የመደመር ፍልስፍና እንደ ገዳፊነት   ! (Ethiopiansism as Reductionism)

የመደመር ፍልስፍና እንደ ገዳፊነት   ! (Ethiopiansism as Reductionism)

Dr. Yoseph Mulugeta Baba, Onkoloolessa 28, 2019

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውስ መፍታት የሚቻለው በመደመር ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ ሳይሆን የጋራ ግብ አልያም የዓላማ አንድነት ሲኖር ነው። የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ‹‹በመጨፍለቅ›› የሚመጣ ሀገራዊ ለውጥና አንድነት የለም። በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው አንኳር ጥያቄ የማንነት እና የራስን እድል በራስ የመወሰን ሆኖ ሳለ፣ ኢህአደግ የተያያዘው የውህዴት ወይም የመደመር ፖለቲካዊ ፍልስፍና ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድ ፈጽሞ የለም። ምክንያቱም፣ ሕዝባዊ ድጋፍ የለውምና ነው!

የኢትዮጵያ እንድነት ሊኖር የሚችለው በሕዝቦቿ ፍቃድ እንጂ አንድም በመለኮታዊ ፍቃድ፣ ሁለትም የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን ፓርቲዎችን በግድ/በስምምነት አንድ ላይ በ‹‹መጨፍለቅ›› አይደለም። ‹‹ሀገራዊ መተማመን እና መግባባት የሚኖረው አንድ ቋንቋ፣ ባህል እና ሃይማኖት ያለው አንድ ወጥ የሆነ ሕዝብ መፍጠር ሲቻል ነው›› የሚል ግልብ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ሕልውና በጣም አደገኛ ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ታሪክ ውስጥ ለማንነት ፖለቲካ ስር መስደድና መስፋፋት አሐዳዊ-ሥርዓት ዋነኛ ምክንያት መሆኑ እየታወቀ፣ ኢህአደግ ምን ዓይነት ‹‹አንድነት›› ወይም ‹‹ውህዴት›› እንደሚፈልግ ግልጽ አይደለም።

ኢትዮጵያዊ_ብሔርተኝነት በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ እንጂ ከሕዝቡ ታሪካዊ አድማስ (historical horizon) ተነጥሎ ያለ/የሚኖር ነገር አይደለም። ‹‹ኢትዮጵያዊነት ረቅቅ ነው!›› የሚሉ ግለሰቦች የሰው ልጅ ሕልውና (ontological characterstics of human existence) ምን መሆኑን ያልተገነዘቡና በምዕራቡ ‹‹ዓለም›› ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ ምክንያት ለህልና ባርነት የተዳረጉ ማንነት-አልቦ ሰዎች ናቸው። በመጀመሪያ፣ የብሔር ማንነት ጽንሰ-ሐሳብ የደም ትስስር ያላቸውን ሰዎች አያመለክትም። ይልቅስ ብሔርተኝነት በረዥም ዘመናት በኢትዮጵያ ሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት ሂደት ውስጥ የተፈጠረ ታሪካዊና ማህበራዊ ክስተት ነው። ስለዚህ፣ ከታሪክና ከባህል ነጥለን መገንዘብ የሚንችለው ኢትዮጵያዊ ማንነት ፈጽሞ ሊኖር አይችልም።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የራሳቸውን “ዓለም” የሚመለከቱበት፣ የሚረዱበት እና የሚተነትኑበት የራሳቸው የሆነ ፍልስፍናዊ ስልት ወይም ዘዴ አላቸው። ይህም ንጽረተ-ዓለም (Weltanschauung) ተብሎ ይጠራል። ስለዚህ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን (ኢትዮጵያዊነትን) የሚገነዘቡበት መንገድ ከዚህ ንጽረተ-ዓለም ጋራ ፈጽሞ የተቆራኘ ነው።የሰው ልጅን ከሚኖርበት “ዓለም” ነጥሎ መረዳት አይሞከርም። በሌላ አገላለጽ፣ የሚታወቀውን “ነገር” (known object—ኢትዮጵያዊነትን) ከ“እኔታ” (knowing subject-የራስ ማንነት/ባህል) ነጥሎ መረዳት አይቻልም። “ሌላ”ውን (the Other) በመረዳት ሂደት ውስጥም የራስን ቅድመ-ግንዛቤ ወይም አረዳድ (pre-understanding) ማስወገድ ወይም ችላ ማለት ፈጽሞ አይቻልም።

