“የብልጽግና” (ኢህአዴግ ቁ. 2) መሪ የሚሉትንና የሚሠሩትን ልብ ሊሉ ይገባል

“የብልጽግና” (ኢህአዴግ ቁ. 2) መሪ የሚሉትንና የሚሠሩትን ልብ ሊሉ ይገባል

ኦብሳ ጉተማ

የብልጽግና

አንድ የኢኮኖሚክስ ባለሙያ በኢኮኖሚክስ የሚሰጠውን ከፍተኛ ዲግሪ (የዶክትሬት ዲግሪ) ለማግኘት የሚፈጅበት ጊዜ ረጅምና አድካሚ ነው፡፡ ከዚያ አልፎ ፕሮፌሰር ለመሆን የሚጠይቀው ጊዜና ልፋቱም በዚያው ልክ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ መማር፤ ማንበብ፤ መመራመር፤ የምርምር ውጤትን ማሳተም ዋና ዋና ተግባራቱ ናቸው፡፡ ይህ ሲሆን የበረቱቱ ብዙ መጣጥፎችን፤ መጻህፍትንና የመሳሰለውን ያሳትማሉ፡፡ የሆነ ሆኖ ዋና ሥራቸው ማስተማር፤ መመራመር እና ማሳተም ነው፡፡ ሌሎች የሚማሩበትን የሚያሳትሙ በርካቶችም አሉ፡፡ ከስንት አንድ ድግሞ ተሳክቶለት በኢኮኖሚክስ የኖብል ተሸላሚ የሚሆንም አለ፡፡ ኢኮኖሚስቶችን የምንጠብቀው በዚህ አካባቢና የኢኮኖሚ ዕድገትና ፖሊሲዎችን በማውጣት በማማከርና በመሳሰለው ቦታ ለይ ነው እንጂ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ እንዳሉት ግሮሰሪ እንዲኖራቸው፤ ሆቴል እነዲገነቡ፤ የኮንስትረክሽን ኩባንያ እንዲኖራቸው፤ ወዘተ አይደለም፡፡ ሊገነቡ የሚችሉ ቢኖሩም ይህ ባብዛኛው የሚሳካለት ለሌሎቹ ነው፡፡ ያንን ለማድረግም ያ ሁሉ ልፋት አያስፈልግም፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ከሾፌርነት፤ ከቡና ቤት ሠራተኛነት ተነስተህ ሚሊኒየር መሆን በሚቻልበት ሁኔታ ያንን ያህል ልፋት ለምን ያስፈልጋል?

የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰሮችም እንደዚሁ ነው፡፡ መማር፤ መመራመር፤ ማስተማር፤ ማሳተምና ማማከር ነው፡፡ ዕውን ጠቅላይ ሚኒሰትሩ እንዳሉት የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ወረዳ ማስተዳደር ቢጠበቅባቸው እራሳቸው ዶ/ር ዐብይ እንዴት የሀገር መሪ ይሆናሉ? የማንም ጉልበተኛና ብልጣብልጥ ተነስቶ የሀገር መሪ በሚሆንበት፤ ሚኒሰትር ለመሆን ታማኝነት እንጂ ዕውቀት በማይፈለግበት እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሀገር የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ወረዳ አላስተዳደረም ብሎ መክሰስ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ዬትኛው ሥርዓታችን ነው ለዕውቀት ቦታ ሰጥቶ ዕውቀት ያለው እንዲያበረክት የተደረገበትና ምሁራን ሚና መጫወት አልቻሉም ተብሎ ወቀሳ የሚደርስባቸው? ዋናው የፖለቲካ ፕሮፌሰር ሥራ እንደነ ዶ/ር ዐብይ ያሉ ሰዎች የሚተገብሩትን ሃሳቦች ማስተማርና ማፍለቅ እንጂ ወረዳ ማስተዳደርም አይደለም፡፡

የብልፅግና መሪ ባለሀብቶችን አስፈራርቶ ቢሊዮን ብሮችን ከተረከበ በኋላ እነርሱን ለማመስገን ምሁራኑን ማኮሰስ ለምን አስፈለገ? ምሁራኑን መስደብ ቀርቶ ብትዘቀዝቁአቸውም የሚሰጡአችሁ ነገር ስለሌላቸው እነሱን ለማዋረድ መሞከር ምንም ትርጉምም ጥቅምም የለውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ባለሀብቶችን ለማመስገን ወይም ለማስደሰት ምሁራኑን ለማዋረድ የሞከሩ ጊዜ ይህንን ሃሳብ ለመሰንዘር አስቤ ተውኩት፡፡

