የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? – ሁለተኛ ዙር፥ ቁጥር ሰባት

የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? – ሁለተኛ ዙር፥ ቁጥር ሰባት

ብርሃኑ ሁንዴ, Waxabajjii 28, 2019

tears

በሁለተኛ ዙር ክፍል ስድስት ፅሁፍ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ ትዕግስት እንደ ሞኝነት መታየት እንደሌለበት፤ እንደዚሁም የኦሮሞ ሕዝብ ከዚህ ለውጥ ያገኘው ጥቅም እንደሌለ የሚያሳዩ የተለያዩ ምሳሌዎችን በማንሳት አንዳንድ ጉዳዮችን ለማብራራት ሞክሬ ነበር። በዚህኛው ቁጥር ሰባት ፅሁፍ ውስጥ እንደ ብሔርና ሕዝብ በኦሮሞ ላይ እየተቃጣ ያለውን የማጥቃት ሙከራና እንደዚሁም የኦሮሞ ነፃነት ትግል (ኦነት) አስካሁን ያስመዘገባቸው ድሎች አደጋ ውስጥ እንዳሉ ለመግለፅ አንዳንድ ነገሮችን ማንሳት እፈለጋለሁ።

ለአንባቢዎች፥ ካሁን በኋላ የማቀርባቸው ተከታታይ ፅሁፎች በክፍሎች ሳይሆኑ በቁጥሮች እንደሚቀርቡ ማስታወቅ እወዳለሁ።

ትልቅ ነገር ስንፈልግ ጭራሹኑ በእጃችን ያስገባናቸውን ድሎች እንዳናጣ!!

በቅርብ የተደረገው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ብዙ ነገሮችን ሊያስተምረንና ሊያስገነዝበን ይገባል። ይህ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በአማራ ክልል ብቻ ሊደረግ የታቀደ ሳይሆን፣ ለማስመስል ካልሆነ በስተቀር ዋንኛው ዕቅድና ዓላማ በአብይ አህመድ የሚመራውን ማዕከላዊውን የኢትዮጵያ መንግስት ለመግልበጥ እንደሆነ ብዙ የሚያመላክቱ ነገሮች አሉ። ይህ ዕቅድ ደግሞ በቅርብ የተነደፈ ወይም እንደ አጋጣሚ የተደረግ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የታሰበበትና በደንብ ሲሰራበት የቆየ ነው ብዬ አስባለሁ። ማዕከላዊውን መንግስት ለመገልበጥ ለምን አስፈለገ? በወያኔዎች ጊዜ ያልታሰበና ያልተሞከረ ለምን ባሁኑ ጊዜ ሊሆን ቻለ? ለነዚህ ጥያቄዎች የተለያዩ መልሶች (ምክንያቶች) ቢኖሩም፣ እኔ ግን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ምክንያቶች እገመታለሁ።

