አማራ ካልተወከለ፣ ማን ተወከለ?

አማራ ካልተወከለ፣ ማን ተወከለ?

Tsegaye Ararssa, Caamsaa 28, 2019

ሕገ-መንግሥቱ ሲረቀቅ እና ውይይት ሲካሄድ አርቃቂው (ክፍሌ ወዳጆም)፣ የእርሱ ረዳት የሕግ ባለሙያዎቹም (እነ መዓዛ አሸናፊን ጨምሮ)፣ በኮሚሽኑ የኢሕአዴግና የመንግሥት ቡድን መሪና የኮሚሽኑ ዘዋሪውም (ዳዊት ዮሃንስ)፣ አደሽዳሽ-አጨብጫቢ አባላት የነበሩትና የሕገ-መንግሥት ጉባኤውም የሽግግር መንግሥት ምክር ቤቱም ባለ ብዙ ቁጥር አባላት የነበሩት ድርጅትም (ብአዴንም)፣ በውይይቱ ሂደት በትጋት ሲካፈሉ የነበሩት (እነ ሕላዊ ዮሴፍ፣ ተፈራ ዋልዋ፣ እና ታምራት ላይኔም)፣ እና ብዙ ብዙ በጽሕፈት ቤትና ባጠቃላይ በቢሮክራሲው ውስጥ የነበሩና እስከዛሬም ያሉ ሌሎችም ባለሙያዎች በአብዛኛው አማሮች ነበሩ።

ከማንኛውም አባል በላይ ብዙ ጊዜ የተናገሩት ሰው (ሻለቃ አድማሴም) አማራ ነበሩ።

ሰነዱም የተረቀቀው፣ ውይይቱም የተካሄደው፣ በመገናኛ ብዙሃንም የተሰራጨው፣ ቃለ-ጉባኤውም የተመዘገበው፣ በአማርኛ ነው።

ነገረ-ሥራው የተዋቀረበት የእውቀት ሥርዓት (epistemic system) እና የተቃኘበት ትርክት ማዕከለ-አማራ (Amhara-centric) ኢትዮጵያዊነት ነበር።

በወቅቱ የበታች ካድሬ ሆኖ ባላንጦቹን እየጠቆመ ሲያሳስርና ሲያስር የነበረ የብአዴን ካድሬ፣ ልክ ዛሬ ገና ከእንቅልፉ የነቃ ይመስል፣ ተነስቶ፣ “ሕገ-መንግሥቱ ሲረቀቅ አማራ አልተወከለም ነበር፤ ቢወከልም ብዙ ጊዜ አልተናገረም ነበር፤ ተፅዕኖ ለመፍጠርም እድል አልነበረውም” ብሎ ማለት (አቶ ዮሃንስ ቧያለው ሰሞኑን እንዳሚለው)፣ አውቆ መደንቆር (willful ignorance) እና ሕዝብን ማደናቆር ነው።

ሕገ-መንግሥቱ ተረቅቆ የጸደቀበት ሂደት ዴሞክራሲያዊ (ማለትም፣ ነፃ፥ ፍትሃዊና እውነተኛ ፉክክር ያለበት) ምርጫ ተደርጎ የተመረጠ የሕገ-መንግሥት ጉባኤ ባልነበረበት አውድ ውስጥ ነበር፤ ከዚህም የተነሳ፣ የትኛውም ሕዝብ (የአማራን ሕዝብ ጨምሮ) በመረጣቸው ወኪሎች አልተወከለም ነበር ማለት አንድ ነገር ነው። የለም፣ ሌላው ሁሉ ሲወከል አማራ ብቻ ሳይወከል ቀርቶአል ብሎ ማለት ግን “ተጨፈኑ እናሞኛችሁ” የሚል ቀጣፊነት ነው።

እውነት እንነጋገር ከተባለ፣ እንዲያውም፣ በነበረው የቋንቋና የባህል የበላይነት ውርስ ምክንያት፣ በዴሞክራሲ አለመኖር ውስጥም እንኳን፣ በፖለቲካም ሆነ በቢሮክራሲው ውስጥ በብዛት በመገኘት የተሻለ ድምፅ፣ ተሰሚነትና፣ ተጠቃሚነት የነበረው የአማራ ልሂቅ ነው።

እና ምን ለማለት ነው? ይሄ “እናሞኛችሁ ተሞኙልን ዓይነት ወሬአችሁንና የመንደር ህፃናት ወግ ትታችሁ፣ የትላልቅ ሰዎች (የ adult) ፖለቲካ ላይ በመሰማራት፣ “እውነተኛ ተቀባይነት ያለው ሕገመንግሥታዊ ሂደት እንዴት እንመሥርት? በአገር ደረጃ፣ የተሻለ ሕዝባዊ ተቀባይነት እንዲኖረው እንዴት እናድርግ? በዘላቂነትስ እንዴት ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካን ለማስተዳደር የሚረዳ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እንዘርጋ?” በሚሉ ጭብጦች ላይ ብትመክሩ ይበጃችሁ ነበር።

ከሌላው የተለየ ውክልና ይገባኝ ነበረ ማለት ግን የበላይ ስለሆንኩ ያልተገባ መብት (privilege) ይገባኛል የሚል የእብሪት ክርክር ነው። አያስኬድም። እንደ ቡድን፣ የበላይነትን ብቻ በመፈለግ እኩልነትን መፍራት ለዴሞክራሲ የማይመጥን ፋሽስታዊነት ነው። ወይም ከሌሎች ጋር ተግባብቶና ተቻችሎ በእኩልነት ለመኖር አለመፈለግ ነው። ይሄ ደግሞ ካንተ ይልቅ፣ በእኩልነት እጦት ምክንያት ተገፍቶ ለሚሄደው የተመቸ ይሆናል። ግልግል ነውና። ከፋሽስታዊ የበላይነት አቀንቃኞች ጋር አገርን ከመጋራት የከፋ እርግማን የለምና።

በዛ መጠን አማራም ተወክሏል። ታሪክን ማጣመም ትተህ፣ ዛሬ ሁሉም በትክክል በሕዝብ ድምፅ በተመረጠ ወኪል የሚወከልበትን ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥታዊ ሂደት ለመፍጠር ትጋ። የመንግሥት ሥልጣን ይዘህ፣ ሽፍትነት የሞላበት የመንደር ህፃናት ፖለቲካህ ለሥልጣንህም፣ እወክለዋለሁ ለምትለው ሕዝብም፣ ለአገርም አይመጥንም።

***********************//*******************************
“ጠመንጃ ማወዛወዝ ሀገርን አደጋ ላይ እየጣለ ነው” አቶ ጌታቸው ረዳ


ገና ጉድ እንሰማለን


“ጠመንጃ ማወዛወዝ ሀገርን አደጋ ላይ እየጣለ ነው”
አቶ ጌታቸው ረዳ

የህወሓት እና የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት #አቶ_ጌታቸው_ ረዳ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙርያ ከዘመን መፅሄት ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ

ዘመን፦ኢህአዴግ አለ? 

አቶ ጌታቸው፦በመሰረቱ አንድ ድርጅት አለ የሚባለው የቆመለት ፕሮግራም ካለ ነው፤ ኢሕአዴግ የቆመለት ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ የሚባልና ሁሉም ድርጅቶች ከሞላ ጎደል እናምንበታለን የሚሉት ፕሮግራም አለ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የድርጅቱ ሕገ ደምብ ነው ድርጅቱን ድርጅት የሚያደርገው፡፡ አለ? የለም? ለማለት እነዚህን ጥያቄዎች በአዎንታዊ መመለስ ተገቢ ነው፡፡ ድርጅት አለ፤ የኢህአዴግ ጽ/ቤት የሚባል አለ፤ እኔ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነኝ፡፡ ዋናው ነገር ፕሮግራሙ እየተከበረ ነው? ፕሮግራሙን ለማስፈጸም የሚያስችሉት የድርጅቱ ሕገ ደንቦች በስራ ላይ እየዋሉ ናቸው ወይ የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡

ከዚሕ አንጻር ፕሮግራሙን ከሞላ ጎደል ባለፈው ጉባኤ ላይ ተስማምተን የወጣንበት ሁኔታ አለ፡፡ እርግጥ አዝማሚያዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ድርጅቶች በይፋ የኢሕአዴግ ፕሮግራም አይመለከተንም ብለው የሚናገሩበት ጊዜ አለ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ባለፈው ጉባኤ ላይ የተጠቃለለው ፕሮግራማችን ለውጥ አያስፈልገውም የሚል ነው፡፡ በእኛ በኩል ዋናው መሰረታዊ ነጥብ ፕሮግራሙን በተግባር ላይ ለማዋል ምን ያህል ዝግጁነት አለ የሚለው ነው፡፡ ኢህአዴግ በጉባኤው እስካረጋገጠው ድረስ ፕሮግራሙ አለ ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ሕገ ደንቡን ከመተግበር አንጻር ውስንነቶች አሉ፤ በተግባር ማየት ያለብን ግን ኢህአዴግ ለፕሮግራሙ፣ ለሕገ ደንቡስ ምን ያህል ታማኝ ነው? ሁሉም ድርጅቶች ፕሮግራሙን ማእከል ያደረገ አንድነታቸው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው ወሳኝ የሚመስሉኝ፡፡

ዘመን፦በኢሕአዴግ ውስጥ ክፍፍል አለ የሚል አስተያየት ይሰነዘራል፤ እውነት ነው?

