ወጣቶች — ቄሮ-የወጣቶች ንቅናቄ?

ወጣቶች — ቄሮ-የወጣቶች ንቅናቄ?

“እኩልነት ኢትዮጵያ ውስጥ መስፈን አለበት”

(DW) — ባለፉት ሁለት ዓመት በላይ በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ ክልል በሚደረጉ ተቃውሞዎች አንድ ሥም ጎልቶ ይሰማል። «ቄሮ!»። ከኅዳር 2008 ዓ.ም.ጀምሮ ወደ 1,500 ሰዎች በተገደሉበት ተቃውሞ የተሳተፉ ወጣቶች ስለ እንቅስቃሴያቸው ምን ይላሉ?


የ27 አመቱ ወጣት በትውልድ ቀዬው አደባባይ በተደረጉ ተቃውሞዎች ከተሳተፈ በኋላ በዚያው መቆየት አልቻለም። ለደኅንነቱ ሲል ዘወር ማለት ነበረበት። “እኩልነት ኢትዮጵያ ውስጥ መስፈን አለበት። ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት አለበት። የአፍ ዴሞክራሲ ሳይሆን የተግባር ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት አለበት። በዴሞክራሲ ስም ኢትዮጵያ ውስጥ መነገድ ይቁም” የሚለው ወጣቱ የእድሜውን ያሕል አገሪቱን የሚያስተዳድረውን መንግሥት ይቃወም ከያዘ ሶስት ክረምቶች አለፉ። ብቻውን አይደለም። ወጣቱ በኦሮሚያ ክልል በታዩ ተቃውሞዎች ስሙ የሚነሳው የቄሮ እንቅስቃሴ አካል ነው። “ቄሮ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ግድያ ይቁም፤ አፈናው ይቁም፤ ከቤት ንብረትም ሰው ማፈናቀል ይቁም። የሚሉ ጥያቄዎች ይዞ ነው።” ሲል ይናገራል።

ጥቂት ወደ ኋላ እንመለስ።

ሐሙስ ኅዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ 75 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ትንሺቱ የጊንጪ ከተማ ተቃውሞ ተነሳ። የደንብ ልብሳቸውን የለበሱ፣ ደብተር እና መፅሐፎቻቸው ያልተለያቸው ተማሪዎች ከሌሎች ወጣቶች ጋር ሁለት ቀበሌ ብቻ ባላት ጊንጪ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያሰሙ ያዙ። በጊንጪ የሚኖር ወጣት እንደሚያስታውሰው ተቃውሞው የተነሳው “የመጀመሪያው የጪሊሞ ጫካ ተሽጦ ነው። ከዛ ደግሞ ተመልሶ የትምህርት ቤት መሬት ተሸጠ። የትምህርት ቤቱ መሬት ከተሸጠ በኋላ ነው የማስተር ፕላኑ የቀጠለው።”

በተለይ ወጣቶች የበረከቱበት ተቃውሞ ጊንጪ ላይ ይሰማ እንጂ አዲስ ግን አልነበረም። ያደረ ጥያቄ፣ የከረመ ቅራኔ እና ብልጭ ድርግም የሚል ተቃውሞ ቀድሞም በዚያ ነበር። «ጫጫታው አምቦም ነበረ። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወከባ ላይ ነበሩ። ምንድነው ብለህ ስትጠይቅ ያው የማስተር ፕላኑ ጉዳይ ነው። ተቃውሞው ጊንጪ ላይ ፈነዳ እንጂ አምቦም ውጥረት ነበረ።”

መካከለኛው እና ምዕራብ ኦሮሚያ አምቦ፤ ነጆ፤ ጉሊሶ፤ ደምቢዶሎ፤ ነቀምት፤ ጊምቢና ሌሎች ከተሞችን አዳረሰ። ከጊንጪው በኋላ የኦሮሞ ተቃውሞ ገታ ይል እንደሁ እንጂ ፈፅሞ ሲቆም አልታየም። የጊንጪው ወጣት እንደሚለው ተቃውሞው እንዲህ ይሰፋል፤ ከዚህ ይደርሳል ብሎ አላሰበም ነበር።

