እውነታውን የረሳው መንግስት እና ውሉን የሳተው ተሐድሶ

እውነታውን የረሳው መንግስት እና ውሉን የሳተው ተሐድሶ

ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ

የዶክተር አቢይ መንግስት የኢትዮጵያ ህዝቦች በከፈሉት ከባድ መስዋእነት ወደ ስልጣን ከመጣ አመት ከመንፈቅ ሊሆነው ነው። ይህ መንግስት በመጋቢት 2010 መጨረሻ ላይ ስልጣን ሲይዝ በርካቶች “የኢትዮጵያ ህዝቦች ለብዙ ዘመናት ሲጠይቋቸው የነበሩት ብሄራዊ የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙበትን መሠረት ይጥላል፣ የተዳከመውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያነቃቃል፣ በተለያዩ ብሄሮችና ማኅበረሰቦች መካከል ብሄራዊ መግባባትን ፈጥሮ የሀገሪቷን አንድነት ከአደጋ ይታደጋል፣ በታሪካችን የመጀመሪያውን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የምናካሄድበት ጊዜ ደርሷል” በማለት ተስፋ ጥለውበት ነበር። ነገር ግን የሀገሪቷን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ እንኳ የማይችልና የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ማስፈፀም የተሳነው ደካማ መንግስት ደካማ ሆኖ ተገኝቷል።

የአሁኑ መሪ ወደ ስልጣን ከመጣ ከአስራ ስምንት ወራት በኋላ እንኳ ራሱን ከማስተዋወቅና የራሱን ስብእና ለመገንባት ከሚሰራቸው የህዝብ ግንኙነት ስራዎች መውጣት አልቻለም። ዛሬም የግጥም ምሽት፣ የባህል ምሽት፣ የአንድነት ምሽት፣ የመነቃቃት ምሽት፣ የፍቅር ምሽት፣ የመደመር ምሽት ወዘተ እያልን ቀናቱን ሸንሽነን ህዝቡን እያደረቅን እንገኛለን።

የዚህ መንግስት ቀዳሚው ችግር እንዴት ወደ ስልጣን እንደመጣ መዘንጋቱ (ወይንም ሆን ብሎ መርሳቱ) ነው። የአሁኑ የለውጥ ሂደት የመጣው በህዝብ ትግልና መስዋእትነት ነው። ትግሉ የተጀመረው ትናንት ሳይሆን ከሃምሳ ዓመታት በፊት ነው። በዚህ ሂደትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ውድ ህይወታቸውን ሰውተዋል።

የዶክተር አቢይ መንግስት ግን ትግሉ የዛሬ ሁለት ዓመት የተጀመረ ይመስለዋል። በትግሉ የተሳተፉትም ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጓዶቹ ብቻ እንደሆኑ አድርጎ ደምድሟል። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጓዶቹ በተደጋጋሚ ጊዜያት “የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና የዲያስፖራ አክቲቪስቶች ምህረት አድርገንላቸው ወደ ሀገር እንዲገቡ ከፈቀድንላቸው በኋላ እየበጠበጡን ነው” በማለት የሚናገሩት። እኝህ ሰው ክቡር አቶ ለማ መገርሳ የኦህዴድ ሊቀመንበርነታቸውን ባይተውላቸው ኖሮ ለኢህአዴግ ሊቀመንበርነት ምርጫ የማይቀርቡ መሆናቸውን እንኳ ረስተውታል (ለማ መገርሳ ያኔ ወንበራቸውን ለቀውላቸው በአሁኑ ወቅት ከጨዋታ ውጪ ሆነዋል)።

እርግጥ ጠቅላዩና ጓዶቹ የነበሩበት “ቲም ለማ” በወያኔ የመጨረሻ ዓመታት በኢህአዴግ ውስጥ ያካሄዱት ትግል ለድሉ አስተዋጽኦ ነበረው። ለዚህም እጅግ በጣም እናመሰግናቸዋለን። ነገር ግን በፓርቲው ውስጥ የፈነዳው ትግል ከፓርቲው ውጪ ሲካሄድ በነበረው ትግል ባይደገፍ ኖሮ ቲም ለማ የትም አይደርስም ነበር። ለምሳሌ የወያኔ ገዲም ጄኔራሎች አብዲ ኢሌን ቆስቁሰው በሚሊዮን የሚቆጠር ኦሮሞ ባፈናቀሉበት ወቅት ሴራውን በጥልቀት አስረድቶ ህዝቡ ከቲም ለማ ጋር እንዲቆም የቀሰቀሰው ጀዋር መሐመድ አልነበረምን? ቄሮ ቲም ለማን ደግፎ ህይወቱን ሲሰዋ አልነበረንም? ሌሎች የሀገራችን ማኅረበሰቦች፣ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞችስ ከኦሮሞው ጋር ወግነው አልታገሉምን? አዎን! ቲም ለማ ያንን ሁሉ ድጋፍ ባያገኝ ኖሮ የፌዴራሉን ስልጣን የያዘውን ወያኔን እየተገዳደረ በትግሉ መቀጠል እንደማይችል እርግጠኛ ሆነን እንናገራለን።

