የራስ ማንነት ቅድምያ ማግኘት አለበትና ኦሮሙማ ይቅደም!

የራስ ማንነት ቅድምያ ማግኘት አለበትና ኦሮሙማ ይቅደም!

ብርሃኑ ሁንዴ, Waxabajjii 6, 2020

ኦሮሙማ

ብዙ ጊዜ በአእምሮዬ የሚመላለስ አንድ ነገር ስላለ፣ እስቲ ዛሬ በዚህ ርዕስ ይህንን ጉዳይ ማንሳት እፈልጋለሁ። በቅድሚያ ሌሎች የማንነት መገለጫዎች ብኖሩም፣ ማንነት ወይም በእንግሊዝኛ identity የሚባለው በሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎች (main pillars) ላይ የተመሰረተ ነው።  እነዚህ ሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ናቸው። የየትኛውም ብሔር ወይም ብሔረሰብ ማንነት በነዚህ ሶስት ነገሮች ይገለፃል። የኦሮሞ ሕዝብም እንደ ብሔር ሶስት ምሰሶዎችን የያዘ አንድ ማንነት አለው። እሱም ኦሮሙማ (Oromummaa) ነው። የኦሮሙማ ሶስት ዋና ዋና ምሳሶዎች የኦሮሞ ቋንቋ ወይም ኦሮምኛ (Afaan Oromoo)፣ የኦሮሞ ባህል (Aadaa Oromoo) እና የኦሮሞ ታሪክ (Seenaa Oromoo) ናቸው። ማነንት በፍፁም መቀየር ወይም መለወጥ የማይችል ነገር ነው። አንድ ሰው የተፈጠረበትን ማንነት ፍቆ ሌላ መሆን አይችልም። ማንነት እንደ ቆሻሻ በሳሙና የሚታጠብ ወይም እንደ ልብስ አውልቀው የምያስቀምጡት ወይንም የምቀይሩት አይደለም። ይህ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ታሪክ በትምህርት ቤት የሚማሩት ጉዳይ ቢሆንም ቋንቋና ባህል ግን ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ አብሮ የምኖሩበትና አብሮ የምያድጉበት ጉዳዮች ናቸው። ቋንቋና ባህል እንደ ራስ አካል ናቸው ማለት ይቻላል። የራስ አካል ደግሞ ብጠሉትም እንኳን ወደ ጎን የሚተው አይደለም።

ይህን ካልኩኝ በኋላ ወደ ርዕሱ ልመለስና፣ ይህንን ጉዳይ እንዳነሳ ያደረገኝ ነገር የኦሮምኛ ቋንቋ ነው። እንደሚታወቀው ወደንም ይሁን በግድ፤ ስርዓቱ በኛ ላይ ጭኖም ይሁን በሌላ ምክንያት፣ የአማርኛን ቋንቋ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ተምረናል። ከነበረውም የስርዓት ተፅእኖ የተነሳ ይህንን ቋንቋ መናገር ወይም መፃፍ እንደ ዘመናዊነት ሲታይ ነበር፣ ዛሬም ይህ ጉዳይ ባንዳንድ ቦታዎችና ባንዳንድ ኦሮሞዎች ዘንድ እንደዚሁ እየታየ ነው። ለምን ግን? የአማርኛን ቋንቋ ልዩ ያደረገው ምንድነው? የዓለም ቋንቋና የቴክኖሎጂ ቋንቋ የሆነውን እንግሊዝኛን መቻል ራሱ እንደ ልዩ ነገር የሚታይ አይደለም። የትኛውም ቋንቋ መግባቢያ በመሆኑ፣ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ አንድን የሚያግባባ ቋንቋ መጠቀም ሀጥዓት አይደለም። ነገር ግን ባንዳንድ ኦሮሞዎች ወይም የኦሮሞ ቤተሰቦች ዘንድ የሚታየው የራሳቸው የሆነ የማንነታቸው መገለጫ ኦሮምኛ እያለ ይህንን ወደ ጎን በመተው አማርኛን ስጠቀሙ ወይም ይባስ ብሎ ሁለቱን ቀላቅለው ስናገሩ ይሰማል። ለምን? አማርኛን ትተን ኦሮምኛ ብቻ ከተጠቀምን አማርኛ ያኮርፈናል ብለው አስበው ይሆን? አማርኛ ይረሳል ብለው ሰግተውስ ይሆን? የተለያየ ቋንቋ መቻል የቋንቋን እውቀት (language skills) ያዳብራል እንጂ ሌላ ቋንቋ መጠቀም ጉዳት የለውም። ያራስን ማስቀደም ማለት የሌላውን መጥላት እንዳልሆነም መገንዘብ ያስፈልጋል።

