የምንመኘውን እናገኝ ይሆን?

የምንመኘውን እናገኝ ይሆን?

Dr. Abiy Ahmed is surrounded by the TPLF old guards. Will they give him a chance?

ባይሳ ዋቅ-ወያ, Ebla 12, 2018

የዶ/ር ዓቢይን መሾም አስመልክቶ ብዙዎቻችን የተሰማንን ስሜት ከያቅጣጫው አሰምተን ነበር፣ ዛሬም እያሰማን ነው። የሚሰነዘሩትን አስተያየቶችና የድጋፍ ወይም የተቃውሞ ድምጾችን በሚከተሉት አራት ክፍሎች መድቤያቸዋለሁ። የመጀመርያው ቡድን የዶ/ር ዓቢይን መመረጥ ለኢትዮጵያ ትልቅ እፎይታ ነው፣ ሰላምና መረጋጋትን ብሎም ዲሞክራሲና እኩልነትን ያሰፍንልናል፣ እግዜር እንደ ሙሴ ከምድረ በዳ አውጥቶ ወደ ተስፋዋ ምድር ሊመራን በትሩ ተሰጥቷቸዋል በማለት መቶ በመቶ እምነታቸውን የጣሉባቸው ነው። ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ከዚህ በጣም ተቃራኒ የሆነና ዶ/ር ዓቢይ ሥርዓቱ ኮትኩቶ ያሳደጋቸውና ሥርዓቱ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ላይ ያደርስ የነበረውን ግፍ ከውስጥ ሆነው በዕቅዱም በአፈጻፀሙም ላይ ተካፋይ የነበሩ ግለሰብ ስለሆኑ አንዳችም ዓይነት ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም፣ እንዲያውም ኢህአዴግ አሁን ያጋጠመውን ውጥረት ለማስተንፈስ ለጊዜው መፈናፈኛ እንዲሆን ወያኔ  ሆን ብላ ህዝቡን ለማወናበድ ያደረገችው የፖሊቲካ ጁዶ ነው እንጂ ለህዝቡ አንዳችም ዓይነት ለውጥ ሊመጣ አይችልም ይላሉ። ሶስተኛው ቡድን ደግሞ ክስተቱ በጣም ከመፍጠኑ የተነሳ ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም ግራ ተጋብቶ ሁኔታዎችን በአንክሮ ከመመልከት ሌላ አንዳችም አቋም ለመውሰድ ያልቻለ ነው። የመጨረሻውና አራተኛው ቡድን ደግሞ፣ የኦቦ ለማ ቡድን የሥርዓቱ ምርት መሆናቸው ባይካድም፣ በሰው ልጆች ታሪክ ሁሌም የምንገነዘበው፣ ለውጥ አምጪዎች የሚወለዱት ከዚያው ኮትኩቶ ካሳደጋቸው ሥርዓት እንጂ ከውጭ ስላይደለ፣ ዶ/ር ዓቢይ ፍላጎቱ ካላቸው አብዮታዊም ባይሆን ጥገናዊ ለውጥን ሊያመጡ ይችላሉ ባይ ናቸው። እኔም ራሴን የመደብኩት ከዚህኛው ቡድን ጋር ነው። በተለያዩ ግምቶች ተመርተን የተለያዩ አቋሞች መውሰዳችን ተፈጥሮያዊ ነውና ማንንም ሊያስደንቅ ወይም ሊያናድድ  አይገባም። ታሪክ የራሱን ቦይ ተከትሎ ስለሚሄድ በፖሊቲካ ህይወት ውስጥ ደግሞ ሰዎች በዕውቀትና ልምድ ላይ ተመሥርተው አንዳንድ ሊከሰቱ ይችላሉ የሚሏቸውን ሃሳቦች ከማቅረብና አንድን ክስተት ከመደገፍ ወይም ከመቃወም ባሻገር፣ ለክስተቱ ሂደት አንዳችም ሂሳባዊ ፎርሙላ ለማቅረብ ስለማይቻል፣ ይህኛው ሃሳብ ትክክል ነው ያኛው ግን ትክክል አይደለም ብሎ መፈረጅ ግን ተፈጥሮያዊ አይመስለኝም።

