የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሃያ አንድ

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?
– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ, Waxabajjii 20, 2018

ክፍል ሃያ አንድ

ባለፈው ክፍል ፅሁፍ ውስጥ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጎራ (camp) ለምን መለያየት እንደተፈጠረና በዚህ የተነሳ ድርጅቶች ወይም ቡድኖች እንደበዙ ኣንስቼ ነበር። ከኦነግ በመለየት ለብቻ ወጥተው ቡድን ያቋቋሙትንም ሆነ ሌሎች የኦሮሚያ ነፃነት ኃይሎችን እስከማውቀው ድርስ ስማቸውን ዘርዝሬም ነበር። በዚህኛው ክፍል ፅሁፍ ውስጥ በቀሩት ሁለት ነጥቦች ላይ ሀሳበን ኣቀርባለሁ። የቀሩት ሁለቱ ነጥቦች፥

(2) አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ የትግል ዓላማና ግብ ያላቸው የኦሮሞ ድርጅቶች ለምን የትግል አንድነት መመስረት እንዳልቻሉ

(3) በኦሮሞ ሕዝብና ቄሮ በኦሮሞ ድርጅቶ ላይ መደረግ ያለበት ጫና ምን መሆን እንዳለበት

2) አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ የትግል ዓላማና ግብ ያላቸው የኦሮሞ ድርጅቶች ለምንድነው የትግል አንድነት መመስረት ያልቻሉት?

ባለፈው ክፍል ፅሁፍ ውስጥ ስማቸው ተዘርዝረው እንደነበረ፣ በፊት አንድ ኦነግ ውስጥ የነበሩትና አሁን ተለያይተው ለብቻ ያሉት ዋናውን ኦነግ ጨምሮ ባሁኑ ጊዜ አምስት ናቸው። እኔ እንደምገባኝ ከኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር (ኦዲግ) በተረፈ የቀሩት አራቱ ድርጅቶች አንድ የትግል ዓላማም ሆነ ግብ ያላቸው ይመስለኛል። ይህ የትግል ዓላማና ግብ በኦሮምኛ እንደሚገለፀው Bilisummaa Uummata Oromoo fi Walabummaa Oromiyaa “የኦሮሞ ሕዝብ ነፃነትና የኦሮሚያ ነፃ መንግስትን ማቋቋም” ነው። የትግል ዓላማቸው ኣንድ እስከሆነ ድረስ ደግሞ ኣንድ ላይ ተዋህደው ባንድ አመራር ስር አንድ ድርጅት መሆን ባይችሉም እንኳን የትግል አንድነት (unity of purpose) ፈጥረው አብረው መስራት ፍላጎት ብቻም ሳይሆን ግዴታም ጭምር መሆን ነበረበት። ይህን ማድረግ ቀርተው የምነጋገሩም አይመስለኝም። እንዲያውም ኣንዳንድ ጊዜ እንደሚሰማው የድርጅቶቹ አባላትና ደጋፊዎቻቸው ኣንዱ ሌላውን መተቸት ወይም ኣንዱ በሌላው ላይ ፕሮፓጋንዳ  ስያካሄዱ ይታያል።

ምንም ያህል የግል ችግሮች በመካከላቸው ቢኖርም፣ ለአንድ ዓላማ የተነሱት ታጋዮች ለአንድ ሕዝብ እስከቆሙና የኦሮሞን ሕዝብ ጭቆና ለማብቃት እስከፈለጉ ድረስ አንድነት ለመፍጠር ወይም አብሮ ከመስራት የሚያግዳቸው ምክንያት ለኔ አይገባኝም። አንድነት ከመፍጠር ፋንታ ለየብቻ ሆነው እውቀታቸውን፣ ችሎታቸውንና ንብረታቸውን (resources) መበታተን፤ ባጠቃላይ በዚህ መንገድ ኃይላቸውን ማዳከም ወደ መሸነፍ እንደሚያመራ ከነሱ የበለጠ የሚረዳ ኣለ ብዬ አላስብም። እኛ ቀድመን ስልጣን እንይዛለን ብለው የሚያስቡ ከሆነ፣ እነሱ የሚጣሉበት ስልጣን ባሁኑ ጊዜ የለም። እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅቶች ተወዳድረው ለምርጫ ለመቅረብ ቢሆን ኖሮ ተለያይተው መደራጀት ችግር የለውም። እንሱ ግን እንደ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ስለሚታዩ፣ ኣንድ ነፃ አውጪ ድርጀት ደግሞ ኣንድ ዓላማ ብቻ ነው ያለው። ይኸውም የቆመለትን ሕዝብና አገር ነፃ ማውጣት ነው።