አቶ ጌታቸው፦ስራ ብንሰራ ኖሮ እኮ ነው ወጥነት የሚኖረው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ፕሮግራማችን ነው አንድ የሚያደርገን›› ስንል በዲሞክራሲና በሰላም ጉዳይ ላይ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ አቋም ይዘን እንቀሳቀሳለን ማለት ነው፡፡ አሁን የዚህች ሀገር ሰላም ጠንቆች ምንድናቸው ብለህ ስትጠይቅ አንዱ ድርጅት የሚሰጠው ምላሽና ሌሎቹ ድርጅቶች የሚሰጡት ሁኔታ የተለያየ ነው፡፡ ለዚህች ሀገር ሰላም መደፍረስ ምክንያቱ የሆነ ከሩቅ የሚዳሰስ የማይዳሰስ ወገን ነው ብሎ የሚያስብ አለ፡፡ የወጣት ስራ አጥነት ነው መሰረታዊ ችግሩ፡፡ የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ጥያቄአችንን ለመፍታት በሚደረገው እንቅስቃሴ ኢህአዴግ በግልጽ ያስቀመጠው ወጣቶቻችንን፣ ሴቶቻችንን ተጠቃሚ ማድረግ የሚል ነው፤ ትልቁ አቅማችን ሕዝባችን ስለሆነ ሕዝቡን እንደ ልማት ኃይል ተጠቅሞ መንቀሳቀስ የሚለው ስራ ላይ ያለው ድክመት ግልጽ ነው፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ዐይን ለዐይን እንተያያለን ማለት አይደለም፤ ከዚህ አንጻር ነው የኢሕአዴግ ሕልውና መጠየቅ ያለበት፡፡

ዘመን፦በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ሰላም ሲደፈርስ፣ ሰዎች ሲገደሉና ሲፈናቀሉ ‹‹ከችግሩ ጀርባ ሁሌም የሕወሀት እጅ አለ›› የሚል ሰፊ ክስ ይሰማል፤ ምን መልስ አለዎት?

አቶ ጌታቸው፦ ሕወሐት በጣም ስራ በመስራት ነው ጊዜውን የሚያሳልፈው፡፡ እንኳን ሌላ ጉዳይ ውስጥ ገብተን ልንፈተፍት ሙሉ ትኩረት ሰጥተነውም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አልፈታነውም እንጂ የወጣቶችንን ችግር ለመፍታት እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው፤ ሕወሀት ለበርካታ አስርት አመታት የሕዝብን አቅም ተጠቅሞ ለውጥ እያስመዘገበ የመጣ ድርጅት ነው፡፡ ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ፣ ለልማት አርአያ መሆን የሚችል ተግባር ያከናወነ ድርጅት ነው፡፡

የሀገሪቱ ሰላም መጠበቅ አለበት ብቻ ሳይሆን እንዲጠበቅም ምናልባትም ከማንም የተሻለ ሚና የተጫወተ ድርጅት ነው፡፡ በዚህ ሰዓት የወንድም ሕዝቦችን ሰላምና መረጋጋት የሚረብሽበት የሚያናጋበት ምክንያት የለም፡፡ይሄንን ክስ የሚያቀርቡት ሰዎች ጠበቅ ያሉ ፖለቲከኞች ናቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ጠበቅ ያለ ፖለቲከኛ በወጣትና በሴቶች አቅም አካባቢን መለወጥ መቻል ላይ ነው ትኩረት አድርጎ መስራት ያለበት፡፡ ሕወሐት የሰራው ይሄንን ነው፡፡ሩቅ ሳንሄድ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ይሄ አካባቢ በጦርነትና በተፈጥሮም የተጎሳቀለ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰውን ጉልበት በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያተረፉ በርካታ ስራዎችን የሰራ ነው፡፡

በዚህ መልኩ ወጣቱን አንቀሳቅሶ ስራ እንደመፍጠር ጠመንጃ እያወዛወዙ ‹‹ጥራኝ ጫካው ጥራኝ ዱሩ›› እያሉ ጊዜ ለመግዛት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው ይሄን ሀገር አደጋ ላይ እየጣለ ያለው፡፡ ቀበቶን ጠበቅ አድርጎ ስራ መስራት ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡ የወጣት ጥያቄ በብዙ መዝሙር በብዙ ፉከራ ሊድበሰበስ አይችልም፤ መመለስ መቻል አለበት፡፡ ለመመለስ ደግሞ እኛ የምናደርገው እንቅስቃሴ አለ፡፡ በኢህአዴግም ደረጃ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አሉ፡፡ ሌላ አዲስ ተአምር መፍጠር አይጠበቅብንም፡፡ ያንኑ መልሰህ በማየት እዚህ ላይ ነው ያጠፋሁት፤ እዚህ ላይ ነው መልስ መስጠት ሲገባኝ መልስ መስጠት ያልቻልኩት ብለህ አስተካክለህ ለመንቀሳቀስ መሞከር ነው እንጂ የምክንያቶች መብዛት አወዳደቅህን አያሳምርም፡፡

ዘመን፦በቅርቡ ጠ/ሚሩ በሰጡት መግለጫ ኢህአዴግ ወደ አንድ ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲነት ይለወጣል ብለዋል፤ በሕወሀት በኩል ደግሞ ያልተሟሉ ሁኔታዎች ስላሉ ውህደቱን አንቀበልም የሚል ሀሳብ እንዳለ ተሰምቶአል፤ እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ ጌታቸው፦ ውሕደት የመቀበል ያለመቀበል ጉዳይ አይደለም፡፡ ይሄ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በሕወሀትም ሆነ በሁሉም ድርጅቶች ዘንድ አደረጃጀታችንን እንፈትሸው፤ ተብሎ የቆየ ነው፤ አደረጃጀት ታክቲክ ነው እንጂ የመጨረሻ ግብ አይደለም፡፡ እንደገለጽኩት ፕሮግራም ነው የሚያገናኘን ካልን ፕሮግራሙን ለማስፈጸም በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ አሁን ያለው አደረጃጃት እንቅፋት ይሆንብናል ወይ የሚለውን ማየት ይጠይቃል፡፡ ይሄ ተፈትሾ በጥናት ላይ ተመርኩዞ ይደረጋል፡፡ የዓላማ አንድነት ሊኖር ይገባል፡፡ በተለይ ድርጅት /ፓርቲ የሚባለው ዝም ብለህ አላፊ አግዳሚው በሙሉ የያዘውን ያምጣ ብለህ የሚቀመጥ አይደለም፡፡ ቆሜለታለሁ የምትለውን ማህበራዊ መሰረት ጥቅሞች በሚመለከት በደምብ የተዘረዘረ፣ በደምብ የተተነተነ አቋም መኖር አለበት፡፡ ይሄን ይዘህ ያንን ጥቅምን ለማስከበር የሚያስችሉ አቅጣጫዎች እነዚህ እነዚህ ናቸው፤ ይሄ ፕሮግራም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ያስችላል፤ ፕሮግራሙ ለይቶ ያስቀመጣቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ደግሞ ስትራቴጂዎችን፣ ፖሊሲዎችንና፣ ደንቦችን ቀርጸን መንቀሳቀስ ይኖርብናል ብሎ ማሰብን ይጠይቃል፤ የሀሳብ አንድነትን ይጠይቃል፡፡

ምስራቅ አውሮፓ ውስጥ በተለይ ከሶቭየት ሕብረት መፈራረስ በኋላ ወደ ስልጣን የመጡ ፓርቲዎች ምን ያደርጉ ነበረ? ኮሚኒስት ፓርቲው ብቻውን ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለው እድል ስለማይኖር ከሌሎች ስልጣን በትንሽ በትልቁ መቀራመት ከሚፈልጉ ወገኖች ጋር በመሆን እነሱ ‹‹ፓርቲ ኦፍ ፓወር›› የሚሉት ስልጣን ላይ ለመቆየት ያሰበ ፓርቲ የመመስረት አዝማሚያ ነበራቸው፡፡ እሱ ፓርቲ በየሶስት ሳምንቱ የሚታመስ ኃይል ከመሆን ውጭ የፈየደው ነገር አልነበረም፡፡ አሁን ዋና ትኩረት ማድረግ ያለብን የጋራ ብለን ያስቀመጥናቸውን ፕሮግራሞቻችንን የሚያሰሩ የማያሰሩ ብለን መፈተሽነው፤ ይሄ ቀኖና አይደለም፤ እስከጌታ መምጫ ድረስ ይኸው ነው ፕሮግራማችን ተብሎ የሚቀመጥ አይደለም፤ በየጊዜው መለወጥ ያለበት ነገር ካለ እየተፈተሸ ይሄዳል፡፡

ከኢሕአዴግ አንጻር ሕብረብሄራዊ አደረጃጀት ማለት የብሄር ድርጅቶችን ማጥፋት ማለት አይደለም፡፡የብሄር ድርጅቶችን ለማጥፋት ማሰብ ራሱ የኢትዮጵያን ሁኔታ አለማገናዘብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለው እውነታ የብሄር ቅራኔ የሚባል በመሰረታዊ ደረጃ ተፈትቷል የሚባል ቢሆንም ብሄሮች ከአሁን በፊት ያነሷቸው ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ ተፈትተዋል ተብሎ አይወሰድም፡፡