  በመሆኑም፣ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ያላቸውን ሕዝቦች በጉልበት ጨፍልቀው አንድደመሩ ማድረግ ጽንፈኛ አመለካከት ነው። ይህ አካሄድ ስበዛ አደገኛ ነው። አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ሃይማኖት የሚለው ተረታ-ተረት ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ህያው ምስክር ነው። እንዲህ ዓይነቱ ፍልስፍናዊ አመለካከት ገዳፊነት (reductionism) የሚባል ሲሆን፣የሰው ልጅ ስለ ራሱ ንጽረተ-ዓለም (worldview) ያለው ቅድሜ-ግንዛቤ (pre-understanding) ተቀዳሚና (primordial) መሠረታዊ (fundamental) መሆኑን ስለሚዘነጋ፣ ለብዙኃ-እይታ (multi-perspective) ፈጽሞ ቦታ የለውም።

አብዛኛውን ጊዜ፣ አሀዳውያኑ የሚመሩበት የፍልስፍና መሠረት በሌለው ኢትዮጵያዊነት ላይ የሚታወቅ መሆኑ ነው። ኢትዮጵያዊነት ሲባል በኢትዮጵያ ብሔሮች በታሪክና በባሕል መካከል ያለውን ልዩነት ከመካድ በስተቀር ሌላ ትርጉም በግልፅ አይሰጥም። ኢትዮጵያውያኑ በዚህ ረገድ ለራሳቸው የሚስጡት ትርጉም በአንድ ወገን ብቻ ኢትዮጵያዊነትን የሚተርክ ሲሆን ለብዝሃነት ዕውቅና አይሰጥም። ይልቁንም አንድ-ወጥ የሆነ ባህልና ቋንቋ የፖለቲካ ሥርዓትን በማራመድ የባህል ልዩነትን ይሰርዛል። የትምህርት ፖሊሲውም ይህንን የሚመለከት አተያይ እንዲይዝ ያበረታታል። በዘመናት የሀበሻ ገዢ መደብ ከሰሜን በመነሳት የደቡቡን ግዛት “ያልሰለጠነ” በማለት ልክ እንደ ሰሜናዊው ክፍል በማስተማር/በሃይል እንዲቀየር ማድረጉን ቀጠለበት። ይሁንና ኢትዮጵያ የባለ ብዙ ብሔሮች እንዲሁም እያንዳንዱ የራሱ የሆነ ባህልና ቋንቋ ያላት ስትሆን የአሀዳውያን ኢትዮጵያ አስተሳሰብ ግን አገሪቱን ወደ አንድ አገራዊ ይዘት የሚያሳንስ ዕውነታ ነበር። በዚህ ድርጊትም መላ አገሪቱን በእነርሱ ዕይታ ብቻ ሊቀርፁ ሞክረዋል። ኢትዮጵያዊ-ብሔርተኞች የማንነት ፖለቲካ ፍፁም ምቾት አይሰጣቸውም። በመሆኑም የባህል ልዩነትን በማስወገድ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነትን ብቻ የማረጋገጥ ጥረትን ቀጠሉበት። ትኩረታቸውም ሁሉም የሚኮራበት ታሪክ ማበጀት ብቻ ላይ ሆነ።

ከሁሉም በላይ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጥያቄ የቅርብ ጊዜ ክስተት እንደሆነ አድርገው ለማቅረብ የምሞክሩ አንድ አንድ ሰዎች አሉ። ይህ አረዳድ ስህተት አለበት። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፍልስፍና ታሪክ ውስጥ ሁለት አንኳር አንኳር ጥያቄዎች ነበሩ፡- የመደብ ጥያቄ (ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል) እና የብሔር ማንነት ጥያቄ። እነዚህ ጥያቄዎች ጎልተው የወጡት በአብዮቱ ጊዜ (በ1960ዎቹ) ቢሆንም ቅሉ፥ ከዚያ በፊትም ነበሩ። የብሔር ጥያቄ የኢህአዴግ የፖለቲካ ሥራ ውጤት አይደለም። “የብሔር ጥያቄ አልነበረም” እና “የብሔር ጥያቄን ከኢትዮጵያዊነት ጋር እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?” ለየቅል ናቸው። የብሔር ማንነትን ወደ ጎን የሚገፋ “ኢትዮጵያዊነት” ቅርጽ (form) ብቻ እንጂ ይዘት (content) ስለሌለው ዘላቂነት የለውም። አንድ ሰው ሐመር ወይም ኮንሶ ሆኖ ምርጥ ኢትዮጵያዊ መሆን ካልቻለ ችግር አለ ማለት ነው። መቼም ቢሆን አንድ ወጥ ማንነትን ብቻ የሚያስተናግድ “ኢትዮጵያዊነት” መፍጠር አይቻልም። ኢትዮጵያዊነት የብሔር ማንነትን ማቀፍ ካልቻለ ሕዝቡ የራሱ የፖለቲካ አማራጭ መፈለጉ አይቀረ ነው። የሕዝቡን ማንነት (ቋንቋ እና ባሕል) ሳያከብሩ፣ መሬቱን (ወንዙን እና ተራራውን) ብቻ መውደድና መፈለግ የንቀት ንቀት ነው። ከኤርትራ ሕዝብ የሚንማረው ይህንን የታሪክ እውነታ ነው።