ባለፉት ፅሁፎች ውስጥ በተደጋጋሚ እንደ ገለፅኩት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ድርጅቶች ጋር ውይይት ማድርግ እንደፈለገ ሲገልፅ ነበር። ይህ የመንግስት ዕቅድ እውነት ሰላምና እርቅን ፈልጎ ይሁን ወይንም ለተንኮል ይሁን ለማወቅ ያስቸግራል። ለተንኮል መሆን እንድሚችል ባለፉት ፅሁፎች ውስጥ ግምቴን ለመግለፅ ሞክሬ ነበር። ምክንያቱም ከኢትዮጵያ መንግስት ባሕርይ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ከዚህ ዕቅድ በሰተጀርባ ተንኮል መኖር ይችላል የሚል እምነት ስላለኝ ነው። የመንግስት ዕቅድ ምንም ይሁን ምን፣ ተንኮልን ለመቋቋምም ሆነ ለአንድ እውነተኛ ውይይት ከመቅረብ በፊት የኦሮሞ ድርጅቶች ኣንድነት መፍጠር ወይም ኣንድ የጋራ አቋምና አጀንዳ መያዝ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ወሳኝም ነው። ኣንድ የጋራ አቋምና አጀንዳ ይዘው ባንድነት ለውይይት ካልቀረቡና ብቻ ለብቻ የሚሄዱ ከሆነ ይህ ለሁሉም አደገኛ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ስገልፅ ነበር የቆየሁት።

እንድሚታወቀው የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ከትግል ዓላማቸው አንፃር ባሁኑ ጊዜ በሁለት ዋና ዋና ቡድኖች ተከፍለዋል።

1) የኦሮሚያ ነፃነት ኃይሎች ሲሆኑ እነዚህ ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነትና ለኦሮሚያ ነፃ መንግስት የሚታገሉ

2) የኦሮሞ የዲሞክራሲ ኃይሎች ሲሆኑ እነዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ዲሞክራሲ ከተረጋገጠ የኦሮሞ ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ይችላል ብለው የሚያምኑ

(እዚህ ላይ ለአንባቢዎች ግልፅ መሆን ያለበት በቡድን 1) ውስጥ የሚገኙት ድርጅቶች በዲሞክራሲ አያምኑም ለማለት ሳይሆን፣ እነዚህ ኃይሎች የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ለማስቻል የሚታገሉ መሆናቸውን ነው። የሕዝቦችን መብት ማስከበር የዲሞክራሲ አካል መሆኑ ግልፅ ነውና።)

የዓላማ አንድነት (unity of purpose) የመፍጠሩም ሆነ የጋራ አቋምና አጀንዳ ይዘው ከመንግስት ጋር ለውይይትና ድርድር የመቅረቡ አካሄድ ለሁለቱም ቡድኖች ኣንድ መሆን ኣለበት። በመሆኑም በሁለተኛ ቡድን ውስጥ መመደብ የሚችሉት ለምሳሌ እንደነ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (OFC) የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ODF) እና ተመሳሳይ የትግል ዓላማ ያላቸው ሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች ተመካክረው አስፈላጊ ከሆነ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው በዚህ መንገድ ኣንድ የጋራ አቋምና አጀንዳ ይዘው ከመንግስት ጋር ለውይይት መቅረብ ግዴታ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። ይህ ስልታዊና እስትራቴጂካዊ አካሄድ  በቡድን 1) ውስጥ ለሚገኙት ድርጅቶችም ተመሳሳይ መሆን አለበት። ይህም ማለት እነሱም የኦሮሚያ ነፃነት ኃይሎች ኮሚቴ (Committee of Oromia Liberation Forces) በማቋቋም በዚህ መንገድ የጋራ አቋምና አጀንዳ ይዘው ለውይይትና ድርድር መቅረብ ኣለባቸው ማለቴ ነው።

(3) በኦሮሞ ሕዝብና ቄሮ በኦሮሞ ድርጅቶ ላይ መደረግ ያለበት ጫና ምን መሆን አለበት?

ከመቶ ዓመት በላይ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ተጭኖ ከሚገኘው የጭቆና ስርዓት ለመውጣትም ሆነ የሕዝባችንን የወደፊት ዕጣ ለመወሰን ይህ ከላይ እንደ ንዑስ ርዕስ የቀረበው ጥያቄ በጣም ወሳኝ ነው። የኦሮሞ የነፃነት ትግል ጎራ (camp) ምን መሆን እንደሚችል የሚወስነው የኦሮሞ ድርጅቶች ጥንካሬና በግንባር ቀደምትነት ግን ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ በተለይ ደግሞ ቄሮ ኦሮሞ (Qeerroo Oromoo) ሁሉንም ነገር ለመቀየር ጉልበትም ሆነ አቅም እንዳላቸው ለዓለም እንኳን ኣሳይተዋል። የኦሮሞ ሕዝብ አንቅስቃሴና የቄሮ መራራ ትግል ነው ኦሕዲድ (OPDO) እንኳን በከፊሉም ቢሆን ከእስር ቤት እንዲለቀቅ ያስቻለው። ይህ እንቅስቃሴ ነው “ቲም ለማ (Team Lammaa)” ተብሎ የሚጠራውን የለውጥ ፈላጊ ቡድን ወደፊት እንዲመጣ ያደረገው። ይኸው እንቅስቋሴና ጫና ነው የአገሪቷ ጠ/ሚኒስተር ኦሮሞ እንዲሆን ያደረገው። ይህ እንቅስቃሴ ነው በዚህች አገር አዲስ የለውጥ አየር እንዲታይ ያደረገው። በመሆኑም የኦሮሞ ሕዝብና የቄሮ ኦሮሞ አቅም ማንኛውንም ነገር መቀየር እንደሚችል ጥርጥር የለውም።

