የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ ሦስት

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ , Ebla 29, 2018

Jiraክፍል አስራ ሦስት

በፅሁፌ ክፍል አስር ውስጥ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ የአዲሱ ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ጉዳይ ኦሮሞዎችን በሀሳብ ለሁለት ከፍሎ የነበረው አሁንም በዚሁ እንደ ቀጠለ ነው። በዚያ ፅሁፌ ውስጥ ለማብራራት የሞከርኩት እንዳለ ሆኖ፣ ግን ጠ/ሚኒስተሩ በተለያየ ወቅት ስያደርግ የነበረው ንግግሮች እና እንዴት ስራውን እንደጀመረ በኦሮሞዎች መካከል ክርክሮችን ፈጥሯል። እንደኔ አመለካከትና ትኩረት ዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስተር ሆኖ ተመርጦ ስራውን ከጀመረበት ጊዜ ኣንስቶ የተለያዩ ስህተቶችን እንደሰራ የማይካድ ሀቅ ነው። የዶ/ር አብይ ስራዎችን በሚመለከት በዛሬው ፅሁፌ ውስጥ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማንሳት እሞክራለሁ።

ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይ የኦሮሞን ሕዝብ ሙሉ ድጋፍ ለማግኝትና በስራውም ጥሩ ውጤት ለማምጣት ምን ማድረግ ይኖርበታል?

የግሉ ፍላጎትና ዓላማ ምን እንደሆነ በደንብ ማወቅ አስችጋሪ ቢሆንም፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ኢሕአድግ ሊቀመንበርና የአገሪቷ ጠ/ሚኒስተር ለየትኛው ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት መፈለጉን ለሱ በመተው፤ ነገር ግን በሱ ላይ ዘመቻ ማድረጉን ትተን እንደ አንድ የኦሮሞ ልጅ ስህተቶቹን እንዲረዳና እንዲታረም እስቲ ትንሽ ጊዜ ሰጥተነው እንየው። ጊዜ እንስጠው ስል ሀሳቤ ለስራው ጊዜ ይሰጠው ከሚሉት ሰዎች ሀሳብ የተለየ ነው። እኔ ማለት የፈለኩት የሰራቸውን ስህተቶች አይቶና ተገንዝቦ ይህንን ለማረም እንዲችል ጊዜ ይሰጠው እያልኩ ነው ያለሁት። ይህ ደግሞ እንደ ኣንድ የኦሮሞ ልጅና ወንድም በማየት ነው።

ዶ/ር አብይ የአገሪቷ ጠ/ሚኒስተር ሆኖ ከተመረጠ በኋላ ጊዜ ሳይሰጥ የመጀመሪያ ሰራው መሆን የነበረበት አዲስ ካቢኔ አቋቁሞ፤ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች እንደ አንገብጋቢነታቸው በቅደም ተከተል አስቀምጦ፤ ይህንን በተግባር ማሳየት መጀመር ነበር። እንደሚታየው ያንን ማድረግ ትቶ፣ በየ ክልሎቹ በመዘዋወር ጉብኝት ማድረግ የመጀመሪያ ስራው አደረገ። ለምን ይህንን እንደሚያደርግ የራሱ ምክንያትና ዓላማ ይኖረዋል። በዚህ ላይ ያለኝን ግምት ግን ወደ ኋላ ላይ እመለስበታለህ። ይሁን እንጂ በአስቸኳይ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች መስራቱም ቀርቶ፤ እንዲያውም ኦሮሞን የሚያቆስሉ ኣንዳንድ ነገሮችን በንግግሮቹ ውስጥ እየወረወር፣ የኦሮሞ ሕዝብ ከሱ እምነት አንዲያጣ እያደረገ ነው። ይህ ነው ያ ነው ብዬ ሁሉንም እዚህ ማንሳት ስለማልፈልግ፣ ነገር ግን እነዚያን ስህተቶች ለማረም አሁን ጊዜ አለው።

በአስቸኳይ መሰራት ያለበት ስራ ምንድነው?

