የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ሁለተኛ ዙር፥ ክፍል አምስት

የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ሁለተኛ ዙር፥ ክፍል አምስት

ብርሃኑ ሁንዴ, Caamsaa 31, 2019

በሁለተኛ ዙር ክፍል አራት ፅሁፍ ውስጥ የኦዴፓ የፖለቲካ አካሄድ እና ስራቸው ኦነትን ያግዛሉ ወይንስ እንቅፋት እየሆኑበት ነው? ብዬ ጥያቄ ባማንሳት በዚህ ላይ አጭር አስተያያትና እንደዚሁም ደግሞ ይህ ድርጅት (ኦዴፓ) ለኦሮሞ ጉዳይ ለምን ቅድሚያና ትኩረት እንድማይሰጥ የተለያዩ ምክንያቶችን አቅርቤ ነበር። በዚህኛው ክፍል አምስት ፅሁፍ ውስጥ እየተቃረበ ስላለው የአገሪቷ ብሔራዊ ምርጫ እና በኦነግና በመንግስት መካከል የተደረገውን ስምምነት በተመለከተ ቅርብ ጊዜ የቴክኒክ ኮሚቴ ያወጣውን መግለጫ በሚመለከት አንዳንድ ሀሳቦችን አቀርባለሁ።

ኦነግ እኔ የታጠቀና የሚዋጋ ሰራዊት ጫካ ውስጥ የለኝም ማለቱ ለፖለቲካ ስልት ነው ወይንስ እውነት ነው?

በተደጋጋሚ ሲገለፅ እንደቆየና እንደሚታወሰው፣ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የተደረገው ስምምነት ኦነግ በሰላማዊ መንገድ እንዲታገልና ሰራዊቱ (WBO) ደግሞ ከኦሮሚያ ልዩ ኃይል ጋር ተቀላቅለው የክልሉን (ኦሮሚያ) ሰላምና ደህንነት እንዲጠብቁ ለማድረግ እንደሆነ ነው የምረዳው። ይሁን እንጂ ይህንን ስምምነት ስራ ላይ ማዋሉ ላይ የተለያዩ ችግሮች እንደተፈጠሩ ሲገለፅ የነበረ ጉዳይ ነው። ይህ ስምምነት ስራ ላይ እንዲውልና  እንደዚሁም በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ለማስቻል የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቋመ። በዚህ አካሄድ ውስጥ የተወሰኑ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላት ወደ ካምፕ እንደገቡ የሚታወስ ነው። ነገር ግን በካምፕ ውስጥ የተለያዩ ችግሮች እንደደረሱባቸው ከሚዲያ ተሰምቶ ነበር። ይህ ሆኖ እንዳለ አሁንም ጫካ ውስጥ የቀሩት የሰራዊቱ አባላት ወድ ካምፕ እንዲገቡ እየተሰራ ያለ ይመስላል።

ይህ ኣካሄድና አሰራር ስላልገባኝ በቅርብ አንድ አጭር ፅሁፍ አቅርቤ ነበር። http://ayyaantuu.org/waliigaltee-abo-fi-mootummaa-ibsa-koree-teekniikaa-የኦነግና-የመንግስት-ስምምነ/ በዚያ ፅሁፍ የቴክኒኩ ኮሚቴ ያቀረበውን መግለጫ በሚመለከት የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርቤ ነበር። በዚህኛው ፅሁፍ ርዕስ ላይ ወደተነሳው ጥያቄ በመመለስ በኦቦ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ የሰጠው መግለጫ እንደኔ አመለካከት በሁለት መንገድ ሊታይ ይችላል።

