የነፃነት ቀን እንገናኝ ይሆናል!

“የነፃነት ቀን እንገናኝ ይሆናል!”

Lammeessaa Boruu
Gooticha sabboona Oromoo Jaal Lammeessaa Boruu

ጊዜው እንደ ኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር በ 1930ዎቹ አጋማሽ ገደማ በምስራቅ ወለጋ ቡሎ ቦሼ ወረዳ ቦንያ በተባለ ቀበሌ ከሚኖር የድሃ ገበሬ ቤተሠብ ለሜሣ ቦሩ የተባለ ህፃን ተወለደ። ሥለ የልጅነት ወራት ብዙ የታወቀ ነገር ባይኖርም እንደማንኛውም የኦሮሞ ደሃ ገበሬ ልጅ የንጉሳዊው ጨቋኝ ሥርዓት ባላባቶችን ከብቶች እያገደ እንዳደገ ለማወቅ ብዙም መረጃ ማገላበጥ አያሻም።

በአንድ ወቅት ለመጀመሪያ ልጁ “ቀኑ የገበያ ስለነበረ አባቴ በሳምንት አንድ ቀን ወደማይቀርበት የቢሎ ቦሼ ገበያ አስከትሎኝ ሄደ። የእለቱን ገበያ ካጠናቀቀ በኋላ ሁሌም ቢሎን ከረገጠ ወደማይቀርበትና የልብ ወዳጁ ወደ ሆኑ ቄስ ቤት አመራን። በጨዋታቸው መሃል አንድ ሰው መጥቶ ለፊደል ሰራዊት ልጆችን እንደሚፈልግ እና ለዚሁም ተልኮ በሚቀጥለው አመት ልጆችን ቄሱ ፈልገው እንዲያቆዩ እንደተነገራቸው ለአባቴ አጫወቱት። አባቴም ልጅ እንደማይሰጥ ለቄሱ ነገራቸው። እኔ ግን ልቤ ሸፈተ።” ብሎ አጫውቶት ነበር።

የክቡር ዘበኛ ወታደር የነበረው ለሜሳ ቦሩ በ1958 ዓ.ም በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ የፍርደ-ገምድል ችሎት ፊት የመጀመሪያው የተቀናጀ የኦሮሞ ህዝብ ትግል የሆነው የሜጫ እና ቱለማ መረዳጃ መሓበርን መስርተዋል ተብለው በሃገር ክዳት ወንጀል ከተከሰሱት ከነ ጄነራል ታደሠ ብሩ መሃል አንዱ የነበረ ሲሆን እጅግ በመረረ እና በከፋ የኦሮሞ ገበሬ ቤተስብ ሕይወት ውስጥ ማለፉ መስዕዋት ለሚጠይቅ መራራ ትግል እንዳነሳሳው መገመት አያዳግትም። ከወጣትነት ወርቃማ ጊዜው ውስጥ ሰባት አመታትን ጭካኔ እና ስቃይ በተሞላበት የንጉሰ ነገሥቱ ማጎሪያ ውስጥ አሳልፏል።

ከእሥር ከተፈታም በኋላ በወቅቱ የነበረው ንጉሳዊ ሥርዓት አብዛኛውን ሰብዓዊ መብቶቹን ነፍጎት ቆይቷል። ይሁን እንጂ ለሜሳን ከጀመረው የትግል መስመር ፊጹም ፈቀቅ አላደረገውም። በጊዜው ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት ደፋ ቀና ከሚሉ የኦሮሞ ሕዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች ጋር በመሆን ትግሉን በበለጠ ገፋበት። ጊዜው ንጉሳዊው አገዛዝ በኢምፓየሯን ጭቁን ሕዝቦች ላይ ከባድ ቀንበርን የጣለበት ወቅት ሲሆን ሁሉም ለለውጥ ደፋ ቀና ይል ነበር። ተማሪው ገበሬው ወታደሩ ሠርቶ-አደሩ ብቻ ሁሉም ታች ላይ በሚልበት ወቅት ለሜሳ ቦሩ የምርት ሱፐርቫይዘር ሆኖ በአዲስ ጎማ ፋብሪካ ይሰራ ነበረ ቢሆንም በትግሉ ገፋበት። የትግሉም ተቃዋሚዎች አልተኙለትም ነበር። እጅግ ብዙ ማሥፈራሪያ ቢደርሰውም አሻፈርኝ በማለቱ ይሰራበት ከነበረው ፋብሪካ ብዙም ሳይርቅ ከባድ ድብደባ ደረሰበት። ብዙዎች ለሜሳን በወርቅ ጥርሱ ያስታውሱታል ለዕርሱ ግን የዛች ቀን የስቃይ አሻራው ነበረች። የወርቅ ጥርሱ።


