የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ አንድ

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?
– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ , Ebla 22, 2018                                            

ክፍል አስራ አንድ

Jaalatamoo fii kabajamoo urjii artii warraaqsa Oromoo Caalaa Bultumee fii Jaafar Yuusuuf yaadannoo Dirree Qabsoo hidhannoo WBO Wajjiin

ዛሬ ይዤ ወደ ቀረብኩት ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ለፅሁፎቼ አንባቢዎችና ተከታታዮች ኣንድ ነገር ይፋ ማድረግ እፈለጋለሁ። በአዲሱ ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ በሚመራው የወያኔ መንግስት ውስጥ የሚፈለገው ለውጥ መምጣት አይችልም በምልበት ጊዜ የዶ/ር አብይን ችሎታና ፍላጎት ጥያቄ ውስጥ ማስገባቴ አይደለም። ኦሕድድም ሆነ ዶ/ር አብይ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ባሁኑ ጊዜ ስልጣን የላቸውም፤ ቁልፍ የሆኑት ሁሉ ማለትም እጅግ ወሳኝ የሆኑት የመንግስት ተቋማት በወያኔዎች እጅ በመሆናቸው፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ አንድ ለውጥ እንደሚፈለገው ሊመጣ አይችልም ለማለት ነው። እኔ በግል ከድርጅቱም ሆነ ከግለሰቦች ምንም ጥላቻ የለኝም። እንደ ኦሮሞ ልጆች ለሁሉም እኩል ፍቅር ኣለኝ። የሰፊውን ኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት የሚፃረሩትን ግን እቃወማለሁ።

የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን መከበርና በስራም መታየት አለበት

እንደሚታወቀው የሕዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረ ሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በኢትዮጵያ ፍደራላዊ ሕግ መንግስት አንቀፅ 39 ላይ ተቀምጧል። የፈዴራሉ ሕገ መንግስታት በኣካሄድ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በስራ ባይታዩም፤ ይህን አንቀፅ ሁሉም ተስማምተውበት በወረቀት ላይ የተቀመጠ ነው። ይሁን እንጂ ኣንዳንድ ኃይሎች በተለይም ደግሞ የድሮው ስርዓት ናፋቂዎች ይህንን አንቀፅ 39 በፅኑ ይቃወሙታል። የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በዓለም ደረጃ እንኳን ተቀባይነት ያለው ጉዳይ በመሆኑ፣ ይህ ለኢትዮጵያ ብቻ የተደነገገ ሕግ አይደለም። ስለዚህ ይህንን ማክበር የሰው ልጅ ሰብኣዊ መብትን ማክበር ነው። የሰው ልጅ ሰብኣዊ መብት ደግሞ የትም ቦታ ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም።

ባሁኑ ጊዜ ያሉትን የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችን ካየን፣ እንደ ትግላቸው ዓላማ በሁለት ትላልቅ ቡድኖች ከፍለን ማየት እንችላለን። እነዚህም፥

  • ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ አገር በሚደረገው ሂደት ውስጥ የኦሮሞ ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ይችላል፤ ስለዚህ ይህች አገር ባንድነት መኖር ኣለባት ብለው የሚያምኑ
  • በዚህች ኢምፓየር ውስጥ ብሔሮችና ብሔረ ሰቦች በቅኝ ግዛት በመያዛቸው፤ ይህች አገርም በዚሁ በቅኝ ግዛት መልክ ስለተመሰረተች፣ ይህ ቅኝ ግዛታዊ ስርዓት ፈርሶ፣ ብሔርና ብሔረሰቦች ነፃ ወጥተው የራሳቸውን ነፃ መንግስታት ማቋቋም ኣለባቸው የሚሉ

የፖለቲካ ዓላማና ግባቸው የተለያየ ይሁን እንጂ እኔ እንደሚገባኝ ሁለቱም ቡድኖች ለኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት የቆሙና የሕዝቡንም መብት ለማስጠበቅ የሚሰሩ ወይም የሚታገሉ ይመስለኛል። የኦሮሞን ሰፊ ሕዝብ ፍላጎት የማይጠብቁ፣ የሕዝቡ መብት እንዲጠበቅ የማይሰሩ ደግሞ የዚህን ብሔር ወይም ሕዝብ ስም ይዘው መደራጀት የለባቸውም። በዚህ ሕዝብ ስም ሕዝባችን መሃል ውዥንብር መፍጠርም የለባቸው። ተወደደም ተጠላ የሰፊውን ኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት የሚፃረር በዚህ ሕዝብ ውስጥ መሰረት የለውም። የዚህን ሕዝብ ፍላጎት የማይጠብቅ የሕዝቡ ጠላት ነው። በመሆኑ የተላያዩ የፖለቲካ ዓላማ ቢኖራቸውም፣ የሕዝቡን ፍላጎት መጠበቅና የሕዝቡንም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱን ማክበር የግድ ይሆናል።

