የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሃያ ሁለት

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?
– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ, Waxabajjii 21, 2018

Oromooክፍል ሃያ ሁለት

እንደሚታወቀው ቁቤ አፋን ኦሮሞ (Qubee Afaan Oromoo) የኦሮሞ ነፃነት ትግል ካስመዘገባቸው ድሎች ውስጥ ኣንዱ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ የማንነት ምልክት ሆኗል ቢባል ሀሰት አይሆንም። በመሆኑም እስቲ ዛሬ ቁቤን በሚመለክት ኣንዳንድ ጉዳዮችን ማንሳት እፈልጋለሁ። ስለ ቁቤ ብዙ ጊዜ በአእምሮዬ ቢመላለስም ይህንን ጉዳይ ዛሬ እንዳነሳ ያነሳሳኝ ኣንድ በዶ/ር ጉሉማ ገመዳ ስለ ቁቤ የቀረበ ፅሁፍ ነው። http://ayyaantuu.org/history-politics-qubee-alphabet/ ዶ/ር ጉሉማ የቁቤን ታሪክ በማንሳት በዙ ነገሮችን በስፋትና ጥልቀት አብራርተዋል። ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝን ሀሳብና አስተያየት መጨመር ፈልጌ ነው።

የኢትዮጵያን ኣንድነት መጠበቅ በሚል ስም ቁቤን ለማጥፋት መሞከር የኦሮሞን ማንነት ማጥፋት ነው 

ብዙውን ጊዜ የኦሮሞ ነፃነት ትግል ጠላቶችና አጋሪዎቻቸው የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር የኦሮሞን ማንነት የሚገልፁትን ሁሉ ለማጥፋት ስሞክሩ ይታያሉ። ለምሳሌ ያህል ባሁኑ ጊዜ  በቋንቋ ክልሎች ላይ የተመሰረተውን የፌዴራሊዝም ስርዓትን (current ethnic based federal structure) የሚቃወሙት ዋንኛው ምክንያት ኦሮሚያን በካርታ ላይ ማየት ስላልፈለጉ ነው። ይህን ማየት ለነሱ ትልቅ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል። ይህን ማጥፋት የማይቻል ከሆን ደግሞ በሌላ መንገድ ሌላ ሙከራ በማድረግ በኢትዮጵያ ኣንድነት ስም ቁቤ ኣፋን ኦሮሞ በግዕዝ ፊደላት እንዲተካ ለት ተቀን ስንከራተቱ ይታያሉ። በኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴና በተለይ ደግሞ በቄሮ ኦሮሞ (Qeerroo Oromoo) ትግል ወደ ፊት የመጡት የኦሮሞ ተወላጅ መሪዎች እንደነ ኦቦ ለማ መገርሳና ዶ/ር አብይ አህመድ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” እያሉ ስለዚህች አገር ኣንድነት በተደጋጋሚ ስለምናገሩ፣ በኦሮሙማ (Oromummaa) ላይ ዘመቻ ለሚያደርጉት ኃይሎች ሞራል ይሆናቸዋል። ለዚህም ነው ፍላጎታቸውን ለማሟላት ብለው እንደዚህ ደፍረው በኦሮሞ የማንነት መገለጫ በሆኑት ላይ ግልፅ ዘመቻ የሚያካሄዱት።

ስንትና ስንት ጥናት ተደርጎበት፤ በስተመጨረሻ ለኦሮሚኛ ቋንቋ መፃፊያ እጅግ ኣመቺ መሆኑ ተረጋግጦ ስራ ላይ የዋለው ቁቤ የተመረጠው ኦሮሞ ከግዕዝ ፊደላት ጥላቻ ስላለው ሳይሆን፣ የግዕዝ ፊደላት ጭራሽ ኦሮሚኛን ለመፃፍ ስለማይመቹ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ። በቁቤ ላይ ዘመቻ የሚያካሄዱት አውቀውም ይሁን ባለማወቅ ይህንን እውነታ መቀበል አይፈልጉም። እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች በኢትዮጵያ ኣንድነት መጋረጃ በስተጀርባ ሆነው የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት እንቅልፍ ያጣሉ። ይህ ዓላማቸው ደግሞ የአማርኛን ቋንቋ የበላይነት ለማስጠበቅ ተብሎ ነው እንጂ ለአንድ ቋንቋ የሚመች ሌላ ፊደል መምረጥ የአገሪቷን ኣንድነት የሚጎዳ አይመስለኝም። ያለው እውነታ ይህ ነው። ያም ሆነ ይህ ቁቤን ኣጥፍተው በግዕዝ ፊደላት መተካት ይህችን አገር ወደ መፍረስ ይወስዳል እንጂ ኣንድነቷን ማስጠበቅ በፍፁም አይችልም። ወደዱም ጠሉ ይህንን እውነታ ተቀብለው፣ ከቁቤ ላይ ቆሻሻ እጃቸውን ማንሳት ኣለባቸው።