ነገር ግን ደግሞ በቅርቡ የአሜሪካ አይሁዶችንና አፍሪካዊ አሜሪካኖችን ያወዳደሩበትን ክሊፕ አይቼ ነው እነዚህን ሃሳቦች ለመሰንዘር የተገደድኩት፡፡ የአሜሪካ አይሁዶችንና አፍሪካዊ አሜሪካኖችን ለማወዳደር ምንም ዓይነት መሠረት የለም፡፡ አይሁዶች አሜሪካ በቅኝ ግዛት ከነበረችበት ጊዜ ገደማ ጀምረው ነው እንደ ማንኛውም ነጭ የአውሮፓ ስደተኛ ወደ አሜሪካ የሄዱት፡፡ ሄደው ሲያበቁም በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ በተወሰነ የአሜሪካ ከተሞች በመወሰን ንብረት ማፍራት የጀመሩት፡፡ በተለይም በልብስ ፍብረካና ንግድ የጎላ ሚና ነበራቸው፤አለቸውም፡፡ አሁንማ ያልገቡበት የሥራ መስክ የለም፡፡ በጊዜ ብዛት በኢኮኖሚ፤ በፖለቲካና ሌሎች መስኮች ንቁ ተሳታፊዎች ከመሆን አልፈው ሀብታም አይሁዶች በአሜሪካን ሀገር አድራጊና ፈጣሪ መሆናቸው ስለአሜሪካ ትንሽ ዕውቀት ላለው ሰው ሁሉ የሚሰወር አይደለም፡፡

የአሜሪካን አይሁዶች ቁጥር እየበረከተ የመጣው ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአንድ በኩል በጀርመን ሀገር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከባድ ጭፍጨፋ ከተፈፀመባቸው በኋላ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ በምሥራቅ አውሮፓና በሶቪየት ህብረት እንዲሁም ሌሎች ሀገሮች በነበሩት ፀረ ሴማዊ (anti-semitic) መድሎዎችና ጭቆና የተነሳ ነው፡፡ ከነዚህ ጭቆናዎች የሚሸሹ አይሁዶች የአሜሪካንን አይሁዶች ቁጥር ከፍ አድርገውት አሁን አይሁዶች ከአሜሪካ ህዝብ ወደ 2 በመቶ ገደማ ደርሰዋል፡፡

ከአውሮፓ የሚሰደዱ አይሁዶችን አሜሪካ እጆችዋን ዘርግታ ተቀብላቸዋለች፡፡ እነርሱ በሀገሩ እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ ሀብታምና በፖለቲካ ረገድ ከባድ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ከመሆናቸው የተነሳ የአይሁድ ሎቢ (Jewish lobby) የሚባለው በአሜሪካ ውስጥ ያለው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ እንዲያውም ለፕሬዚዳንትነትም ሆነ ለሴኔት አባልነት ወይም ለሌላ ከፍ ላለ ቦታ ለመታጨትና ለማሸነፍ የሎቢውን ድጋፍና ቡራኬ ማግኘት ወሳኝ ነው፡፡እንግዲህ በዚህ ሁኔታ መጥተው የሀገሪቱን ቁልፍ የኢኮኖሚ አውታሮች ከተቆጣጠሩ ነጮች ጋር ነው ጠቅላይ ሚኒሰትራችን በባርነት ተሸጠው የሄዱ አፍሪካዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያወዳደሩት፡፡ ይህንን ለተገነዘበ ሁለቱን ለማወዳደር የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም፡፡ አይሁዶቹ በቀለም ነጭ ናቸው፡፡ እንደሌላው አውሮፓዊ ተሰደው ሄደው የሚናገሩአቸው ቋንቋችም ሌሎቹ አውሮፓውያን የሚናገሩአቸው ናቸው፡፡ ለመዋሃድ የሚያጋጥማቸው ችግርም ይህ ነው አይባልም፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አድራጊና ፈጣሪ፤ የሥርዓቱ ዘዋሪ ወደ መሆን አድገዋል፡፡