ስለዚህ፣ መቼም ቢሆን አንድ ወጥ ማንነትን ብቻ የሚያስተናግድ “ኢትዮጵያዊነት” መፍጠር አይቻልም። ከእንግዲህ ወዲህ በኢትዮጵያ ምድር ልዪነትን የማይታገስ እና አንድ ዓይነት አመለካከት ብቻ ማስፈን የሚችል የምድራችን ኃይል ፈጽሞ አይኖርም። ያለን ብቸኛው አማራጭ ብዙ ማንነቶችን እና የተለያዩ ኃይማኖቶችን ማስተናገድ እና ማቀፍ የሚትችል ኢትዮጵያዊነትን መፍጠር ነው። ፈላስፈው እንዳለን “በሠላም ለመኖር ብቸኛው አማራጭ ሌሎች እንድኖሩ መፍቀድ  ነው።” የማንነት ፖሊቲካን ማራመድ ሀገርን በማፍረስ አይደለም። ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን ማንነትን ጨፍልቆ አይደለም። ኢትዮጵያዊነትን ተጸይፎ ብሔርን ብቻ መውደድ እንደማይቻል ሁሉ፣ ብሔርን ጠልቶ ኢትዮጵያዊነትን መውደድ አይቻልም። “ባልን ወዶ ፂሙን ጠልቶ አይሆንም” የሚንለው ለዚህ ነው!

በሌላ ቡከል፣ አሁን ኢህአደግ የተያያዘው የውህዴት ወይም የመደመር ፍልስፍና በከፍል አዲሱ_የአለም_አሰላለፍ (New_World_Order) የተሰኘውን የምእራቡን ዓለም የእጅ አዙር ቅኝ-ግዛት በውስጡ ያዘለ ነው። አዲሱ_የአለም_አሰላለፍ ጽንሰ-ሐሳብ  የአውሮፓውነት ግልባጭ ሲሆን ራሱን የሁሉም ነገር ፍፁማዊ መለኪያ አድርጎ የሚያቀርብ ትምክህተኛ ርዮተ-ዓለም ነው። አዲሱ_የአለም_አሰላለፍ አንድ ወጥ አመለካከት (አንድ ዓይነት አስተሳሰብ፣ አንድ ዓይነት መንገድ፣ አንድ ዓይነት እምነት) ብቻ መኖር አለበት ብሎ ይተርታል። በሌላ አገላለጽ፣ አዲሱ_የአለም_አሰላለፍ/አውሮፓውነት የባህል ብዙኃነትን (cultural pluralism) የማይቀበል ወይም ልዩነትን የማይታገስ፣ የባህል ወጥነትን (uniformity of culture) የሙጥኝ ያለ ፣ በግለሰባዊነት (individualism) አምልኮ የታወረ፣ ያለ አቅሙ ተፈጥሮን ለማስገበር (ለመቆጣጠር) የሚንጠራራ፣ ራሱን ከተፈጥሮ ነጥሎ የሚረዳ፣ ለሰው ልጅ ችግር ሁሉ መልስ አለኝ የሚል፣ በ“ስላጣኔ” (civilization) ወይም በ“ዘመናዊነት” (modernism) ስም ቅኝ-ግዛት እና የእጅ-አዙር ቅኝ ግዛት (neo-colonization) የሚያስፋፋ በጣም አደገኛ እና ኋላቀር አስተሳሰብ ነው።

ውይይት ምርጫ የለውም!

