢትዮጵያዊነትን መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው። ኢትየጵያዊነትም ሆነ የባሕል ብዝሃነት የምንደሰትበት ውበታችን መሆን ይገባል።

ከሁሉም በላይ፣ የብሔር ማንነት ምንም ስህተት የሌለበትና ጥሩም ሆነ መጥፎም ያልሆነ ነው፤ ብሔር በራሱ (per se) መልካም አልያም መጥፎ አይደለምና። ይሁን እንጂ፣ሁላችንንም ሊያሳስበን የሚገባው ብሔርን መልካም ወይም መጥፎ የሚያስብለውን የግለሰቡ ወይም የማኅበረሰቡ አረዳድና የስነ-ልቡና አቀራረጽ መገንዘቡ ላይ ነው። ምክንያቱም አዎንታዊ ብሔርተኝነት ሀገር ገንቢ (state making) ሲሆን አሉታዊ ብሔርተኝነት ደግሞ ሀገር አፍራሽ (state breaking) ነውና። መቼም ቢሆን የብሔር ወይም የባሕል ልዩነቶች የበላይነትም ሆነ የበታችነት ትርጉም ሊሰጡ አይገባም። ለምሳሌ፣ አንድን ብሔር ከሌላው ከፍ አድርጎ ማዬት፣ የመነጠል፣ የጅምላ ፍረጃ፣ ከሰው ደረጃ ማሳነስ…ወዘተ አሉታዊ ብሔርተኝነት ሲሆን እንደ ሀገር አፍራሽ የሚታይ ነው። ስለዚህ፣ የችግሩ ፍሬ ጉዳይ የብሔር ግጭት በተፈጥሮ/በማኅበረሰቡ የተሰጠን ብሔር ራሱ ሳይሆን አሉታዊ ብሔርተኝነት መሆኑ በአጽንኦት ሊሰመርበት ይገባል።

በመሆኑም አዎንታዊ ብሔርተኝነትን ማጥላላትና መዋጋት እጅግ አደገኛ ነው። አዎንታዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን የሚቃወመው ጨፍላቂ ሥርዓት ወይም ጨፍላቂ ፖለቲካዊ አስተዳደርን ነው። ስለዚህ ነው ኢህአደግ  በ‹‹ውህዴት›› ወይም በ‹‹መደመር ፖለቲካዊ ፍልስፍና›› ስም ጨፍላቂ ሥርዓተ-መንግስት ላለማስፈን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት የሚለው።  ምክንያቱም፣ አንድነት ማለት አንድ ዓይነት መሆን አይደለም። የሳሙና ፋብሪካ አንድ አይነት ሳሙና ነው የሚያመርተው፤ የሰው ልጅ ሳሙና አይደለም፤ የራሱ ማንነት (ባህል፣ ቋንቋ፣ ፍልስፍና) አለውና! ስለዚህ የፌደራል ሥርዓቱን ከጨፍላቂ ሥርዓት  መከላከልና በሀገራችን ሰፍኖ የቆየውን የብሔር ጭቆና በሕጋዊ መንገድ ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድ በጋራ መስራት ያስፈልጋል።

የብሔር ማንነት ምቾት የማይሰጣቸው አንዳንድ ግለሰቦች የብሔር ጥያቄን እንደ ‹‹ጠባብነት›› እና ‹‹የጎሳ ፖለቲካ›› አድርጎ ይወስዳሉ። አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር እንደዚህ ዓይነት ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ አንድነት እጅግ አደገኛ ነው። ባለፈው ጊዜ በግልጽ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት የብሔር ማንነት ጽንሰ-ሐሳብ የደም ትስስር ያላቸውን ሰዎች አያመለክትም። ብሔርተኝነት በረዥም ዘመናት በኢትዮጵያ ሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት ሂደት ውስጥ የተፈጠረ ታሪካዊና ማህበራዊ ክስተት ነው። ስለዚህ፣ ‹ብሔር› የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ ባህል፣ ቋንቋ፣ የታሪክ አረዳድ፣ የስነ-ልቦና አቀራረጽ…ወዘተ መሠረት ያደረገ እንጂ እንደ ጎሳ የደም ትስስርን የሚያመላክት አይደለም።