የአሜሪካ ጥቁሮች ወደዚያ ሀገር መጋዝ ከጀመሩ አራት መቶ ዓመታት አልፈዋል፡፡ እንደሚታወቀውም የሄዱት እንደሌሎቹ ወደው ተሰደው ሳይሆን በባሪያ ፈንጋዮች ተሸጠው በሰንሰለት እንደውሻ ታስረው ከእንግልትና ሞት ተርፈው አትላንቲክን አቋርጠው አሜሪካ የገቡት በጣም ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ተይዘው በጉልበታቸው ሠርተው አሜሪካን ሀብታም ሲያደርጉ ለነሱ የተረፋቸው ብዝበዛ፤ሥቃይ፤ ግርፋትና ሞት ነው፡፡ በህግ በተደነገገ ባርነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ከማቀቁ በኋላ ነው ባርነት በህግ የተከለከለው፡፡ በህግ ነፃ ይሁኑ እንጂ ሥርዓታዊ ዘረኝነት (systemic racism) እስከዛሬም ድረስ እንደቀጠለ ግልጽ ነው፡፡

የአፍሪካዊ አሜሪካኖች ጭቆና የሚጀምረው ከቀለማቸው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ከብዙ ነገሮች ይገለላሉ:: ታሪኩ ረጅምና ውስብስብ ቢሆንም ጂም ክሮው (Jim Crow) የተባሉትን ህጎች ብቻ ማየት የጥቁሮቹን ሁኔታና እንዴት በመሠረቱ ምንም ከአይሁዶች ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ ያሳያሉ፡፡ ጂም ክሮው የሚባሉት ህጎች እስከ 1968 እአአ ድረስ ለአንድ መቶ ዓመታት ጥቁሮችን ድምፅ ከመስጠት፤ሥራ ከማግኘት፤ከትምህርት እና ከሌሎች መብቶች ያገለሉ ነበሩ፡፡ እነዚህን ህጎች የጣሱ እንደየሁኔታው በገንዘብ፤ በእሥር፤በድብደባ፤ አለፍ ሲልም በሞት ይቀጡ ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ በርካታ ጀግና አፍሪካዊ አሜሪካኖች በተለያየ መንገድ ህጉን በመጣስ ይታገሉ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ሮዛ ፓርክስ የፈፀመችውን ተግባር ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ባርነት በህግ ከተወገደ በኋላም ጥቁሮች በርካታ መድሎዎችና መገለሎች እስከዛሬም ድረስ ይደርሱባቸዋል፡፡ ባልተጻፈ ህግ እንደሚዳኙ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃው በየጊዜው ያለምክንያት በነጭ ፖሊሶች የሚገደሉት ጥቁሮች፤ የአሜሪካንን እስር ቤቶች ያጨናነቁት ጥቁሮች፤ሥራ አጥ ጥቁሮች፤በኮሮና ህመም የሚያልቁ ጥቁሮች ቁጥርና የመሳሰለውን ማየት በቂ ነው፡፡ ጥቁሮች ከአሜሪካን ህዝብ 13 በመቶ ሆነው በኮሮና ቫይረስ ህመም እስካሁን የሞቱት 30 በመቶ ናቸው፡፡ ሰሞኑን በሚኒያፖሊስ ከተማ በሦስት ነጭ ፖሊሶች በመኪና ሥር ተይዞ አንደኛው ፖሊስ በተለይ አንገቱ ላይ ለ9 ደቂቃዎች ገደማ በጉልበቱ ተንበርክኮበት ተጠቂው ጆርጅ ፍሎይድ መተንፈስ አልቻልኩም ብሎ እየተማጸነ የተገደለበት ሁኔታ እንዴት ዓለምን እንዳሳዘነ ብቻ ሳይሆን ለትግል እንዳነሳሳ ያየነው ጉዳይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ እኛንም ይመለከተናል፤ድማጻችንን ልናሰማ በተገባ ነበር፡፡ ነገር ግን በሰላማዊ ሰልፍ ይህንን ጉዳይ እናሰማ ብንል ደግሞ የኦነግ ሸኔ አባላት/ደጋፊዎች ናችሁ ወይም የህወኃት ተላላኪዎች ናችሁ ተብለን ስቃይ ይደርስብናል ብለን ፈርተን ነው እንጂ ነገሩ ተገቢ ነበር፡፡ ተላላኪ የነበረና ይህንንም ያመነ ቡድን አሁን ተመልሶ ሌሎችን ተላላኪ ሲል ከዚህ የበለጠ ምን እንቆቅልሽ አለ?