የሥርዓት ለውጥ የሚመጣው አሮጌው ሥርዓት በስብሶ በቦታው አዲስ ዘር መብቀል ሲጀምር ነው።

የህረተሰብ አስተዳደራዊ ሥርዓት ልክ እንደ ማንኛውም የእህል ወይም የአትክልት ዘር፣ የሚበቅለውና የሚያድገው ቀድሞ በተዘራው ወይም በተተከለውና በበሰበሰው ዘር ላይ ብቻ ነው። በየመደብሩ ተቆልለው የምናያቸው የጎጃም ወይም የአድዓ ማኛ ጤፍ እንዲሁም የሃረር ብርቱካንና የአሶሳ ማንጎ፣ አብበውና ለፍሬ የበቁት ቀድሞ የተተከለው ወይም የተዘራው ዘር ከበሰበሰ በኋላና በዚያው ቦታ ላይ በቅለው ለምልመውና አድገው ለምርት በቅተው ነው። የዘመኑን ሰው ሰራሹን የአትክልት ወይም እህል ዘር የመፍጠር ዘዴ (genetically modified) አምላኪዎች ካልሆንን በስተቀር በተፈጥሮ ከዚህ በሳይንስ ዲያሌክቲካዊ ከምንለው የመፈጠር የማደግና የመሞት ሂደት ውጪ የሚከሰት ነገር የለም። ስለዚህም ማንኛውም ዓይነት አዲስ ዘር የሚበቅለው ከአሮጌውና ከበሰበሰው ብቻ ነው። ኦቦ ለማና ዶ/ር ዓቢይን የመሳሰሉ አዳዲስ ብቅሎችም ከዚያ ከበሰበሰው ዘር መውጣታቸውም ተፈጥሮያዊ ነው። ከበሰበሰ ዘር ላይ የሚወጣው አዲሱ ዘር በመሰረቱ አሮጌውን የሚንቅና የሚጠላ ከመሆኑም በላይ ያንን እየበሰበሰና እየከሰመ ያለውን አሮጌውን ዘር እየተጫነው ዳግመኛ እናዳያንሰራራ ስለሚያደርገው፣ በሂደት አሮጌው ዘር እየከሰመና ብሎም ከናካቴው እየጠፋ፣ አዲሱ ብቅል ግን እያደገና እያማረበት ይሄዳል። ይህ ማንም ልክደው የማይችለው ተፈጥሮያዊ ሃቅ ነው። ለከተሜ ወዳጆቼ ካልሆነ በስተቀር ይህ ክስተት ለእኛ ለአርሶ አደር ልጆችማ ዘወትር የምናስተውለው ዕውኔታ ነው።

አዲስ ብቅል በሥነ ሥርዓት አድጎ የተፈለገውን ምርት እንዲሰጥ ከተፈለገ ደግሞ፣ በተፈጥሮ ከሚያገኘው ምግብ ለምሳሌ ያህል ከዝናብና በአፈር ውስጥ ከሚገኙ ንጥረ ነገሮች በተጨማሪ የባለቤቱን በትዕግሥት የተሞላ ጥብቅ ክትትልና እንክብካቤ ይጠይቃል። ከዱር አውሬዎችና ከሌሎችም ለማዳ እንስሳዎች ለመከላከል ይቻል ዘንድ ባለቤቱ የአትክልቱን/የችግኙን ዙርያ በእሾህ ማጠር አለበት። እንደ ሁኔታውም ቀን ቀን ልጆቹን ማማ ላይ ተቀምጠው ከአዕዋፋት እንዲከላከሉለት ወንጭፍ አስታጥቆ ያሰማራቸዋል፣ ማታ ማታ ደግሞ እሱ ራሱ ጎጆው ውስጥ እያደረ ከጀርትና ምጥማጦች ወይም ከቀናተኛ የጎረቤት ሌቦች ተከላክሎ ምርቱ እንዲያድግለት ያልተጓደለ ጥበቃና እንክብካቤ ያደርግለታል። ከዚህ ተፈጥሮያዊ ሂደት ውጭ አቋራጭ የሆነ መንገድ ስለሌለ በትዕግሥት የታገዘን እንክብካቤ አድርጎ የምርን ውጤት እስኪደርስለት ጠብቆ የልፋቱን ዋጋ እያጣጣመ ለሚቀጥለው ዙር ይዘጋጃል። ተቃራኒው ደግሞ ብቅሉን ለጠላት አጋልጦ በመስጠት ፍሬ ሳይሰጥና ለምርትነት ሳይበቃ ማስቀረት ነው። አሮጌው ዘር በስብሶ አዲሱ ብቅል እስኪያብብና ለፍሬ እስኪበቃ ድረስ በትዕግሥት መጠበቁ ያሰሰለቸው ሰነፍ ገበሬ ደግሞ፣ በዘመናዊው ሳይንስ ድጋፍ ያለዘር የሚበቅለውንና ባቋራጭ ለምርት ሊቀርብ የሚችለውን genetically modified እህል ሸምቶ መመገብ ይቻላል። ያ ደግሞ ተፈጥሮያዊ ካለመሆኑም በላይ ከምርቱ ለዘር የሚሆን ማስቀረት ስለማይቻል በያመቱ ሻጮቹ ጋ እየሄድን እነሱ በወሰኑብን ዋጋ መሸመት ስለሚኖርብን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።