ለዚህ ለተለያዩ የፖለቲካ ዓላማዎች ምክንያት የሆነው ወይም የሚሆነው የኦሮሞ ታሪክና ብሔራዊ ጥያቄ አገላለፅ ይመስለኛል። በዚህ ላይ በተለይም በኦሮሞ ብሔራዊ ጥያቄ ላይ በደንብ የተግባቡበት አይመስለኝም። በዚህ የተነሳ አንድ የጋራ በሆነ የፖለቲካ ዓላማ ላይ ለመስማማት አስቸጋሪ ይሆናል። በሚኒሊክ የተደረገው ጦርነትም በተለያየ መንገድ ይገለፃል። ይሁን እንጂ ሚኒሊክ ይህችን አገር እንዴት እንደያዛትና እንደመሰረታት ሲታይ፣ ይህቺ አገር በቅኝ ግዛት መልክ የተቋቋመችና የአንድ ብሔር የበላይነት ሲነግስባት እሰከ ዛሬ የደረሰች አገር መሆኗ የማይካድ ነው። በመሆኑም ይህንን የቅኝ ግዛት መልክ ያለውን ስርዓት ማፍረስ አስፈላጊ ይሆናል። በዓለም ታሪክ ውስጥ እንደታየው የቅኝ ግዛት ስርዓት ማፍረስ ማለት ደግሞ የብሔሮች ነፃነትና የየራሳቸው ነፃ መንግስታትን ማቋቋም ማለት ነው።

በኢትዮጵያ መግባባቶች በሌሉበትና የሕዝቦች ጥያቄ በተለያየ መንገድ በሚተረጎምበት ሁኔታ ውስጥ ግን የመጨረሻ ውሳኔ የሰፊው ሕዝብ መሆን አንዳለበት የግድ ይሆናል። የሕዝቡ ፍላጎትና መብት መጠበቅ ኣለበትና። ባጭሩ የኦሮሞን ጥያቄ በተመለከተ ምን እንደሚፈልግ፣ እንዴት መኖር እንደሚፈልግና ከማን ጋር መኖር እንደሚፈልግ የሚወስነው ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ነው ማለት ነው። ይህንን የሚቃወሙት የዚህን ሕዝብ ፍላጎት የማይጠብቁና መብቱንም የማያከብሩ በመሆናቸው፣ እነዚህ የሕዝቡ ጠላቶች ናቸው። ባጠቃላይ የኦሮሞን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱን ማስጠበቅ የሁሉም የኦሮሞ የፖላቲካና ሌሎችም ኃይሎች ግዴታ ነው። ይሁን እንጂ ይሀኛው ወይም ያኛው የፖለቲካ ግብ ይሻለሃል ብለው ሕዝብን መቀስቀስ የሁሉም ድርጅቶች መብት ነው። የሁሉም መብት መጠበቅ ኣለበት ማለት ነው።

ስር ሰደው የመጡትን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት በሀሳብ ደረጃ ሦስት አማራጭ መፍትሄዎች አሉ። እነዚህም፥

                 ሀ) እውነተኛ የክልል ፌዴሬሽን (አሁን ባለው ላይ የተመሰረተ)
                 ለ) የብሔር/ብሔረ ሰቦች ነፃ መንግስታት
                 ሐ) የብሔር/ብሔረ ሰቦች  ነፃ መንግስታት ሕብረት

ከዚህ በላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ከነዚህ አማራጮች ውስጥ የሚስማማውን የሚመርጠው ግን ሰፊው ሕዝብ መሆን እንዳለበት ሊሰመርበት ይገባል።

ሀ) እውነተኛ የክልል ፌዴሬሽን (አሁን ባለው ላይ የተመሰረተ)

የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችና የነፃነት ግንባሮች በምያምኑበት መንገድ መስራት ወይም መታገል መብታቸው እንዳለ ሆኖ፤ ሕዝቡንም አሳምነው ከትግል ዓላማቸውና ግባቸው ጎን ማሰለፍም አንደዚሁ መብታቸውና ጥንካሬኣቸው ሆኖ፤ ነገር ግን እንደ ኣንድ እጅግ በጣም አንስተኛ አማራጭ (as a minimum requirement) ይህ አሁን ያለውን ስርዓት ወይ ስሩን ነቅሎ በመጣል ወይንም ደግሞ ለሕዝብ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ መልስ እንዲሰጥ ስር ነቀል ተሃድሶ በማድረግ፤ እውነተኛ የክልሎች ፌዴሬሽን ማቋቋም እንደ አንድ አማራጭ የፖለቲካ ግብ ሊታይ ይችላል። የዚህ የፖለቲካ አማራጭ ቅድመ ሁኔታ መሆን ያለበት ግን የኦሮሞ ብሔራዊ መሰረታዊ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ሳይሸራረፍ መልስ ማግኘት አለበት። ሳይሸራረፍ ሙሉ በሙሉ ያልኩትን ጉዳይ ሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ። ይህ ካልሆነ ትግሉ ይቀጥላል። ኢትዮጵያ የምትባለዋን አገር አሁን እንዳለች ከነ ዳር ድንበሯ ማቆየት የሚፈልጉት ሁሉ ይህንን የፖለቲካ አማራጭ መቀበል የግድ ይሆናል።

