የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ ሰባት

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ , Caamsaa 23, 2018 

A D-Day for Lencho Leta. How much it is painful to land in self-inflicted Knightian uncertainty. Finfinne Bole International Airport, May 23, 2018

ክፍል አስራ ሰባት

የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ደርጅት (ኦሕዲድ) ከቅርብ ወራት በፊት ባደረገው የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ኣንዳንድ ውሳኔዎችን እንዳስተላለፈና የአቋም መግለጫ እንዳወጣ የሚታወስ ነው። ከነዚህ ውስኔዎች ወስጥ ኣንዱ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር መነጋገር እንደሚፈልግ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ይመስለኛል፣ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውይይት ኣድርጎ ይኸው አገር ቤት እንደሚገባና የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ኣባላት ፊንፊኔ እንደገቡ እየተነገረ ነው። በዚህኛው ክፍል ፅሁፍ ውስጥ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር የሚደረገውን ወይይት በሚመለከት ሀሳቤን ማቅረብ እፈልጋለሁ።

የኢትዮጵያ መንግስት ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ለመወያየትና ለመደራደር ማቀዱ ለተንኮል ነው ወይንስ  እውነት ስላምና እርቅ ፈልጎ ነው?

እንደ ርዕስ በተነሳው ጥያቄ ላይ አስተያየቴን ወይም ለጥያቄው መልስ ከመስጠቴ በፊት፣ ኣንድ የገረመኝ ነገር የጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይን አካሄድ በተመለከተ ኣንድ ነገር ማለት እፈልጋለሁ። እንደሚታወቀው ዶ/ር አብይ እንደ አገሪቷ ጠ/ሚኒስተር ከተመረጠ ይኸው ዘጠኝ ሳምንታት ሆኖታል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአገር ውስጥና በውጭ አገር በመዞር ጉብኝት እያደረገ ነው። በዚህ አካሄድ ውስጥ ትርፍ ተግኝቶ ሊሆን ይችላል፤ የማውቀው ነገር የለኝም። ወደ ውጭ አገር የመሄዱ ዋናው ዓላማው በውጭ አገራት የታሰሩትን የኢትዮጵያ ዜጎችን ለማስፈታት ነው ይባላል። ከነዚህ ታሳሪዎች ውስጥ ኣንዱ ደግሞ ሼክ ኣላሙድን ነው።

የታሰሩትን ዜጎች የማስፈታት ጥረት የሚደገፍ ቢሆንም፤ ነገር ግን በአገር ውስጥ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በየ እስር ቤቶች እየተሰቃዩ በሚገኙበት፤ በተጨማሪ ደግሞ ሌሎችም እየታሰሩ በሚገኙበት ወቅት፣ እነዚህን ማስፈታት ኣቅቶት፤ በነዚህ ላይ ዘሎ ወደ ውጭ አገር መሄዱ ለምን ኣስፈለገ? ጠ/ሚኒስተሩ እውነት ለዜጎች ተጨንቆ ነው ወይስ ሌላ ተልዕኮ ለማሳካት ይሆን? የኢትዮጵያ ዜጎች መታሰር የኢትዮጵያ መታሰር ነው ብሎ ስናገር ተሰምቷል። ታዲያ በየአገሪቷ እስር ቤቶች እየተሰቃዩ ያሉት ኦሮሞዎች የኢትዮጵያ ዜጎች አይደሉም ማለት ነው?

በ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም የኮማንድ ፖስቱ እንደ ፈለገ አሁንም አገሪቷን በተለይም ኦሮሚያን እያመሰ በሚገኝበት ወቅት፤ ቁጥራቸው ወደ ሚሊዮን የሚጠጋ የኦሮሞ ሕዝብ ከሱማሌ ክልል ተፈናቅለው አሁንም ከባድ ችግር ላይ በሚገኙበት ወቅት፤ ሕዝባችን አሁንም ሰላምና መረጋጋትን ባጣበት ወቅት፤ የለገ ደንቢ የወርቅ ችግር መፍትሄ እየፈለገ በሚገኝበት ወቅት፤ ይህንን ሁሉ ችግሮች በመርሳት ወይም ለነዚህ አንገብጋቢ ጉዳዮች ቅድሚያ ከመስጠት ፋንታ፣ የሼክ ኣላሙድን ጉዳይ ጨንቆት ለዚህ ጉዳይ ትኩረትና ቅድሚያ መስጠቱ ለምንድነው? ኣላሙድን የኦሮሚያን ንብረት እየዘረፈ ያለ፤ አካባቢን በኬሚካል አየበከለ ያለ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ለበሽታ እንዲጋለጥ ያደረገ ግለሰብ፤ በመሰረቱ ለፈፀመው ጥፋትና ወንጀል ተጠያቂ ሆኖ ለሕግና ፍርድ መቅረብ ያለበት ለዚህ ግለሰብ እንዲህ ተጨንቆ፤ እሱን ለማስፈታት ወዲያና ወዲህ ማለት ለምንድነው?

