“ክስተቱ ‘የግድያ ሙከራ’ እንደሆነ ነው የምረዳው” ጀዋር መሐመድ

“ክስተቱ ‘የግድያ ሙከራ’ እንደሆነ ነው የምረዳው” ጀዋር መሐመድ

(BBC Amharic) — ትናንት ሌሊት በአክቲቪስት ጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት አጋጠመ የተባለውን ክስተት ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተነግሯል።

ጀዋር ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ትናንት እኩለ ለሊት ላይ በመኖሪያ ቤቱ ተፈጽሟል ስላለው ጉዳይ እና ምልከታውን ለቢቢሲ አጋርቷል።

ጃዋር እኩለ ሊሊት ላይ የተፈጸመውን ሲያስረዳ “ተኝቼ ነበር፤ በፌደራል ፖሊስ ተመድበውልኝ የነበሩት ጠባቂዎች ‘በአስቸኳይ መሳሪያችሁን ይዛችሁ ውጡ’ ተባሉ። ይህ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጠረ” ይላል።

• “ኢትዮጵያ የኢህአዴግ አባት እንጂ፤ ኢህአዴግ የኢትዮጵያ አባት አይደለም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

ድንጋጤ የፈጠረበትን ምክንያት ሲያስረዳ፤ “አንደኛ እኩለ ለሊት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ‘ጀዋር ሳይሰማ ውጡ’ ነው የተባሉት። በዚያ ላይ የሚተኩ ጠባቂዎች የሉም” ይላል።

በሁኔታው የተደናገጡት ጠባቂዎች ሁኔታውን ለእርሱ እንደነገሩትና እሱም በስም የሚጠቅሳቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግለሰብ ጋር ስልክ መደወሉን ያስረዳል። “በሰልክ ሳፋጥጠው ‘ጌታዬ እኔ ደሃ ነኝ። የተሰጠኝ ትዕዛዝ ልጆቹን አስወጣቸው ነው እንጂ ማን ይተካ? ምን ይሁን የተባለ ነገር የለም’ አለኝ” ይላል።

ግለሰቡም ይህን ትዕዛዝ ማን እንደሰጣቸው ከነገሩት በኋላ፤ አሁንም በስም ወደሚጠቅሳቸው የበላይ አለቃ ጋር ቢደውልም ሊያገኛቸው እንዳልቻለ ያስረዳል።

“የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጋር ወደልኩ። ስልክ አያነሱም። ምክትላቸውም ጋር ደወልኩ፤ እሳቸውም ስልክ አያነሱም። ከዚያ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን ጋር ደውዬ ምክትል ኮሚሽነሩ ስልክ እንዲያነሱ አስደረኩ። ምክትል ኮሚሽነሩ ትዕዛዙ ትክክለኛ መሆኑን ሲናገሩ በጣም ተገርምኩ” ይላል።

ከዚህ የስልክ ጥሪ በኋላ በሦስት ፓትሮል መኪና ተጨማሪ ጸጥታ አስከባሪ ኃይል መምጣቱን ጃዋር ይናገራል። “ይህ በልጆቹ ላይ [በእርሱ ጠባቂዎች] ከፍተኛ ጫናን ፈጠረ፤ ፍጥጫም ሆነ። ይህ ሲሆን ከለሊቱ 7 ሰዓት ነበር።

የተፈጠረውን ውጥረት ሊያረጋጋ የሚችል እና ኃላፊነት የሚወስድ የመንግሥት ባለስልጣን ማግኘት ስላልቻልኩ ይህን ጉዳይ ህዝብ ማወቅ አለበት ብዬ አስተዋወኩ” በማለት በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቹ እየሆነ ያለውን ለማሳወቅ መገደዱን ያስረዳል።

• “በመንግሥትም በፖሊስም በኩል ምንም ዓይነት እርምጃ አልተወሰደም” ፌደራል ፖሊስ

ጃዋር ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው በመታመኑ በመንግሥት ተነሳሽነት ጥበቃ የሚያደርግለት ኃይል መመደቡን ያስረዳል።

“ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር፣ የደህንነት ኃይሎች በአጽንኦት የተናገሩት ‘ብዙ ባላንጣዎች ስላለህ ጥቃት ቢሰነዘርብህ በሃገር ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ስለዚህ የደህንነት ጥበቃ ሊኖርህ ይገባል’ ነው የተባልኩት። እኔ ወደ የግል ሴኪዩሪቲ መግባት ፈልጌ ነበር ግን ግዴታ የመንግሥት ጥበቃ ያስፈልግሃል ተባልኩ” በማለት ይናገራል።

“እኔን ማሰረ ከተፈለገ በፈለጋቸው ጊዜ ቢጠሩኝ የምገኝላቸው ሰው ነኝ። ‘ና ታሰር’ ቢሉኝ እንኳ ክሱ አሳማኝ እስከሆነ ድረስ እምቢ የምልበት ምክያት የለም።”