  • አንደኛ ለኦሮሞ እውነተኛ ለውጥ ማምጣት ባይችልም፤ የኦሮሞን ጥያቄ ለመመለስ ፈቃደኛ ባይሆንም፣ ይህ በዶ/ር አብይ የሚመራው መንግስት የኦሮሞ መንግስት ነው ተብሎ ፕሮፓጋንዳ ስለሚነዛለት፣ የኦሮሞ ጠላቶች ደግሞ ከወያኔዎች ይልቅ ኦሮሞን ስለምጠሉና ስለምፈሩትም፣ ይህ በኦሮሞ ተወላጅ እየተመራ ያለውን መንግስት ለማጥፋት ይፈለጋሉ።
  • ሁለተኛ የዶ/ር አብይ ፖለቲካዊ አካሄድ የኦሮሞ ጠላቶች ወኔ እንድኖራቸው አድርጔል፤ ሞራል እንድያገኙም አስቻላቸው። ምን ማለቴ ነው? ዶ/ር አብይ እንደ አገሪቷ ጠ/ሚኒስተር ከተሾመበት ቀን አንስቶ በየሄደበት ሁሉ ንግግር ሲያደርግ የድሮ ንጉሶችን በተለይ ደግሞ ሚኒልክን ሲያደንቅና ሲያሞግስ ስለቆየ፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች ራሳቸውን እያደራጁና እያጠናከሩ፤ በውስጥና በውጭ መዋቅራቸውን እየዘረጉ፤ ኃይላቸውንም እያጠናከሩ መጥተዋል። ይህ የኃይላቸው መጠናከር ደግሞ መንግስትን እንድንቁ አስቻላቸው።
  • ሶስተኛ፣ ሌላው ምክንያት አሁንም ከዶ/ር አብይ ፖለቲካዊ አካሄድና ፍልስፍና ጋር ይያያዛል። የአብይ ትዕግስት ማሳየት፣ ፍቅርና ይቅርታን ደጋግሞ መናገር፣ በኦሮሞ ጠላቶች ዘንድ እንደ ልመና ወይንም ደግሞ የመንግስት አቅም ደካማ እንደሆነ ታይቶ ሞራል የሰጣቸው ይመስላል። እዚህ ላይ አንባቢዎችን ማስገንዘብ የምፈልገው እኔ አሁን ያለው መንግስት ደካማ ይሁን ጠንካራ ለዚህ ማስረጃ እንደ ሌለኝ ነው።
  • አራተኛ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን (WBO)ን ትጥቅ ማስፈታት ወይም ወደ ካምፕ ማስገባት በሚል ስም የመንግስት አካሄድና አሰራር በኦሮሞ መካከል የተላያዩ ችግሮችን ስለፈጠረ፣ የኦሮሞ ጠላቶች ደግሞ ይህንን ስለተገነዘቡ፤ የኦሮሞን ኃይል በመናቅ የፈለጉትን ለማድርግ ሞራል አግኝተዋል። በሌላ በኩል ሲታይ ደግሞ፣ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች አንድ እንሆናለን ወይም በጋራ እንሰራለን እያሉ መግለጫ ከማውጣት ይልቅ ይህንን አንድነት በተመለከተ በመሬት ላይ በተግባር የታየ ነገር ስለሌለ፤ እውነተኛ አንድነት ፈጥረው የኦሮሞ ጉልበትና ኃይል እንዲጠናከሩ ባለማድረጋቸው፣ ይህ በኦሮሞ ጎራ (Camp) ድክመት እንዳለ ለጠላቶቻችን ማሳያ ሆኗል።
  • አምስተኛ በኦሮሞ መካከል አለመገባባት እየተፈጠረ በሄደ ቁጥር በተቃራኒው ግን ጠላቶቻችን ሁሉ ቦታ (ኦሮሚያን ጨምሮ ማለት ነው) መዋቅራቸውን እያሰፉ፣ ራሳቸውን እያደራጁና እያስታጠቁ፤ በዚህ መንገድ ጉልበትና ኃይላቸውን እየገነቡና እያጠናከሩ ስለሆነ፣ ይህ ሁሉ ተደማምረው የበለጠ ወኔ ስለሰጣቸው መንግስትን እስከመገልበጥ አደረሳቸው ማለት ነው።

እንግዲህ ከላይ የተዘረዘሩት እንደ ራሴ አመለካከትና ግምት እንጂ ምክንያቶቹ ሌሎች ወይንም ከዚህ ውጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ ከላይ ጠቅሼ እንዳለፍኩት፣ ይህ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ለኦሮሞ ትልቅ ትምህርት መስጠት አለበት። ባጠቃላዩ የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ሕዝብና ብሔር አደጋ ውስጥ እንዳለና በተለይ ደግሞ ኦነት መጥፎ ሁኔታ ውስጥ እየገባ እንደሆነ በንቃት አይተን፤ የሚመጣብንን አደጋም በሩቁ ማየት ችለን፣ ይህንን ለመከላከል ደግሞ ከምንጊዜውም የበለጣ የኦሮሞ አንድነት አሁን አስፈላጊና ወሳኝ ነው። የኦሮሞ አንድነት ስል ደግሞ፣ እንደ ብሔርና እንደ ሕዝብ፤ እንደ ኦሮሞ ትውልድ፤ በፖለቲካ አመለካካትና አይዶሎጂ፣ በክልልና በእምነት ሳንከፋፈል በጋራ ቆመን ጠላቶቻችንን ለመመከትና ከዚህም አልፈን ለማሸነፍ መቻል ዝግጁ መሆን አለብን ማለቴ ነው።