ስለዚህ በቋንቋ የመጠቀም፤ ባሕልን የማበልጸግ፤ በራስ የመዳኘት፤ በራስ የመተዳደር ጥያቄዎች በተሟላና ሁላችንም እኩል ነን ብለን በምናምንበት መልኩ እስኪረጋገጡ ድረስ የብሄር አደረጃጀትን በህግ የምታጠፋውም አይደለም፡፡ አንዳንዱ ዝምብሎ ፋሽን መስሎት አይ በዚህ በዚህ መደራጀት አይፈቀድም የሚል አስተሳሰብ ይኖራል፡፡ ፓርቲዎቹ ግን ሲራኮቱ የምታያቸው በብሔር ዙሪያ ነው፡፡ ለምሳሌ ኬንያን የወሰድን እንደሆነ የብሔር ወይም የጎሳ አደረጃጀት ተከልክሏል ከሚባሉት መሰለኝ፡፡ ምርጫ በቀረበ ወቅት የምታየው መራኮት በጎሳ ዙሪያ ነው፡፡ አለባብሶ የማረሱ ጉዳይ በአረም ከመመለስ አያስቀርምና ዋናው ትኩረታችን መሆን ያለበት የዓላማ አንድነት ፈጥረናል ወይ ነው፤
የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች አንዱ ሌላውን እየከሰሰ፤ አንዱ የራሱን የቤት ስራ መስራት ሲያቅተው በሌላው ላይ ጣት እየቀሰረ፤ በፍጥነት ተጠፍጥፈን በድንገት አንድ እንሆናለን ማለት አይቻልም፤ መሆን ያለበት የራሳችንን ጠባብ ልዩነትና ጠባብ ጥቅሞች ያመጧቸውን ልዩነቶች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየጫንን፤ እርስ በእርስ ለማጋጨት እንቅስቃሴ ማድረግ ባልቆመበት ሁኔታ ኢሕአዴግ በፈለገው ስሌት አንድ ሆኜአለሁ ቢል ቀልድ ነው የሚሆነው፡፡ የሕወሀት አቋም አንድ መሆን አያስፈልግም የሚል አይደለም፤ የሕወሀት አቋም የታይታ አንድነት አይደለም የሚያስፈልገን፤ ፕሮግራማችን ለማስፈጸም የሚያስችል ስለሆነ ቅድሚያ የሕዝባችንን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል እንቅስቃሴ ማድረግ አለብን የሚል ነው፡፡

ከዚህ ውጭ ተሰባስበን ስልጣን ላይ ለመቆየት፣ ድምጽ ለማግበስበስ በሚያመች መልኩ ፓርቲ ማቋቋም ነው የሚል ሀሳብ ካለ እንዲህ አይነት አስተሳሰብ አይኖርም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ካለ ግን የጥፋት መንገዱን ከማራዘም በዘለለ እዚህ ግባ የሚባል ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለንም፡፡

ዘመን፦ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መሪ ርእዮተ ዓለም ሆኖ እንዲቀጥል ሕወሀት ይፈልጋል፤ ሌሎች የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ደግሞ እየተቃወሙ መሆኑ ይሰማል፤ ስለሁኔታ ቢገልጹልን?

አቶ ጌታቸው፦ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስሙ ላይ ከሆነ ጠባችን መቀየር እንችላለን ተብሎ እኮ በ2003 ዓ.ም አቶ መለስ በነበሩበት ወቅትም ‹‹የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ እንቅስቃሴአችንን በደምብ የሚገልጸው ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመር የሚለው ስለሆነ ይሄኛው ተመራጭ ነው›› ከሚል ነጥብ ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ያ ሲባል ‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ›› የሚለው ቃል አርጅቶ አፍጅቶ ተቀባይነት አጥቶአል ማለት አልነበረም፡፡ ቃሉ በደርግ ጊዜም ስለነበረ ብዙ የረከሱ ቃሎች አሉ፤ ‹‹አብዮት›› ሲባል ከግርግርና ከቀይሽብር ጋር የማያያዝ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከስሙ ሳይሆን ከይዘቱ አንጻር ነው መመዘን ያለበት፡፡ አስተሳሰቡ ሰላምና ዲሞክራሲ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕልውናና ቀጣይነት ማረጋገጫ ምሰሶዎች ናቸው የሚል ነው፡፡

ዘመን፦በአንድ ድርጅት ውስጥ ሁለት አይነት ርእዮተ ዓለም ሊኖር ይችላል?

አቶ ጌታቸው፦ምን ርእዮተ ዓለም ያስፈልገዋል? ስለዲሞክራሲና ልማት መግባባት ካልቻልን በምንም መግባባት አንችልም፡፡ ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ አይደለም የሚያስፈልገኝ ሌላ ነው የሚል ካለ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ሊበራል ዴሞክራሲ ምን እንደሆነ አንድም ቀን ሰምቶ የማያውቅ ሰው ሊበራል ዴሞክራቲክ አስተሳሰብ ነው የሚሻለኝ ይላል፡፡ ሊበራል ዴሞክራሲ ምንድነው ብንል ሊበራል ዴሞክራሲ የሚባለው አንድ ወቅት ብርና ንብረት ላላቸው ሰዎች ብቻ የመምረጥ መብትን ማጎናጸፍ የፈለገ ሀብታሞችን ከድሆች ለመከላከል ተብሎ ሲራመድና ሲቀነቀን የነበረ ስርዓት ነው፡፡ በሂደት መታገል የጀመሩ ድሀ ነጮች ትንሽ ንብረት ሲቋጥሩ ምርጫ ውስጥ መግባት አለብን ማለት ጀመሩ፤ ሴቶችም እኛም ተምረናል ዲሞክራሲ ይመለከተናል ማለት ጀመሩ፡፡

ጥቁሮች በተሟላ ደረጃ የሰብአዊ መብት አዋጅ የሚባለው እስኪወጣ ድረስ የመምረጥ ነጻነት መብት አልነበራቸውም፡፡ አሁንም ቢሆን የተሟላ ነጻነትና መብት አላቸው ተብሎ አይገመትም፡፡ አስተሳሰቡ ምን እንደሆነና ከየት ተነስቶ ምን እንደደረሰ በወጉ የማይረዳ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የቋንቋ የቡድን መብት በተሟላ ደረጃ መረጋገጥ አለበት ብሎ የሚያምን ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ባለበት ሀገር አይ የግለሰቦችን መብት ማረጋገጥ ብቻ ነው የኢትዮጵያን ችግር የሚፈታው ማለት አስገራሚ ነው፡፡

የሙስሊሞች፣ የሴቶችና የብሔሮች መብት በቡድን ደረጃ መረጋገጥ አለበት፡፡ ብዝሀነታችንን በወጉ ማረጋገጥ ስንችል ፌደራል ስርአታችንን እናጎለብታለን ነው፡፡ እነዚህን ጉድለቶች መቀበል አለብን፡፡

እውነቶቹን የማይቀበል አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ልጫን ብትል ኢትዮጵያን ለመበተን አቋራጭ መንገድ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄኛውን አልቀበልም የሚል ፓርቲ አንደኛ ውሸቱን ነው፤ ምን እያለ እንደሆነም አያውቀውም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ወይንም ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በምንለው ጉዳይ ላይ እንኳን ከአስተሳሰብና ከጽንሰ ሀሳብ፤ ከአፈጻጸም ጋር የተያያዘ ጉዳይ ቢመጣ ይሄንኑ በሂደት አስተካክሎ ተራማጅ ድርጅትነቱን ጠብቆ ወደፊት ማራመድ ይቻላል፡፡ ኢሕዴግ ስንል ተራማጅነት ማለት ከምንም ነገር በላይ ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተህ በየጊዜው ፕሮግራምህን ስትራቴጂዎችህን ፖሊሲዎችህን ስልቶችህን እየፈተሽክ ወደፊት በሚያራምድህ ደረጃ መንቀሳቀስ ማለት ነው፡፡ ይሄንን ለማድረግ ዝግጁ ያልሆነ ዝም ብሎ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ሊበራል ዴሞክራቲክ ነው እከሌ ዲሞክራቲክ ነው፣ ቅብጥርስ እያለ የሚያወራው አንደኛ የሕዝቡን ጥቅም አያውቅም፤ ሁለተኛ በምሁርነት ደረጃም መካን ነው፤ መፈክር ከማሰማት በዘለለ እዚህ ግባ የሚባል ሳይንሳዊ ትንታኔ የለውም፡፡

እንኳን የእኛ ግልገል ሊበራል ዴሞክራቶች ቀርቶ የኒዮ ሊበራል አስተሳሰብ የመጨረሻ መገለጫ የሚባሉት የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግስታት ሳይቀሩ በፍጹም አይመክቱትም፤ ለእኛ ለእኛ ሲሆን መንግስት ጣልቃ አይግባ የሚባል ጨዋታ ውስጥ ይገባሉ፤ እሱ ቀልድ ነው፤ የዚያ ድራማ አካል ለመሆን የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ካለ መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት፤ ዋናው ትኩረት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት የልማት የሰላምና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ሲፈቱ ነው፤ ከእነዚህ ጋር ጠብ ያለው ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ካለ ሌላ ርእዮተ ዓለም መምረጥ ይችላል፡፡

ዘመን፦በትግራይና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በመሬት ይገባኛል ጥያቄ ላይ የተፈጠረውን አለመግባባት በዘለቄታው ለመፍታት በእናንተ በኩል ምን እየተደረገ ነው?

አቶ ጌታቸው፦በትግራይም ሆነ በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረ ልዩነት የለም፤ ከአሁን በፊት ግጨው አካባቢ የይገባኛል ጥያቄ ነበረ እሱ በስምምነት ተፈቶአል፤ ተግባራዊ ከማድረጉ ላይ እስከአሁን ያልተሰሩ ስራዎች አሉ፡፡ ከዚህ ውጭ በትግራይና በአማራ አካባቢዎች በተለየ መልኩ የቀረበ እስከአሁን የማውቀው የአዋሳኝ አካባቢዎች ጥያቄ የለም፡፡ በእርግጥ ባሕርዳር አካባቢ በሚደረጉ ሰልፎች አንዳንዴ የአማራ ክልል ባለስልጣናት በሚያደርጓቸው ቀረርቶዎች የምንሰማው ይሄ ይገባናል የሚል ነገር አለ፡፡

ዘመን፦የራያና የወልቃይት ጉዳይስ?