የሆነ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምን ላይ ተመስርተው ነው እነኚህን የሰማይና ምድር ያህል የተራራቁ ወገኖችን ያወዳደሩት፡? ሁለቱን ሲያወዳደሩ፤ ነጮች ወደፊት ስላዩ ሀብታም ሲሆኑ ጥቁሮች የድሮ ታሪካቸው ላይ ስለተቸከሉ “ነፃ ድሀ” ሆነው ቀሩ ነበር ያሉት፡፡ ነፃ እንዳልሆኑ ይኸው አሁንም ድረስ በሥርዓተዊ ዘረኝነት የሚደርስባቸው ብዝበዛ ያሳያል፡፡ በመሆኑም ድህነት፤ ጭቆናና ሞት ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህንን ነጻነት የተባለውን ለማግኘት የከፈሉት መስዋዕትነት ከባድ ነው፡፡ የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርን፤ የማርከስ ጋረቬይን፤የዱቦይስን፤ የሃርለም ሬዚስታንስን (Harlem Resistance)  እና በርካታ የተደረጉ ትግሎችን ታሪክ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ነጻነት ተገኘ ቢባልም ቅርጽ ብቻ እንጂ ይዘቱ ይህንን ያህልም ስላልሆነ ሥርዓቱ እንኳን ጥቁሮችን ቀርቶ ደሀ ነጮችንም ያገለለ የሀገሪቱ ሀብት ከህዝቡ ቁጥር በጣም አነስተኛ በሆኑ ከዚያም ውስጥ የአይሁዶች ቁጥር የማይናቅ በሆነበት ምን ዓይነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ነው ሁለቱም ዕድል ኖሮአቸው አንዱ ሲጠቀምበት ሌላኛው ሳይጠቀምበት ቀርቶ “ነፃ ደሀ” ሆኖ ቀረ የሚባለው…

በታሪካቸው ላይ ተቸክለው ቀሩ በሚለው ላይ አንድ ነገር ማንሳት ፈለኩ፡፡ መነሻ መድረሻ ነው የሚል በጣም መሠረታዊ የሆነ አባባል አለ፡፡ ጀርመኖች “Herkunft ist Zukunft”  ይላሉ፡፡ትርጉሙ እላይ ያልኩት ነው፡፡ በሀገራችን በተለይ ታሪክን አስመልክቶ ብዙ ጊዜ የምንሰማው የመጣበትን የማያውቅ መድረሻውንም ሊያውቅ አይችልም የሚል ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ከታሪክ ምንም መማር አልቻልንም እንጂ ብዙ ሰዎች የታሪክን አስፈላጊነት የሚናገሩት ታሪክ መነሻችን ዬትና ምን እንደሆነና መድረሻችን ምንና ወዴት ሊሆን እንደሚችል በማሳየት ጉልህ ሚና ስላለው ነው፡፡

ጥቁሮች በግፍ ታሪካቸው ላይ ቢያተኩሩ የታሪክ እስረኛ ለመሆን ሳይሆን ይህን እላይ የተባለውን ቁም ነገር ስለተገነዘቡ ይመስለኛል፡፡ ደግሞም አሁንም የሚደርስባቸው ግፍና መከራ የታሪክ እስረኛ ስለሆኑ ሳይሆን ጠ/ሚኒስትሩ አለ ያሉት ዕድል እሳቸው በተረዱት መሠረት ስለሌለ ነው፡፡ ሁለቱም ያለፉበትም ያሉበትም ሁኔታ ጨርሶ የማይወዳደር ነው፡፡

ጠ/ሚኒሰትሩ በተለያዩ ጊዜያት የኦህዴድ ካድሬዎችን በሚሰበስቡበት ጊዜ ለቅሶ ተው (Booyicha dhiisaa) የሚል አባባል በተደጋጋሚ ሲሰነዝሩ ተሰምተዋል፡፡ እሳቸው ለቅሶ የሚሉት ታሪክን መጥቀስን ነው፡፡ የሰው ልጅ በታሪክ የደረሰበትን በደል የሚያነሳው ከሱ ለመማር ብቻ ሳይሆን ያ ታሪክ የትግል መሣሪያ ስለሆነም ጭምር ነው፡፡ የኦሮሞ ታጋዮች ስለኦሮሞ ህዝብ ታሪክ፤በኦሮሞ ህዝብ ላይ ስለተፈጸመው በደል ታሪክ ሲናገሩ የነበረውን መግለጻቸው ነው፡፡ ታሪክ ያለፉትን ጥሩም መጥፎም ድርጊቶቻችንን የምንማርበት ነው፡፡ ስለሆነም የሚደበቅበት ምክንያት የለም፡፡ የሆነውን ነገር መደበቅ አይቻልም፡፡ መኖሩን ተቀብሎ ከእርሱ ትምህርት ለማግኘት መሞከርና መጥፎ የሆነው እንዳይደገም መጣር ያስፈልጋል፡፡ በታሪካችን የምናፍር ከሆነ ያንን ማረሚያው መንገድ እንደማይደገም አድርጎ ከእርሱ ትምህርት መቅሰም ነው፡፡ ለጠቅላይ ሚኒሰትሩ ይህ በአፍሪካ አሜሪካኖችና በሌሎች ጭቁን ህዝቦች ላይ የተፈጸመን ታሪክ ማንሳት ለቅሶ ነው፡፡ ከጭቆና ከበደልና መድልዎ ጋር መተባበር ላለመሆኑ ምን ዋስትና አለን?