ወታደራዊ ሰደድ እራሱን ደርግ በማለት የመንግስት ስልጣንን ከተቆናጠጠ በኋላ በኦሮሞ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ በሆነው የ‘በሪሣ’ ጋዜጣ ውስጥ ለጥቂት ጊዜያት ሰርቷል። በመቀጠልም ወደ ሃገር አስተዳደር በመዛወር በቤጊ እና በሊሙ ወረዳዎች ዋና አስተዳዳሪ የነበረ ሲሆን በጊዜው የኦሮሞ ነፃነት ግምባርን ለማጠናከር በኦሮሞ ህዝብ መሃል ቅስቀሳን ለማድረግ እድሉን ሊያገኝ ችሏል።

በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ደርግ የኦሮሞ ነፃነት ግምባርን ከፍተኛ የአመራር አባላትን ማደኑን ተያያዘው። ለሜሳ ቦሩም ከዚህ አፈና አላመለጠም ነበር። ከአሶሳ ተይዞ ወደ ፊንፊኔ ተወሰደ። ከሞት የከበዱ ድፍን አስር አመታትን በደርግ ጽ|ቤት በማዕከላዊ ምርመራ እና በከርቸሌ እስር ቤቶች ውስጥ እጅግ አሰቃቂ የሆነ ግፍ በመርማሪዎቹ ተፈፅሞበታል። የስፓይናል ኮርዱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቷል፤ ከእግሩ በቀዶ ጥገና የተሰበረ አጥንት ወጥቷል፤ እንዲሁም የዘር ፍሬው ውሃ በተሞላ ጠርሙስ ታስሮ እንዲኮላሽ ተደርጓል። በእስር ቤት በነበረው ቆይታ ወቅት በድብደባ ለተጎዱ እስረኛ የትግል አጋሮቹ ለእርሱ ይሰጠው የነበረውን የህመም ማስታገሻ መድሃኒት ለሌሎች አስልፎ ይሰጥ የነበረና ከራሱ ሥቃይ ይበልጥ ለሌሎች ሥቃይ የሚያዝን እንደነበር ኢብሳ ጉተማ ‘ፕሪዝን ኦፍ ኮንሰስ” በሚለው መጽሓፉ ላይ እማኝ ምስክርነቱን ጽፏል።