ለ) የብሔር/ብሔረ ሰቦች ነፃ መንግስታት

በጣም ቢያንስ በ ) ስር የተገለፀው አማራጭ የማይሳካ ከሆነ፤ የሕዝቦች ትግል በተለይም ደግሞ የኦሮሞ የነፃነት ትግል ተጠናክሮ መቀጠል የግድ ይሆናል። ትግሉ በዚህ መንገድ ከቀጠለ ደግሞ የመጨረሻ ግብ “ነፃይቷን ኦሮሚያ ማለትም የኦሮሞ ነፃ መንግስት” ማቋቋም ይሆናል። ይህ ሁለተኛው የፖለቲካ አማራጭ ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ፍላጎታቸው ከሆነ ለሁሉም የአገሪቷ ብሔርና ብሔረ ሰቦች ይሆናል ማላት ነው። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ግን የፅሁፎቼ ዓላማና ይዘት፣ ዋናው ርዕስ እንደሚያሳየው የኦሮሞ የነፃነት ትግልን ስለሚመለከት ለሌሎች ብሔርና ብሔረ ሰቦች አስትያየት መስጠት አልፈልግም። ይሁን እንጂ ይህ አማራጭ እንደ ሀሳብ ለሁሉም ብሔርና ብሔረ ሰቦች ሊሰራ ይችላል ብዬ ኣስባለሁ።

ሐ) የብሔር/ብሔረ ሰቦች  ነፃ መንግስታት ሕብረት

ነገሩ እንደ አበሾች ተረት “የሚለበስ የላት፣ መከናነብ አማራት”  አይሁንና፤ ይህንን አማራጭ ስራ ላይ ማዋሉ ከባድ ቢሆንም፣ እንደ ሀሳብ እንደ አንድ የፖለቲካ መፍትሄ ሊታይ ይችላል። ይህ የፖለቲካ አማራጭ በእውነት በጣም ሩቅ የሆነና ተግባራዊነቱም በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ቢሳካ ግን በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን የሚያመጣ፤ እንዲሁም ደግሞ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግና ወሳኝ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። አዚያ መድረስ ግን ከፊት ለፊት ያለውን ወንዝ ሳይሻገሩ ስለ ሚቀጥለው ወንዝ እንደ ማሰብ እንደሚሆን ይገባኛል። ነገር ግን እንድ ኣንድ አማራጭ ሀሳብ ማቅረብ ክፋት ወይም ስህተት የለውም፤ ነገር ማጋነንም አይደለም።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ሲታይ፣ የዚህ ዓይነት የብሔርና ብሔረ ሰቦች ነፃ መንግስታት ሕብረትን ማቋቋም ተግባራዊነቱ ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳል። የነፃ መንግስታት ሕብረትን ከማቋቋም በፊት እነዚህ ብሔርና ብሔረ ሰቦች እያንዳንዳቸው ለየብቻ ነፃ መንግስታት መመስረት ይኖርባቸዋል። ከዚያ በኋላ ነው ለምሳሌ እንደ አፍሪካ ወይም አውሮፓ ሕብረት፣ ወይንም ደግሞ እንደ ቀድሞቹ  የሶቭየት ህብረት አባል አገራት የሶሻልስት ህብረቱ ከፈረሰ በኋላ አንዳደረጉት፣ኣንድ ላይ ተመልሰው የኢትዮጵያ የብሔርና ብሔረ ሰቦች ነፃ መንግስታት ሕብረትን የሚያቋቁሙት ማለት ነው። ከላይም እንደተባለው፣  ይህችን አገር እንደ ጂኦግራፊዋ አቀማመጥ ባንድነት ለማየት ለሚፈልጉት ሁሉ እንደ አንድ ሌለኛው አማራጭ ሊታይ ይችላል። ይህ ካልሆነ ግን ይህቺ አገር ተበታትና ትቀራለች ማለት ነው።

እንደ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሱማሌ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል የመሳሰሉት ትላልቅ ብሔሮች ወይም ክልሎች የተወሰነ የመሬት አቀማመጥና ድንበር ስላላቸው፣ የየራሳቸውን የክልል ነፃ መንግስታት ለማቋቋም አያስቸግርም ይሆናል። ነገር ግን የአገሪቷ የደቡቡ ክፍል ብሔረ ሰቦች የተወሰን ወጥ የሆነ የመሬት አቀማመጥና ድንበር ስለ ሌላቸው፣ አሁን ባለው የደቡብ ክልል ላይ የተመሰረተ ካልሆነ በስተቀር የነፃ መንግስታት ማቋቋሙ ላይ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። እንግዲህ የትኛውም የፖለቲካ አማራጭ ሊተገበር የሚችለው፣ በሕዝቦች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ የመጨረሻ ውሳኔ የሰፊው ሕዝብ ይሆናል። የመጨረሻና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ግን ወሳኙ የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ/ለራስ የመወሰን መብት ሲከበርና ይህም ሲረጋገጥ ነው።  ይህንን ማረጋገጥ ደግሞ የሁሉም ግዴታ ይሆናል።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

10. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስር
9. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ዘጠኝ
8. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስምንት
7. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሰባት
6. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስድስት
5. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አምስት
4. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አራት
3. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሦስት
2. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሁለት
1. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አንድ

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.