በሀገራችን ብዙ ሰዎች ከመሪዎቻችን ተግባር በመነሳት እውቀት ከሥልጣን ይመነጫል ወይ የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ይሰማል፡፡ ሥልጣንና ጉልበት ያላቸው ሰዎች እርሱን በመተማመን የማያውቁትን ሁሉ ሲናገሩ ይሰማል፡፡ እንደጠቅላይ ሚኒሰትሩ ላሉ ሰዎች ያለኝ ምክር መሪ የሆኑት አዋቂ ስለሆኑ ነው ብለው ባያስቡ ጥሩ ነው፡፡ ባለፉት መቶ ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ መሪ የሆነ ሁሉ በተንኮል፤ በጉልበትና ባጋጣሚ እንጂ ህዝባችን የሚመኘውን አዋቂና ብልህ መሪ አግኝቶ አያውቅም፡፡ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ግን የዕውቀቱን ነገር በሚችሉት ልክ  አድርገው የማያውቁትን ነገር ከመናገር ተቆጥበው በህግ የሚጠበቅባቸውን ብቻ ቢሠሩ ምንኛ ጥሩ አገልግሎት በሰጡን… ሶክራቲስ እንዳለው ብልህነት ወይም ዕውቀት የሚጀምረው አለማወቅን ከመረዳት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለማወቅ ተነሳሽነትን ይፈጥራል፡፡ አውቃለሁ ወይም ተመራምሬአለሁ ብሎ በትክክል ባላወቁት/ባላሰቡበት ነገር ላይ ሃሳብ መስጠት ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ አፍሪካዊ አሜሪካኖችንና አይሁዶችን ያነጻጻሩበት ሁኔታ ስህተትና ከአንድ አፍሪካዊ መሪ የማይጠበቅ ብቻ ሳይሆን በህዝብ ጉዳት መሳለቅ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ቦታ ከያዘ ሰው የሚጠበቀው ሰከን ማለት፤ ታሪክን መረዳት አዋቂና በሳል በሆኑ ሰዎች መመከር፤ የአገር መሪ መሥራት ያለበትንና የሌለበትን ለይቶ ማወቅ፤ ሌላውን ለባለሙያ መተው ነው፡፡

ሌላው ከዚሁ ጋር የሚያያዘው እንዴት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በሶቺ (ራሽያ) የአሜሪካንን መንግሥት ወደ አባይ ውህ አሞላል ጉዳይ እንዲገቡ የተቀበሉበት ሁኔታ ማንሳት ተገቢ መሰለኝ፡፡ ግብፅ ጉዳዩን ለማሰናከል የማትፈነቅለው ድንጋይ ስለሌለ ዶናልድ ትረምፕን ያደራድሩን ብላ ትጠይቃለች፡፡ ትረምፕ ጠቅላዩን በታዛቢነት እንግባ ብለው ይጠይቃሉ፡፡ የግብፅና አሜሪካ የሩቅ ግብ ያልገባቸው አብይ ከባለሙያዎች ጋር ልማከር ማለት ሲገባቸው ውይይት ምን ችግር አለው? ይላሉ፡፡ ይኸውና እንግዲህ ስንት እርምጃ ሄዶ የነበረ ውይይት ስንት እርምጃ ወደ ኋላ እንደተመለሰ አስቡት፡፡