የመጀመሪያ ልጁ ያንን ጊዜ እንዲህ ሲል ያስታውሰዋል “ በአንድ የክረምት ወራት በግምት የዘጠኝ ወይም የአስር አመት ልጅ በነበርኩበት ወቅት፤ አመተ ምህረቱን አላስታውሰውም፤ በጎረቤታችን የምትኖር አንዲት ሴት ከምጫወትበት ቦታ ጠርታኝ ‘አባትህ የት እንዳለ ታውቃለህ?’ በማለት ጠየቀችኝ። ‘እስር ቤት ነው ያለው ይባላል ግን የት እንደሆነ አላውቅም።’ አልኳት። ‘ሰሞኑን እኔ እወስድሃለሁ ግን ለማንም እንዳትናገር’ በማለት አስጠነቀቀችኝ። ‘እሺ’ ብያት ተለያየን። ለቀናት ከጠበኳት በኋላ ከቤት አስጠርታኝ ከእህቷ ጋር ሆነን ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል ወሰዱኝ። ከብዙ ሰአታት በኋላ አንዲት የወታደር መኪና በተሽከርካሪ አልጋ ላይ የታሰረና በፖሊስ የሚጠበቅ እስረኛን ይዛ ከተፍ አለች። ፖኢሶቹ ተሸክመው አወረዱት። ልብሱ በደረቀ ደም የተለወስ እጅግ የተጎሳቆለ ቢሆንም ረጅም ቁመናውና መልከ መልካም ጥቁር ገጽታው ግርማ ሞገስን አላብሶታል። ትኩስ የእምባ ዘለላዎች የልጅነት ጉንጬን እያቃጠሉ ሲወረዱ ይሰማኝ ነበር። ወደ ሰውየው ሮጥኩ ፖሊሶቹ ገፈታትረው መለሱኝ። እርሱን ግን በተኛበት አልጋ እየገፉ ወደ ውስጥ አስገቡት። አባቴ ሳያየኝ እኔ ብቻ አይቼው እያለቀስኩ በሥሥት ወደ ቤት ተመለስኩ። ለረጅም ዘመናት ያ ትዕይንት ከአዕምሮዬ ሊጠፋ አልቻለም ነበር። ‘እኔም ሣድግ እንደዚህ እሆን ይሆን ወይ?’ በማለት የልጅነት እድሜዬ በፍርሃት የተሞላ ሆነ።

በነዚያ አስር አመታት ውስጥ ይህችን ቀን ሳይጨምር አንድ ጊዜ በመአከላዊ ምርመራ እና ሶስት ጊዜ በከርቸሌ ከወንድሜ እና ከእህቴ ጋር በመሆን አባታችንን የማየት መልካም እድል አግኝተን ነበረ። እንደ መልካም እድል ከተቆጠረ ማለቴ ነው።”

ለሜሳ ለአስር አመታት ወደ እስር ቤት ሲወረወር በቤቱ ሁለት ወንዶች እና አንዲት ሴት ህፃናትን ከኋላው ጥሎ ነበር። በዕሥር በነበረበት ወቅት ቤተሠቡ ተበትኗል። እነዚህን መራራ አመታት ያለ ጠያቂ በናፍቆት ተጋፍጧቸዋል። ልጆቹ በርሃብና በርዛት በቅማልና በትኋን ተገርፈዋል። የሚገርመው አባታቸው ያወጣላቸው ሥም ተቀይሮ ከፊንፊኔ ከተማ ተወስደው በማያውቁት ሃገርና ህብረተሰብ መሃል በጎንደር የከብት እረኛ እስከመሆን ደርሰው ነበር። ከዚህ ባሻገር ኦሮሞ ሆነው በመፈጠራቸው ከስነ-ልቦና ጥቃት አላመለጡም ነበረ። ይህንን የመጀመሪያ ልጁ እንዲህ ሲል ያስታውሰዋል “የሁለተኛ ክፍል ተማሪ በነበርኩበት ወቅት እጅግ ከሲታ እና አይን አፋር ነበርኩ። ሁል ጊዜ ይርበኛል። አባት ስሌለኝ በጣም ይከፋኛል። ጓደኞቼ ሥለ አባቶቻቸው ሲያወሩ እጅግ እቀናለሁ። የአማርኛ አስተማሪዬ የሥም ጥሪ ሲጠራ ከነ የአያት ሥሜ እየጠራ’ይሄ ደግሞ ምን አይነት ሥም ነው?’ እያለ ያስቅብኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከልጆች ጋር ስንጣላ እንኳን ከመታኋቸው ለአባታቸው እንደሚናገሩልኝ ያስፈራሩኛል። ይሁን እንጂ አንድ ጊዜ ግን ልቋቋመው የማልችለውና የልጅነት አይምሮዬ የማይሸከመው ጉዳይ ገጠመኝ። ነገሩ እንዲህ ነው ከኔ በእድሜ የሚበላልጡ ሴቶች ልጆች ‘የኔ ባል ነው!’ ‘የኔ ባል ነው!’ እያሉ ያሳፍሩኝ በነበረበት ጊዜ አንደኛዋ ልጅ አንድ ጥያቄ ጠየቀችኝ። ‘ማሙሽ ስምህ ማን ነው?’ የሚል ነበር። ፈጠን ብዬ ‘ሞሲሳ’ አልኳት። ሁሉም ሴቶች ደነገጡ።ጠያቂዋ ልጅ ወደ እነሱ ዘወር በማለት ‘ውይ ጋላ አይመስልም አይደል?’ አለቻቸው። ከዛን ቀን በኋላ ‘ጋላ! ጋላ! ጋላ!’ እያሉ ይሰድቡኛል እኔም ምርር ብዬ አለቅስ ነበር። እናም ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ጠላሁ። ግዴታ ባይሆንብኝ ኖሮ!!”