ባገራችን ታሪክ ላለፉት መቶ ዓመታት የተከሰቱትን ለውጦች ያመጡት በራሱ የፊውዳሉ ወይም በድህረ ፊውዳሉ ሥርዓት ተኮትኩተው ያደጉ ነበሩ፥ ጃንሆይን ገልብጦ ጥገናዊ ለውጥ ለማምጣት መፈንቅለ መንግሥቱን የመራው ጄኔራል መንግሥቱ የዚያው የበሰበሰው ሥርዓት አባልና ምርት ነበር። ከዚያም በኋላ “መሬት ላራሹ” በማለት የታገሉትና ብሎም ከሳባ አምስት በመቶ በላይ የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከገ(ባ)ርነት ነጻ ያወጣውንና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የዘመኑ አብዮታዊ ለውጥ ተብሎ የተነገረለትን የመሬት ዓዋጅ በተግባር እንዲተረጎም ያደረጉት ከዚያው ከበሰበሰው ሥርዓት የወጡ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶችና ምሁራን ነበሩ። የፊውዳሉን ሥርዓት ለመገርሰስ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ታሪካዊ ሚና የተጫወቱት የደርግ አባላትም የወጡት ከዚያው ከበሰበስው የፊውዳል ሥርዓት ሲሆን፣ የደርግ ሥርዓትም የወደቀው ከዚያው ከበሰበሰው ሥርዓት በበቀሉ ለውጥ ፈላጊ ኃይላት እንጂ ከሌላ ቦታ በውሰት በመጡ ግለሰቦች አይደለም። ስለዚህ የዛሬው ዘመን ለውጥ ፈላጊ የሆነው የነለማ ቡድንም ከዚሁ ከበሰበሰ ሥርዓት መፈጠሩ ፍጹም ዲያሌክቲካዊ ነው ለማለት ነው።

ሥርዓቱ በርግጥ በስብሷል ወይ?

ኢህአዴግ እንደ አንድ ድርጅት መበስበሱን የሚያመላክቱ ብዙ ተጨባጭ ማስረጃዎች ይገኛሉ። በመጀመርያ ደረጃ የሰው ልጅ እጆች እንኳ ሳይገባበት ተፈጥሮ ብቻውን የራሱን ሂደት ተከትሎ በሚያመጣው የትውልድ መሸጋሸግ ምክንያት የሚያመጣው ነባሩን የሚቃረን የአስተሳሰብ ለውጥ አለ። ያኔ በለጋ ዕድሜያቸው የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ብለው ደደቢት የገቡና ወደ ኋላም የኢትዮጵያ መሳፍንት የሆኑት የቀድሞ የህወሃት አባላት የድርጅታቸውን ስም የሙጥኝ ብለው ይዘው ቀሩ እንጂ ዛሬ በአካል የሉም፣ ቢኖሩም የነበራቸው የተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ኃይል በጣም ቀንሷል። አዲሱ ትውልድ የህወሃት አባልም እንዳንጋፋዎቹ ጠብመንጃ ነካሽ ያልነበረና ከየመንደሩ የተሰባሰበ፣ በሌሎች አዳዲስ የኢህአዴግ አባላትም ላይ አንዳችም ዓይነት ተጽዕኖ ሊያሳድር የማይችልና፣ ሁሉም በእኩልነት የሚያዩት አባል ነው። በዚህም ምክንያት ወጣቶቹ የኢህአዴግ አባላት ለምሳሌ የነለማ ቡድን ሌሎቹን የህወሃት አባላትን የሚያዩት፣ ቢበዛ በእኩልነት አለበለዚያም በንቀት ነው። በመሆኑም በዓደባባይ ከመዳፈር አልፈው በየስብሰባውም በግልጽ መገዳደርን ጨምሮ፣ ውሳኔ በሚተላለፍበትም ጊዜ የፓርቲውን የዘመናት ዲሞክራሲያዊ ማዕከልነትን ባህልና አሰራር ዳግመኛ እንዳይንሰራራ ገርስሰውታል። የፓርላማው አባላትም በኢህአዴግ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ “ተገዥነታችን ለህገ መንግሥቱና ለመረጠን ህዝብ ነው” በማለት የኢህአዴግን አመራር ውሳኔ በግልጽ መቃወም ጀመረዋል። ላንድ የጠ/ሚር ቦታም እንደወትሮው በህወሃት ታማኝ ግለሰቦችን መሾሙ ቀረና የተለያዩ ግለሰቦች ተወዳድረው አንደኛው ሲያሸንፍ ኢህአዴግንም ለሁለት ከፍሎ ነበር። ሙስና ባገሪቷ ከዳር እስከዳር ሰፍኖ እንኳን ገንዘቡን አፍስሶ ንግድ የጀመረውን ዜጋ ይቅርና በዓመት አንድ ቀን ብቻ ግብርና የማዳበርያ ዕዳውን ሊከፍል ወደ ፍ/ቤት የሚሄደውን ደሃውን ህዝብ አንገሽግሾታል። ያገሪቷ ሃብት በጥቂቶች እጅ መጠቃለሉና ለተማረው ወጣት የሥራ ዕድል አለመገኘቱ የህዝቡን በኢህአዴግ ላይ ያለውን የለውጥ ተስፋ አሟጦታል። ኢህአዴግም የመልካም አስተዳደርንና የህዝቡን የመብት ጥያቄ ለመመለስ ሳልችል ቀርቼ ለተከሰተው የህዝብና የንብረት መጥፋት ተጠያቂ ነኝ ብሎ ይቅርታ ጠይቋል። ባጠቃላይ፣ ኢህአዴግ እንደ አንድ መንግሥት ህዝቡና ማስተዳደር የማይችልና ለህዝቡም የመብት ጥያቄ ተገቢ መልስ ሊሰጥ የማይችል የበሰበሰ ዘር ስለሆነ፣ ከዚያው ከበሰበሰው አካል አዲስ ብቅል መውጣቱ ተፈጥሮያዊ ነው።

