የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ ሁለት

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ, Ebla 24, 2018

ክፍል አስራ ሁለት

ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይ ሲያደርግ የሰነበተውን ንግግሮች በሚመለክት ሰሞኑን ብዙ ነገሮች ተሰምተዋል ተፅፈዋልም። ባንዳንዶቹ ላይ ሀሳቤን ከመስጠት ተቆጥቤ ነበር። ነገር ግን ሊታለፍ የማይችልና እንደ ዋዛም መታየት የማይችል የኦሮሞን ብሔርተኝነት የሚመለከት ኣንድ ጉዳይ ትኩረቴን ስለሳበ፣ በዚህ ላይ አጭር ሀሳብ ለማቅረብ ተገደድኩ። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ነገር ተብሏል። ይሁን እንጂ በዚህ እጅግ በጣም ወሳኝ በሆነው ጉዳይ ላይ ሀሳቤን ሳልሰጥበት አልተውም ብዬ የሚከተለውን ሀሳብ ይዤ ቀርቤኣለሁ።

የኦሮሞ ብሔርተኝነት የኦሮሙማ (Oromummaa) የእድገት ምልክት በመሆኑ ይህንን አሳንሶ ማየት ትክክል አይደለም

እንደ ራሴ አመለካከትና ግንዛቤ፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ከኦሮሙማ እድገት የመነጨ ነው። ባጭሩ ለመግለፅ፥ በኦሮሙማ የበሰለ፣ ኦሮሙማን በደንብ የተገነዘበ፣ ስለ ኦሮሙማ ጥሩ እውቀት ያለው፣ ኦሮሙማን የሚወድና ለኦሮሞ ሕዝብ ወይም ብሔር የሚቆረቆር ሰው ነው የኦሮሞ ብሔርተኛ ተብሎ ሊጠራ የሚችለው። ነገር ግን እዚህ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት በኦሮሙማ መብሰልና ኦሮሞ ሆኖ በመወለድ መካከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ ነው። ባጭሩ ይህንን ለመግለፅ ወይም ለማብራራት ስለ ኦሮሙማ ትርጉም ማንሳት አስፈላጊ ነው። ኦሮሙማ በሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ የተመሰረት ነው። (the three pillars of Oromummaa  እነዚህም፥

  • የኦሮሞ ባሕል
  • የኦሮሞ ታሪክ እና
  • የኦሮሞ ቋንቋ (Afaan Oromoo)

የነዚህ የሶስቱ ጉዳዮች እውቀት፣ ግንዛቤና ፍቅር መኖር ነው በኦሮሙማ መብሰልን የሚያሳየው። በኦሮሙማ መብሰል ደግሞ ወደ ኦሮሞ ብሔርተኝነት ይወስዳል ማለት ነው።

እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ከታየ፣ የኦሮሙማ ማደግ ነው ወደ ኦሮሞ ብሔርተኝነት ማደግ የሚወስደው። የኦሮሙማ ማደግ የኦሮሞ ማንነት ለዓለም ማህበረሰብ ግልፅና ይፋ እንዲሆን ያደርጋል። የኦሮሞን ማንነት ለዓለም ማሳወቅ ማለት ደግሞ፣ ኦሮሞን ያሳድጋል እንጂ ወደ መንደር ዝቅ እንዲል አያደርገውም። እውነታው በዚህ መንገድ ከታየ፣ በኦሮሙማ ላይ የተመሰረተ የኦሮሞ ብሔርተኝነት የኦሮሞን ብሔር ወይም ሕዝብ ከፍ ያደርገዋል እንጂ ዝቅ አያደርገውም። ታዲያ የብሔራችን ማደግ ነው እንደ መንደር ጉዳይ የሚታየው? ይህ እጅግ ባጣም ወሳኝ የሆነ ጉዳይ ነው እንደ ዋዛ ታይቶ ዝቅ ተደርጎ የሚገለፀው?

እስቲ ወደ ኋላ መለስ ብለን ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ አልፈን እዚህ እንደ ደረስን እንይ። ለተሰውት የነፃነት ታጋዮቻችን ምስጋና ይግባና፤ ያ በድሮው ስርዓት ወስጥ ከመረሳትም አልፎ ሞቶ ለመቀበር የመቃብር አፋፍ ላይ ደርሶ የነበረው ኦሮሙማ (የኦሮሞ ማንነት) ከዚያ ጥፋት ድኖ፣ እያደገም መጥቶ፣ የኦሮሞን ብሔርተኝነት አጠነከረ። በሺዎች የሚቆጠሩትን የኦሮሞ ብሔርተኞችን ማፍራት ቻለ። እነዚህ ብሔርተኞች ደግሞ ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን የኦሮሙማ ሶስት ምሰሶዎችን በማሳደግ፣ በ1991 ትላልቅ ድሎችን ማስመዝገብ ችለዋል። ኦሮሚያ በካርታ ላይ ተስላ በራሷ ቋንቋ (Afaan Oromoo) እንዲትተዳደር ተደርጋለች። የኦሮምኛ ቋንቋም የሚፃፍበት ለቋንቋው የሚስማማ ፊደል (Qubee Afaan Oromoo) ተወልዶ፣ ስራ ላይ ውሎ፣ ኣድጎ ይሀው በዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል። ከዚያም የቁቤ ትውልድ ተወለደ። ይህ ትውልድ ደግሞ ጭቆናን መሻከም እንቢ ብሎ ይሀው ጠላትን እያንቀጠቀጠው ይገኛል። ይህ ትውልድ ነው አዲሱን ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይን ለዚህ ትልቅ ሹመት እንዲበቃ ያደረገው።