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያዊ-ብሔረተኝነትና በብሔር-ብሔርተኝነት ያለውን ሚዛን ማስጠበቅ አስቸጋሪ የሆነበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ስለሆነም ያለፈውን የብሔር ቁርሾና የወቅቱን ያለመግባባት ችግር ማስወገድ አስፈላጊ ይሆናል። እንዴት ነው ለኢትዮጽያዊ ዘግነታችን ተመሳሳይ ዕውቅና በመስጠት ችላ የማይባለውን የተለያየ ታሪካዊ ተሞክሯችንን ከኢትዮጵያዊ-ብሔርተኝነት ጋር የምናዛምደው? የመዋሃድም ሆነ የመገንጠል አተያይ የጠነከረ አገራዊና የጋራ ዘግነትን ድጋፍ አይሰጡም። የአሁኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አመራር የሚያስፈልገው በመዋሃድና በመገንጠል መካከል ያለውን ግንኙነት ማቀራረብ ነው። የዚህ ትርጉምም በአገር ፍቅርና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ስሜትና የብሔር አስተሳሰብ ያለውን መነቃቃት ሚዚናዊነቱን መጠበቅ ያስፈልጋል። ዛሬ የኢትዮጵያ የማሕበራዊ ፖለቲካ መሪዎች የትኛውን ትክክለኛ እቅጣጫ በመከተል ተቀባይነት ያለው ሁሉን የሚያስማማ አቃፊ የሆነ የመልካም አስተዳደር ማድረሱ ላይ ነው። የውህዳን አስተሳሰብ አራማጆች (የቀኝ ክንፍ ፖለቲከኞች) እና የመገንጠል ሀሳብ (ብሔር ተኮር ፖለቲከኞች) በመካከላቸው ያለውን ያለመግባባት በማስወገድ የጋራ ስኬት ሊይዙ ይገባል። መወያየት ያለመግባባትን ዋና ማስወገጃ ቁልፍ መሣሪያ ሲሆን ለዕውነተኛ ትብብርና የጋራ መተማመንንም ያመጣል። የወል አቋም ሲያዝ መተባበርን እንደ አስፈላጊነቱ የሚለዋወጥ ሀሳብ መከተልን ይጨምራል። የሁለቱ ተፎካካሪ ወገን ለፍትህ ለነፃነትና ለዕኩልነት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊታገሉ ይገባል። ሚዛናዊ የሆነ አቀራረብ ለታሪካዊ መግባባትና ትርጉም በሁሉም ወገን ተቀባይነትን ያስገኛል። በእያንዳንዱ የአመለካከት ለውጥ መኖር ለጊዜው የኢትዮጵያ ማሕበራዊ ፖለቲካ አመራር መሸጋገር ዋስትና ሰጪ ይሆናል። በተለይ፣ የአንድነት ኃይሎችና ብሔርተኞች “የሀገራችንን ታሪክ” የሚረዱበትና የሚተነትኑበት መንገድ፣ ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዳንደርስ ትልቅ እንቅፋት ሆነዋል። ከዚህ “ጽንፋዊ የታሪክ ትንተና” ለመራቅ ብቸኛው መንገድ ደግሞ፣ “ሌላው ወገን” የሚለውን ልብ ብሎ ማዳመጥ ያስፈልጋል። የበለጠ ግልጽ ለማድረግ፣ የማንነት ጥያቄን ከጠባብነት፣ የሀገር አንድነት ጉዳይን ከትምክህተኝነት ጋር ብቻ አቆራኝቶ መገንዘብ፣ ወደ ፖለቲካዊ ጽንፍ ሊያመራ ይችላል። ስለዚህ፣ በሁለቱ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ውስጥ ያለውን እውነታ በትክክል ለመረዳት፣ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ወገኖች በኩል የተደረሱትን ጥልቅ የምርምር ሥራዎች በሰከነ መንፈስ መመርመር ያስፈልጋል።

በመጨረሻም፣ አሁን የሚያስፈልገው (1ኛ) የጋራ ተቋማትን ማቆም (2ኛ) የፖለቲካና የሕግ አግባቦችን ማደራጀት እና (3ኛ) የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥ፤ አራት ነጥብ! በኦላና ዞጋ መልእክት ሐሳቤን ለሳረግ፡-