አዲሱ ብቅል ለውጥን ሥራ ላይ የማዋሉ ፍላጎትና አቅም አለው ወይ?

በኔ ግምት ችግሩ ያለው በኢህአዴግ መበስበስ ላይ ሳይሆን፣ የተፈጥሮ ሂደትን ተከትለው ከዚህ ከበሰበሰ ሥርዓት ብቅ ብቅ ያሉ አዲስ ብቅሎች፣ ለምልመው አድገው ጠንክረው የህዝቡን የመብት የሰላምና የዲሞክራሲን ጥያቄ ሊመልሱና ባገሪቷ ሰላምና መረጋጋትን ብሎም ማንም ማንንም የማይበድልባትን ዲሞክራሲያዊቷን ኢትዮጵያን ለመገንባት አስተማማኝ መሰረት ለመጣል ዝግጁ ናቸው ወይ የሚለው ላይ ነው። በበኩሌ መቶ በመቶ ሥራ ላይ ያውላሉ ብዬ የምሞግትበት ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ሳይኖረኝ እንደሁ ከልምድ ተነስቼ፣ እነዚህ አዲስ ብቅሎች አንዳንድ ውስጣዊና ውጫዊ እክሎች ካላስተጓጎሏቸው በስተቀር የህዝቡን ጥያቄ እስከተወሰነ ድረስ ለመመለስ ፍላጎቱ አላቸው ባይ ነኝ።

ኢህአዴግ እንደ ድርጅት በስብሷል ስል ከናካቴው ሞቷል ወይም መንቀሳቀስ አይችልም ማለቴ እንዳልሆነ አንባቢዎች የሚረዱት ይመስለኛል። ለሩብ ምዕተ ዓመት ያስተዳደርና የመጨቆኛ መዋቅሩን ባገሪቷ ከዳር እስከዳር ያንሰራፋውን መንግሥት እንደው በቀላሉ እንደ አሸዋ ካብ ይፈርሳል ብሎ ማሰብ የህብረተሰብን አስተዳደር ሥርዓት በቅጡ አለመረዳት ነው። ህወሃት የመከላከያውንና የደህንነቱን እንዲሁም የኤኮኖሚ የበላይነቱን በደንብ ያደላደለ በመሆኑ ዛሬ ብቅ ብቅ ያሉት ለጋ ብቅሎች ይህንን ሥር የሰደደን ያገዛዝ ሥርዓት በቀላሉ ገርስሰው ባገሪቷ እኩልነት ሰላምና ዲሞክራሲን ያለችግር ያሰፍናሉ ብሎ መጠበቅ፣ ለችግራችን ቅጽበታዊ መፍትሄ ከመመኘት የተነሳ እንጂ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት፣ ሊሆን እንደማይችል እያወቅን ራሳችንን በተስፋ መደለል ይመስለኛል።