እንደሚታወቀው ከአገሪቷ እስረኞች ውስጥ ከሰማኒያ እጅ (80%) በላይ ኦሮሞ ናቸው። እነዚህ ውስጥ ደግሞ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩት የኦሮሞ ቀሮዎች ይገኛሉ። የኦሮሞ ቄሮ ደግሞ መራራ ትግል ኣድርጎ፤ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ፤ ኦሕዲድ (OPDO) ራሱ ከእንቅልፉ እንዲነቃ ያደረገ ነው። ኦሕዲድ በኢሕአዲግ (EPRDF) ውስጥ ቁልፍ ቦታ እንዲኖረው ያስቻለው የቄሮ ኦሮሞ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ነው። ዶ/ር አብይንም ለዚህ ትልቅ ሹመት ያበቃው የኦሮሞ ሕዝብ አንቅስቃሴና የቄሮ ኦሮሞ ትግል ነው። ጠ/ሚኒስትሩ ራሱ አየተናገር እንዳለው፣ ገና በሰባት ዓመቱ የኢትዮጵያ ሰባተኛ ንጉስ አንደሚሆን ህልም እንደነበረውና ይህ ህልሙ ደግሞ ይኸው ዛሬ በኦሮሞ ሕዝብና በቄሮ መራራ ትግል እውን ሆኗል። ታዲያ ጠ/ሚኒስትሩ ከኣብራኩ የወጣው የኦሮሞ ሕዝብ ብድር ይህ ሆኖ ዛሬ የዚህ ሕዝብ አንገብጋቢ ጉዳዮች ትኩረት ሳያገኙ ቀሩ?

እንግዲህ፣ ጠ/ሚኒስተሩን በሚመለከት ይህን ካልኩኝ በኋላ፣ ለዚህ ፅሁፍ ርዕስ ሆኖ ወደቀረበው ጥያቄ ለመመለስ፣ ከዚህ በፊትም በክፍል አስራ አምስት ፅሁፌ ውስጥ ለማብራራት እንደሞከርኩት፣ እኔ እንደሚመስለኝ የኢትዮጵያ መንግስት ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር እነጋገራለሁ ማለቱ እውነት ሰላም ለማምጣትና የለውጥ ሽግግር ለማመቻቸት ሳይሆን፣ ከዚህ አካሄድ በስተጀርባ ተንኮል እንዳለ ኣስባለሁ። ይህ መንግስት እውነት አገራዊ እርቅና (national reconciliation) ለስርዓት ለውጥ ለሚደረገው ሽግግር (transition to regime change) ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያስብ ቢሆን ኖሮ፣ ሦስተኛ ገለልተኛ አካል በሚገኝበት ሁሉንም የተቃዋሚ ድርጅቶችን ጋብዞ ማነጋገር በፈለገ ወይም ባደረገ ነበር። ነገር ግን ይህንን ከማድርገ ይልቅ ኣንዳንድ ድርጅቶችን ብቻ መርጦ ማነጋገርን መረጠ።