ይሁን እንጂ አንድ መረሳት የሌለበት ጉዳይ በኦሮምኛና አማርኛ መካካል ያለው ግንኙነት (relationship) የሚፃረር ነው። ያንዱ ማደግ ሌላኛውን የሚገፋ ጉዳይ ተደርጎ ነው የሚታየው። በመሰረቱ ይህ አስተሳሰብ የሚታየው በአማሮች ዘንድ ነው። የኦሮምኛን ቋንቋ እድገት ለአማርኛ መቅሰም እንደሆነ አድርገው ነው የምመለከቱት። የኦሮምኛ ማደግ ለአማርኛ እድገት እንቅፋት ሆኖ ሳይሆን፣ እንዲህ የምሉት ወይም የምያስቡት ራሱ ኦሮምኛ አንዳያድግ ስለፈለጉ ነው። የራሳቸውን ማንነት በሌላው ላይ ለመጫንና የአማርኛን የበላይነት ስለምፈልጉ ነው። ባጭሩ ፖለቲካዊ ዓላማ በስተጀርባ አለ ማለት ነው።  ታዲያ የራሳችን የማንነት መገለጫ የሆነውን ኦሮምኛ ወደ ጎን ትተን ለአማርኛ ቅድሚያ የምንሰጠው ይህ የአማሮች የፖለቲካ ዓላማ እንዲሳካ አጋር መሆናችን ነው? ወይስ በይፋ የማይገለፅ ለራሳችን ቋንቋ ንቀት ስላለን ነው? ወይንስ ልምድ ሆኖብን ነው? እዚህ ላይ አንባቢዎች መገንዘብ ያለባቸው ስለ አማርኛ ቋንቋ ጥላቻ ሳይሆን በሌሎችም አገሮች ለምሳሌ እንደ ጀርመን ያሉ አገሮች ምን ያህል ለራሳቸው ቋንቋ ፍቅርና ክብር እንዳላቸው ባይኔ ያየሁትና በጆሮዬ የሰማሁት ነው። ጀርመኖች ወይም የጀርመን ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው ያራሳቸው የሆነ ያጋራ ቋንቋ ጀርመንኛ (Deutsch) እያለ ይህንን ወደ ጎን ትተው ሌላ ቋንቋ ስጠቀሙ አይታዩም።

በርግጥ አንድ ኦሮምኛ የማይችል ሰው ቁጭ ብሎ እያለ በኦሮምኛ መነጋገር ተገቢ ላይሆን ይችላል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ አንድ የጋራ የሆነ ቋንቋን መጠቀም የግድ ይሆናል። በመሰረቱ ይህ ማንኛውንም ቋንቋ ይመለከታል። የምገርመው ነገር ግን ሁሉም የምችሉት የጋራ የሆነ ይኸውም የማንነት ምልክት የሆነ የራስ ቋንቋ እያለ ይህንን ወደ ጎን ትተው በሌላ መጠቀም ወይንም ይባስ ብሎ መቀላቀል ትርጉሙ ምንድነው? ይህ ነው የማይገባኝ። የራስን ነገር ካልወደዱ፣ የረስን ነገ ካላከበሩ ሌላ አካል እንዲያከብር ነው? ወይንስ ዛሬም እንደ ድሮው እያፈርንበት ነው? የዚህ ዓይነት ድርጊት የሚታይባቸው ሰዎች ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። ይህ የማንነት ጉዳይ ወይም ጥያቄ ከተነሳ፣ ባንዳንድ ኦሮሞዎች ዘንድ የሚታየው ሌላኛው ጉዳይ ራስን መሆን አለመቻል ወይም አለመፈለግ ነው። ኦሮሞ መሆናቸውን እንኳን ለመደበቅ የምፈልጉና የአማራ ሰም ስላላቸው ብቻ አማራ የመምሰል ባሕርይ የሚታይባቸው ጥቂት አይደሉም። አልፈውም እኔ ወይም እኛ የአማራ ዘር አለብኝ/አለብን ብለው በዚህም እንደመኩራራት የምሞክሩም አሉ። የዚህ ዓይነት ባሕርይ የሚታይባቸው ኦሮሞዎች ውሎአቸው ከሀበሾች ጋር የሆነ ወይም በጋብቻም ሆነ በሃይማኖት ከሀበሾች ጋር ትስስር ያላቸው ናቸው።