የኦሮሞ ሕዝብ ነፃ ሆኖ የራሱን ዕድል በራሱ/ለራሱ መወሰን እስከሚችልበት ጊዜ ድረስ በሁለቱም የኦሮሞ ድርጅቶች ቡድኖች ላይ ጫና በማድረግ፣ አንድ የጋራ አቋምና አጀንዳ እስከምይዙ ድረስ ሕዝባችን በተለይ ደግሞ ቄሮ ከፍተኛ ጫና ማድረግ ኣለባቸው። ድርጅቶቻችም ሌላ አማራጭ ስለማይኖራቸው፣ የሚደረግባቸውን ጫና በመቀበል፤ የትኛውም ቡድን ይሁኑ የዓላማ አንድነት (unity of purpose) መፍጠር ገዴታቸው መሆኑን መረዳት ኣለባቸው። አለበለዚያ ጉዳዩ ጨው ለራስሽ ስትዪ ጣፍጪ፣ ኣለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሻል  እንደሚባለው ተረት ይሆናል። ያለንበትን ሁኔታ መረዳትና ሊመጣብን የሚችለውን አደጋ ከሩቁ ማየት በመቻል የሚያስፈልገውን ሁሉ ማድረግ የጊዜው ግዴታ ነው። ካለፈው ታሪክ ተምረው ወደፊት ለሚመጠው ራስን ማዘጋጀትም ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው።

በስተመጨረሻ ኣንድ መረሳት የሌለበትና ሁሉም መገንዝብ ያለባቸው፣ ሕወሃቶች (TPLF) ኣድፍጠውና በOPDO በስተጀርባ ሆነው የተለያዩ ተንኮሎችን እየሰሩ ወይም እያቀዱ እንደሆኑ ነው። OPDOን እንደ ድልድይ በመጠቀም ወደሚፈልጉት ለመሸጋገር ይሞክራሉ። ሕወሃት ጊዜው ኣልፎበታል፤ ካሁን በኋላ ምንም ማድረግ አይችልም ወዘተ ብሎ መናገር ስህተት ነው በዬ ኣምናለሁ። ምንጊዜም ቢሆን ጠላትን መናቅ ወደ መሸነፍ ይወስዳል። አሁን ለጊዜውም ቢሆን ወሳኝ የሆኑት ነገሮች በሕውሃቶች እጅ እንዳለ መዘንጋት የለብንም። በቀጥታም ሆነ በእጅ ኣዙር አሁንም ባላቸው ስልጣንና ጉልበት በመጠቀም ሁሉንም ወደነበረው ለመመለስ ለት ተቀን እየሰሩ እንደሆነ ከማንም የሚደበቅ አይመስለኝም። በሌላ በኮል ደግሞ ለኦሕዲድ (OPDO) ሁሉንም የፖለቲካ ፊልድ ነፃ ኣድርጎ መተው ወደማይሆን አቅጣጫ ሊወስደን እንድሚችልም መረዳት አስፈላጊ ነው።

ኦሕዲድ አሁንም በኦሮሚያ EPRDF/TPLFን የሚወክል ድርጅት እንጂ የኦሮሞን ሕዝብ የሚወክል ድርጅት ኣለመሆኑ ይህ እውነታ መታወቅ ኣለበት። ይህ ድርጅት እውነት የኦሮሞን ሕዝብ የሚወክልና የዚህ ሕዝብ ስቃይና መከራ የሚሰማው ቢሆን ኖሮ የዚህን ሰላም ወዳድ ታላቅ ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ በቻሉ ነበር። ሕዝባችን በየቀኑ እንደ ቅጠል ሲረግፍ ዝም ብለው ማየትን ባልመረጡ ነበር። ይህ ድርጅት ዛሬም ሆነ ነገ የዚህን ሕዝብ ስላምና ደህንነት ማስጠበቅ የሚችል አይመስለኝም። መሪዎቹም ቢሆኑ ጥሩ ንግግር ካማድረግና ለት ተቀን ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ከመዝፈን ውጪ ለኦሮሞ ሕዝብ ብዙ የሚጨነቁ አይመስሉም። በኦሮሞ ላይ የሚደርሰው ጉዳት አይታያቸውም። አንድ ሕዝብ ጦርነት ተክፍቶበት እየተጎዳ፤ የአገሪቷ አንድነት መጠበቅ ኣለበት ማለት ትርጉሙ ምንድነው? የOPDO መሪዎች ባንድ በኩል ጌታችን ሕዝባችን ነው እያሉ በሌላ በኩል የጌቶቻቸውን ሰላም ማስጠበቅ ካልቻሉ ንግግር ብቻውን ምን ያደርጋል? በመሆኑም ከኦሕዲድ በዙ ነገር መጠበቅ የዋህነት ነው። የነፃነት ትግሉ መቀጠል ኣለበት።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.