‹‹በእውነቱ በእኛ ትውልድ ፊት የተደቀነው ፈተና ራሳችንን መሆን አለመቻላችን የሚመስለውም ለዚህ ነው። የትናንቱን በቅጡ ሳይረዳ ዛሬን ሊተረጉምበት የተነሳ አሳዛኝ ትውልድ ስለሆነ። አንዳዶቻችን የትናትናውንና በቅጡ የማናውቀውን ታሪክ ዋቢ እየጠራን ዛሬን ልንኖርበት እንፈልጋለን። ኖረንበታልም። ሌሎቻችን ደግሞ በቅጡ ያላወቅነውን የትናንትናውን እያነሳን ዛሬን መኖር አቅቶናል። አንዳዶቻችን ደግሞ ከትናንቱም ሆነ ከዛሬው ይልቅ የትናንት ወዲያውኑ ከርቀት ማጣቀሱን መርጠናል። ይባስ ብለን በሌላው ታሪክ ውስጥ ተሸሽገን መኖርን የመረጥንም አለን። በመሰረቱ በአንዳንድ ጥቃቅን ነገር ላይ እንለያይ እንጂ ችግራችን ተመሳሳይ ነው። ሁላችን በዛሬው ፊት እኩል መሆናችንና የነገውም ምን መምሰል እንዳለበት የሚወስነው የዛሬው ተግባራችን መሆኑን አለመገንዘባችን በተለያየ አቅጣጫ ከዛሬ የምሸሽ መሆናችን ነው። የትናንት ወዲያው ትውልድ ለፈጸማቸው ገድሎች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ትቶልን የሄዳቸው ነገሮች ከአንድ መንደር ሕዝብ አልፈው መላው የአህጉሪቱን ህዝብ የሚያኮሩ የታሪክ ቅርስ ሆነው በሚታዩበት በዛሬው ወቅት የእኛ ብቻ ነው በሚል ስሜት ወደ መንደር ለመመለስ ከመጣር የበለጠ ምን የሚያዛዝንና የሚያስገርም ነገር አለ። ይህ ትውልድ የበኩሉን የታሪክ ድርሻውን ተወጥቶ ለነገው ትውልድ የተሻለ ነገር ማስረከብ እንዲችል ከትናንቱ የተዛባ ታሪክ ተጽእኖ መላቀቅ አለበት የሚባለውም ለዚህ ነው።›› (ኦላና ዞጋ፣ ግዝት ና ግዞት፣ ገጽ፣ 385)

#Amen_Ra!

* Yoseph Mulugeta Baba is a qubbee generation born in Eastern Wollega, Konchi/Nekemte, Ethiopia. He holds a B.A, M.A, and Ph.D. degrees in Philosophy from The Catholic University of Eastern Africa (CUEA), Nairobi-Kenya. He also holds a B.D, in Sacred Theology (Magna Cum Laude Probatus) from Pontifical Urbaniana University, Rome. His research interests involve: Metaphilosophy, Oromo Philosophy, Continental Philosophy, Post-colonial African Philosophy, Sage Philosophy, and Post-modernism. His publications include, Metaphilosophy or Methodological Imperialism? (2015); Philosophical Essays (2016); The Oromo Concept of reality: Epistemological Approach (2016); የኢትዮሮፒያንስ የአስተሳሰብ ቅሬ፤ ‹አበበ በሶ በላ› vs ‹ጫላ ጩቤ ጨበጠ› (2017); KANA DUBBIIN (2017); Negritude As The Recovery of Indigenous African Political Leadership፡ The Case of Gadaa Oromo Political Philosophy (2017); Remembering Great African Thinkers (2018). His book titled, African Philosophical Hermeneutics, is forthcomingCurrently he teaches African philosophy at CFIPT. He can be reached at:  kankokunmalimaali@gmail.com

 

 

 

1 Comment

  1. Effort conglomerate and METEC. Messobo Cement factory had been putting/burried low quality standard materials even in some places leaving empty with no material . Also burried by METEC Effort conglomerate are dynamite chemical explosives deep inside the GERD dam all these done by falsifying records , explosives are put so no evidence remains when the GERD dam collapses due to the low quality sometimes no materials the METEC Effort Conglomerate put starting from deep inside the foundation upto the middle part of the dam by breaching the contract they were hired to do , resulting in possible collapse of the entire dam with no evidence remainimg .

    When the collapse happens due to the low quality materials , any of the remaining evidence of the low quality materials are intended to get blown into pieces with the dynamite chemical explosives put burried so no evidence remaining survives to hold the METEC EFFORT CONGLOMERATE liable for the GERD dam collapsing.

    http://www.ginbot7.org/List_of_TPLF_Companies_Under_EFFORT.htm

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.