በመሰረቱ አንድ ሰው ከፈለገው ማህበረ ሰብ ጋር የመዋል፤ የወደደውን ግለሰብ የማግባት፤ የፈለገውን ሃይማኖት የመከተልና በዚህም የተነሳ ይህንን እምነት ከሚከተሉት ሰዎች ጋር የቅርብ ትስስር የማድረግ ተፈጥሯዊ ሙሉ መብት አለው። ይህን እንጂ ይህንን እንደ ምክንያት በመጠቀም የራሱን ማንነት መርሳት የለበትም። አንድ ኦሮሞ ማንነቱን ቢጠላም፣ ወደደም ጠላም ኦሮሞ ሆኖ ነው የተወለደው፣ ኦሮሞ ሆኖ ነው የሚኖረው፣ ሲሞትም ኦሮሞ ሆኖ ነው የሚቀበረው። አለቀ በቃ። ይህ የተፈጥሮ ሕግ ነውና። ሌላው ባንዳንድ ኦሮሞዎች ዘንድ የሚታየው ደግሞ አሁንም ከቋንቋ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ በአማርኛ የተሰሩትን ፊልሞችና ዘፈኖች ልክ በዚህች ዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ እጅግ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የሌላቸው አድርገው ስያቀርቡና በኦሮምኛ ቋንቋ የሚሰሩትን ስንቁ ነው። እውነት ነው የኦሮምኛንና የአማርኛን የእድገት ደረጃ አወዳድረን ካየን እጅግ የተራራቀ እንደሆነ የማይካድ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያቶች ደግሞ ብዙ በመሆናቸው ይህንን ሁሉ እዚህ ለመዘርዘር ፅሁፉን በጣም ያረዝመዋልና ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። መረሳት የሌለበት አንድ ትልቅ ጉዳይ ግን አማርኛን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት እጅግ ትልቅ ሲሆን፤ ኦሮሞኛ ግን ባለቤትም ያጣበት ሁኔታ ውስጥ ስለሆነ፣ ይህንን ቋንቋ ለማሳደግ የሚደረግ ጥረት አይታይም።

ፅሁፌን ላማጠቃለል፣ ለኦሮሞዎች በተለይም ደግሞ ለማነንታቸው ትኩረት ለማይሰጡት ኦሮሞዎች ማስተላለፍ የምፈልገው ወንድማዊ መልዕክት የራስ ማንነት ቅድምያ ማግኘት አለበትና እባከችሁ ራሳችሁን ለመሆን ሞክሩ፤ ለማንነታችሁ ቅድሚያ ስጡ፤ የራሳችሁን ነገር ውደዱ፣ አክብሩ፤ ኦሮምኛም ከሆነ ይህ ቋንቋ በሚያድግበት መንገድ ላይ የራሳችሁን ድርሻ ለመወጣት ሞክሩ እንጂ ከሌላው በተለይም ከአማርኛ ጋር በማወዳደር ይህ ቋንቋ እድገቱ ዝቅተኛ እንደሆነ በማስመሰል በባዕድም እንዲናቅ መንገድ አታሳዩ፣ በር አትክፈቱ። በስተመጨረሻ ማለት የምፈልገው፣ ምናልባትም ለአማርኛ ቅድሚያ አትስጡ አያልክ ለራስህ ግን ለምን በዚህ ቋንቋ ትፅፋለህ ትሉኝ ይሆናል። መልሴ ግን ከቋንቋው ፍቅር ይዞኝ ወይንም የራሳችን ቆንጆ ቋንቋ ኦሮምኛ ወደ ጎን ትቼ ሳይሆን፣ ይህንን መልዕክት በአማርኛ ማስተላለፍ አስፈላጊ ስለሆነ ነው። እንደኛ፣ እነዚህ ጉዳይ የሚመለከታቸው ኦሮሞዎች ምናልባትም በቁቤ ብፅፍ ላያነቡም ስለምችሉ ሲሆን፣ ሁለተኛ ኦሮምኛን ማንበብ የማይችሉት ነገር ግን በኦሮሙማ የበለፀጉ ውድና ቆራጥ ኦሮሞዎች ስላሉ ይህ መልዕክት እነሱም ጋ እንዲደርስ ነው።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ ቸር እንሰንብት

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.