የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ አምስት

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?
– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ, Caamsaa 15, 2018 

ክፍል አስራ አምስት

ከተለያየ ዜናና ኢንፎርሜሽን መረዳት እንደሚቻለው፣ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) የድርጅቱን የአመራር ኣባላት ልኡካን ወደ አዲስ አበባ (ፊንፊኔ) ለመላክ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ነው። ይህ ድርጅት ወደ አገር ቤት ተመልሶ ለመስራት ዓላማ እንዳለው ቀድሞዉኑ ስገልፅ የቆየ በመሆኑ፣ አሁን ለመግባት መወሰኑ አዲስ ነገር አይደለም። አይደንቅምም። ይሁን እንጂ፣ ይህ ድርጅት ባሁኑ ጊዜ በዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱን ሳስብበት፣ የተለያዩ ሃሳቦች በአእምሮዬ እንዲቀረፁ ያደርጋል። ስለዚህ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት በዛሬው ፅሁፌ ውስጥ ኣንዳንድ ነገሮችን ማንሳት አፈልጋለሁ።

ወያኔ በኦሕዲድ (OPDO) በስተጀርባ ተደብቃ እየሰራች ያለችውን ተንኮልና ደባ በደንብ የተረዳን አይመስለኝም

ወያኔዎች የኢትዮጵያን ሕዝቦችና ተቃዋሚ ድርጅቶችን በተለያዩ ስልቶች ከፋፍለው የግዛት ዕድሜኣቸውን ለማራዘም ጥረት ስያደርጉ እንደቆዩና እያደረጉም እንደሆኑ አዲስ ነገር አይደለም። በሃይማኖት ወይም እምነት፣ በክልልና በመንደር እንደዚሁም በፖለቲካ አመለካከት በመከፋፈል፤  የተቃዋሚ ድርጅቶች ጎራ (camp እንዲዳከም ማድረግ ችለዋል። ለዚህ ተንኮል ደግሞ የረጅም ጊዜ ልምድ ኣላቸው። አሁን ግን ከሕዝቦች አመፅና ንቅናቄ ማምለጥ እንደማይችሉ ስለተገነዘቡ፣ በኦሮሞ ሕዝብ ተቃውሞና ንቅናቄ ከእንቅልፉ በነቃው ኦሕዲድ (OPDO) በስተጀርባ ተደብቀው፤ አዲስ ተንኮልና ደባ እየሰሩ የሕዝብን ንቅናቄ ለማቀዝቀዝ ጥረት እያደረጉ ነው። ከነዚህ ተንኮልና ደባ ውስጥ አንዱና ዋንኛው በአገራዊ እርቅና ሰላማዊ ሽግግር ስም ለተቃዋሚዎች ጥሪ በማድረግ፣ በዚህ በኩል በሌላ ስልት ተቃዋሚዎችን ለመያዝ እየጣሩ ነው። ይህ ተንኮልና ደባቸው ግን ለሁሉ ሰው ግልፅ የሆነ አይመስልም።

አገራዊ እርቅና ሰላማዊ ሽግግር እንዴት ሊሳኩ ይችላሉ?

እውነት አገራዊ እርቅና ሰላማዊ ሽግግር የሚፈለግ ከሆነ፣ ለተቃዋሚ ድርጅቶች ጥሪ ከማቅረብና ለውይይት ከመጋበዝ በፊት በቅድሚያ መሰናክል መሆን የሚችሉትን ነገሮች ከመንገድ ላይ ማንሳት ነው። አንደኛውና ዋንኛው የእስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማንሳት ሲሆን፤ ሌላው በጠም ወሳኝ ጉዳይ ደግሞ የፀረ ሽብርተኝነት ህጎችን ማንሳት ነው። እነዚህ በቦታው እስካሉ ድረስ ምንም ዋስትና ስለማይኖር፣ ጥሪውን ተቀብለው ለውይይት መቅረብ ፍፁም አይቻልም። ሁለተኛከሁሉም የተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር መነጋገር ከፈለጉ፣ ከሁሉም ጋር በእኩልነት መነጋገር ነው እንጂ፣ ኣንዳንዶቹን ብቻ አየመረጡ በማንጋገር፤ ሌሎችን ወደ ጎን መተው ምንም ትርፍ የለውም። በተለይ ደግሞ እንደ ኦነግ የመሳሰሉትን የሰፊውን ሕዝብ ድጋፍ ያላቸውን አንጋፋና ትልልቅ ድርጅቶችን ትተው ትናንሽ ድርጅቶችን ብቻ ወደ ራሳቸው ለመሳብ መሞከር ለተንኮል ነው እንጂ በእውነት ለእርቅና ለሰላም አይሆንም የምል እምነት ነው ያለኝ።