አቶ ጌታቸው፦ የራያና የወልቃይት ጥያቄ የራያና የወልቃት ህዝብ ጉዳይ ነው፤ ከባሕርዳር መጠየቅም መመለስም አይችልም፤ ጥያቄው መመለስ የሚችለው ሕገመንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት በእነዚህ ሕዝቦች ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የሰዎችን ማንነት በርቀት መቆጣጠሪያ አትወስንም፤ ጥያቄው ቀርቦም ከሆነ የቀረበበትን ጊዜ አላውቅም፤ እንደእናንተው በሬዲዮ በቴሌቪዥን ነው የምንሰማው፡፡ ፍላጎቱ አለ፤ ይሄ እየፈጠረ ያለው እጅግ አደገኛ ስሜት ነው፡፡ በተግባር የሁለቱን ክልሎች ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ሰላም የሚያውክ እንቅስቃሴ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ውስጥ ያለው ዋናው ጠብ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል የአዋሳኝ ልዩነት ሳይሆን ሕገመንግስቱን የመቀበልና ያለመቀበል ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ ሕገመንግስቱን የመቀበልና ያለመቀበል ጉዳይ አንድ ሰፈር ተቀበለ ሌላ ሰፈር አልቀበልም የሚባልበት ነገር የለም፡፡

ሕገመንግስቱ የፈጠራቸው ክልሎች አሉ፤ የክልሎችን ወሰን ከሕገ መንግስቱ ውጭ በሆነ መንገድ እወስናለሁ ብለህ መንቀሳቀስ ስትጀምር አጠቃላይ ሀገሪቱ የቆመችበትን ሕገመንግስታዊ ምሰሶ መናድ ነው፡፡ ያንን ስትንድ የአፋርን፣ የኦሮሚያን፣ የደቡብ ክልልን ታፈርሳለህ፡፡ ከዚህ ውጭ በአማራና በትግራይ ሕዝቦች መካከል የነበረውን ትስስር ባሕርዳርና መቀሌ የተቀመጥን ፖለቲከኞች መቼም ቢሆን ልንበትነው አንችልም፡፡

ዘመን፦ የራያንና የወልቃይትን ማንነት ጥያቄ ላለመመለስ የትግራይ ክልል ከመጠን በላይ ሰራዊት እያሰለጠነና እያስታጠቀ ነው የሚል ክስ ከአማራ ክልል ይደመጣል፡፡ ከትግራይ ክልል የሚሰጠው መልስም በተመሳሳይ የአማራውን ክልል የሚከስ ነው፤ ወደ ሰላሙ ለመምጣት ምን መደረግ አለበት ይላሉ? 

አቶ ጌታቸው፦ ወደ ሰላሙ ለመምጣት መለወጥም ካለበት በሕገመንግስታዊ መንገድ ብቻ ነው መለወጥ ያለበት ብሎ ማመንና ሕገመንግስቱ ያስቀመጣቸውን መፍትሄዎች እስከ መጨረሻው መፈተሸ ነው፤ ሌላ ነገር የለውም፤ ጠመንጃ ማወዛወዝ ለማንም አይጠቅምም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ጠመንጃ የማወዛወዝ ሱስ የለበትም፤ ለዘመናት ጠመንጃ አወዛውዟል፤ ራሱን ለመከላከል ሲል ጠላቶቹን ለማጥፋት ሲል ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ ብዙ መስዋእትነት ከፍሏል፤ አሁን ራሱን ማልማት ነው የሚፈልገው፡፡

ከወጪ አንጻር የፌደራል መንግስት ሰዎችን ብትጠይቁ ጥሩ ነው፡፡አንዳንድ ክልሎች ጠመንጃ ለመግዛት የሚያስችል ጥያቄ በይፋ ሲያቀርቡ እንሰማለን፤ የትግራይ መንግስት ጠመንጃ ሽጡልኝ ብሎ በይፋ ጥያቄ አቅርቦ አያውቅም፡፡ እኛ የመልማት ፍላጎት ነው ያለን፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ከሩቅም ይምጣ ከቅርብ በየትኛውም ቀረርቶ የሚንበረከክ ሕዝብ አይደለም ያለን፡፡ ምክንያቱም ይሄ የሕዝቦች ጥያቄ አይደለም፡፡ ዝምብሎ ሽፍቶች እየመጡ እንጨብጣለን እያሉ የሚያቅራሩ አሉ፡፡ ለእነዚህ ብለህ ሞርታር ላዘጋጅ የምትልበት ምክንያት የለም፤ እሱ ጨዋታ ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን የህዝቦቻችንን አንድነት የሚያላሉ በእኛ በፖለቲከኞች ዘንድ የሚሰሩ ስራዎች መኖር የለባቸውም፤ ወደሰላም መምጣት መቀራረብ መቻል አለብን፡፡

ዘመን፦አስከፊ ሁኔታ እንዳይከሰትና ችግሩ በሰላም እንዲቋጭ የትግራይና የአማራ ምሁራን ማድረግ የሚገባቸው ምንድነው ይላሉ?

አቶ ጌታቸው፦መልሱ አጭር ነው፤ የአማራውም የትግራዩም ምሁር(ኤሊት) ስለራሱ ቆዳ ሳይሆን ስለ ሕዝቡ ነው መቆርቆር ያለበት፤ ቁጭ ብሎ ‹‹የአማራ ጥቅም ማለት ራያን ማስመለስ ነው›› የሚለውን እንዴት ነው የሚተረጉመው? ማስመለስ ካለብኝ ደግሞ ጦርነት እገጥማለሁ የሚለው አስተሳሰብ ነወይ ትክክል? የሚፎክረው ሁሉ ጦርነት ውስጥ አይገባም፤ ገበሬውን ነው ለጦርነት የሚዳርገው፡፡ የገበሬን ጥቅም የምታረጋግጠው ማዳበሪያ አቅርበህለት መልካም የአስተራረስ ዘዴ አስተዋውቀሀው ሕይወቱን ስትለውጠው ነው፡፡ ሌላውን ሕዝቡ ይለየዋል፤ ምሁሩ (ኤሊቱ) ማላመጥ ከሚችለው በላይ እየጎረሰ ነው ችግር እየተፈጠረ ያለው፡፡

ዘመን፦በፌደራል መንግስቱና በፓርላማው የሚወጡ አንዳንድ አዋጆችን የትግራይ ክልላዊ መንግስት ‹‹አልቀበልም›› የሚሉ መግለጫዎችን ሲያወጣ ይደመጣል፤ ይሄ ሁኔታ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ተናቦ በመስራት ረገድ ችግር አይፈጥርም? 

አቶ ጌታቸው፦ ችግር መፍጠር የለበትም፤ የፌደራል መንግስት የክልሎች ውክልና ነው ስልጣን የሰጠው፡፡ ሕገመንግስቱ የብሄር ብሄረሰቦች ቃልኪዳን ውጤት ነው፡፡ እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ ራሱን ለማስተዳደር በህገመንግስቱ የተቀመጠለት መብት የሚረጋገጠው በክልሎች ነው፡፡ እነዚህ ክልሎች ሕገመንግስቱ ተጣሰ ብለው እዬዬ ማለት መጀመራቸው ስህተት አይደለም፤ ምክንያቱም ፌደራል መንግስቱን ብቸኛ ምንጭ አድርጎ የሚቆጥር አስተሳሰብ ካለ ስህተት ነው፤ እውነት ከአራት ኪሎ ነው የሚመነጨው ብሎ የሚያስብ ካለ ስህተት ነው፡፡

አራት ኪሎ ቤተመንግስቱም ይሁን ፓርላማው የወሰናቸው ውሳኔዎች ሕገ መንግስቱን ይጻረራሉ ብዬ ለማመን ምክንያት ካለኝ ይጻረራሉ ብሎ መግለጹ ምንድነው ስህተቱ? ሌሎችን አሳምኜ ነው መሆን ያለበት? እኛ ያልነው ‹‹ሕገመንግስቱ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር አለ፤ የማንነት የወሰን ጥያቄዎች ካሉ በክልሎች መካከል ይፈታሉ›› ይላል፤ ‹‹ክልሎች ካቃታቸው ፌዴሬሽን ምክርቤት ይፈታዋል›› ይላል፤ ይሄንን አንስተን ሞግተናል፡፡ ጥያቄአችንን ለፌዴሬሽን ምክርቤት አቀረብን፤ ይሄንን ማለት ምን ሀጢያት አለው፡፡ እንዲያውም ሕገመንግስቱ ጥብቅና የሚቆሙለት ክልሎች እያጣ በሄደ ቁጥር ስልጣን አራት ኪሎ የሚማከልበት ሁኔታ ይፈጠርና ወደድሮው ስርአት እንመለሳለን፡፡ ስልጣን ወደ አንድ ሰፈር የሚማከልበት ሁኔታ ካለ ነው አደጋው መሆን ያለበት እንጂ እኛ አቅማችን በፈቀደ መጠን ተናበን እየሰራን ነው ያለነው፡፡ ከዚህ ውጭ አላነበቡኝም የሚል እስከአሁን አልሰማሁም፡፡

ዘመን፦ በትግራይ ክልል በእንደርታ፣ በአድዋና በራያ ከነበሩ ተቃውሞዎች ጋር ተያይዞ ሰዎች ይታሰራሉ፤ ይደበደባሉ፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት አለ የሚሉ ክሶች ከተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ ይሰማሉ፤ የሚሰጡት መልስ ምንድነው?

