የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?  ሁለተኛ ዙር፥ ቁጥር ዘጠኝ

የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?  ሁለተኛ ዙር፥ ቁጥር ዘጠኝ

ብርሃኑ ሁንዴ, Adooleessa 12, 2019

jira

በሁለተኛ ዙር ቁጥር ስምንት ፅሁፍ ውስጥ የተሞከረውን መፈንቅለ መንግስት በሚመለከት ከዚህ ሙከራ በኋላ ምን ሊደረግ እንደሆነ፤ እንደዚሁም በኦሮሞ ብሔርተኝነትና በአማራ ብሔርተኝነት መካከል ያለውን ልዩነት በሚመለከት አንዳንድ ነገሮችን አቅርቤ ነበር። በዚህኛው ቁጥር ዘጠኝ ፅሁፍ ውስጥ ባሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ውስጥ እየተደረገ ያለውን በሚመለከት አንዳንድ ጉዳዮችን አቀርባለሁ።

የኦሮሞን ሕዝብ የሚከፋፍል ስራ እየተሰራ የኦሮሞን አንድነት እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?

ባሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተለያዩ ችግሮች እየደረሱ እንደሆነ ከአንዳንድ ሚዲያዎች ይሰማል። ይህ በአገሪቷ እየመጣ ያለው ለውጥ የኦሮሞ ሕዝብ በከፈለው ከባድ መስዋዕትነት መሆኑን ዓለም ሙሉ የሚያወቀው ጉዳይ ነው። በመሬት ላይ ያለው እውነታ ሌላ ቢሆንም፣ ይህ ያሁኑ መንግስት የኦሮሞ መንግስት ነው ተብሎ ይወራል። የኦሮሞ ሕዝብ ግን ዛሬም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኝ የማይካድ ጉዳይ ነው። የሚገርመው አንድ መንግስት የሕዝብ ነው ከተባለ፣ ሌላ ነገር እንኳን ቢቀር ቢያንስ ቢያንስ የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ወይም ማስጠበቅ መቻል ነበረበት። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም ሆነ የፌዴራል መንግስት ግን ይህንን እያደረጉ አይደሉም። ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ሕዝባችን ዛሬ በተለያዩ ምክንያቶች እየታሰረ፣ እየተገደለና ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረገ ነው ያለው።  በዚህኛው በዛሬው ፅሁፍ ውስጥ ከነዚህ ችግሮች ውስጥ አንዳንዶቹን ለመግለፅ እሞክራለሁ።

በእውነት እስቲ አሁን ኦሮሞ “አብን” የሚባለው የአማራ ድርጅት አባልና ደጋፊ ነው ተብሎ ይከሰሳል?

ይህ አብን የሚባለው ድርጅት የኦሮሞ ፀር እንደሆነ ብዙ የሚያመላክቱ ነገሮች እያሉ፣ ምን ዓይነት ኦሮሞ ነው በእውነት የዚህ ድርጅት አባል ወይም ደጋፊ ነው ተብሎ የሚጠረጠረው? ይህ ከእውነት የራቀና የሚደንቅ ነገር ነው። ኦሮምኛን የሚችል በኦሮሚያ ውስጥ የሚኖር አማራ ከሆነ ይህ ሌላ ጉዳይ ነው። ከዚህ ውጭ ግን በዚህ እያሳበቡ ኦሮሞን መከታተልና ማሰር ወይም ማስፈራራት በጭራሽ ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው። ይህ አብን የሚባል ድርጅት የኦሮሞን ሕዝብ ለመጉዳት ኦሮሚያ ውስጥ የተለያዩ ቡድኖችን አደራጅቶ ስንቀሳቀስ እንደነበረና እንዳለ ይነገራል። እነዚህ ዓይነቶቹን ፀረ ኦሮሞ ኃይሎችን ማሳደድ ነው እንጂ በዚህ ድርጅት ስም ኦሮሞን መጠርጠርና መወንጀል ተገቢ አይደለም። ጉዳዩ “ሊጣላ የመጣ ሰበብ አያጣ” እንደሚባለው ካልሆነ በስተቀር፣ ይህ በእውነት የሚያስቅም ጉዳይ ነው።

ዛሬም እንደ 1991 ኦነግን ለማዳከምና ከተቻለም ለማስወገድ ተብሎ የግንባሩ አባላትና ደጋፊዎች ዛሬም መታሰር አለባቸው?