አንደኛ, ኦነግ የግንባሩ መሪዎች ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በድርጅቱ ላይ የተለያዩ ጫናዎች ያሉ ይመስላል። በሀበሾች ጎራ በኩል እንደተለመደው በዚህች አገር ውስጥ ኦነግ ነው ጦርነት እያካሄደ ሰላምን የሚያደፈርሰው እያሉ የዚህን ግንባር ስም ያጠፋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ኦሕዴድ (ኦዴፓ)ም ኦነግን ምክንያት በማድረግ በኦሮሚያ ውስጥ የተለያዩ ችግሮችን እየፈጠረ ነው። ይህ በመሆኑ ኦነግ አሁን ከነዚህ ሁሉ ወቀሳ ለመውጣትና እንደዚሁም ለሚመጣው ምርጫ መንገድ ለማመቻቸት ብሎ እኔ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስኛለሁ፤ ታጣቂም ሆነ ተዋጊ የለኝም ማለቱ ለፖለቲካ ስልት ሊሆን ይችላል የምል ግምት ነው ያለኝ።

ሁለተኛ, ፊንፊኔ ያለው የኦነግ አመራር እውነትም አሁን ጫካ ውስጥ ያሉትን የሰራዊቱ አባላት ለማዘዝ አቅም ስላጣ ወይንም ደግሞ እነዚህ የሰራዊቱ አባለት ለኦነግ ስለማይታዘዙ፣ ኦነግ ደግሞ በኦሮሚያ ውስጥ እየተደረጉ ላሉት ሀላፊነትን ላለመውሰድ እውነትም በዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰም ይመስላል። እዚህ ላይ የማይገባ ጉዳይ ግን ከሰራዊቱ ውስጥ የሚሰጡት መግለጫዎች ናቸው። ጃል መሮ (Jaal Marroo) እየገለፀ እንዳለው አሁን ጫካ ውስጥ ያሉት የሰራዊቱ አባላት የኦነግ አካል እንደሆኑና የኦነግን ዓላማ ከግብ ለማድረስ እንደሚዋጉ ነው። እውነታው ይህ ከሆነ ደግሞ፣ ኦነግ ሰራዊት የለኝም ብሎ መግለጫ መስጠትና ጫካ ካሉት የሰራዊቱ አባለት ራሱን ማግለሉ የዚህን ድርጅት (ግንባር) አካሄድና ዓላማ ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል።

ኦነግ በሰላማዊ መንገድ ታግሎና በምርጫ አሽንፎ፣ የተቋቋመለትን ዓላማ ከግብ ማድረስ ይችላል?

ለኔ ይህ ትልቅ ጥያቄ ነው። ለምን ከተባለ፣ ባሁኑ ጊዜ በአገሪቷ በተለይም ደግሞ በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ካየን፣ እውነትም እውነተኛና ፍትሓዊ ምርጫ ተደርጎ፤ በዚህ ምርጫ ውስጥ ኦነግ አሸንፎ ዓላማውን ከግብ ያደርሳል ብሎ ማሰብ እጅግ አስቸጋሪ ነው። የኢትዮጵያን መንግስት ባሕርይና እንደዚሁም ደግሞ የኦሕዴድን ፀባይና ተንኮል የሚያውቅ ሰው ይህንን ሁኔታ ለመረዳትና ለመገመት የሚያዳግተው አይመስለኝም። ባሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ውስጥ እየተደረገ ያለው ጦርነት በዚህ መልኩ ከቀጠለና ሰላምና መረጋጋት በክልሉ ካልተፈጠረ፣ ምርጫው ራሱ እንዴት ሊደረግ ነው? ይህ ጦርነት እንዲቆም ከተፈለገ ደግሞ፣ ጫካ ውስጥ ካሉት ሰራዊት ጋር እውነተኛ ውይይት ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። እነዚህ ሰራዊት እያቀረቡ ያሉትን ጥያቄዎች መስማትና የጋራ መፍትሄ መፈለግ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ወሳኝ ነው።