ችግሩ ያለው በኦቦ ለማ ቡድን ለውጥን ለማምጣት ባላቸው ፍላጎት ላይ ሳይሆን ፍላጎታቸውን በተግባር ለመተርጎም ባላቸው አቅም ላይ ይመስለኛል። በኔ ግምት እነዚህ አዲስ ብቅሎች የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ፍላጎቱ እንዳላቸው አንዳችም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም። ለለውጥ ያላቸውን ፍላጎት የሚያመላክቱ ብዙ ብዙ ሥራዎቻቸውን መጥቀስ ቢቻልም የኦቦ ለማ የፖሊቲካ ሥልጣን ወንበሩን ማለትም የድርጅታቸውን ፕሬዚዴንትነት ቦታቸውን ለዶ/ር ዓቢይ ሰጥተው ለጠ/ሚር ቦታ ዕጩ እንዲሆኑ ማቅረባቸው ከግል ሥልጣን የላቀ አገራዊ አጄንዳ እንዳለ የሚጠቁምና ለዚያም አገራዊ አጄንዳ በጋራ መቆማቸውን የሚያሳይ ባገራችን የፖሊቲካ ታሪክ ተደርጎም ተሰምቶም የማይታወቅ ጀግንነት ይመስለኛል። ዋናው ስጋቴ ግን ያሰቡትንና በዓደባባይ ከኢህአዴግ ጋር ፍልሚያ ገጥመው ያሸነፉበትን ለለውጥ ያላቸውን ህልም ዕውን ለማድረግ አቅሙ አላቸው ወይ ነው። አዎ እነዚህ አዲስ ብቅሎች እንዳንጋፋዎቹ ከጫካ  ያልመጡ፣ ተዋግተው ኢትዮጵያዊውን ያልገደሉ፣ የማረኩ ወይም ያልተማረኩ፣ ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላም በቢሮክራሲው ውስጥ ከማገልገል ባሻገር ተቃዋሚ ናቸው የሚሏቸውን ዜጎችን ያልገደሉ ወይም ያላስገደሉና ያላግባብ ሃብትን ያላካበቱ በመሆናቸው የበላያቸውን ህወሃትን መዳፈር ብሎም ያላንዳች የህወሃት ድጋፍ ተወዳድሮ ማሸነፍና ጠ/ሚር መሆን የሥልጣን ሳይሆን የሞራል የበላይነትን ያጎናጸፋቸው ይመስለኛል።

ግን ለውጥን ለማምጣት ደግሞ የሞራል የበላይነትና የለውጥ ፈላጊውን ህዝብ ጊዜያዊ ድጋፍ ማግኘት ብቻ በቂ አይመስለኝም። ህዝብ በተፈጥሮው ለለውጥ ትእግሥት የለውም። በተለይም ለዘመናት ህገ መንግሥታዊ መብቶቹ ተጥሰውበት፣ መልካም አስተዳደርን ለተነፈገና ከሁሉም በላይ ለለውጥ ብሎ የራሱን የጓደኞቹንና የጎረቤቶቹን ህይወት የሰዋን ወጣት የዲሞክራሲን ጥማት በቀላሉና ባጭር ጊዜ ውስጥ ማርካት ስለማይቻል፣ ለዚህ ላዲሱ ብቅል የመጀመርያው ተግዳሮት ይህንን የወጣቱን ክፍል ጥያቄ ባስቸኳይ መመለስ ይሆናል። ይህ ራሱን የቻለ የራስ ምታት ሲሆን ሌላም ከዚህ ያላነሰ ከዚያው ከበሰበሰው የኢህአዴግ ውስጥ የሚመነጭ የችግር ነዶ አለ። ህወሃት እንደማንኛውም ገዥ መደብ የፖሊቲካ ሥልጣኑንና የበላይነቱን በፈቃዱ ለመልቀቅ አይፈልግም። ከሥልጣን ወንበሩ ጋር የተያያዙ ለምሳሌ በኤኮኖሚ የበላይነቱም ስላለ ያንን ለዓመታት ”ተዋግተውበትና ሞተውበት ያገኙትን የሥልጣን ወንበር” እና ወንበሩንም ተጠቅመው “ለፍተውበት ያካበቱትን” ሃብት ለአዲሱ ብቅሎች በቀላሉ ትተው ያላንዳች ትግል በፈቃዳቸው ይሰናበታሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ስለዚህም ለነዚህ አዲስ ብቅሎች ፈታኙ ተቃውሞና መሰናክል የሚመጣው ከህወሃትና ህወሃት በየቦታው ከተከላቸው አውታሮቹ ይሆናል።  የነዚህን ሁለት ዓቢይ ጉዳዮችን ማለትም የህዝቡን በአስቸኳይ ለውጥ መፈለግና የህወሃትን የበላይነቱን ቦታ ላለመልቀቅ የሚያደርገውን ትግል ለማፋፋምና የለውጥ ፈላጊውን ብቅል ዓላማ ለማክሸፍ፣ ህወሃት ህዝቡን ለዓመጽ አነሳስቶ የነፍሳት መጥፋትንና የንብረት መውደምን የሚያስከትሉ ግጭቶችን በየቦታው የመፍጠር ችሎታው ሌላው ተጨማሪ መሰናክል ይመስለኛል። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን አዲሱ ብቅል፣ ለለውጥ ያላቸው ፍላጎት እንደተጠበቀ ሆኖ እነዚህን ከላይ የጠቀስኳቸውን መሰናክሎች አስወግደው ፈታኝና ረጅም ጊዜ የሚጠይቀውን የለውጥ ጉዞ መቀጠል ይቻላሉ የሚል ግምት አለኝ።