አቶ ጌታቸው፦ አሁን በምትላቸው አካባቢዎች ላይ ጥያቄዎች የሚያነሱ ሰዎች አሉ፤ መግለጫ የሚያወጡት ጭር ሲል አልወድም የሚሉ ተቃዋሚዎች ናቸው፤ አንዳንዶቹ 60 ሰው ሊከተላቸው የማይችሉ ሰዎች ናቸው፡፡ አባላቶቻችን የሚሏቸው ሰዎች ሳይቀር በቁምነገር አይወስዷቸውም፡፡ ከእነሱ በላይ የሕዝብ ጥያቄ የሚባሉትን መመለሱ ላይ ትኩረት ብናደርግ ጥሩ ነው፡፡ በእኔ እምነት ከከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚነሱ የካሳና መሰል ጥያቄዎች አሉ፤ ይሄን ጥያቄ የክልሉ መንግስት ከሕዝቡ ጋር ሆኖ መፍታት አለበት፡፡ የወጣቶች የመኖሪያ ቤት ጥያቄ አለ፤ መፈታት መቻል አለበት፤ ለመፍታትም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ኢንተርፕሬነርስ አሉ፤ በግርግር መክበር የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የትግራይ ክልል መንግስትና ገዢው ፓርቲ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ በመጀመራቸው አንድም ቀዳዳ አናገኝም ብሎ የሚያስብ ከሩቅም ከቅርብም ያለ ጉግማንጉግ ይህቺን አጋጣሚ ተጠቅሜ ግርግር እፈጥራለሁ ብሎ ያስብና ብዙ ሙከራዎችን ያደርጋል፡፡ ይሄን ሙከራ ማድረጉ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ጠላት የሚተኛ ነገር አይደለም፡፡ ዋናው ትኩረት መሆን ያለበት የትግራይ መንግስት የሚሰራው የወጣቶቻችንን የሕዝባችንን ጥያቄ እንዴት እንመልሳለን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ጥሩ ስራዎች እየተሰሩ ነው፤ አንተ ባነሳሀቸው አካባቢዎች ተቃውሞ በሚል ደረጃ የተገለጸ ሳይሆን ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡

ዘመን፦ይደበደባሉ የሚለውስ?

አቶ ጌታቸው፦የታሰረ ወንጀል የፈጸመ እንኳን በአደባባይ ወንጀል ፈጽሞ ይቅርና ሲያሴር የተያዘ የፓርቲ አመራር ካለ ሴራ ላይ ከያዝነው እስር ቤት ከመወርወር የሚያድነው የለም፤ ይሄን ያህል ግልጽ መሆን አለብን፡፡ ሕግን የማስከበርና የሕግን የበላይነት የማረጋገጥ ጉዳይ በከባድ ሁኔታ የሚወስድ ሕዝብና መንግስት ነው ያለው፡፡ እዚህ ውስጥ የፓርቲ ሊቀመንበር ም/ሊቀመንበር እከሌ የሚባል አያድንህም፤ ወንጀል ውስጥ እስከተገኘህ ድረስ ከቦታህ ነው የምትመደበው፤ ሰዎችን የሚያድናቸው ሕግን ማክበር ብቻ ነው፡፡

ዘመን፦ ባለፈው አንድ ዓመት የተካሄደውን የለውጥ እንቅስቃሴ እንዴት ይገመግሙታል? ‹‹ሕወሀት አዲስ አበባ ላይ ይደመራል፤ መቀሌ ላይ ይቀነሳል›› የሚሉም አሉ፡፡

አቶ ጌታቸው፦ ሰፊ ትንታኔ የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም፤ በአለፈው አመት የነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ መልካም ጅምሮች ነበሩት፤ ለውጡን የምረዳው በአለፈው ታህሳስ ኢሕአዴግ ካደረገው ግምገማ ጀምሬ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ያየናቸው ነገሮች አሉ፡፡ ‹‹የሕዝባችንን የመልካም አስተዳደር ችግር መፍታት አለብን፤ የታዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መስተካከል አለባቸው፤ የዲሞክራሲ ምህዳሩ መስፋት አለበት›› ተብሎ የተወሰኑ ውሳኔዎች ነበሩ፡፡ በራሳችን ጥፋት ምክንያት እስርቤት ውስጥ ያጎርናቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነሱን ፈትተን ከሕዝባችን ጋር እንታረቅ ነው የተባለው ከዚያ አንጻር ነው ማየት ያለብን፤ እነዚህ መልካም ጅምሮች ናቸው፡፡ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት፣ ሁሉም ተቃዋሚ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገባ መደረጉ ሀጢያት የለውም፡፡

ችግሩ የሚጀምረው ያደረግናቸው የእርቅ በለው የይቅርታ እንቅስቃሴዎች ምንም አይነት የሞራል መሰረት የሌላቸው ናቸው፡፡ በወንጀል ተጠርጥሮ ሳይሆን ተፈርዶበት የነበረ ሰውዬ በይቅርታ የገባ ድል አድራጊ ሆኖ ይመጣል፤ እዚህ መጥቶ በመስዋእትነት የተገኘውን መብት ከሰዎች እጅ ሊነጥቅ ሲሞክር ታየዋለህ፡፡ ለዲሞክራሲ ምህዳር መስፋት አንድም እዚህ ግባ የሚባል አስተዋጽኦ አድርጎ የማያውቅ ሰው በሳምንት ‹‹ኢሕአዴግ መቃብር ነው መውረድ ያለበት›› ብሎ ሲፎክር ትሰማለህ፡፡

የተጀመረውን ለውጥ በተሟላና አዎንታዊ በሆነ መንገድ መምራት ሲገባ እንደ ጨረባ ተስካር ወንጀለኛውም ሀገር ሊያፈርስ ሲሞክር የነበረው ሁሉ፤ የሌሎችን አጀንዳ ይዞ ሲያተራምስ የነበረው ሁሉ መጥቶ የሀገሪቱ የበላይ ገዢ እኔ መሆን አለብኝ ብሎ የሚራኮትበትን ሁኔታ ፈጠረ፡፡ ከዚህ አንጻር ያለንበት ፈተና፣ የሰላም እጦት፣ እና የግጭቶችን መስፋፋት በብዛት ፈጠረ፡፡ በፊት እንደዚህ አይነት ሁኔታ አልነበረም፡፡

አዲስ አበባ ብዙ ወሬ አለ፤ አንዳንድ ሹመኞች ‹‹አይ ለውጥ ውስጥ ያለ ነገር ነው›› ይላሉ፤ እንደዚህ ብሎ ነገር የለም፡፡ ለውጥ በአመጽ፣ በኃይል መሆን የለበትም፡፡ ለውጥ በሁከት በሰላም መደፍረስ መመራት መሞላት፤ የለውጥ አየሩ ከፈትፈት ሲል እንዲህ አይነት ነገር ይፈጠራል የሚባል ነገር አለ እንዴ? ይህን አይነት ነገር በተመለከተ ፈረንጆች ‹‹ልጁን ከነእንትኑ መወርወር›› የሚሉት ነገር አለ፤ እንደዚህ አይደለም መሆን ያለበት፡፡

ለውጥ ያሉህን ጠብቀህ የጎደሉትን ማሟላት ነው፡፡ ከዲሞክራሲ አንጻር የጠበበ ምህዳር የሚባለውን ነገር ማስፋት ካለብን መስፋት አለበት፤ ከዚህ ውጭ ለምሳሌ ሰብአዊ መብት ጥሰት ነበር ብለህ የሆነን አካባቢ ፓርቲ ወይንም ግለሰብ ስታብጠለጥል ትቆይና በተራህ ‹‹አሁን የእኔ ተራ ስለሆነ ማድረግ አለብኝ›› ብለህ ይሄንን ስህተት ለመፈጸም መንቀሳቀስ ከጀመርክ የለውጡን ቀጣይነት አይደለም የሚያረጋግጠው፡፡ ለውጥ የሚባለው ታህሳስ የጀመርነው እንቅስቃሴ አሁን ፈተና ላይ የገባንበትን እንቅስቃሴ ተፈጥሮአል፡፡ ፈተና ውስጥ ገብቷል፤ ይሄ ነው ግምገማችን፡፡ ፈተና ውስጥ በመግባቱም የሕግ የበላይነት ባለመኖሩም ግጭቶች በየቦታው የተለመዱ ክስተቶች መሆን ጀምረዋል፡፡ የጅምላ ፍርድ ይታያል፤ ፍርድቤት ያልቀረበን ሰው የዓይኑ ውሀ ዓላማረኝም ብለህ መቀጥቀጥ፣ መስቀል፣ የመሳሰሉ ነገሮች የኢትዮጵያን ህዝብ አይገልጹም፤ ለውጡም አመጣቸዋለሁ ብሎ ያሰባቸው ነገሮች አይደሉም፡፡

በገለጽኩት ምክንያት የሞራል መሰረት በግልጽ ባለመቀመጡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ተስፋ ያጫሩ ነገሮች አሁን የስጋት ምንጮች እየሆኑ የመጡበት ሁኔታ በስፋት እየታየ ነው፡፡ የልማት እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟል፤ የውጭ ርዳታና ብድር እየተገኘ ነው ይባላል ጥሩ ነው፤ ይጎዳናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በዋናነት የዚህች ሀገር የኢኮኖሚ አቅም የሚገነባው በተነቃቃ የግል ባለሀብት ነው፡፡ መንግስት የሚሰራው ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ የግል ባለሀብቱ በስፋት ስራ ውስጥ መግባት መቻል አለበት፡፡ ወጣቱ በሚሊዮኖች የስራ እድል ሊፈጠርለት ይገባል፡፡ ይሄ እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ አቅም ሲለወጥ ነው ሀገር የሚሸጋገረው፡፡

ሀገር የፈለገውን ያህል የአሜሪካ ርዳታ ብታገኝ ሀገር የሚለውጥ ርዳታ አይገኝም፤ በጣም እርግጠኛ ሆኜ እነግርሀለሁ፤ አሜሪካኖች ገንዘባቸውን ይፈልጉታል፡፡ አሁን የሚሰጡት እገዛ ነው፤ እግዜር ይስጣቸው፡፡ በአሜሪካና በቻይና ርዳታ የሚለወጥ ሀገር የለም፡፡ የራስን አቅም በማጎልበት ብቻ ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፡፡ ከዚህ አንጻር ቋንቋችንም መለወጥ ጀምሯል፤ በቅርቡ በራሳችን ጥረትና ድካም ወጣቶቻችን የስራ እድል ይፈጠርላቸዋል በሚል ነው መስራት ያለብን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳንድ መድረኮች ላይ የሚያነሷቸው መስኖ አስፍተን የስራ አድል መፍጠር ወዘተ የሚለው እሱ ጥሩ ነው፡፡