“በውድቅት ለሊት በጣም አጣራጣሪ በሆነ መልኩ የተሞከረው ምን እንደሆነ አልገባኝም። የእስርም አይመስለኝም። ከውስጥ እንደምሰማው ሰሞኑን የነበረን ክርክር እየጦፈ ስለመጣ ሴኪሪቲውን በማስነሳት እንዲፈራ እና እንዲሸማቀቅ እናደርጋለን’ የሚል የውስጥ ንግግር እንደነበረ፤ ከዚያም በገፋ መልኩ በዱርዬዎች ቤቴ ላይ ጥቃት በማድረስ ለማሳበብ እንደታሰበ ነው ያሉኝ መረጃዎች የሚያሰዩት” ይላል ጃዋር።

በፌደራል ፖሊሰ ኮሚሸን ኮሚሽነር መግለጫ ላይ ያለው አስተያየት

“በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ወይ አንድ አደገኛ ሴራ አለ ወይም የሚያሳፍር ልፍስፍስነት አለ። ኮሚሽነሩ ዛሬ የተናገረው ነገር ከአንድ ከፍተኛ የደህንነት ኃላፊነት ካለበት የፖሊስ መሪ የማይጠበቅ እና አሳፋሪ ነው። … ሴራ ያለበት ኦፕሬሽን ሞክረው ስለከሸፈባቸው ነው። ምንም አልተሞከረም የሚለው ነገር ነጭ ውሸት ነው። ይህም ሊታረም የሚገባው ነው”

ከመንግሥት ጋር ስላለው ግንኙነት

ጃዋር ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ስላለው ግንኙት ሲያስረዳ ”ከፌደራል መንግሥት ጋር በቅርበት ነው የምሰራው። እዚህ አገር የመጣሁት ባለኝ ልምድ እና እውቀት ልረዳቸው ነው። ከፖለቲካል ማኔጅመንት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሥራን ነው የምሰራው። ችግር በተፈጠረ ቁጥር ይጠይቁኛል ተንቀሳቅሼ አረጋጋለሁ። ከአንዳቸውም ጋር የግል ቁርሾ የለኝም፤ አዎ እተቻለሁ።

አሁን ያለው አያያዝ ወደ አህዳዊ ሥርዓት እየተቀየረ ስለሆነ፣ የሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝሙን አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ፣ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በጣም ያሳሰበኝ ድርጅቶቹ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ሥራ አስፈጻሚ አባላት በፕሮጄክቱ እንደማያምኑ በግል እየገለጹልኝ፤ ነገር ግን ደግሞ ካላቸው ፍራቻ የተነሳ የሚደግፉበት ሂደት ስላለው ይህ መተቸት አለበት።”

• በዓለማችን የተበራከቱት የተቃውሞ ሰልፎች የሚያመሳስላቸው ነገር ይኖር ይሆን?

‘የግድያ ሙከራ’

“የእኔ ጽሁፍ እና ትችት ትናንት ለተፈጸመው የግድያ ሙከራ የሚጋብዝ አይደለም” ያለ ሲሆን፤ ትናንት በመኖሪያ ቤቱ ተፈጸመ ስላለው ክስተት እስካሁን ያለው መረጃ የሚጠቁመው በእርሱ ላይ የተደረገ ‘የግድያ ሙከራ’ እንደሆነ መደምደሚያ ላይ መድረሱን ተናግሯል።

የተጋነነው የጀዋር ተጽእኖ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ 20 ለዓመት ሲሳተፍ እንደቆየ የሚናገረው ጃዋር፤ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅምን እንደገነባ ይናገራል። “እኔ በተለያዩ የዓለም አገራት ፖለቲካን ተምሬና ብዙ ጽሑፍ ጽፌ፤ ወጣቶችን አሰልጥኜ የዚህ ለውጥ ዋና ቀያሽ ሆኜ ስሰራ ነበር” ይላል።

“እውቀቴንና ጉልበቴን ለእዚች አገር ለግሼ መንግሥት ሳይናድ ሃገር ሳይፈርስ ለውጥ እንዲመጣ ረዳሁ። ይህም ተዋቂ እና ተጽእኖ ፈጣሪ እንድሆን ረድቶኛል።”

“ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳለው ሰው ስልጣን አካፍሉኝ ማለት እችል ነበር። እኔ ግን አልፈለኩም። እንደ ግለሰብ በደሎችን ሳይ ግፎችን ሳይ እናገራለሁ እጽፋለሁ። … ለዚች ሃገር በጎ እንጂ መጥፎ አላደረኩም” ሲል ይናገራል።

ጀዋር ለሁሉም ነገር እኔ ተጠያቂ የማድረግ አባዜ በዝቷል ያለ ሲሆን “… ባል እና ሚስት ከተጣሉ ተጠያቂው እኔ፣ ዝናብ ከጠፋ ተጠያቂው እኔ፤ እኔ ዲዛይን ያደረኩትና እኔ እስትራቴጂስት የሆንኩለት ንቅናቄ ጠቅላይ ሚንስትር እንደዛ አይነት ትችቶችን ፓርላማ ፊት ሲያቀርብ በጣም ነው ያሳዘነኝ” ሲል ቅሬታውን ገልጿል።

ጃዋር ባነሳቸው ጉዳዮች ላይ የጸጥታ ጥበቃው የሚመለከተው አካል ከሆነው ከፌደራል ፖሊስ በኩል ምላሽን ለማግኘት ያደግነው ሙከራ አልተሳካልንም።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.