እዚህ ላይ ሌሎች ሊነሱ የሚችሉት ጥያቄዎች ከነዚህ ጫካ ካሉት የሰራዊቱ አባላት በስተጀርባ ሌላ አካል አለ? ሌላ አካል ካለ ይህ ለኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት የሚሰራ ነው? እነዚህ ጫካ ያሉት የሰራዊቱ አባላት እያነሱ ያሉት ጥያቄዎችና እየሰጡ ያሉት መግለጫዎች እንደሚያሳዩት፥ የኦሮሞ ጥያቄ መልስ ያግኝ፤ የኦሮሞ የአገር ባለቤትነት ይረጋገጥ፤ የኦሮሞ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ይጠበቅ ወዘተ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ምን ስህተትና ችግር አለባቸው? እነዚህ ጥያቄዎች የኦሮሞ ሕዝብ እየጠየቀ ያለው አይደሉም? እነዚህ የሰራዊቱ አባላት ለማስመሰል ብለው ነው ሕይወታቸውን መስዋዕት እያደረጉ የሚዋጉት? እውነት እንናገር ከተባለ እነሱ እያቀረቡ ባሉት ጥያቄዎችና መግለጫቸው ውስጥ ምን ስህተት አለ?

እዚህ ላይ አንባቢዎች እንዲገነዘቡት የምፈልገው፥ እኔ ለነዚህ ለሰራዊት አባላት መናገሬ ሳይሆን ቢቻልና በሰላማዊ መንገድ ችግሮች መፈታት ቢችሉና ሕዝባችን ሰላም ማግኘት ብችል ለኔ ወስን የለሽ ደስታ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳቤን ስፅፍ ለየትኛውም አካል ለመናገር ሳይሆን የሕዝባችን ሰላምና ደህንነት ስላሳሰበኝ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ፅሁፌ ሌላ ዓላማም ሆነ መልዕክት የለውም።

ተመልሰን እስከምንገናኝ በደህና ቆዩ

2 Comments

  1. “የኦሮሞ ጥያቄ መልስ ያግኝ፤ የኦሮሞ የአገር ባለቤትነት ይረጋገጥ፤ የኦሮሞ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ይጠበቅ ወዘተ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ምን ስህተትና ችግር አለባቸው? እነዚህ ጥያቄዎች የኦሮሞ ሕዝብ እየጠየቀ ያለው አይደሉም? እነዚህ የሰራዊቱ አባላት ለማስመሰል ብለው ነው ሕይወታቸውን መስዋዕት እያደረጉ የሚዋጉት? እውነት እንናገር ከተባለ እነሱ እያቀረቡ ባሉት ጥያቄዎችና መግለጫቸው ውስጥ ምን ስህተት አለ? ” ……. ይህ ፍፁም ትክክል ነዉ። ጥያቄያቸው መጀመሪያዉኑ የትጥቅ ትግል ሲጀምሩ አንግበዉ የወጡት የነበሩ በመሆናቸዉና በአብዛኛዉ ጥያቄዎቹ ባለመመለሳቸዉ በአቋማቸዉ ቢፀኑ አያስደንቀንም። ሆኖም የወቅቱን ፖለቲካዊ የሃገሪቷንም ሆነ የቀጠናዉን ነባራዊ ሁኔታ ግንዛቤ ዉስጥ አስገብቶ፣ ከምንም በላይ ለኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች መመለስ ዋስትናዉ የኦሮሞ ሕዝብ አንድ መሆንና የንቃተ ኂሊናዉ ማደግ መሆኑን ተገንዝቦ፣ በአሁኑ ወቅት በአንፃራዊነት ያ በተወሰነ ደረጃ ስለተገኘ ጦሩና ሕዝቡም ከዚሁ አንፃር ትግሉን ቢያስተካክል አይሻልም ወይ ነዉ ጥያቄዉ። ኦዲፒ ብዙ ኃጥያት ቢኖርባቸዉም ለኦሮሞ አንድነት ሲባል እነ ጀዋር እንደሚያደርጉት አብሮ በመስራት ጫና መፍጠሩ ተመራጭ አይሆንም? በግልፅ እንደሚታወቀዉ የኦዲፒ ታችኛዉ መዋቅር ጭምር የሚደግፈዉ ኦነግን በመሆኑ የኦሮሞን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያግደዉ ምን ምድራዊ ሃይል አለ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.