የዶክተር ዐቢይ መንግስት ሁለተኛ ችግር የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚፈልጓቸውን ነገሮች እና የታገሉላቸውን ጥያቄዎች በትክክል አለማወቁ (መዘንጋቱ) ነው። ከመሠረታዊው ነገር እንጀምርና ህዝቡ ከባድ የሆነ የኑሮ ውድነት እየጠለዘው ነው። የመሠረታዊ ሸቀጦች፣ የምግብና የአልባሳት ዋጋ በየዕለቱ እየናረ ነው። በመሆኑም ይህ መንግስት በትኩረት ሊሰራባቸው ከሚገባቸው ችግሮች አንዱ ገበያውን ማረጋጋት ሊሆን በተገባ ነበር። እርሱ ግን የሚታዩ ችግሮችን ትቶ “የከፍታ ቀን፣ መደመር፣ የመነቃቃት ቀን” እያለ የማይጨበጡ ሃሳቦችን በህዝቡ ውስጥ ለማስረጽ ሲደክም ይውላል።

በሌላ በኩል ህዝቡ በወያኔ ላይ ዱላውን ሰንዝሮ የታገለው ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ትግሎች የተጎናፀፋቸውን ድሎች ለማጣት እንዳልሆነ የአሁኑ መንግስት ዘንግቷል። ህዝቡ ወያኔን የታገለው ከተፈጥሮአዊ መብቶቹ መካከል ወያኔ እየሸራረፈ ያስቀራቸውን ለመጎናጸፍ እንጂ በወያኔ ዘመን የተመለሱለትን ጥያቄዎች አፈር ድሜ ለማስበላት አልነበረም።

ለምሳሌ ያህል በቅርቡ ሀገሪቱን ሊያናጋ ደርሶ የነበረውን የቋንቋ ጥያቄ እንውሰድ። ቋንቋን ማወቅ በጣም ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ልጆቹ የሚማሩበትን ቋንቋ መምረጥ የሚችለው ህዝቡ ራሱ ነው። የአቢይ መንግስት ለዚህ ዓለም አቀፋዊ መርህ ቦታ ሳይሰጥ በእውርና በደንባራ አማካሪዎቹ እየተመራ የትምህርት ቋንቋን ሊወስንልን ተነሳ። ስድስት ወር ሙሉ “ተው” እየተባለ ቢነገረው አልሰማ አለ። ስለዚህ ህዝቡ የራሱን መብት ለማስከበር ተንቀሳቀሰ (የትምህርት ቋንቋን ለመሰወን የተሰጠው ምክንያት አስቂኝ ከመሆኑ አልፎ ዘረኝነትም የሚንፀባረቅበት ነበር። “ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ሲባል ህፃናት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ አማርኛን እንደ ተጨማሪ ቋንቋ እንዲማሩ ተወስኗል” ነበር የተባለው። ህፃናቱ በኦሮምኛ ሲማሩ ጠባብነትን ይወርሳሉ ለማለት ነው? ይገርማል!!)።

ይህ በጭራሽ የህዝቡ ጥያቄ አይደለም። አልነበረምም። ቋንቋን በተመለከተ ብዙ ኦሮሞዎች ሲያነሱት የነበረው ጥያቄ “አፋን ኦሮሞ የፌዴራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ ይሁን” የሚል ነበር። ይህንን ጥያቄ መመለስ ካልተቻለ ሌላ ነገር ሳይነካኩ ጥያቄውን ለመጪው መንግስት ማስተላለፍ ይገባ ነበር።

አሁን ከዋናውና እጅግ ወሳኝ ከሆነው ነጥብ ላይ ደርሰናል።

አዎን! የዚህ መንግስት ዋነኛው ችግር በህዝብ የተመረጠ መንግስት በምርጫ እስኪተካው ድረስ ሀገሪቷን ወደ ዲሞክራሲያዊ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተመሠረተ የባለ አደራ መንግስት መሆኑን መዘንጋቱ ነው። ይህ መንግስት የተመረጠው በኢህአዴግ ምክር ቤት ምርጫ እንጂ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በተሳተፉበት ህዝባዊ ምርጫ አይደለም። በመሆኑም የአሁኑ መንግስት ፖሊሲና ህገ መንግስት እንዲቀይር ከየትኛውም አካል mandate አልተሰጠውም።