እንደሚታወቀው የኣስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (State of Emergency) በድጋሚ ስራ ላይ የዋለው፥ ሕዝቦችን ለማፈን፣ ሰላምና መረጋጋትን በማስጠበቅ ስም ተቃራኒ በሆነ መንገድ ሕዝብን ሰላም ማሳጣት፣ በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ ለማድረግ፣ ሰዎችን ለማሰርና ለማሰቃየት፣ ሴቶችን ለመድፈር፣ ለመግደል እና ንብረቶችን ለመዝረፍ ተብሎ ታስቦበትና ታቅዶ የተደረገ አዋጅ ነው። ይህንን እውነታ በኢሕአድግ ውስጥ የሚገኙት ሁሉ በሚገባ ያውቁታል። ይህ አዋጅ ደግሞ በይበልጥና በግንባር ቀደምትነት እየጎዳ ያለው የኦሮሞን ሕዝብ ነው። በኦሮሚያ ላይ ያነጣጠረ ነው። የቄሮን ጉልበትና ኃይል ለማዳከም ተብሎም የታቀደ ነው። ከአገሪቷ ሕዝቦች በይበልጥ ሰላም ያጣውም የኦሮሞ ሕዝብ ነው። በጅምላ እየታሰረና እየተሰቃየ ያለውም ይኸው ሕዝብ ነው። የጠ/ሚኒስተሩ አንገብጋቢና ዋናው የመጀመሪያ ስራው ይህንን ለሕዝብ ስቃይ የሆነውን አዋጅ ማስቆም ነበረ። ይህንን ለማስቆም ደግሞ አሁን ጉልበት ባይኖረውም እንኳን የአገሪቷ ሕገ መንግስት ስልጣን ይሰጠዋል። ይህንን ስልጣን መጠቀመ ነበረበት።

የኣስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሕዝብ ላይ እንዲነሳ ከተደረገና ሕዝቡም ሰላምና መረጋጋትን ካገኘ በኋላ ነበር የክልሎች ጉብኝት መሆን የነበረበት። ይህ የኣስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለመነሳቱ ይኸው ዛሬም በሕዝባችን ላይ ስቃይ እየደረሰ ነው ያለው። ይህ ሆኖ እያለ ለዚህ እጅግ አንገብጋቢ ለሆነው ችግር መፍትሄ ማግኘት ሲገባው፤ ዶ/ር አብይ ይባስ ብሎ በኦሮሞ ብሔርተኝነት ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማድረግ፣ ይህንንም ወደ መንደር ለመግፋት መሞከሩ በይበልጥ የኦሮሞን ሕዝብ እምነትና ድጋፍ እያጣ እንዲሄድ ያደርገዋል። ነገሩን ለማሳጠር ዶ/ር አብይ የሰፊውን ኦሮሞ ሕዝብ ሙሉ ድጋፍ ለማግኘትና አኩሪ ታሪክ ለመስራት ከፈለገ፣ የኣስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሕዝብ ላይ እንዲነሳ ማድረግ አለበት። ይህን ካላደረገ እሱ ራሱ የልታሰበና ያልተጠበቀ አደጋ ውስጥ መግባቱ የማይቀር ይሆናል። ለዚህ ትልቅ ሹመት ያበቃውም የኦሮሞ ሕዝብና የኦሮሞ ብሔርተኝነት ማደግ መሆኑን መርሳ የለበትም።

ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይ ክልሎችን የመጎብኘት ጉዳይ ለምን የመጀመሪያ ስራው ኣደረገ?

ጠ/ሚኒስተር ሆኖ ከመታጨቱና ከመመርጡ በፊት በተለያየ ወቅት ሲያደርጋቸው የነበሩትን ንግግሮች ካየን፣ የዚህ ሰው የኢትዮጵያዊነትን (Itoophiyummaa) ስሜት ምን ያህል እንደሆነ ለመረዳት አያስቸግርም። ኦቦ ለማ መገርሳን ጨምሮ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” እያሉ መናገራቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በመሆኑም በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ አይቶ የኣስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሕዝቡ ላይ እንዲነሳ ከማድረግ ይልቅ እሱን ያስጨነቀውና ያሳሰበው የኢትዮጵያ አንድነት ስለሆነ፣ የኦሮሞ ሕዝብ እየደማና እየሞተ በሚገኝበት ወቅት በየክልሎቹ በመዘዋወር ሕዝቦችን ማባበል ምርጫው ሆነ። በዚህ አካሄድ ውስጥ ደግሞ ባዕድን ለማስደሰትና እንሱን ወደ ራሱ ለመሳብ ብሎ የኦሮሞን ብሔርተኝነት እንኳን እስከ ማሳነስ ሞክሯል።