እስቲ ይታየን ይህ መፈንቅለ መንግስት ቢሳካና የኦሮሞ ጠላቶች ስልጣን ብይዙ ኖሮ የኦሮሞ ሕዝብ ሁኔታ ዛሬ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይህን ስል ሕዝባችን ወደ ድሮው ያረጃና የበሰበሰ ስርዓት ተመልሶ በባርነት ስር ይወድቃል ማለት ሳይሆን፣ በሚፈጠረው ሁኔታ ውስጥ ምን ያህል መስዋዕትነትን ሊያስከፍለን እንደሚችል ማወቅ አለብን ለማለት ነው። ዶ/ር አብይን በሚመለከት ካላይ እንደ ምክንያት ያቀረብኩት በመሬት ላይ ያለ እውነታ ሆኖ ነገር ግን የሱ ጥፋት ብቻ ተደርጎ ተውስዶ ባንድ ሰው ጣት መቀሰር ተገቢ አይሆንም። የፈለገውንም አይዶሎጂና ዓላማ ቢኖረውም፣ ከኦሮሞ ሕዝብ አብራክ ውስጥ እንደወጣ ልጅ ታይቶ በችግር ጊዜ ከሱ ጋር መቆም የኦሮሞ ልጆች ግዴታ ነው ብዬ አምናለሁ።

የሰፊውን የኦሮሞ ሕዝብ ብሔራዊ ፍላጎት የሚፃረር አካሄዱንና ስራውን እየተቸን ነገር ግን በደህንነቱ ላይ ችግር እንዳይደርስ በሚቻለው መንገድ መርዳት አስፈላጊ ነው። ይህ የዜግነት ገዴታ እንዳለ ሆኖ የኦሮሞ ነፃነት ትግልን በሚመለክት ግን ይህ ትግል ከግቡ እስኪደርስ ድረስ፤ የኦሮሞ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱ እስክረጋገጥ ድረስ ይህ ትግል መቀጠል አለበትይህን የነፃነት ትግል ወደ ተፈለገው ግብ ማድረስ ብቻ ነው ለኦሮሞ ሕዝብና ብሔር የመጨረሻ መፍትሄና ዋስትና መሆን የሚችለው። ይህ ካልሆነ ሁሌም አደጋ ውስጥ እንኖራለን ማለት ነው። ሌላ መንገድ የመጨረሻ መፍትሄ የሚያመጣ አይመስለኝም። የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ በሚል ሽፋን ካሁን በኋላ የኦሮሞ ሕዝብ መታለል የለበትም። ጉዳዩም ቅድሚያ ማግኘት አለበት እንጂ መረሳት የለበትም። ተወደደም ተጠላ የዚህ ሕዝብ ጉዳይ ቅድሚያ ማግኝት የግድ ይሆናል።

በስተመጨረሽ በዚህ አጋጠሚ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ማስተላልፍ የምፈልገው፥ በእውነት ለዚህ ሕዝብ የምታስቡ ከሆነ (ለራሳችሁም ደህንነት ብላችሁ!!!) በኦሮሚያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ራሳቸውን አደራጅተውና ታጥቀው ያሉ ፀረ-ኦሮሞ ኃይሎች እንዳሉ ስለሚታወቅ፣ በአስቸኳይ ይህንን መረብ መበጣጠስ ካልቻላችሁ አደጋው በቅድሚያ ለእናንተ ከዚያ በኋላ ለሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ እንደሚሆን ተገንዝባችሁ ቶሎ አስፈላጊ እርምጃ እንድትወስዱ ኦሮሙማዊ መልዕክቴን መስተላለፍ እወዳለሁ። ሽፍቶች እያላችሁ በገዛ ወንድሞቻችሁ ላይ ጦርነት ከማወጅ፣ በጉያችሁ ስር ያሉትን ፀር-ኦሮሞ ኃይሎችን መቆጣጠር መቻል አለባችሁ። ባጭሩ በጉያችሁ ስር ያለውን እሳት ለማጥፋት ቅድሚያ ስጡ። የራሳችንን የቤታችንን ችግሮች ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሞክሩ።

ተመልሰን እስከምንገናኝ በደህና ቆዩ

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.