በፖሊቲካ አመራር ደረጃ፣ ከላይ እንዳልኩት የዲሞክራሲያዊ ማዕከልነት መሪህ ስለፈረሰ ህወሃት እንደ “መሪ ድርጅት” ካሁን በኋላ በተለምዶ ራሱ አርቅቆ የሚያቀርባቸውን ውሳኔዎች ያላንዳች ተቃውሞ በሶስቱ የኢህአዴግ “ተመሪ” አባላት ሊያስጸድቅ የሚችልበት ጉልበት ቀስ በቀስ እየሸሸው ነው። ካሁን በኋላ፣ የብአዴንና የኦህዴድ ትብብር እስቀጠለ ድረስ፣ ህወሃት በኢህአዴግ ውስጥ ሊኖረው የሚችለው ሚና ”የእኩልነት” እንጂ “የመሪነት” ሊሆን አይችልም። ህወሃት የማዘዝ ጉልበቱ ከከዳውና የእኩልነት መብቱም በሌሎች ጸረ እሱ በሆኑት የድርጅቱ አባላት ትብብር ወደ አናሳነት ዝቅ የሚያደርገው ስለሆነ አዲሶቹ ብቅሎች የለውጥ ዕቅዳቸውን በሥራ ላይ ለማዋል ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል የሚል ግምት አለኝ።

ይህንን የታሪክ አጋጣሚ በመጠቀም አዲሶቹ ብቅሎች፣ ህወሃት በበላይነት ሲመራው የነበረውን የኢህአዴግ የአሰራር ልምድ ወደ ጎን በመተውና ህገ መንግሥቱን ብቻ መመርያ በማድረግ፣ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስና ብሎም ከህዝቡ ጋር ተስማምቶ የወደፊቷን የዲሞክራሲያዊቷን ኢትዮጵያን ግንባታ መሰረት ለመጣል የሚችሉ ይመስለኛል። ለምሳሌም ያህል ዶ/ር ዓቢይ የተለምዶውን የኢህአዴግን ውስጣዊ አሰራር ትተው ህገ መንግሥቱን ብቻ በመጠቀም፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለአገሪቷ ቀውስ ተጠያቂ ናቸው የሚባሉትን የሲቪልና የመከላከያ እንዲሁም የደህንነት አካሉን የበላይ አመራር ከሥልጣን አሰናብተው፣ ለለውጥ ጉጉና ብቁ በሆኑ በአዲስ ብቅል አባላት መተካት ይችላሉ። የምርጫ ኮሚሽኑን አፍርሰው ሁሉን ዓቀፍ በሆነና አዳዲስ የለውጥ ደጋፊዎችን ባቀፈ አባላት መተካትና አዲስ የምርጫ ህግ ረቂቅ አዘጋጅተው ለፓርላማው አቅርበው ሊያስጸደቁ ይችላሉ። ተፎካካሪ ኃይላትን በሽብርተኝነት የፈረጀውን የጸረ ሽብር ዓዋጅን አሻሽለውና ምርጫው የሚካሄድበትንም ቀን ወስነው፣ ባገር ቤትም ሆነ  በውጭ አገር የሚገኙ ተፎካካሪ ኃይላት በሰላም ወዳገራቸው ተመልሰው በእኩልነት በተደላደለላቸው የመፎካከርያ ሜዳ ላይ እንዲወዳደሩ ለመጋበዝ ይችላሉ። ያላንዳች ጥፋት፣ ህገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው በመጠየቃቸው ብቻ በየወህኒ ቤቱ ታጉረው ያሉትን የፖሊቲካ እስረኞችን በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊፈቷቸው ይችላሉ። ይህ እንግዲህ ለለውጥ ያላቸውን ፍላጎትና ለውጡንም በተግባር ለመተርጎም የሚያስችል አዎንታዊ ሁኔታም አለ የሚለውን አቋሜን ለማጠናከር ያህል ነው። ሥራ ላይ ያውሉት አያውሉት በርግጠኝነት ለመናገር ባልችልም፣ “ሊፈጽሙ ይችላሉ” የሚለው ሃሳብ ሚዛን ደፍቶ ስለሚታየኝ ሂሳዊ ድጋፍ እሰጣቸዋለሁ።