ዘመን፦ሕወሀት ለወጣት አመራሮች ቦታ የለውም፤ አብዛኛው አመራር እድሜ ጠገቦች ናቸው፤ በየጊዜው ራሱን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር እያገናዘበ አይጓዝም የሚሉ አስተያየቶች አሉ፤ እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ ጌታቸው፦አጭሩ መልስ ውሸት ነው፤ ሕወሀት ውስጥ ወጣቶች አሉ፡፡ ሀሳብ የሚያቀርቡ በርካታ አመራሮች አሉ፤ እጅግ በጣም እምቅና የሚያጓጓ ችሎታ ያላቸው ወጣት አመራሮች አሉ፡፡ ወጣትነት ማለት ከነገሮች ጋር፣ ከወጣቶች፣ ከሕዝብ ጥያቄ ጋር ራስን እያስተካከሉ የመሄድ ጉዳይ ነው፡፡ ባረጀ አስተሳሰብ የሚመሩ የ28 አመት ወጣቶች ብትሰበስብ ኢትዮጵያ ገናና ነበረች፤ እያለ ሲያነበንብ ቢውል ወጣት ስለሆነ ብቻ ሀገርን አንድ ስንዝር ያራምዳል ማለት አይደለም፡፡ ሕወሀት ካሉት 55 አመራሮች ከ70 ፐርሰንት ያልተናነሱት ከ35 አመት እድሜ በታች ናቸው የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ በዚህ ምድብ ውስጥ ካየሀው እኔም ወጣት በሚባለው ውስጥ አይደለም ያለሁት፡፡ ዋናው ወጣት የመሰብሰብ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡

ዘመን፦በቅርቡ ስለተካሄደው የኢሕአዴግ ስብሰባ እንሂድ፤ ውሳኔዎች በአብላጫ ድምጽ መወሰናቸው ተገልጾአል፤ይህ ማለት ውሳኔውን ያልደገፉ ወይም የተቃወሙ ነበሩ ማለት ነው፡፡ እርስዎ እንዴት አዩት?

አቶ ጌታቸው፦ ከኢሕአዴግ የምክር ቤት ስብሰባ በፊት ስራ አስፈጻሚው የተነጋገረበት አጀንዳ ነበረ፡፡ በጸጥታ፣ በሰላም፣ በዲሞክራሲ፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ኑሮ የታዩ ፈተናዎች ምንድናቸው የሚል ነበር አጀንዳው፡፡ በዚያ ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀውን ጽሁፍ መዳበር አለበት ያልነው፤ በተደጋጋሚ የተወያየንበት ጽሁፍ ነበረ፤ያ ጽሁፍ ነው የቀረበው፡፡ ሀገር ፈተና ላይ ነች ብለን አምነን ነው ስብሰባ የሄድነው፤ ውይይቱ ሀገር በፈተና ላይ መሆኗን በሚገልጽና በሚያስመስል መልኩ ሄዶአል ብዬ አላምንም፡፡እዚያ መድረክ ላይ የምታየው ነገር አንዳንዱ ጣት ይቀስራል፤ እከሌ የሚባል ሰው ይሄን ስላለ ይላል፡፡ የሀገር ችግር የዕገሌ ብእር ወይም የአፍ ወለምታ የፈጠረው ነው፤ እከሌ የሚባል ሰው የፈጠራቸው ናቸው ብለህ የምታስብ ከሆነ የሀገር ችግር እየገባህ አይደለም ማለት ነው፡፡

እንደዚያም ሆኖ ችግሩን ለማመን የሚያስችል ዝግጁነት መጓደል አለ፤ እንደገባኝ ከሞላ ጎደል የሊቀመንበሩ ማጠቃለያ ጥሩ ነበር ማለት ይቻላል፤ እሳቸውም ቢሆኑ ፍራስትሬት አድርገዋል፡፡ መድረኩ ላይ ነጥብ የማስቆጠር አዝማሚያ በብዛት ታያለህ፤ ‹‹እከሌ የሚባል ግለሰብ እንዲህ እንዲህ›› የሚል፡፡ የኢትዮጵያን ችግር የሚመጥን እይታ ማየት ላይ እንደ ሕወሀት አልገመገምነውም በግሌ ግን በዚያ ስብሰባ ይህ አይነት እይታ በተሟላ መልኩ መጥቶአል የሚል እምነት የለኝም፡፡ምክንያቱም ወደዚያ መድረክ ስንሄድ እንደ ድርጅት አንሄድም፤ በግል ነው የምንሄደው፡፡ ስራ አስፈጻሚም ሲሆን እንደ ምክርቤትም ሲሆን እንደ ሕወሀት አቋም ይዘህ አትሄድም፡፡

ዘመን፦ለምን?

አቶ ጌታቸው፦በኢሕአዴግ አሰራር አባሉ በግሉ ነው እዚያ መድረክ ገብቶ አቋም የሚይዘው፤ ሕወሀት ለምሳሌ በብሎክ ይሄን ድምጽ ስጡ አትስጡ አይልም፡፡ ሁሉም ድርጅቶች በዚህ መልኩ ይሰራሉ ማለት አይደለም፤ ተነጋግሮ የሚመጣ ሊኖር ይችላል፡፡

ዘመን፦በእርስዎ እይታ ከዚህ የፖለቲካ ምስቅልቅልና ቀውስ መውጫ መንገዱ ምንድነው?

አቶ ጌታቸው፦ ብቸኛው መውጫ መንገዳችን ‹‹ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ገብታለች›› ብሎ አምኖ መቀበል ነው፤ ይሄ አቋራጭ የለውም፡፡ ይሄን ችግር አምነን ከህዝባችን ጋር ከሰራን ደግሞ ድሮ የተፈተኑ መንገዶች አሉን፡፡ እነዚያን ከህዝባችን ጋር ሆነን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመርን ችግሩን እንፈታዋለን ብሎ ማመን ነው፡፡ ችግሩን ፊት ለፊት መጋፈጥ ነው የሚያዋጣው፤ ይሄን ካላደረግን በስተቀር ከችግሩ መውጣት አይቻልም፡፡ መግለጫውን ሰምቼዋለሁ፤ የውይይቱን መንፈስ በደምብ የያዘ አይመስለኝም፤ ለእኔ መግለጫ ምንም አይደለም፡፡ ራስህን የምታስደስትበት መሆን የለበትም፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግሩን በደምብ አውቀህለት ደግሞም ልትፈታለት እንደምትችል የምታሳይበት መሆን መቻል አለበት፡፡ በእኛ አመራር ውስጥ ምን አይነት ነገር አለ አሉታዊ ነገር ላይ ብቻ እያተኮርን ሕዝባችንን ተስፋ ባናስቆርጠው የሚሉ አሉ፡፡ አሉታዊ ነገር ላይ ማተኮር ሳይሆን አሉታዊ ነገርን ማጥፋት ነው ሕዝባችን ተስፋ እንዳይቆርጥ የሚያደርገው፡፡

የጸጥታ ችግር አለ፤ የሰላም ችግር አለ፤ አንዳንድ አካባቢዎች እኮ መንገድ ከተዘጋ ከዓመት በላይ ሆኖታል፤ ማንም ሰው ማመን አይፈልግም ‹‹ተከፍቷል አሉ›› ይልሀል፡፡ ‹‹እዚህ ቦታ በግ አይሄድም፤ ስንዴ አይሄድም›› እየተባለ በአደባባይ እየተዘረፈ ፖሊስ ቆሞ እያየ በዚህ አይነት መልኩ ምን አይነት ሕብረት ነው የምትፈጥረው? እንደ አመራር ሀፍረት ሊሰማን የሚገባው ህዝቡ በየቀኑ እያየው ያለውን ችግር እኛ አይ መስሎሏችሁ ነው እንጂ ኢኮኖሚው እኮ ተነቃቅቶአል፤ ሰላም እኮ ተፈጥሯል፤ እያልን እስከመቼ ስናድበሰብስ እንኖራለን፡፡ ለማንኛውም ባለፈው የኢህአዴግ ምክርቤት ስብሰባ ችግሮቹን ለማንሳት ተሞክሮአል፡፡ እንዳልሁህ ጽሁፉ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎአል፡፡ ሊቀመንበሩም ያጠቃለለበት መንገድ ከሞላ ጎደል የራሱ ውስንነቶች የነበሩበት ቢሆንም ቢያንስ መድረኩን የሚመጥን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ችግሩ ማጠቃለያዎቹ መፍትሄ ብለን የምንላቸው ስራዎች አካል ሆነው ይቀጥላሉ ወይ የሚለው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የመርሳት አዝማሚያ አለ፤ አንድ መድረክ ላይ ‹‹አዎ አዎ እነዚህ ችግሮች አሉ›› ትልና ከሳምንት በኋላ ችግሮቹ የሄዱ ይመስልህል ወይንም አይንህን ስትጨፍን ችግሮቹ የጠፉ ይመስልሀል፡፡ ኢህአዴግ ይሄን ካላስተካከለ የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግር ይፈታል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አሁን አለሁ ለማለት በሚያደርገው እንቅስቃሴ፤ ችግሮችን ለመሸሽ በሚሄድበት መንገድ ረዥም ርቀት ይወስዳል አልልም፤ አሁንም ቢሆን አቅሙ አለ፡፡ የህዝባችንን አቅም ተጠቅመን ነው መፍትሄ ማምጣት የምንችለው ብሎ አመራሩ በማመን መጠራጠሩን ትቶ ከተንቀሳቀሰ በህብረት ሆኖ ለመስራት ከሞከረ ከባድ እንደሆነ ይገባኛል እድሉ መቶ በመቶ የተዘጋ ነው ማለት አይደለም፡፡

ዘመን፦ ሕወሐት በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ ላይ አቋሙ ምንድነው?