በ1991/92 የነበረውንና ዛሬ በ2019 ያለውን ሁኔታ ሳወዳድር፣ ተመሳሳይነት እንዳላቸው ነው የምረዳው። በ1991 ኦነግና ኢሕአዲግ በጋራ የሽግግር መንግስት አቋቁመው 1992 ለሚደረገው አገራዊ ምርጫ ለመዘጋጀት ተስማምተው ነበር። ይሁን እንጂ ለዚያ ምርጫ በሚደረገው ዝግጅት ውስጥ ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆኑ የኦነግ አባላትና ዳጋፊዎች በገፍ ሲታሰሩና ሲገደሉም እንደነበር ታሪክ መስረጃ የሚሆን ሀቅ ነው። ያ ብቻ አልነበረም። ይህ ነው የማይባል ትልቅ አደጋ በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (WBO) ላይ ደርሶ በኦነግ ጎራ ትልቅ ኪሳራ እንዳስከተለ የሚታወስ ነው። ዛሬም በ2019 እየታየ ያለው ሁኔታም በ1991/92 ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት አለው። በ2018/19 ኦነግ ከመንግስት ጋር ስምምነት አድርጎ፤ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስኖ አመራሩም ወደ አገር ቤት ተመለሶ ለምርጫ እንዲዘጋጅ ተደረገ። ይሁን እንጂ ከተለያዩ ሚዲያዎች እንደሚሰማው፣ የኦነግ አባላት እንደ ፈለጉ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉና ከዚህም አልፎ አንዳንድ ቦታዎች የግንባሩ አባላትና ደጋፊዎች እየታሰሩም እንደሆነ ነው። በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በኩልም ከታየ፣ ልክ እንደ 1992 ይህንን ሰራዊት ለማጥፋት፣ ሌላ ስያሜ አውጥተውለት “ሽፍቶች” ተብለው ጦርነት ተከፍቶባቸው ይገኛል። ይህ እዚህ የምፅፈው ጉዳይ በመሬት ላይ የታየ ወይም የሚታይ እውነታ ነው እንጂ ለፕሮፓጋንዳ አይደለም እየፃፍኩ ያለሁት። ከዚህ በላይ ለተጠቀሱት ሁለት ዋና ዋና ነጥቦች ማስረጃ ካስፈለገ፣ ከተላያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ከተውጣጡ የኦነግ አባላት ጋር በቅርብ በONN ላይ የተደረገውን ቃለ ምልልስ ማየት በቂ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።

ወደ ፅሁፉ ዋናው ርዕስ ለመመለስ፣ ስለ ኦሮሞ አንድነት ያነሳሁበት ምክንያት፣ “የኦሮሞ ምሁራን ለሰላምና ለእድገት የሚደረግ ውይይት” ተብሎ በቅርብ በአዳማ ከተማ በተደረገው ውይይት ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት ኦቦ ሽመልስ የተናገረውን አስታውሼ ነው። በኦቦ ሽመልስ ንግግር ውስጥ አንዱ እንደ ዋንኛ ጉዳይ ትኩረት የተሰጠው የኦሮሞ ሕዝብ አንድነት ነው። ይህ ጥሩ ነገርና ሊደገፍም የሚጋባ ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ ባንድ በኩል ስለ ኦሮሞ አንድነት እያወሩ፤ በሌላ ብኩል ግን በኦቦ ሽመልስ በሚመራው የክልሉ መንግስት አመራር ስር የኦሮሞን አንድነት የሚፃረሩ ነገሮች መፈፀማቸው ባንድ እጅ እየገነቡ በሌላ እጅ ማፍረስ አይሆንም? እኔ እንደምታየኝ፣ OPDO የነበረ አሁን ግን ስሙን ወደ ODP የቀየረው ድርጅት የድሮውን ባሕርዩን ይዞ ያለ ይመስላል። አካሄዱ፣ ስልቱና ስትራቴጂው ከድሮው ጋር ይመሳሰላል። ይህ ጉዳይ በደንብ ካልታሰበበትና ካልተስተካከል፣ ይህ አካሄድ ለኦሮሞ አንድነት ትልቅ አደጋ ይሆናል።

በስተመጨረሻ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ በሚል ስምና ሽፋን እንደዚሁም የሕግን የበላይነት ማስጠበቅ በሚል አካሄድ እነዚህን ጉዳዮች ካባ በማድረግ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ተንኮልና ደባ መፈፀም የትም አያደርስም። የቤታችንን ችግሮች (የኦሮሞን ችግሮች) ለመፍታት በሰላማዊ መንገድ መሄድ ነው እንጂ ኣንዱ ሌላውን በኃልና ጉልበት ለማጥፋት መሞከር የመጨረሻ መፍትሄ አያመጣም። በመሆኑም፣ የኦነግን አባላትና ደጋፊዎችን ማሳደድና ማሰር እንደዚሁም የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላትን ሽፍቶች በማለት በነሱ ላይ ጦርነት ማድረግ ትክክል ስላልሆነ፣ የቤታችንን እሳት ማጥፋት ለሁሉም ይጠቅማል ብዬ አምናለሁ። ከዚህ ውጭ የሚደረገው ስራ ሁሉ በስተመጨረሻ ራስን ማጥፋት ይሆናል። እውነት ግን በስተመጨረሻ እንደምታሸንፍ ምንም ጥርጥር የለውም።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ በደህና ቆዩ

1 Comment

  1. mogni yemitichilewun; sibal gebito mistun debedebe yibalal. Sijimer talaku ye oromo hizib inezihin ye ingide lijoch(created by devilish Tplf not by safu) yashagirugnal bilo tesfa madiregu ijig asinewar sira nebere. Yihe dagimawi sihitete kezinib mar indemetebiki newu. Libeluat yefelegutin amora jigira nat ayinet tirikit hager yemitierawu begna newu yilhula andandi fezegnoch. Yih dirigit dagim lela yetifat miraf megabez inji lela minim ayihonim.
    New branded naz/tplf that systematically developed must stop such deragatory & stupid faking as usual.

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.