የዚህ በምርጫ ያልመጣው መንግስት አጣዳፊ ስራዎች መሆን የነበሩባቸው

 1. ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚያስፈልጉ ተቋማትን መገንባት
 2. የሀገሪቷን የዲሞክራሲ ጉዞ ሰንገው የያዙ ህጎችና መሻርና ማሻሻል
 3. ፓርቲና መንግስትን ሙሉ በሙሉ መለያየት (ይህ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ በድርጅት ጽ/ቤት የተመደቡ ሰዎች እንደ መንግስት ሰራተኛ ደመወዝ እየተከፈላቸው ነው። ፓርቲው በመንግስት መኪናዎች ነው የሚጠቀመው። የህወሓት፣ የኦዴፓ፣ የአዴፓ እና የደኢህዴን ቢሮዎች የሚገኙት በወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤቶች ውስጥ ነው። እንዲህ ዓይነቱ አሰራር ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ ስሩን ሰዷል። ይህ ዐይን ያወጣ ወንጀል ነው)።
 4. በመንግስት ጫና የተመሠረቱ ህዝባዊ ማህበሮችን (ለምሳሌ ኦልማ፣ አልማ፣ ትልማ፣ የወጣቶች ማህበር፣ የሴቶች ማህበር ወዘተ) ከመንግስት ተፅእኖ ነፃ ማድረግ
 5. የዳኝነትና የፍትሕ ስርዓቱን ከመንግስት ተፅእኖ ነፃ ማድረግ
 6. የምርጫ ህጉንና የምርጫ ስርዓቱን ማሻሻል (የምርጫ ቦርዱን አባላት ከፓርቲ ንክኪ ነፃ በሆኑ ሰዎች መሙላት)
 7. የጸጥታ አካላት ህጋዊነትን በተላበሰ ሁኔታ ህዝቡን እንዲያገለግሉ ማድረግ
 8. ያለፉት ስርዓቶች በረጩት መርዝ ሳቢያ በተቋሰሉ ህዝቦች መካከል ትክክለኛ ሂደትን በተከተለ ሁኔታ እርቀ ሰላምን መፍጠር
 9. ህዝብን ሲገድሉ፣ ሲዘርፉ፣ ሲገርፉና ሲያፈናቅሉ የኖሩ ባለስልጣናትንና የፀጥታ አካላትን ለፍርድ ማቅረብ
 10. ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሁሉም ስፍራ፣ ክልል፣ ወረዳና ዞን በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት (የተዘጉ ቢሮዎቻቸውን መክፈት)
 11. በህዝባዊ ትግሉ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ማቋቋም (በባሌና በሀረርጌ ለረሃብና ለችግር እየተጋለጡ ነው)
 12. ህገ ወጥ ታጣቂዎች በክልሎችና ድንበር አቅራቢያ በሚኖሩ ህዝቦች ላይ የሚፈፅሙትን ጥቃት ማስቆም
 13. ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውርን ማስቆም
 14. ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለሚሄደው የኑሮ ውድነት አፋጣኝ መፍትሔ ማፈላለግ
 15. ወዘተ

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ እንዳየነው ከሆነ የዶክተር አቢይ መንግስት እነዚህን ትልልቅ ተግባራት መስራቱን ዘንግቷል። ከእነርሱ ይልቅ ለጊዜያዊ ታይታና ጭብጨባ ብቻ የሚመቹ ስራዎችን ማጧጧፉን ቀጥሎበታል። ውጤቱ ግን የትም የሚያስኬድ አልሆነም። የመነቃቃትና የኩራት ቀንን ማክበር ከፌዝና ከሽሙጥ በቀር ሌላ ትርፍ የሚያስገኝ አልሆነም (ሁሉም የተደሰበት ነገር ቢኖር የዛፍ ተከላ ዘመቻው ብቻ ነው)።