እንደሚታወቀው በኦሮሚያ ሕዝብን ትጥቅ እያስፈቱ ነው። ይህ የሚደረግበት ምክንያት ደግሞ ሕዝቡ ከታጠቀ፣ ለወያኔዎችና ጀሌዎቻቸው አደገኛ እንደሚሆን ስለምያውቁ ነው። በተቃዋሚ ድርጅቶች በኩልም የትጥቅ ትግል የምያካሄዱትን ለይተው ልዘምቱባቸው፤ በተቃዋሚ ድርጅቶች መካከልም መከፋፈልና መጠራጠር እንዲኖር፤ አስቀድመው የትጥቅ ትግል የማይከተሉትን ድርጅቶች ወደ ራሳቸው በመሳብና በጉያቸው ስር ለማድረግ በሌላ ስልት እየሰሩ ነው። በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን የሚሉትም ድርጅቶች የትጥቅ ትግል የሚያካሄዱትን ድርጅቶ እንዲኮንኑ ያደርጋሉ። ይህንን ጉዳይና አካሄድ ደግሞ ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) የአመራር አባላት አንጋገርና ጥሪ በግልፅ መረዳት ይቻላል። እኛ ወደ አገር ቤት ገብተን ልንታገል ነውና እናንተም የትጥቅ ትግል የምታካሄዱት ይህንን ትታችሁ እንደኛ አድርጉ ለማለት እንደፈለጉ ግልፅ ነው። እንግዲህ በተቃዋሚ ድርጅቶች መካከል የሚፈጠረው መከፋፈል ከዚህ ይጀምራል ማለት ነው።

አድርባይነት ነው ወይስ የትግል እስትራቴጅና ስልት ነው?

እውነት ለመናገር የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) አቋም እኔ አይገባኝም። ለምን ይህን እንዳልኩት የተለያዩ ምክንያቶች አሉኝ። እስቲ ከቅርብ ጊዜ ትውስታ ኣንዳንድ ነገሮችን ለማንሳት እሞክራለሁ። ጊዜውን በደንብ ባላስታውስም፣ ከሁለት ዓመት በፊት ይመስለኛል የኦሮሞ ሕዝባዊ ንቅናቄ ስላስፈራቸው፣ በውጭ አገር ያሉት ኣንድ አራት የሚሆኑ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ኦዲግን ጨምሮ ማለት ነው የትግል አንድነት ለመፍጠር ወይንም ደግሞ አብሮ ለመስራት የሆነ ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር ትዝ ይለኛል። በዚያን ወቅት የሁሉም ድርጅቶች ተወካዮችም በOMN ላይ ማብራሪያም ሰጥተው ነበር። ያ ሆኖ እንዳለ ኦዲግ ይህንን ትቶ ወደ ባዕድ ጎራ (camp) በመሄድ ከነ ግንቦት 7 ጋር ትብብር ለመፍጠር ሲሰራ እንደ ነበር የሚታወስ ነው። ከዚያው ጋር በተያያዘ በቀርብ ጊዜ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ (Ethiopian National Movement) ተብሎ ከሚጠራ ድርጅት ጋር ይህንኑን ትብበር ለማጠናከር እየሰሩ እንደሆነ እረዳለሁ።