ስለዚህ አንድ ግለሰብ የብሔር ማንነቱን ኢትዮጵያዊ ወይም ኬንያዊ በመሆን ሊክደው አይገባውም። ኢትዮጵያዊ ወይም ኬንያዊ ለመሆን የእርሱ የብሔር ማንነትን የመቀየር ግዴታ አለበት እንዴ? በጭራሽ የለበትም! ኪዊሪያን ኬ. አንጎም እንዲህ ሲል ይሞግታል፡-

‹‹የማይካደው ዕውነታ ሁላችንም ልንቀበለው የሚገባ በባሕል ውስጥ ነው የተወለድነው፣ ዕድገታችንም በባሕል ውስጥ ሲሆን፣ ራሳችንንም የምንመራበትም ሆነ የምንገልፅበት ማህበራዊ ሥርዓት የሚያረጋግጥልንና ለተገቢው ብስለት የሚያበቃን በመሆኑ ነው። በሌላ አባባል እኛነታችን ባሕላችንን እንድንሆን አድርጎ ያበጀን በመሆኑም ነው። በዕርግጥ የምንቀበለው ጉዳይ ከራሳችን ባሕል ዙሪያ እየራቅን በሄድን ቁጥር ወይም ከሌሎች ጋር ስንገናኝ፣ የሚበዛውን የሌላውን ባሕል ከራሳችን ጋር እናዋህዳለን። ነገር ግን ዕውነታው የራሳችን ባሕል ለማንነታችን ዋናው መሠረታዊ ትርጉም መሆኑ ላይ ነው። እንግዲህ በዚህ መሠረት ላይ ነው የሌላው ባሕል ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆን መሠረቱ የሚገነባው፣ ምንም እንኳን የሌላው ባሕል ኋላ ቀር [sic] ቢሆንም። የራስን ባሕል ማናናቅ ማለት በራስ ማንነት ላይ ያልተፈለገ የነቀፌታ ምንጭ መሆኑና የራስን መሠረት ትርጉም የመናድ ያህል ነው። ይህን ማድረግ ሰብዕናን በአጠቃላይ የማፍረስ ያህል ይሆናል። ምክንያቱም ባሕል አልባ መሆን ማለት። ማንነት የጎደለው ሰው ማለት ነው። እንዲህ ያለው ሰው ራሱን/ሷን መረዳት የማይችል ማለት ነው። ለዚህ ነው ሁልጊዜ የሌላውን ባሕል ማክበር የሚመከረው።››

ስለዚህ፣ “ሮም ውስጥ ስትሆን እንደ ሮማውያን ሁን!” የሚለው ታዋቂው ብሒል  ሮማዊ አያደርግህም! ይህ የሚያሳየው ብሔርተኝነት የማይደራደሩት ይልቁንም በራሱ ግልፅ የሆነ ተፈጥሯዊ ባሕሪ በመሆኑ በቀላሉ የማይወገድ መሆኑን ነው። ስለሆነም የባሕልና የብሔር ልዩነቶች የበላይነትም ሆነ የበታችነት ትርጉም ሊስጡ አይገባም። በዛሬዋ ኢትዮጵያም የማንነት ልዩነት ዕውቅና ሊሰጠው ሊቻቻልና ሊጎለብት ይገባዋል። የብሔር ልዩነት ተዘንግቶ፣ ተንቆ ወይም በተቃራኒው በመረዳት የአገር ፍቅር፣ ኢትዮጵያዊነት ዕውን ሊሆን አይችልም። መቃወም ያለብን ጠርዝ የረገጠ የብሔር-ብሄርተኝነት እንጂ ብሔርተኝነት ራሱን አይደለም። ሀገርን የሚያፈርሰው አሉታዊ ብሔርተኝነት ነው እንጂ አዎንታዊ ብሔርተኝነት አይደለም። አዎንታዊ ብሔርተኝነት ስጎለብት አገሪቱ አንድ የሆነ የባሕል ትስስር እንድኖራት ያደርጋታል።  ለምሳሌ፡- አዎንታዊ ብሔርተኝነት አንድን ቡድን ወይም ግለሰብ በብሔሩ ማንነት ብቻ ከመመልከት ይልቅ እንደ አንድ የአገሪቱ ዜጋ ይመለከታል። ይህ ማለት ማንም ቢሆን የባሕል ልዩነቶችን መውደዱ ለልዩነት ሲባል ብቻ መሆን የለበትም። የተለያዩ ባሕሎች መኖሩ በመሠረቱ የኢትዮጵያዊ-ብሔረተኝነትን ሊክድ አይገባም። ጁ. ኔሬሬ እንዳረጋገጠው፡- “እውነተኛው የአፍሪካ ሶሻሊዝም የአንድን መደብ ሰዎች በተለየ መልክ ወንድሞቹ አድርጎ በመመልከት ሌላውን ወገን እንደ ጠላት አይመለከትም። ‘ወንድሞቼ’ ብሎ ከሚያያቸው ጋር በመወገን ሌላውን ‘ወንድም ያልሆኑትን’ ለማጥቃት አይነሳሳም። ይልቁንም ሁሉንም ሰዎች እኩል እንደ ሥጋ ዘመዶቹ ይቆጥራል ( ኡጃማ በሚባለው ፍልስፍናዕይታ) (ኔሬሬ 1965፡170) በኢትዮጵያም ይህ የአፍሪካዊ ስሜት/አስተሳሰብ ለጋራ ጥቅም ሲባል ሊወሰድ ይገባል።

