ኦብነግ “በገዢው ፓርቲ ጥቃት እየተፈጸመብኝ ነው” አለ

ኦብነግ “በገዢው ፓርቲ ጥቃት እየተፈጸመብኝ ነው” አለ

February 23, 2021

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) የሶማሌ ክልልን ከሚያስተዳድረው ገዢ ፓርቲ “ብዙ ጥቃቶች እየተፈጸሙብኝ ነው” አለ። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ50 በላይ የኦብነግ አባላት መታሰራቸውን አንድ የግንባሩ አመራር ተናግረዋል።
የኦብነግ የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ አህመድ መሐመድ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጠራው ስብሰባ ላይ ዛሬ እንደገለጹት፤ በሶማሌ ክልል በዶሎ፣ ቸረር፣ ሸበሌ እና ቆራሔይ ዞኖች በሚገኙ የድርጅታቸው አባላት ላይ የእስራት እና ሌሎችም ጥቃቶች ደርሶባቸዋል። ከታሰሩት አባላቶቻቸው ውስጥ ለመጪው ምርጫ ግንባሩን ወክለው የሚወዳደሩ ዕጩዎች እንዲያዘጋጁ የተላኩ ልዑካን እንደሚገኙበት አስረድተዋል።
“በዶሎ ዞን በዋርዴር የእኛ ቢሮ ተዘግቷል። ዕጩዎች እንዲያዘጋጁ የላክናቸው ሰዎች ደግሞ ከዞኑ ወደ ጅግጅጋ አምጥተዋቸው፤ ሰሞኑን ጅግጅጋ ታስረው ነው የነበሩት” ብለዋል። በቀድሞው የድርጅቱ ሊቀመንበር የተመራና ወደ ደገሐቡር የተጓዘ ልዑክም ወደ ከተማይቱ እንዳይገባ መከልከሉንም አክለዋል። አንድ ድርጅት “መንቀሳቀስም ሆነ ዕጩ ማዘጋጀት ካልቻለ”፤ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እንደሚቸገር የስራ አስፈጻሚ አባሉ ገልጸዋል። ኦብነግ በምርጫው ለመሳተፍም ሆነ ላለመሳተፍ ገና ውሳኔ ላይ እንዳልደረሰም በንግግራቸው ጠቁመዋል።
“አሁን ሀገሪቱ ባለችበት ሁኔታ እኛ ምርጫውን ለመሳተፍ መገምገም አለብን። ሜዳው ነጻ አይደለም” ያሉት አቶ አህመድ፤ “አሁን ባለው ሁኔታ ሂዱና [ምርጫ] ተወዳደሩ ማለት፤ ሂዱና ተጣሉ ማለት ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለአቶ አህመድ አቤቱታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እና የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለሙ ስሜ ምላሾችን ሰጥተዋል። የሰብሳቢዋን እና የኃላፊውን ምላሽ ከታች የተያያዘውን ቪዲዮ ተጭነው ይመልከቱ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.