አቶ ጌታቸው፦ ሕወሐት አዲስ አበባንም ሆነ ሁሉንም ጉዳዮች በሚመለከት ያለው አቋም ከሕገመንግስቱ የሚቀዳ ነው፤ የትግራይ፣ የአማራ፣ የደቡብ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አላቸው አይልም፡፡ የኦሮሚያ ክልል ግን ልዩ ጥቅም አለው ዝርዝሩ በሕግ ይቀመጣል ይላል፡፡ ሕግ ለማውጣት ተሞክሮ እንደነበረ አውቃለሁ፡፡ ካቢኔ ላይ ውይይት ተደርጎበታል፤ ለምን ተፈጻሚነት እንዳላገኘ አላውቅም፡፡

ዘመን፦ ሕወሀት በተደጋጋሚ ‹‹ሕገመንግሥቱ ተጥሶአል›› የሚል ሀሳብ ያሰማል፤ በማስረጃ አስደግፈው ቢገልጹልኝ?

አቶ ጌታቸው፦ሕገመንግስቱ ተጥሶአል ሲባል ዝም ብሎ ለጨዋታ ድምጹ ስለሚያምረን አይደለም፤ ሲጣስ ስለምናይ ነው፡፡

ዘመን፦ከማሰር፣ ከሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ከሙስናና ከሌሎችም ጉዳዮች አንጻር በመጀመሪያ ደረጃ ሕገመንግስቱን የጣሱት የሕወሀት ባለስልጣናት ናቸው፤ አሁን ሕገመንግስት ተጥሶአል ለማለት የሞራል መሰረት የላቸውም የሚሉ አሉና ቢያስረዱን?

አቶ ጌታቸው፦ በመጀመሪያ ደረጃ ሕወሐት የሚባል መንግስት አልነበረም፤ የነበረውም ያለውም አንድ ኢሕአዴግ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ሌሎቹ ድርጅቶች ሁሉ እኛም ድርሻችንን እንወስዳለን፤ ልክ እንደ ብአዴን(አዴፓ) እንደ ኦህዴድ(ኦዴፓ) እንወስዳለን፡፡ የሕወሐት አባል የነበሩና በተለይ በእንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ የታዩ ከነበሩም እንደ ሕወሐት ሳይሆን እንደ ግለሰብ ኃላፊነታችንን ምንም ጥያቄ የለውም እንወስዳለን፡፡ ማንኛውም ሰው መጠየቅ ካለበት ይጠየቃል፡፡ እሺ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞአል እንበል፡፡ የሕወሀት አባል የሆነ ባለስልጣን የብአዴን የሆነ የፈጸመው የኢህአዴግ መንግስት የፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞአል፡፡ ይሄንን ማስተካከል ማለት አይ አሁን ደግሞ ኦሕዴድ(ኦዴፓ) በሚመራው ኢህአዴግ የቀድሞው ችግር ቢፈጸም ችግር የለውም ብለህ ልትሞግተኝ አትችልም፡፡ ራሱ ቋንቋው እያሳቀኝ ነው፤ ነገ ደግሞ ብአዴን(አዴፓ) በሚመራው ኢህአዴግ የድርሻችንን ሰብአዊ መብት ጥሰት እንፈጽም የሚል ነገር ሊመጣ ነው ማለት ነው፡፡ ታህሳስ ላይ ሁላችንም ስህተት ፈጽመናል፤ ብዙ ነገር አበላሽተናል ይሄንን እናርም ነው ያልነው፡፡ እናርም ስንል ድሮ እከሌ እከሌ በሚባሉ ሰዎች አሁን ከስልጣን በወረዱ ሰዎች የተፈጸሙ ጥሰቶች ናቸውና እንድገማቸው ነው ያልነው እንጂ በወጣቶች እንድገማቸው አላልንም፡፡ ቀድሞ የነበሩትን ስህተቶች በወጣት አዲስ ሹመኞች እንድገም አላልንም፡፡ በዚያ መልኩ ሊመጣ አይችልም፡፡ ስለዚህ ሕወሐት ሕገመንግስት ተጣሰ ሲል ትላንት አላልክምና ዛሬ ማለት አትችልም የሚባል ነገርም የለም፤ ብለናል፡፡ ድሮ ሕወሐት ይል ነበረ በግምገማ፡፡ ነገርኩህ እኮ የታህሳሱን ግምገማ በዋናነት የገፋፋው ሕወሐት በውስጡ ያደረገው ተሀድሶ ነው፡፡ማንም እዚህ ውስጥ ድብብቆሽ መጫወት የለበትም፡፡

ዘመን፦መቀሌ ላይ በተካሄደው 10ኛው የኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔና ከዚያም በኋላ በተደረጉ ግምገማዎች መነሻነት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ጥልቅ ተሀድሶ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ወደስራ ተገብቶ ነበር፤ ጥልቅ ተሀድሶው ተሳክቶአል?

አቶ ጌታቸው፦በሁሉም ድርጅቶች በእኩል ደረጃ ተሳክቶአል ማለት አይቻልም፤ አልተሳካም ነው መባል ያለበት፡፡

ዘመን፦ በትግራይ ክልል ካሉ አመራሮች ውስጥ ለውጡን የተቀበሉና ያልተቀበሉ አሉ የሚል ነገር ይሰማል፤ እንደ አንድ ብሄራዊ ድርጅት ይሄ የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድነው?

አቶ ጌታቸው፦ እያምታታን ነው፤ ለውጥ ማለት ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ የሚመጣን ማንኛውንም ሰርከስ (ትርኢት) መቀበል ማለት አይደለም፡፡ ለውጥ የሚመስለኝ ታህሳስ 2010 ላይ በገመገምነው ላይ ተመስርቶ ኢህአዴግ ያስቀመጣቸው መሰረታዊ አቅጣጫዎች አሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ቢሆን በይፋ የሚቀበሏቸው ናቸው፡፡እነዚህን የሚቃወም ሰው የለም፡፡ የሚቃወም ካለ ልክ እንደ ሀገሩ ሁሉ አድሀሪ ነው አስወግደነዋል ማለት ነው፡፡ እንደ ማንኛውም አድሀሪ ይወገዳል፡፡ ጸረ ለውጥና ለውጥ ደጋፊ የሚባለውን ቅድም አንስተህልኝ ነበር፡፡ ሕወሐት አዲስ አበባ ይደመራል መቀሌ ይቀነሳል በሚል የተነሳው ምን ማለት ነው፡፡ ደርጅታችን በይፋ ስላልፈረሰ፤ እንዲፈርስም ስለማንፈልግ አዲስ አበባ ስብሰባ ስንጠራ እንሄዳለን፡፡ አዲስ አበባ ያለው መንግስት እኮ የሁላችንም ነው፡፡ ለእከሌ ብለህ የምትተወው አይደለም፡፡ኢትዮጵያ ሀገራችንን እከሌ የሚባለውን ቡድን አኩርፈን የምንተዋት ነገር አይደለም፡፡ከዚህ አንጻር ስብሰባ ስትሄድ እነዚህ ሰዎች ሊደመሩ ነው ብሎ የሚያስብ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም፡፡ በገባኝ ልክ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የሚሰሯቸውን መልካም መልካም ነገሮችን መደገፍ ኢትዮጵያን መደገፍ ነው፡፡ አጥፊ መንገዶች ካሏቸው መተቸት ኢትዮጵያን መደገፍ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሕወሐት በመርህ ነው የሚመራው የሚራመደው፤ የክልሉ ባለስልጣን እከሌ እከሌ በሚል አይደለም፤ ጸረ ለውጥ ካየን እኛ እዚሁ እንዋጋዋለን፡፡

ዘመን፦በአንድ ወቅት ‹‹የገነባናትን ሀገር አናፈርስም፤ ሕወሐት ሀገሩን ጥሎ የትም አይገነጠልም›› ብለው ነበር፤ እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ይግለጹልን?

አቶ ጌታቸው፦ ኢትዮጵያዊነትን ማን እንደ አዲስ ሊያስተምረን እንደሚፈልግ ነው ትንሽ የማይገባኝ፤ ኢትዮጵያ በ1983 ሕወሐት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ሆኖ አዲስ አበባ ሲገባ እንደ ሀገር የመቀጠልና ያለመቀጠል አደጋ ላይ ወድቃለች ብሎ ተንትኖ ኢትዮጵያዊነት መዳን አለበት ብሎ ለመዳን ደግሞ በቆየው ቀመር ከሆነ መዳን አትችልም፤ ስለዚህ አዲስ ቀመር ያስፈልጋል ብሎ የሰራ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የምንኮራበት ማንነታችን ነው፤ ኢትዮጵያዊነት መዳን ካለበት ማንነትን አምኖ የተቀበለ፣ ለማንነት ክብር የሰጠ ኢትዮጵያዊነት እናድርገው ተብሎ ነው የቀጠለው፤ ኢትዮጵያዊነት መስዋእትነት የከፈልንበት ነው፡፡ በቃን ወደየቤታችሁ ሂዱ ለማለት 1983 በቂ ነበር ለሕወሐት፤ አላደረገውም፡፡ ከ100 ሺህ በላይ ሰራዊት ነበረው፤ የደርግን ሰራዊት ለመበተን በተደረገው እንቅስቃሴ የአምበሳውን ድርሻ የወሰደው ሕወሐት ነው፡፡ አብዛኛው ሰራዊትም የሕወሐት ነው የነበረው፡፡ መገንጠል የሚፈልጉ ብዙ ድርጅቶች ነበሩ፤ ደም መፋሰስ ላይቀር ይችል ነበር፡፡ አሁን ምን ተገኝቶ ነው ይሄ ጉዳይ የሚነሳው፡፡ ዛሬ ማንም አምታች ተነስቶ ኢትዮጵያዊነትን ለትግራይ ሊሰብክ ሲሞክር ታየዋለህ፤ ይሄ አይሰራም፡፡

