የሕዝቦች ጥያቄ የግለሰቦች ሹመት አይደለም

የሕዝቦች ጥያቄ የግለሰቦች ሹመት አይደለም

ብርሃኑ ሁንዴ, February 23, 2018

የወያኔው መንግስት ጠ/ሚኒስተር አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ከስልጣናቸው ለመውረድ ካስታወቁ ወዲህ፤ እሳቸውን ሊተኩ የሚችሉ ግለሰቦችን በሚመለክት የሚደረገው በተለይም የፌስ ቡክ ውይይት ወቅታዊ የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል። እገሌ ጠ/ሚኒስተር መሆን አለበት፣ እገሌ መሆን የለበትም፣ እገሌ ብቃትና ደጋፍ አለው፣ እገሌ ደግሞ ችሎታም ድጋፍም የለውም ወዘተ አየተባለ የተለያዩ ሀሳቦች ይቀርባሉ። እንደዚህ ዓይነት ሀሳብ የሚያቀርቡት ስዎች በተለይም አክቲቪስቶች የሕዝብን ጥያቄ በደንብ የተረዱ አይመስልም። ወይንም ደግሞ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ውዥንብር የሚፈጥሩ ይመስላሉ።

አክቲቪስቶች አንዳንዴ የሚያቀርቡት ሀሳብ ከእስትራቴጂና ስልት አንፃር ሲታይ ገንቢ መስሎ ቢታይም፤ በተዘዋዋሪ ግን የሕዝብን የትግል ዓላማ የሚያስት ሆኖ ይገኛል። ለምሳሌ ከሶስት ዓመት በፊት ተጀምሮ አሁንም አየቀጠለ ያለው የኦሮሞን ሕዝብ እንቅስቃሴና አመፅ ብንወስድ፣ እኔ እንደሚገባኝና ከሕዝቡም መፈክሮች ማየት እንደሚቻለው፣ ሕዝቦች የስርዓት ለውጥ አንደፈለጉ ነው። “Down Down Wayyaanee; Down Down TPLF” የሚለውን መፈክር እንኳን ብንወስድ ይህ ቀላል ማስረጃ ይሆናል።

ታዲያ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ የሕዝብን ፍላጎት በሚፃረር መንገድ የጠቅላይ ሚኒስተርነትን ጉዳይ ወቅታዊ አጀንዳ በማድረግ፤ ሀገሪቷ በዲሞክራሲ ውስጥ እንደምትገኝ በማስመሰል፤ በተዘዋዋሪ የወያኔን ስርዓት ከውድቀት ለማዳን የሚደረገው ዘመቻ ማንን ለምጥቀም እንደሆነ ለኔ አይገባኝም። ባሁኑ ወቅት የሚፈለገው ይህ የወያኔ አገዛዝ ለኣንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲጠፋና ወደ ሰላማዊ ሽግግር ለሚደረገው ጉዞ ሕዝብን የሚያበረታታ ስራ መስራት ነው እንጂ ሕዝብን የሚያወናብድ ስራ መስራት ወያኔን ከመጥቀም ውጪ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም።

አንደኔ አመለካከት ባሁኑ ወቅት የሚፈለገውና መነሳት ያለበትም ጥያቄ እንዴት ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት መቋቋም እንደሚችልና የሀገሪቷ የወደፊት ዕጣ ፋንታ ምን መሆን እንዳለበት ሁሉንም ያቀፈ ውይይት ማድረግ ነው እንጂ እየሞተ ያለውን መንግስት በተዘዋዋሪ ከውድቀት ለማዳን የሚደረገው ጥረት ምንም ትርፍ አያመጣም። የሕዝቦችንም ጥያቄ ሊመልስ አይችልም። ሕዝብ እየጠየቀ ያለው ግልፅ ነውና።

በነገራችን ላይ ባሁኑ ጊዜ ጎልቶ እየታየ ያለው የጠቅላይ ሚኒስተርነትን ጉዳይ፤ የወያኔ ስርዓት ጥገና እንጂ የስርዓት ለውጥ እንዳልሆነ ግልፅ መሆን አለበት። ለወያኔ መንግስት እውቅና ለመስጠት እንጂ የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት አይደለም። በማይሆን ፕሮጀክት ላይ ሁሉን ነገር ከማባከን፣ የሕዝብ ትግል እንዴት ቶሎ የተፈለገውን ግብ ለመድረስ እንዲችል መስራት ይመረጣል።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.