እውነት ነው፣ አሁን ያሉት የተቃዋሚ ድርጅቶች የተላያዩ የትግል ዓላማዎችና ግብ እንዳላቸው የማይካድ ነው። ኣንዳንዶቹ የሕዝቦች፣ የብሔሮችና ብሔረ-ሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንዲከበርና ይህም እንዲረጋገጥ የሚታገሉ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ አገር ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሕዝቦችና ብሔሮች ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ይችላል የሚሉ ናቸው። ኣንዳንዶቹ ደግሞ የድሮውን ስርዓት ለመመለስ የሚመኙም ኣሉ። እነዚህን ሁሉ ባንድ ጠረጴዛ ዙሪያ አምጥተው ለመወያየት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን መገንዘብ ኣያዳግትም። ምናልባትም ለዚህ ሊሆን ይችላል ትንሽ በዓላማ ከኢሕአዲግ ጋር የሚቀራረቡትን ድርጅቶች በቅድሚያ መጋበዝ አስፈላጊ የሆነው። በዚህ በኩል ከታየ ደግሞ ደረጃ በደረጃ መሄዱ አስፈላጊ ሊሆን ይችል ይሆናል። ለዚህም ሊሆን ይችላል እንደነ ኦዲግ የመሳሰሉትን ትንንሽ ድርጅቶችን በቅድሚያ መጥራት ያስፈለገው።

ይሁን እንጂ ይህ አካሄድ አደገኛ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት ኣለኝ። ሁሉንም የተቃዋሚ ድርጅቶችን ባንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ከማወያየት ይልቅ የተወስኑትን ብቻ ለይቶ ማነጋገር፣ በድርጅቶች መካከል ቅራኔ እንዲኖር ያደርጋል። የተቃዋሚዎችን አቅምና ጉልበት ለመከፋፈል ዕድል ይፈጥራል። የተቃዋሚ ድርጅቶች አንድነት አንዳይፈጠር ያደርጋል። የተቃዋሚዎች መቃረን ደግሞ ችግር ሆኖ ወደ ሕዝቦች ልያልፍ ይችላል። እንደነ ፌስ ቡክ (Face Book) በመሳሰሉት የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንደሚታይ፣ ለምሳሌ ያህል በኦዲግና ግንቦት 7 ድርጅት መካከል መተማማትና መወቃቀስ እየታየ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ይህ ችግር ደግሞ ወደ ሕዝቦች ተወስዶ፣ ኦዲግ የአማራን ሕዝብ እንደከዳ ሁሉ ተደርጎ እየተወራ ነው። ቀደም ብዬ ለማብራራት እንደሞከርኩት፣ ይህ ሁኔታ ደግሞ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ሃይል ሊያዳክም ይችላል። በተለይ ደግሞ ይህ አካሄድ በኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ቅራኔን ከመፍጠርም ኣልፎ የኦሮሞን ጉራ (camp) ልከፋፍልና ሊያዳክም ይችላል የምል እምነት ኣለኝ። የወያኔ መንግስት ደግሞ ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር ከመፈለግም ኣልፎ በተግባር እንዲታይ በፅኑ ይሰራል። ለዚህ ነው ይህ አካሄድ አደገኛ ነው ያልኩት።

ይህንን የወያኔ/የኢትዮጵያ መንግስት ተንኮል ለማክሸፍ ምን መደረግ ኣለበት?

የኢትዮጵያ ችግሮች ከመቶ ዓመታት በላይ ስር ሰደው እዚህ የደረሱ በመሆናቸው፣ በጣም የተወሳሰቡና ከባድ ናቸው። በዚህ በተወሳሰብ ሁኔታ ውስጥ የሕዝቦች ጥያቄ በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ብሔራዊ ጥያቄ  በቀላሉ መልስ ያገኛል ብሎ ማስብ አይቻልም። ይህንን ደግሞ ማንም መረዳት የሚችል ይመስለኛል። ይሁን እንጂ የኦሮሞ የነፃነት ትግል ፈተናዎች ብበዙበትም ወደ ፊት እንዲሄድ ምን መደረግ ኣለበት? የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሌሎች ኃይሎችስ ምን ይጠበቅባቸዋል? ለነዚህ ጥያቄዎችና ካላይ ለተነሳው ጥያቄ ያለኝን ሀሳብ በሚቀጥለው ፅሁፍ ይዤ እቀርባለሁ።

ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

16. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ ስድስት
15. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?ክፍል አስራ አምስት
14. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ አራት
13. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ ሦስት
12. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?  ክፍል አስራ ሁለት
11. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ አንድ
10. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስር
9. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ዘጠኝ
8. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስምንት
7. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሰባት
6. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስድስት
5. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አምስት
4. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አራት
3. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሦስት
2. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሁለት
1. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አንድ

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.