ስለዚህ ጤነኛ አህምሮ ያለው ሰው አንድነትን አይጠላም። የእኔ ትልቁ ሥጋት በ‹‹አንድነት›› ስም ጨፍላቂ ሥርዓት እንዳይፈጠር ነው። አንዳንድ ፖለቲከኞች የባሕል አንድነትን በዛሬዋ ኢትዮጵያ ለመጫን ይሞክራሉ።ይህ በፍፁም የተሳሳተና ተቀባይነት የሌለው የፍልስፍና አቀራረብ ነው። የራስ የሆነውን ባሕል በሌላው ላይ መጫን መጫረሻው መገንጠል ያስከትላል። ኬንያዊው ፈላስፋና የካቶሊክ ጳጳስ ማኩምባ ‹‹ማንም ህዝብ የማንነቱ (የብሔሩ) ለጠንካራ አገር ምሥረታ መሠረት ይሆናል›› ሲል እንደሚከተለው ይሞግታል፡- ‹‹[አንድ ሰው] ራሱን ከብሔሩ ለይቶ ወይም ነጥሎ ብሔራዊ ስሜት ለመያዝ መሞከር ከዕውነታው የራቀና ቅዥት ያስመስላል። ይህም ማለት የራስን አገራዊ ማንነትን በመተው የፓን-አፍሪካዊነት አስተሳሰብ አራማጅ እንደመያዝ ያስቆጥራል። በተመሳሳይ ሊባል የሚችለው ራስን በተቃራኒው አስተሳሰብ ራስን በሌላው ውስጥ በመቅበር በፍርሃት የሌላውን ብሔርዎች ወይም አገሮች የተለየ ዋስትና ለማስገኝት ሲባል የሚደረግ …የአገር ፍቅር ስሜት መንስዔው የብሔር ማንነትን በትክክል መረዳቱ ላይ ነው።››

በተመሳሳይ መልኩ፣ ኢያንኤል ማርካሃም እንዲህ ሲል ይሞግታል ‹‹የባሕል አንድነት፣ የአንድ ቋንቋ፣ የአንድ ሃይማኖት፣ የአንድ ታሪክና የአንድ ሃሳብ ተፅዕኖ ይልቅ የተለያዩ ባሕል፣የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ብዙ ሃይማኖቶች፣ የተለያየ ታሪኮችና ሓሳቦች የአብሮ መኖርንና አማራጭ አስተሳሰብ ያስፈልጉናል። የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች፣ የተለያዩ የሃይማኖት ምርጫዎችና የተለያዩ አመለካከቶችን ልናስተናግድ ይገባል። ትምህርት ቤቶችና የመገናኛ ብዙሃን አንድ ሃሳብ ከማሰራጨት ይልቅ የተለያዩ ሃሳቦች እንዲደመጥ ይደረግ።››