እኔ እያልኩ ያለሁት፥ ቅድሚያ ማግኘት ላለበት አንገብጋቢ ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት የግድ ይሆናል፤ ዶ/ር አብይ ከአብራኩ የወጣው ይህ የኦሮሞ ሕዝብ እየተጎዳ እየለ፤ ለዚህ ችግር አስቸኳይ መፍትሄ ማግኘት ይኖርበታል ለማለት እንጂ በየክልሎቹ በመዞር ሕዝቦችን ማነጋገር ወይም መወያየት ትክክል አይደለም ማለቴ አይደለም። ይህ መደረግም አለበት። ነገር ግን ጊዜውንን ተራውን መጠበቅ ነበረበት እያልኩ ነው ያለሁት። ይህ የግድ በስቸኳይ መሆን የነበረበት አይደለም ለማለት ነው። በሰው ልጅ ኑሮ ውስጥ እንኳን ቢታይ፣ አንድ ሰው ቤቱ እየፈረሰበትና ቤተሰቦቹም እየተጎዱ እያሉ መቸም ይህንን ትቶ ወደ ሌላ ሰው ቤት ሄዶ የሌላውን ቤት ከማፍረስ ለማዳንና የሌላውን ሰው ቤተሰብም ከጉዳት ለመከላከል የሚሞክር አይመስለኝም። በቅድሚያ የራሱን ቤተሰቦች ከጉዳት ውስጥ አውጥቶ፣ ከዚያ በኋላ ነው ለሌሎች እርዳታ ለማድረግ የሚሄደው እንጂ ቤተሰቦቹ ላይ ችግር እየደረሰበት እያየ ይህን ትቶ ወድ ሌላ አይሄድም ለማለት ነው። የዶ/ር አብይ ጉዳይ ከዚህ ምሳሌ ጋር ይመሳሰላል።

ዶ/ር አብይ ይህን የኦሮሞ ጉዳይ እንደ ዋዛ ማየት ትቶ፤ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት፣ በዚህ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እንዲቆም፣ የእስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ማድረግ መቻል አለበት። ይህን ካደረገ ስራውም በዚህ ስለሚለካ፣ የሰፊውን ኦሮሞ ሕዝብ ድጋፍ እያገኘ ይሄዳል። ይህን ካላደረገ ግን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ስቃይ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ዶ/ር አብይም ለውድቀቱ ሁኔታን እያመቻቸ ይሄዳል ማለት ነው። አኩሪ ታሪክ መስራት እየቻለ፣ መጥፎ ታሪክ ሰርቶ እንዳይቀር አሁን ያለውን አጋጠሚ በመጠቀም ለኦሮሞ ሕዝብ ካሳ መክፈል መቻል አለበት። ካሳውም በጣም ቢያንስ የኦሮሞን ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ነው። ይህ ሰላምና መረጋጋት የሚገኘው ደግሞ የእስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሕዝቡ ላይ ሲነሳና ሕዝቡም እፎይታ ሲያገኝ ነው።

በስተመጨረሻ፣ ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ስገልፅ እንደነበርኩ፣ የኦሮሞ ብሔራዊ መሰረታዊ ጥያቄ በኢሕአድግ ውስጥ በሚደረጉት ጥቃቅን ለውጦች (ይህ ራሱ የሚቻል ከሆነ??) መልስ ማግኘት እንደማይችል በድጋሚ ላሰምርበት እፈለጋለሁ። ይህ መልስ የሚገኘው የነፃነት ትግሉን አጠናክረው በመቀጠል፤ የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ/ለራሱ መወሰን ስችል ነው ብዬ አምናለሁ። በስብሶ እየፈረስ ባለው በዚህ በወያኔ ስርዓት ውስጥ ምንም ያህል ጥገናና ጥልቅ ተሃድሶ ቢደረግም፣ የኦሮሞን ጥያቄ ይመልሳል በዬ አላስብም።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

12. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?  ክፍል አስራ ሁለት
11. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ አንድ
10. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስር
9. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ዘጠኝ
8. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስምንት
7. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሰባት
6. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስድስት
5. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አምስት
4. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አራት
3. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሦስት
2. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሁለት
1. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አንድ

1 Comment

  1. Bla bla … change wouldn’t come true by talking and writing, barking etc otherwise anyone who talk do so with few sentences and more involve in action. Section one, section 2 …. what it is for these all?

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.