መደምደሚያ

ይህንን ጽሁፍ ከመደምደሜ በፊት ሶስት ነገሮችን ላነሳ እሻለሁ። የመጀመርያው፣ የኛ በተለይም በውጭ አገር የምንኖር በተለምዶ “ተቃዋሚ” የምንባል ኃይሎችን የሚመለከት ነው። በኔ ግምት ይህ በኔ ዕድሜ ክልል ውስጥ የምንገኝ፣ ባገሪቷ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለዘመናት “እየመራነው ነው” እያልን የተማመንበትን “የመሪነቱን” ሚና የተነጠቅን ይመስለኛል። የታሪክ ሂደት ሆኖ ህዝቡ ከራሱ መሃል የራሱን መሪዎች እየፈጠረ ነው። መርተው ለድል ያብቁ አያበቁ ወይም አመራራቸው ዘላቂነት ይኑረው አይኑረው በትክክል ለመናገር ባልችልም፣ ለጊዜው ግን ያላንዳች የውጭ እርዳታ ትግሉን እየመሩ ነው። በኔ ግምት፥ እኛ ውጭ ያለነው “ተቃዋሚ ኃይላት” እንኳን ትግሉን ለመምራት ይቅርና ሂደቱን ለመከታተልም ሆነ አገር በቀል መሪዎቹንም “ለመከተል” ያቃተን ይመስለኛል። አምባገነን መሪዎች የህዝብ ድጋፍ እየቀነሰና ጉልበት እየከዳቸው መሆኑን ላለመቀበል፣ ሁሌም “ህዝቡ ከኛ ጋር ነው” “ህዝቡ ይወደናል ያከብረናል” “አመራሩ በኛ እጅ ነው” እያሉ አንድ ቀን ባልታሰበ መንገድ ሲወድቁ እናይ እንደነበረው ሁሉ፣ እኛም እዚህ ውጭ አገር የምንገኝ ተቃዋሚ ኃይላት ዓይናችንና አዕምሮአችን ከፍተን፣ በርግጥም የትግሉን አመራር አገር በቀል ኃይላት እንደተረከቡት አምኖ መቀበልና ለነዚህ አገር በቀል የትግል መሪዎች ድጋፋችንን ለመስጠት ካልቻልን ታሪክ ሰሪዎች ሳንሆን ታሪክ ሆነን የምንቀር ይመስለኛል። ያም ማለት ግን ከትግል ሜዳ ጠቅልለን እንውጣ ለማለት ሳይሆን፣ “እንመራዋለን” ማለቱን ትተን፣ በተማርነው፣ ባካበትነው ልምድና፣ በሰለጠንንበት ሙያ በመሰማራት ያገር ቤቱን እንቅስቃሴ የሚደጉም ሥራ እንሥራ ማለቴ ነው። ከመሃላችን ላለፉት ሰላሳና አርባ ዓመታት የግል ኑሮአቸውን፣ ምቾታቸውንና ቤተሰባቸውን ሳይቀር ለሰፊው ህዝብ ትግል ሲሉ ሰውተው ትግሉን ይመሩ ስለነበር፣ ዛሬ ላይ ሆኜ ዕድሜ ልካቸውን የለፉበትንና ውድ ዋጋ የከፈሉበትን ትግል እርግፍ አርጋችሁ ተውት ማለቴ እንዳልሆነ ይገባቸዋል ብዬ እገምታለሁ። ታሪክ የራሱን ቦይ ተከትሎ ሄዶ፣ እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ዓመጽ የራሱን መሪዎች ከራሱ መሃል እየፈጠረ ነውና ይህንን እውኔታ ተቀብለን፣ ስንታገልለት የነበረውን ህዝብ ለድል እንዲያበቁ የእነዚህን አዲስ ትውልድ አመራር ተቀብለን አስፈላጊውን ድጋፍ እንስጣቸው ማለቴ ነው።