በተለይ በውጭ አገራት በሚገኙ የኦሮሞ ተቃ ዋሚዎች እና የለውጥ አራማጆች ዘንድ ኅዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ተቃውሞው እንደ አዲስ የተቀሰቀሰበት ተደርጎ ይቆጠራል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። ንብረት ወድሟል። አቶ እንዳልካቸው ጫላ በተቃዉሞዉ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል የተገደሉ ሰዎችን መረጃ የመሰነድ ሥራ ይሰራሉ። አቶ እንዳልካቸው ከኅዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ “እስካሁን ድረስ እኔ በቆጠርኩት መንግሥትም በሚያምነው ከ1,500 የማያንስ ሰው ተገድሏል። በርካታ ወጣቶች፤ ልጆች እና ሽማግሌዎች ይገኙበታል። በኦሮሚያ ክልል ብቻ የተገደሉትን ነው።” ሲሉ ይናገራሉ።

በየጊዜው የሰው ሕይወት ይጠፋል፤ የንግድ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟል፤የመማር ማስተማር ሒደቱ ተስተጓጉሏል፤ የፖለቲካው ውዝግብ ተጧጡፏል። የአምቦው ነዋሪ “ሙሉ በሙሉ ወጣቱ ብሶተኛ ነው። ሕፃን ልጅ ትንሽ ሞባይል እንኳ ቢይዝ በማንኛውም ቦታ የምታዳምጠው የተቃውሞ ዘፈኖችን ነው። ይኼ ምን ያሕል ብሶተኛ እንደሆነ እና ምን ያሕል እንደመረረው ነው የሚነግርህ። ሲል ይናገራል። “የትም ቦታ በተንቀሳቀስክ ቁጥር እያንዳንዱ ወጣት ብታናግረው ስለ ብሶቱ፣ ስለፖለቲካው ነው የሚያወራህ። ቁስሉ ያልደረሰው ወጣት ስለሌለ ሁሉም ስለብሶቱ ነው የሚያወራህ።”

ቄሮ-የወጣቶች ንቅናቄ?

የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ የተከሰተውን ተቃውሞ በኃይል ለመቆጣጠር ከመሞከር ባሻገር ለወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ያላቸውን እቅዶች ሲያስተዋውቅ ቆይቷል። እቅዶቹ እስካሁን የፈየዱት ነገር ስለመኖሩ በተጨባጭ የሚያውቅ የለም። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት አቶ እንዳልካቸው ግን መንግሥት ጥያቄዎቹን ከመመለስ ይልቅ ከተቃዋሚዎቹ ጋር የገጠመው ግብግብ እንዳባባሰው ይናገራሉ።

“2016 በፈረንጆች አቆጣጠር ማስተር ፕላኑን ሰርዤዋለሁ ቢልም ጥያቄው ሊቋረጥ አልቻለም። ምክንያቱም መንግሥት መጀመሪያ ለነበረው ጥያቄ የመለሰው ምላሽ አስከፊ ስለነበረ ሞት፣ እስራት፣ እንግልት ካገር መባረር ስለሆነ ድሮም ከመንግስት ጋር የነበረውን ቅራኔ እያባባሱት፤ ነገሩ እየሰፋ ከቁጥጥር ውጪ እየወጣ መጣ። ከዚያ በኋላ በ2015 የነበረው ምርጫ ትክክለኛ ምርጫ አይደለም፤ አይወክሉንም ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ጭራሽ እኛን የማይወክል መንግሥት ነው ወደሚለው ሔደ ማለት ነው።”

የ27 አመቱ ወጣት በአደባባይ ይቃወምበት ከነበረው የትውልድ ቀዬው ዘወር ለማለት የተገደደው በዚሁ በኦሮሞ ተቃውሞ ሰበብ ነው። የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የፍትኅ መጓደልን፤ እየነቀሰ ከዕድሜው ዕኩል ሥልጣን ላይ የቆየውን መንግሥት የሚወቅሰው ወጣት እንደአብዛኞቹ የተቃውሞው ተካፋዮች ለደኅንነቱ ሲል ማንነቱን መናገር አይሻም።