ከዚህ በተቃራኒው መንግስት ለታይና ለጭብጨባ ሲል የሚፈጽማቸው ተግባራት ቀደም ሲል የተገኙ ታላላቅ ለውጦችንና ድሎችን እየቀለበሳቸው ነው። ለምሳሌ ከሁለቱ ታላላቅ ብሄሮቻችን (ኦሮሞና አማራ) በወጡ ታጋዮችና ወጣቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው የትግል አንድነት በዚህ ወቅት ድምጥማጡ ጠፍቷል። በነሐሴ 2010 መጀመሪያ ላይ OMN በሚሊኒየም አዳራሽ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ የተገኙት ተወዳጁ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ንግግር ሲያደርጉ ህዝቡ “ይደገም! ይደገም! ይደገም” እያለ ነበር ንግግራቸውን የተከታተለው። አሁን ግን ያ ሁሉ ተረት ሆኖ ቀርቷል።

እስቲ ሁለትና ሶስት ጊዜ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን እያፈረሱ ማዋቀር ምን ይባላል? የአዲስ አበባ የወንዞች ተፋሰስ ግንባታ የሚባል አቅምን ያላገናዘበ ፕሮጀክት መወጠንስ ፋይዳው ምንድነው? ለዚህ ፕሮጀክት ገንዘብ ለማስባሰብ ተብሎ የሚሊዮን ብር የእራት ስነ ስርዓትስ የሚባል ከሚዲያ ፍጆታ የማያልፍ የfantasy ዝግጅት ማዘጋጀትስ ምንድነው? “ኦነግን ትጥቅ ማስፈታት ቀዳሚ ስራዬ ነው” እያሉ በእርሱ ላይ ብቻ አምስት ወር መፍጀትስ? የማስተር ፕላኑ ጣጣ ሳይፈታ ኮንዶሚኒየም ለማከፋፈል መሞከርስ? የድንበርና የማንነት ኮሚሽን የተባለ አጨቃጫቂ መስራ ቤት አቋቁሞ ለንትርክ ህዝቡን መጋበዝስ? ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ችለው በህዝቡ ውስጥ በመንቀሳቀስ መዋቅራቸውን እንዲያደራጁ እንደመደገፍ በየጊዜው ከፓርቲዎች ጋር ኮንፈረንስ መቀመጥስ? አንዳንድ ፓርቲዎችንና መሪዎቻቸውን (በተለይ ኢዜማን) ከልክ በላይ እያቀረቡና እያሞገሱ በህዝቡና በሌሎች ፓርቲዎች ዘንድ ከባድ ጥርጣሬና መፍጠርስ?
—-
ይህ መንግስት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ጥሩ ስራ ሰርቷል። በሌላው ዘርፍ ግን እስከዚህም ነው። ለዚህ ዋነኛው ምክንያቱ ደግሞ አንድ የባለ አደራ መንግስት መስራት ያለባቸውን ዋነኛ ስራዎች መዘንጋቱ ነው። ስለዚህ ወደ መነሻው ተመልሶ በተቀሩት ወራት ውጤታማ ስራ እንዲሰራ በአክብሮት እንጠይቃለን።

ህዝቡና አክቲቪስቱ እየተፈጠረ ላለው ችግር እንደ ምክንያት ሲጠቀሱ እናያለን። ለህዝባቸው የታገሉት ወጣቶች ጣት እየተጠቆመባቸው “መንጋውና ጎረምሳው ስራ አላሰራ አለ” እየተባሉ ይወቀሳሉ። እርግጥ በወጣቶቻችን ዘንድ አለመስከን እና ችኮላ ይታያል።

ነገር ግን ዋናው የችግሩ ምንጭ ወጣቱን ከጎኑ አሰልፎ ለውጡን ማሻገር ያቃተው መንግስት ነው እንጂ ሌላ አካል አይደለም። ይህ ለህዝቡና ለሀገሩ ለውጥ ለማምጣት ሲል የሞተው ወጣት ዛሬም በአብዛኛው ስራ አጥ ነው። መንግስት ተብዬው ደግሞ ለወጣቱ ስራ መፍጠርን ትቶ በየእለቱና በየሳምንቱ “የምንትስ ቀን አከብራለሁ” እያለ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይረጫል። የሚያደንቁትንና እርሱ የሚወዳቸውን አይነት ግጥም የሚያነቡለትን ሙስኬቶዎች በሸራተንና በቤተ መንግስት እየጋበዘ ራሱን ያሽሞነሙናል።
——
በመጨረሻም!

ቆም ብላችሁ ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ አስቡ። “መደመር” እያላችሁ ፋሽኑ ያለበፈትን ሙዚቃ መሞዘቁን ትታችሁ ህዝቡ የሚጠብቃቸውን ታላላቅ ተግባራት አከናውኑ። አበቃሁ።
—–
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 1/2012 ተጻፈ።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.