በመጨረሻ የአምኔስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ላይ ሰሞኑን ያወጠውን በአጭሩ ጠቅሼ ላጠቃልል፡፡ አምኔስቲ ያወጣው ሪፖርት ዓለም ያወቀው ነው፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰጡት የተቃረኑ ሃሳቦች ምን እንደሚያመለክቱ ጨርሶ ግራ የሚገባ ነው፡፡ በመጀመሪያ ሁለት ሰዎች ከኦሮሚያ ክልላዊ መንገሥት የመጡት ሪፖርቱን ስህተትና ወገናዊ ነው ብለው ነው የደመደሙት፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግሥትም ወገናዊና ተቀባይነት እንደሌለው ነው የገለጸው፡፡ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ደግሞ እናጣራለን የሚል መግለጫ አወጣ፡፡ አምስተኛው የጠቅላዩ ሆኖ እሳቸው ደግሞ ድርሰት ነው ብለዋል ፓርላማ ፊት ቀርበው ሲናገሩ፡፡ አሁን ግራ የሚያጋባው የመንግሥት አቋም የትኛው ነው የሚለው ነው፡፡ ጠቅላዩ እንዳሉት ድርሰት ከሆነ አቃቤ ህግ ምኑን ነው የሚያጣራው?

እንደ ዶ/ር ዐብይ የኖቤል የሰላም ሽልማት ለወሰደ ሰው የሰብአዊ መብት ጉዳይ በቀላሉ መታየት የለበትም፡፡ አምኔስቲ የተከበረ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ያለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሲሆን ከአምባ ገነን መንግሥታት ውጭ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብትን የሚያከብሩ ሀገራት አምኔስቲን አይተቹም፡፡ የሚተችበት ነገር ካለ እንዲያው ወደምዕራብ ያደላና ለምዕራባውያን እሴቶች ቅድሚያ ይሰጣል የሚል ካልሆነ በስተቀር የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ተአማኒ ናቸው፡፡ ሆነም አልሆነ እንደዚህ የተዘበራረቀና እርስ በርሱ የማይገናኝ አቋም እንዴት ከአንድ መንግሥት የተለያዩ አካላት ይወጣል? በማንም ይሁን በምን ኢትዮጵያ ውስጥ ህይወት በየቀኑ እየጠፋ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ዜጎችን ከጥቃት መከላከል ስለሚገባው አንደኛ የእራሱ ጸጥታ ሃይሎች ለገደሉት ኃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡ ሌላ ደግሞ እርሱ በሚያስተዳድርበት ግዛት ለደረሰው በደል ተጠያቂው የታጠቀ ቡድን ነው ማለት መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታውን ወደ ጎን አድርጎታል ማለት ነው፡፡ በህግም ይሁን ተመጣጣኝ ሃይል በመጠቀም የዜጎችን ደህንነትና መብት ማስጠበቅ የራሳቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የማያውቁ ከሆነ ሀገሪቱ ተስፋ የላትም ማለት ነው፡፡ በፓርላማ ፊት ቀርበው አሸባሪዎች እኛ ነን ያሉበትን ንግግራቸውን ባይረሱት ጥሩ ነው፡፡ ወያኔ የበላይ በነበረበት ጊዜ አሸባሪዎች የነበሩ ተለውጠናል ብለው ይቅርታ ስለጠየቁ ይሁን አልን፡፡ ነገር ግን ያው ተግባር ማለትም አሥራቱና ግድያው ለሥልጣን ተብሎ ከቀጠለ ይኸኛውስ ምን ሊባል ነው?

2 Comments

  1. ቤተመንግስትም ገብቶ ኩሊነቱ ከእርሱ ሊወጣ አልቻለም! ቤተመንግስትም ቢቀመጥ ያው ሌሎች ያዘዙትን ስለሚሰራ፣ ልዩነቱ አይታየውም!
    While the country is in deep crisis and burning on all corners, this moron ‘prime minister’ is sweeping in front of Minilik’s palace, as if the palace is the only Ethiopia! Pathetic!

  2. Please let’s put our differences aside , now is the time to find out who are Ethiopia’s true children and who are those biting their mother’s breasts . Currently Ethiopia got only one respiratory therapist person who is qualified to operate ventilators which are needed for treating patients in Intensive Coronavirus units .
    It is a known fact that there are plenty of Ethiopian respiratory therapists in the diaspora who are currently needed in Ethiopia desperately.

    Ethiopian Diaspora respiratory therapists please report your willingness to travel to Ethiopia to work as respiratory therapists , the more the better. Ethiopian embassies will airlift diaspora respiratory therapists as soon as possible. Just answer Emama Ethiopia’s call for help by reporting to your closest Ethiopian embassy so you can save Ethiopia in this time of desperate need of respiratory therapists.

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.