ዘመን፦ በአንድ ዓመት ውስጥ በክልሉ በመንገድ ስራ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፤ በቤቶች ወዘተ መከናወናቸውን ተዘዋውረን ለማየት ሞክረናል፤ የዚያኑ ያህል ሰፊ ስራ አጥ ወጣት አለ፤ እነዚህን ወደስራ ለማስገባት ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ጌታቸው፦ዋናው ነገር የትግራይ ሕዝብ አቅም መደራጀት መቻሉ ነው፤ የተደራጀ ሕዝብ የተፈጠረን ስራ አድምቶ መስራት ብቻ ሳይሆን ስራንም መፍጠር ይችላል፡፡ ዋናው ትኩረታችን ወጣቶቻችንን በዝንባሌያቸው ማደራጀት መንግስት በሚሰራቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሁነኛ ድርሻ እንዲኖራቸው መንቀሳቀስ መቻል ነው፡፡ ለምሳሌ የጸጥታ ስራዎችን በሚመለከት በየከተማው ተደራጅተው ስራውን የሚሰሩት ወጣቶች ናቸው፡፡ ያ መደራጀታቸው በጸጥታ ስራ ብቻ ታጥሮ መቅረት የለበትም፡፡ የምንፈጥራቸው የስራ እድሎች በሙሉ ለነዚህ ወጣቶች ነው መሆን ያለባቸው፡፡ በራስ ተነሳሽነትም ሆነ በመንግስት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ስራአጥነቱ እኮ እንደ ሀገር ሁሉም ክልል ውስጥ ነው ያለው፤ ለአማራ የተለየ ለትግራይ የተለየ ለሌላውም የተለየ አይደለም፤ የሕዝብ እድገቱም በሁሉም ክልል አማካይ ነው፤ ይሄ ፈተና አለ፡፡ ይሄንን ፈተና ግን ፊት ለፊት አይተሀው አይንህን ከመጨፈን ልጋፈጠውና ልመልሰው ብለህ ከተንቀሳቀስክ ህዝባችንም ተባባሪ ነው፡፡ ቀን ቆርጠህለት መስራትህን ማየት ነው የሚፈልገው እንጂ አሁኑኑ ካላመጣህ የሚል ሕዝብ አይደለም፡፡ ዝም ብለህ ተኝተህ ግን የራስህን ቀፈት እያሻሸህ አንድ ወቅት መና ይዘንባል ብትለው አንተን ይበላሀል፤ መና አይጠብቅም፡፡ የሕወሐት አመራሮች ከዚህ ማምለጥ እንደሌለብን ለአፍታም ቢሆን ራሳችንን መሸወድ እንደሌለብን እናውቃለን፡፡

ዘመን፦ የመቀሌ ከተማ ፈጣን ልማትና እንቅስቃሴ የተፈጠረው ሰው ከአዲስ አበባ በብዛት ስለመጣ ነው?

አቶ ጌታቸው፦ከአዲስ አበባ የመጣ ሰው ቤት ይሰራ ይሆናል፤ የከተማዋ መነቀቃት ሰው ከአዲስ አበባ ስለሚመጣ ብቻ አይደለም፤ በእርግጥ ይመጣል፡፡ አንጻራዊ ሰላምም ስላለ ብዙ ሰው እዚህ ይመርጥ ይሆናል፤ አንዳንድ ሰዎች እዚያ አካባቢ ስራ መስራት ስላልቻለን ለቀናል ይላሉ፡፡ እንደዚህ የሚባል ነገር የለም፤ አብረን ነው የምንለማው፡፡ እዚህ አዲስ ኢንቨስትመንት የሚጀምር ሰው ካለ አዲስ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ውጭ ከሆነ ቦታ ነቅዬ እመጣለሁ የሚል ሰው ድምር ጥፋቱ ለሁላችንም ነው፡፡ ከተማይቱ አድጋለች በሚለው ላይ ብዙ ጓደኞቼ አይስማሙም፤ ገና ማደግ በአለባት፤ የተቀናጀ አመራር ይጠይቃል፡፡

ዘመን፦በመጨረሻ ወደ ኤርትራ ልውሰድዎትና አሁን የተፈጠረው ሰላምና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ምን ይመስላል? 

አቶ ጌታቸው፦በጣም ጥሩ ነው፤ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድማማች ሕዝብ ነው፤ ትግራይ ደግሞ ተመሳሳይ ቋንቋ መናገር ብቻ ሳይሆን በታሪክም በባህልም የተቆራኘ ስለሆነ እንቅስቃሴው ሲጀመር እጅግ በጣም የሚገርም ስሜት ነበር የነበረው፡፡ፖለቲከኞች ምን ያህል ሁለቱን ሕዝቦች አራርቀን እንደነበር ነው ያየነው፡፡ አሁንም ቢሆን ሰላም ከፖለቲከኞች እጅ ወጥቶ ወደሕዝቡ እጅ መግባት አለበት፡፡ የፖለቲከኞች የግል አጀንዳ እና ቁማር መሳሪያ መሆን የለበትም፡፡ለዚያ ተብሎ የሕዝብ ሰላም መደፍረስ የለበትም፡፡ የእኛ እምነት ይሄ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚል ነው፡፡ ሰሞኑን እንደሰማኸው በሮች ተዘግተዋል፤ ምክንያቱን አናውቀውም፤ ሕዝቡ ይገባል፤ ይወጣል፡፡ ማንም አይከለክለውም፡፡ ከአሁን በኋላ ለምንድነው በር የምትዘጋው? ግምብ ልትሰራ ነው? ሕዝቡን ማንም አያስቆመውም፤ እሱ ጨዋታ ነው፡፡ መንግስታት ደግሞ ይሄንኑ ተገንዝበው ቢተባበሩ ነው የሚያዋጣቸው፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን እንቅፋት ሊፈጥሩበት ከሚንቀሳቀሱ የበለጠ እንዲቀራረብ ማድረጉ ነው የሚጠቅመው፡፡ ይሄ ለእኛም ለኤርትራ መንግስትም ይሰራል፡፡ ስለዚህ በመንግስት ውስጥ ያለን ሰዎች ይሄንን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንደማናስቆመው አውቀን የሕዝባችን ደስታ አካል ብንሆን ጥሩ ነው፤ የተጀመረው ሰላም ተጠናክሮ መቀጠል መቻል አለበት፡፡

ዘመን፦ስለሰጡን ሰፊ ቃለመጠይቅ እናመሰግናለን፡፡
አቶ ጌታቸው ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

3 Comments

 1. Thank you, Tsegaye Ararssa, for your insightful piece of writing.

  The “Amhara”, in most cases, have more laughs for the rest of the peoples of Ethiopia. They are natural pretenders, and able to play victims while in reality they have worked hard to victimize ethnic others , particularly the Oromo, mercilessly. As we all know the “Amhara” have been number one beneficiaries in what the country has had to offer. After they lost first place to the TPLF (Tigrai), at least supetficially, they never hesitated to use their historical advantages as “the chosen citizens of imperial Ethiopia “, to twist the hands of TPLF, and continue to benefit themsrlves, at the expense of the historically subjugated peoples of Ethiopia. They were king makers in TPLF Ethiopia and had used their influential positions aggressively to manipulate TPLF warlords to craft policies, which not only undermined Oromo interests but also destroyed the Oromo people as a nation. Their representation in EPRDF bureaucracy has been more than the representation of all ethnic groups combined.

  The drafting and formulation of the country’s constitution was not different to ” Amhara ” over representation in other institutions. In fact, Amhara officials used TPLF as cover and inflicted much more harms to the Oromo and others, in the nearly three decades that TPLF gangsters led the country. The “Amhara” used their leverage to encourage the regime to adapt anti Oromo policies and destroy anything Oromo. For instance, Amhara bureaucrats played more roles in crafting the failed (so called) “Addis Ababa Master Plan” under the umbrella of TPLF. Their manipulation was all evident in major policies the TPLF followed in repressing the Oromo people in particular and other ethnic groups in general. Naive Oromo politicians are conned into believing that “Amhara” pretend tears are as genuine as they project to fool others. The Oromo as nation have been targeted and victimized by both TPLF and Amhara National Democratic Movement/ANDM officials and cadre over the last three decades. When ADP and the recently founded National Amhara Movement/NaAM (ultra national extremist organization) claim that they were not represented in the making of the Ethiopian constitution, they are simply playing victims. They are trying to divert attention from historical political wrongs, which have been the makings of their forefathers, and mistakes they are repeating.

  It would have been more civil if Amhara politicians and luminaries come out and say to other ethnic groups in Ethiopia, they “are sorry” for the sufferings their parents (foreparents) inflicted to others, and the toxic and deception politics they are still engaged in. Instead of crying loud that they were “not represented” during the making of the constitution, they could have come clean and reach out to others genuinely, and foster the building of new Ethiopia in which all ethnic groups in Ethiopia enjoy equal rights.

  Justice and truth prevail; may the “Amhara” open their eyes and start to understand other Ethiopians!

  OA

 2. Most of these personalities named above in the article who were student movement ex EPRP and ex MEISON , taxi drivers of the USA back then known as team Assefa Biru didn’t even read the Constitution. They were just happy the red terrorist Derg was out so they blindly heard the then early 1990s political guru, the now drunk bipolar nut Professor Andreas Eshete and the then chairman of election board Assefa Biru who told them to support the constitution.

  Now Ethiopia should restrict the deceptive marketing of the addictive opioids in Ethiopia, just so we don’t loose our children to opioid addiction as we lost Ethiopian farm lands to fertilizer addiction due to this constitution.

  The farm lands of Ethiopia are addicted to fertilizers, they don’t produce as before the TPLF constitution came out . The constitution declared all Ethiopian lands are owned by the government and ordered all lands to use addictive fertilizers. Now farm lands are under full control of the fertilizer companies which the late PM Meles Zenawi was receiving bribes from.
  For an instance Johnson and Johnson pharmaceutical company need to get banned from having any advertisement in Ethiopia since Johnson & Johnson Pharmaceutical is accused of deceptively marketing opioids causing displacements , death and destruction.

  https://www.cbsnews.com/news/johnson-and-johnson-families-impacted-by-opioid-epidemic-closely-watching-trial-today-2019-05-28/

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.