“ይኼ ጥያቄ ዛሬ የተጀመረ አይደለም። ከዛሬ ሐያ ምናንምን አመታት ወዲሕ ያለ ጥያቄ ነው። የኦሮሞን ሕዝብ በዴሞክራሲ ስም ይሸኑበታል። የሰው ልጅ ቤት ውስጥ ነው የሚገደለው። እውነተኛ ዴሞክራሲ የለም። የኢትዮጵያ መንግሥት ትክክለኛ ሕገ-መንግሥት አለው። ግን አተገባበሩ ላይ ዜሮ ነው። የሚተገብረው እና ሕገ-መንግሥቱ ላይ ያለው ሌላ ነው።”

የተቃዋሚዎች ጥያቄ እየተደራጀ እና ቀድሞ የነበሩትንም ታሪካዊ ቅራኔዎች እያሰፋ፣ ስር እየሰደደ ሲሔድ ቄሮ የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ይደመጥ ያዘ። ቄሮ የሚለው የኦሮሚኛ ቃል ቀጥታ ትርጉሙ ወጣት፤ ያላገባ እንደማለት ነው። በተቃውሞዎቹ ወቅት ቄሮ የሚያስተባብራቸው የሥራ ማቆም አድማዎች እና ተቃውሞዎች ስለመኖራቸው በተደጋጋሚ ተደምጧል። በአነስተኛ ከተሞች እና የገጠር አካቢዎች መንገድ የመዝጋት እርምጃም ይወስዱ ነበር። በቄሮ ስም ከሚንቀሳቀሱት አንዱ እንደሚለው ቄሮ በይፋ የሚታወቅ አደረጃጀት የለውም።

“ቄሮ ሊቀ-መንበር መሪ የለውም። ቄሮ ውስጥ እኔም መሪ ልሆን እችላለሁ። ያም መሪ ሊሆን ይችላል። መደማመጥ የሚችል መስማማት የሚችልመሪ የማይፈልግ ራሱ መሪ ሆኖ የሚሄድ ማለት ነው። በአፈ-ሙዝ የሚታገሉ አይደሉም። ለነጻነታቸው የሚታገሉት በአፈሙዝ ሳይሆን አገሪቷ በሰላም እንድትረጋጋ የሚፈልጉ የወያኔን ሥርዓት ደግሞ በግልፅ የሚቃወሙ ናቸው።”


በሌላ በኩል የወጣቶች እንቅስቃሴ መሪ ያለው አደረጃጀት ነው የሚል ሙግትም ይደመጣል። በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፍ ሌላ ወጣት “አደረጃጀት አለው። መዋቅር አለው መሪ አለው። እንጂ በደመ-ነፍስ የሚመራ አይደለም። በደመ-ነፍስ የሚመራማ ቢሆን ይኸን ሁሉ አመትም ባልሔደ ነበር። ኦሕዴድም አላደራጀውም። ወይ ደግሞ ኦነግ ውጪ ያለውም አላደራጀውም። እዚሁ አገር ውስጥ ያለው ችግር የወለደው ነው።”

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን የሚመራውን ኦሕዴድን አብዝተው ይተቹ የነበሩት ተቃዋሚዎች አቋማቸውን ቀይረዋል። የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ባሉባቸው የአደባባይ ተቃውሞዎች የኦሕዴድን አመራሮች ሲያሞግሱ ተደምጧል። ይኸ የኦሮሞ ተቃውሞ ካለፈባቸው ኹነኛ ሒደቶች አንዱ ነው። አቶ እንዳልካቸው የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች እንቅስቃሴ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መሪ አልባ ነበር ሲሉ ይናገራሉ።