እንግዲህ እዚህ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች፥ ፩) ኦዲግ ባንድ በኩል ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የኦሮሞን ጨምሮ ማለት ነው ትብብር ለማድረግ እየፈለገ፣ በሌላ በኩል ግን ያን ሁሉ ትቶ ወደ አገር ቤት ለመሄድ ወይም ለመግባት አሁን መወሰኑ ለምንድነው? ፪) የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የትጥቅ ትግል ስለሚያካሄድና እኛ ግን ሰላማዊ የትግል መንገድ ስለምንከተል በዚህ አንስማማም እያሉ፣ ነገር ግን የባዕድ ጎራ ሄደው የትጥቅ ትግል እያካሄድን ነው ከሚሉት ድርጅቶች ጋር እንዴት ስምምነት ላይ መድረስ ቻሉ? ) አሁን ደግሞ ያን ሁሉ ትተው፣ አገር ውስጥ ያለው ሁኔታ ተመቻችቷልና፤ እናንተም የትጥቅ ትግል ትታችሁ፣ እንደኛ ወደ አገር ቤት ግቡ እያሉ ጥሪ ማቅረብ ለምንድነው? ፬) እነዚህ ሰዎች ለምንድነው እንደ እስስት የምቀያየሩት?  ትግል የተላያየ እስትራቴጂና ስልት እንደሚጠይቅ እንደዚሁም ደግሞ መገለባበጥም ፖለቲካ ውስጥ ኣንዳንዴ አስፈላጊ እንደሚሆን ያለ ነው። ይሁን እንጂ የነሱ ግን ልዩ ሆነብኝ።

ሌላ ደግሞ እንደ ኦዲግ አገላለፅ፣ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በፈረንጆች አቆጣጠር ግንቦት 11 እና 12  20018  ሁለት ቀን የፈጀ ውይይት እንደተደረገና በተጨማሪ ወደ ፊንፊኔ ሄደው ወይይቱን ለመቀጠል እንደፈለጉ ነው። እዚያ ሄደው ውይይቱን ለመቀጠል ለምን አስፈለገ? እዚሁ ለምን አልጨረሱም? ሁለት ቀናት በቂ አልነበሩም? እኔ እንደማስበው እነዚህ ሰዎች አሁን መናገር አልፈለጉም እንጂ፣ ሁሉንም ነገር ጨርሰው፣ ምናልባትም በአገር ቤት ቢሮ ለመክፈት እንደምሄዱ ይመስለኛል። ለማንኛውም መንገዱ ጥሩ ይሁንላቸው። ያሰቡት ይሳካላቸው እላለሁ እንደ ኣንድ የኦሮሞ ልጅ። ይሁን እንጂ ጊዜ የሚያሳየን ጉዳይ ቢሆንም፣ እኔ በነዚህ ሰዎች አካሄድ ላይ ጥርጣሬ ኣለኝ። ይህንን ጉዳይ ሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ።

በስተመጨረሻ፣ ወያኔዎች በኦሕዲድ (OPDO) በስተጀርባ ተደብቀው፣ በሰላምና እርቅ ጥሪ ስም ሌላ ተንኮልና ደባ እየሰሩ እንደሆነ መረዳትና መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው። አሁንም የወያኔዎችና ጀሌዎቻቸው ዓላማ በተቃዋሚ ድርጅቶች መካከል ጥርጣሬ እንዲኖር በማድረግ፣ ሌላውን ወደ ራሳቸው በመሳብ፣ ቀሪውን በተለይም የትጥቅ ትግል የሚያካሄዱትን ለይተው ለመምታት እንደሆነ ግልፅ መሆን አለበት። የኢትዮጵያ መንግስት ዓላማና ፍላጎትም ባንድ በኩል ሕዝቡን ትጥቅ እያስፈቱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የትጥቅ ትግል የሚያካሄዱት ድርጅቶችም ትጥቃቸውን ፈትተው፣ በወያኔዎች እጅ እንዲገቡ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር፣ እውነት አገራዊ መግባባት፣ እርቅና ሰላማዊ ሽግግር ለማምጣት አይመስለኝም። ይህንን ተንኮልና ደባቸውን ከግብ ለማድረስ የመጀመሪያ እርምጃ እንደነ ኦዲግ የመሳሰሉትን ኣንዳንድ ድርጅቶችን ወደ ራሳቸው በመሳብ በቀሪዎቹ ላይ ደባ በመስራት ነው። አስተዋይ የነገሩን መጨረሻ ከመጀመሪያው ያውቃል።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

14. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ አራት
13. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ ሦስት
12. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?  ክፍል አስራ ሁለት
11. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ አንድ
10. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስር
9. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ዘጠኝ
8. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስምንት
7. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሰባት
6. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስድስት
5. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አምስት
4. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አራት
3. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሦስት
2. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሁለት
1. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አንድ

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.