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፍልስፍና ታሪክ ውስት የመዋሃድ ልማድ የኢትዮጵያን ህዝብ የራሳቸውን የተወላጆች ተቋምና አገር የመገንባት ክብር ገፍቷቸዋል። የትውልድ ማንነት ያለውን ከፍተኛ ዋጋ መዘንጋት ልክ አትዮጵያን በአሸዋ ላይ የመገንባት ያህል ነው። ለምሳሌ፡- ዶ/ር መረራ ጉዲና ይህንን እውነታ እንድህ በማለት ነበር የታዘበው

የንጉሡ መንግስት የኤርትራን ፌደረሽን በማፍረስ ያገኘው ጀበሃና ሻዕቢያ የተበሉ[sic] ተቃዋሚዎችን ነው። በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም ዓይነት ጥያቄ የሌላቸውን የመጫ ቱለማ የልማት ማኅበር መርዎችንም በማፈን ያገኘው ውሎ አድሮ የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦነግ) ነው። ደርግ በተራው፣ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም ዓይነት ጥያቄ የሌለውንና በዋናነት በትግራይ ልሂቃን የሚመራውን ኢህአፓን በማፈን ያገኘው ሕወሐትን ነው። በዘመኑ ይሻላሉ በሚባሉ የኦሮሞ ልሂቃን ጭምር የሚመራውንና በኦሮሞ አካባቢዎች ሰፍ ምና የነበረውን መኢሶንን በማፈን ያገኘው ለየት ያለ ሕልም ያላቸውን የኦሮሞ ብሔርተኞችን ነው።›› (ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ሕልሞች፤የኢህአዴግ ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ፣ 2008፣ ገጽ. 23)

ሌላ ምሳሌ እንውሰድበንገሡ ዘመን የኢትዮጵያ የትምህርት ሚንስቴር ሚኒስትር የነበሩት ሣህሌ ፀዳሉ፣ 1933 የሚከተለውን በጣም የተሳሳተ አዋጅ አሳውጀው ነበሩ፡

‹‹ያገር ጉልበት አንድነት ነው፣ አንድነትንም የሚወልደው ቋንቋ ልማድና ሃይማኖት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ቀዳማዊ መሆኗን ለማስከበር አንድነቷንም ለማጽናት እስከሁን በቆየው ልማዳችን ተማሪ ቤቶቻችንን አስፍተን ቋንቋችንና ሃይማኖታችንን በመላው በኢትዮጵያ ግዛት በአዋጅ እንዘርጋው፤ ይህ ካልሆነ እስከ መቼውም ድረስ አንድነት አይገኝም። በመላ በኢትዮጵያ ግዛት ለሥጋዊና ለመንፈሣዊ ሥራ ያማርኛና የግዕዝ ቋንቋ ብቻ በሕግ ጸንተው እንዲኖሩ ሌላው ማናቸውም የአረማዊያን ቋንቋ ሁሉ እንዲደመሰስ ማድረግ ያስፈልጋል።ሚሲዮኖች ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎችንም ቢሆን እንዳይከፍቱ መከልከል ያስፈልጋል፤ ከከፈቱም የውጪ ቋንቋ ማስተማርም ቢሆን እድሉ ለኢትዮጵያውያን መሰጠት አለበት።›› (ባህሩ ዘውዴ 2005፣ ገጽ. 132-14)

ስለዚህ ነው አሃዳዊነትን ማውገዝ ጨፍላቂነት መቃወም እንጂ አንድነትን ማጥላላት አይደለም የምለው። በክፍል ሦስት ኢትዮጵያዊነትን እና ብሔርተኝነት እንዴት በትክክለኛው መንገድ ማስታረቅ እንደሚገባና የብሔር እኩልነትም ሆነ የሀገር እንድነትን ግምት ውስጥ በማስገባት ሁላችንንም በእኩልነት የሚታስተናግድ ድሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንዴት መፍጠር እንደሚቻል በሰፊው ይመለስበታለሁ።

 ቸር እንሰንብት!

 

 

 

 

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.