“ወጣቶቹ መሪ አልባ ነበሩ። ውጪ አገር ያሉ እንደ መገናኛ የሚጠቀሙባቸው ሰዎች አሉ። ከዛ ውጪ ግን ወጣቱ ነው እንቅስቃሴውን እየመራ ያለው የሚል እምነት ነው ያለኝ። በቀጥታ ተጠያቂነት ያለው አደረጃጀት ያለው መሬት ላይ ሰዎችን የሚያደራጅ የፖለቲካ ተቋም ወይም የሲቪክ ማሕበር ቄሮ በሚል እስካሁን ድረስ አላየንም። እስካሁን ድረስ ያየንው ወጣቶቹ ራሳቸውን በማደራጀት ወጥ የሆነ የፖለቲካ ቁመና ያለው ድርጅት የለም።”

ወደ ኹከት ሊያመራ ይችላል?

ባለፉት ሁለት አመታት ተቃዋሚዎች የጸጥታ ኃይሎች እና ሰላማዊ ሰዎች ጭምር ተገድለዋል። የመንግሥት እና የግል ንብረትም ወድሟል።

“ቄሮ መንገድ ይዘጋል። መንገዱን የሚዘጋው ደግሞ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ነው። ለዛ አጋዚ እንዳይገባ ብሎ መንገዱን ይዘጋል። ንብረት አያወድምም ። አንዳንዴ ግን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የመንግሥት ንብረት ላይ የሚያስፈልገው ጊዜ አለ። ለምሳሌ ከኤኮኖሚው ተጠቅሞ ህዝቡም ለመጉዳት የሚያስብ ከሆነ ኤኮኖሚውን እንዲቀንስ ማድረግ ቀላል ነው። በኤኮኖሚው መያዝ ይቻላል በሚለውም ያምናል። ኤኮኖሚውን በማውረድ መንግሥቱን አቅጣጫውን ማስቀየር ይችላል የሚባለውንም በዚህም ያምናል። ሆን ብሎ ግን የግለሰብ ንብረት ማጥፋት ሆን ብሎ የመንግሥት ማጥፋት ሆን ብሎ የተለያዩ ድርጅቶችን ማጥፋት ላይ ቄሮ አይሰማራም።»

አቶ እንዳልካቸው ተቃውሞዎቹ ወደ ኹከት ለማምራታቸው የመንግሥትን እርምጃዎች ተጠያቂ ያደርጋሉ። በተለይ ከኢሬቻ ክብረ በዓል በኋላ በተቃዋሚዎች ዘንድ ወደ ኹከት የማዘንበል አዝማሚያ ታይቷል የሚሉት አቶ እንዳልካቸው የማኅበራዊ ንቅናቄዎች ጠባይ እንደሆነ ይናገራሉ።

“እኔ ኹከት አልባ የሆነ መልኩ ይበዛል ብዬ ነው የማስበው። የኹከቱን መጠን መንግሥት ከወሰደው እርምጃ ጋር አነፃፅረን ነው ማየት ያለብን። እጃቸውን አጣምረው ነው ታስረናል ሰው አንነካም የሰውን ነገር አንፈልግም የሚል ምልክት ነው እጅ ማጣመር።”

ጊንጪ ከተቃውሞው በኋላ

የተቃውሞው ተሳታፊዎችም ይሁኑ ታዛቢዎች በርካቶች የሞቱበት፣ የታሰሩበት እና የተሰደዱበት ተቃውሞ አንዳች አዎንታዊ ለውጥ በማምጣቱ ላይ ይስማማሉ። መለኪያቸው የተለያየ ቢሆንም። የጊንንጪው ወጣት ለግለሰብ ተሸጧል የተባለው የጪሊሞ ደን “ተመልሷል አልተመለሰም ምንም የምናውቀው ነገር የለም። ግን ምንም አይነት እንጨት እየተሸጠ አይደለም። እየተቆረጠምም አይደለም።” ሲል ተናግሯል። እርሱ እንደሚለው ከተቃውሞዎቹ በኋላ “ሁሉም ለመብቱ ተከራካሪ ሆኗል።”

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.