ይህ ማለት ጉዳዩን አያይዘን ካየን፣ ዛሬ ኦሕድድ (OPDO) እንኳን ከእንቅልፉ እንዲነቃ፣ ቲም ለማ (Team Lemma) ተብሎ የሚጠራው ቡድን እንዲፈጠር፣ ዶር አብይ ደግሞ ከዚህ ውስጥ ለጠ/ሚኒስተርነት እንዲታጭና እንዲመረጥ ያደረገው እያደገና እያበባ የመጣው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ነው። ዶ/ር አብይ ለዚህ ለኦሮሞ ብሔርተኝነት ምስጋና መቅረብ ሲገባው፣ ይህንን ትቶ እሱኑ ራሱ ለዚህ ትልቅ ደረጃ ያደረስውን የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ዝቅ ኣድርጎ ወደ መንደር መግፋቱ በምን ጭንቅላት ብያስብ ነው? ምንድነው ለዚህ ደረጃ ያደረሰው? ባዕድን አስደስታለሁ ብሎ የገዛ ቤቱን ለማቃጠል እሳት እየለኮሰበት ነው? ይህ ቤት እንዲፈርስ ነው የምፈልገው? ለኦሮሞ ብሔርተኝነት መሰረት የሆነውን የኦሮሞ ማንነት እንዲጠፋ ነው የሚፈልገው? ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው እንደ ተባለውም፣  በዚህ ሱስ መርቅኖ በዚህ የተነሳ የኦሮሞን ብሔርተኝነት ወደ መንደር እየገፋ ነው?

እኔ ኦሮሞ ነኝ የሚል፣ ለኦሮሞ ሕዝብና ብሔር የሚቆረቆር፣ የኦሮሞን ማንነት የሚወድ፣ በኦሮሙማ የሚኮራ ሰው ከኦሮሙማ የሚመነጨውን ዝቅ ኣድርጎ ማየት እኔ አይገባኝም። ከዚህ በላይ እንደ ተገለፀው፣ ከኦሮሙማ የመነጨውን የኦሮሞ ብሔርትነኝነትን ዝቅ ማድረግ ማለት ኦሮሙማን ዝቅ አድርጎ እንደማየት ነው። የኦሮሙማ (የኦሮሞ ማንነት) ዝቅ መደረግ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብሔርተኝነት (የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት የሚባል ባይኖርም) መንገድ ያወጣል፣ በር ይከፍታል። ይህ ደግሞ እስከ ዛሬ በኦሮሞ ልጆች ደምና አጥንት የተገነባውን ሁሉ እንደማፍረስ ነው። ኦሮሞንና ኦሮሚያን አደጋ ውስጥ ይከታል። ስለዚህ በኦሮሞ ብሔርተኝነት መቀለድ ራሱ እንደ ጠላትነት ሊታይ የሚችል ነው። የኦሮሞ ብሔርተኝነት ቁልፍ ነው እንጂ ቀልድ አይደለም።

በኦሮሞ ብሔርነኝነት ላይ መዝመት ማለት በኦሮሞ ማንነት ላይ እንደ መዝመት ነው። ይህንን ሰፊና ትልቅ የሆነውን የኦሮሞ ሕዝብ ማሳነስ ነው እንጂ፣ በተቃራኒው እንደሚደርገው የኦሮሞ ብሔርነኝነት የኦሮሞን ሕዝብ ኣያሳነስም። የኦሮሞ ብሔርነኝነት የኦሮሞን ሕዝብ ለዓላም ያሳውቃል እንጂ ወደ መንደር ዝቅ ኣያደርግም። በዚህ ዓይነት መንገድ ማየት ትልቅ ስህተት ነው። በኦሮሞ ብሔርነኝነት ላይ መዝመት ማለት በኦሮሞና ኦሮሚያ ላይ መዝመት እንደሆነ መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ነገር ማጋነንም አይደለም። እየመጣ ያለውን አደጋ በሩቅ እንደ ማየት ነው እንጂ። ያለ ኦሮሞ ብሔርነኝነት የኦሮሞ የነፃነት ትግልም የሚፈለገውን ግብ መድረስ አይችለም። ትግሉ ከተፈለገው ግብ መቅረት ማለት ደግሞ ሌላ ዓይነት ጭቆናና ባርነት ውስጥ መግባት ነው።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

11. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ አንድ
10. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስር
9. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ዘጠኝ
8. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስምንት
7. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሰባት
6. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስድስት
5. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አምስት
4. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አራት
3. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሦስት
2. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሁለት
1. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አንድ

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.