ሁለተኛው ነጥብ ከዚሁ ከመጀመርያው ጋር ተያያዥ የሆነ ይሄ ማለቂያ የሌለው ሁሉንም የመቃወም ባህላችን ነው። በኔ ግምት የነለማ ቡድን የራሳቸውን ድርጅት የኢህአዴግን የመምራት ብቃት ጉድለት ነቅተውበት ለለውጥ መሰለፋቸው ቢያንስ ቢያንስ ሂሳዊ ድጋፍ ያሰጣቸዋል እንጂ እንደው በደፈናው “ካሮጌው ሥርዓት የበቀሉ ስለሆኑ አንዳችም ዓይነት ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም” ብሎ በጭፍን ድጋፍን መንፈግ ትክክል አይመስለኝም። በትክክለኝነት መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ብዬ ለመሞገት ባልችልም፣ ዛሬ ባገራችን የሰፈነውን ውጥረት በትንሹም ቢሆን ማርገብ ከቻሉ፣ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠን ለምን ሂሳዊ ድጋፍ እንደማንሰጣቸው አይገባኝም። ማዕከላዊን ሲዘጉ የምናመሰግንበት፣ በማዕከላዊ ውስጥ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ዜጎችን ሲያሰቃዩ የነበሩትን አሰቃዮችን ግን ለፍርድ ሳያቀርቡ ሲቀሩ የምናወግዝበት፣ ከተፎካካሪ ኃይላት ጋር ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ አብረን ለመሥራት ዝግጁ ነን ሲሉ የምንደግፍበትና፣ ተፎካካሪ ኃይላት በነጻነት እንዳይወዳደሩ የሚያደርገውን የጸረ ሽብር ዓዋጅ ግን ካለነሱ የምናወግዝበት ከሂሳዊ ድጋፍ የተሻለ ፍቱን መሳርያ ያለ አይመስለኝም። “ኢህአዴግ መወገድ አለበት” እያልን በሞቀ ሶፋችን ላይ ሆነን ከመፎከር ባሻገር፣ ኢህአዴግ እንዴት እንደሚወድቅና ማን እንደሚጥለው ተጨባጭ የሆነ ሁኔታ በግልጽ ሳናስቀምጥ፣ ዝም ብለን መፈክር ስላሰማንና ስላስፈራራነው ብቻ ኢህአዴግ እንደ አየር ተንኖ የሚጠፋ ይመስል የተገኘውን ሁሉ ከመንቀፍ ፣ ያገኘነውን በጃችን አስገብተን ለሚቀረው ደግሞ ብንታገል የተሻለ ይመስለኛል።

ሶስተኛው ነጥቤ ደግሞ ካሁን በፊት ያለመታከት ሳስተጋባቸው የነበረውን “ከወያኔ ጋር ሥልጣንን በዕኩልነት ለመጋራት መደራደር አለብን” የሚለውና “የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት” የሚሉትን በወቅቱ ዓቢይ ጉዳዮች አድርጌ ስሰብክ የነበረውን ነው። ዛሬ በኢህአዴግ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለውን ድርጅታዊ ቀውስ ሳጤንና፣ ሀ) ወያኔም የነበረውን የበላይነትና ብሎም እንደ አንድ ወሳኝ የሆነ ተደራዳሪ የመሆን ኃይሉን ቀስ በቀስ እያጣ መሄዱን ስገነዘብ፣ ዛሬ እንኳን ስለኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሊደራደር ይቅርና ለራሱም ህልውና እየታገለ ስለሆነ፣ ለ) ኢህአዴግ እንደ አንድ አካል ሳይሆን በተግባር ለሁለት ስለተሰነጠቀ አንዱ ወገን አሸንፎ ወይም ድርጅቱ በአዲስ መልክ እንደ አንድ አካል ካልተደራጀ በስተቀር ለድርድር የማይመች በመሆኑና፣ ሐ) ድርጅቱ ከተሰነጠቀ በኋላ ወጣ ወጣ ያሉት ብቅሎች የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ለምሳሌ ሁሉን አቀፍ ምርጫ ለማድረግ ከወሰኑና ተፎካካሪዎችን ከጋበዙ፣ በጣም ውስብስብ የሆነውን የሽግግር መንግሥትን ለመፍጠር ከወያኔ/ኢህአዴግ ጋር መደራደር ለጊዜው አስፈላጊነቱ አይታየኝም። የፖሊቲካ ሂደትን እንኳን ለኛ ከዳር ቆመን ለምንገመግመው ቀርቶ ለራሳቸው ለአሽከርካሪዎችም ቢሆን ባልታሰበበት ቀን ወዳልታሰበ አቅጣጫ ሊሄድና ግራ ሊያጋባ የሚችል የተፈጥሮ ክስተተ በመሆኑ፣ ትናንት በነበረው ሁኔታ ላይ ተመርኩዤ ከወያኔ/ኢህአዴግ ጋር መደራደርን ያራመድኩትን ያህል፣ ዛሬ ደግሞ በነባራዊው ሁኔታ ተመርቼ መደራደር አያስፈልግም ብል፣ ነገ ደግሞ ሁኔታዎች ሲለወጡ፣ እንደራደር ወደሚለው አልመለስበትም ማለት አይደለም። በኔ እምነት፣ በፖሊቲካ ህይወት ውስጥ ቋሚ መሪህ እንጂ ቋሚ ታክቲክና ቋሚ ጠላት የለም። የፖሊቲካ ጥበብና ውብቱም ደግሞ እዚይ ላይ ይመስለኛል።

 

ጄኔቫ፣ 10 April 2018

Wakwoya2016@gmail.com

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.