ለሜሳ ቦሩ ከረጅም አመት እስር በኋላ ተፈታ። ከእስር የተለቀቀ ዕለት ቤተሠብ ያለው እስረኛ ወደ ቤተሠቡ ዘመድ ያለው ወደ ዘመዱ ሁሉም በየፊናው ሄደ። እርሱ ግን ግራ ገባው የፊንፊኔ ከተማ በጣም ተለውጧል። ማን ጋር ይግባ?ወደ ቤቱ እንዳይሄድ ቤት የለውም ቤተሠቡም ተበትኗል። እግሩ እንደመራው ‘ድንገት የማውቀው ሰው ባገኝ’ ብሎ ከፖሊስ ክበብ በረጅም ቁመቱ እጥፍ እጥፍ እያለ ሽቅብ ወደ ፒያሳ ነጎደ………………….

ለሜሳ ቦሩ ከደርግ እሥር ቤት ከወጣ በኋላ በህፃንነታቸው ትግልን መርጦ ከተዋቸው ጎረምሳ ልጆቹ ጋር በካሳንቺስ አካባቢ መኮንን ገላን የተባለ የትግል አጋሩ እና የዕሥር ቤት ጓደኛው በሰጠው የኪራይ ቤት ውስጥ ከአንድ አመት ለአንሰ ጊዜ አብሯቸው ኖሯል። ወይም ቆይቷል። በዚያች አጭር ጊዜ ውስጥ በአንድ አልጋ ላይ አብሯቸው እየተኛ አፍቃሪ አባትነቱን ደግነቱን ርህራሄውን ጠንካራ ማነነቱን እና ለኦሮሞ ህዝብ ትግል ያለውን ቆራጥ አቋም አሳይቷቸዋል። አብሮነታቸው ግን ብዙም አልዘለቀም የደርግ መንግስት ከስልጣን በተወገደ ማግስት ወደ አልተቋጨው የኦሮሞ ሕዝብ የነፃነት ትግል ተመልሶ ተቀላቀለ። ሙሉ ጊዜውንና ራሱን ለትግሉ አሳልፎ ሰጠ።

በጊዜው የኦሮሞ ነፃነት ግምባር የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የግምባሩ ቃል አቀባይ ሆኖ አገልግሏል። የሽግግሩ መንግስት ሲፈርስ ከኦሮሞ ነፃነት ግምባር ሰራዊት ጋር ወደ ጫካ ከገባ በኋላ በትግል ላይ እያለ በወያኔ ጦር ተከቦ የተያዘ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ በጅማ ሆስፒታል የመጀመሪያ ልጁ ለመጨረሻ ጊዜ የተለያዩበትን ቀን ዕንባ እየተናነቀው ሲያስታውስ “የዚያን እለት አባቴ ከሌላው ቀን በተለየ ትካዜ ይነበብበት ነበር። አሻግሮ ዕሩቅ እየተመለከተ ‘ምናልባት የነፃነት ቀን እንገናኝ ይሆናል!’ብሎ ተሰናበተኝ።”

ለሜሳ ቦሩ በኦሮሞ ህዝብ የነፃነት ትግል ውስጥ በሦስት ተከታታይ የኢምፓየሯ መንግስታት ለ 33 አመታት የታሰረ የነፃነት ታጋይ ያደርገዋል።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.