ኦቦ ለማና ዶ/ር አብይ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር በሌላ መንገድ ያረጋግጡ እንጂ፣ ቁቤን ለሚቃወሙት ግለሰቦችና ቡድኖች አጋር በመሆን፣ ይህንን ፍላጎታቸውን በስራ ላይ የሚያውሉ ከሆነ ከአብራኩ ከወጡት የኦሮሞ ሕዝብ መለየት ብቻ ሳይሆን የዚህን ሕዝብ ታሪክ ማበላሸትም ይሆናል። ከተጠያቂነትም ልድኑ አይችሉም። ይህን ማወቅ ኣለባቸው። የኦሮሞ ነፃነት ትግል አስከ ዛሬ ያስመዘገባቸውን ድሎች ለማፍረስ የሚሞክር ማንኛውም ኃይል የሰፊው ኦሮሞ ሕዝብ ጠላት በመሆኑ፣ ይህን ሕዝብ ኣሸንፎ ዓላማውን ከግብ ማድረስ አይችልም። ኦቦ ለማና ዶ/ር አብይ ኣንድ መዘንጋት የሌለባቸው ጉዳይ እነሱንም ለዚህ ደረጃ ያደረሳቸው በቁቤ የተማሩና “የቁቤ ጄኔሬሽን – Qubee Generation ተብሎ የሚጠራ አዲሱ ትውልድ ነው። በመሆኑም ቁቤን ለማጥፋት የሚሰሩ ከሆነ ከዚህ ትውልድ ጋር እንደምጣሉም ማወቅ ኣለባቸው ማለት ነው። በኦሮሞ ልጆች ደምና አጥንት የተገኘውን ይህንን ድል ማጥፋት ያለ ምንም ጥርጥር የኦሮሞ ሕዝብና ብሔር ጠላት መሆን ነው።

ባለቤቱ ቀንዱን የሰበርው በሬ ሌላው አይኑን ያጠፋል

ከኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ መረዳት እንደሚቻለው፣ የኦሮሞ ጠላቶች ኦሮሞን ማሻነፍ የቻሉት በራሳቸው ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ኦሮሞን በኦሮሞ በመያዝ ነው። የኦሮሞን የነፃነት ትግል እንኳን ብንወስድ፣ ይህ ትግል ከግቡ ሳይደርስ የቆየው ወይም የሚቆየው በጠላት ኃይልና ጥንካሬ ሳይሆን ለጠላት አጋር በሆኑት ኦሮሞዎች ምክንያት ነው። የፅሁፌ አንባቢዎች እንዲገነዘቡ የምፈልገው ኣንድ ጉዳይ የኦሮሞን ማንነት የሚታከብር ኢትዮጵያ ብትመሰረትና ኣንድነቷም ቢጠበቅ እኔ ችግር የለብኝም። በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮሞ “ኦሮሙማን Oromummaa” በማስጠበቅ ለአገሪቷ ኣንድነት ከሰራም ችግር የለብኝም። ነገር ግን ኦሮሙማን የሚጎዳ ነገር እየሰሩ የአገሪቷን ኣንድነት ለመጠበቅ የሚታገሉ ሁሉ የኦሮሞ ጠላት እንደሆኑ ለማንም ግልፅ መሆን ኣለበት። ቁቤ አፋን ኦሮሞ ደግሞ ኦሮሙማን ከሚያንፀባርቁ ነገሮች ኣንዱ በመሆኑ፣ ቁቤን ማጥፋት ማለት ኦሮሙማን ማጥፋት ማለት ይሆናል።

ኦሮሞ የኦሮሞን ጉዳይ ካበላሸ ጠላት ደግሞ ይህን ጉዳይ እስከነጭራሹ ለማጥፋት ይጥራል። ለዚህም ነው በሬን የሚመለከት ይህ አባባል ወይም ተረት እንደ ንዑስ ርዕስ የተቀመጠው። ቁቤን ለማበላሸት ሙከራ እንደተደረገና በኦሮሞ ብሔርተኞች ጥረት እንደ ከሸፈ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የቁቤን የፊደላት ቅደም ተከተል ለመለወጥ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ስለቀረ፣ አሁን ደግሞ በሌላ መንገድ መጥተውብን፣ እስከነአካቴው ቁቤን ለማጥፋት ዘመቻ እያደረጉ ነው። ከላይ ለመጥቀስ  እንደሞከርኩት ይህ ደግሞ ኣለ ምክንያት አይደለም። ባሁኑ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ኣንድነት ጩኸት ከኛው ሰዎች ተነስቶ አገሪቷን እያዳረሰ ነው ያለው። በዚህ በተፈጠረው ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ለጠላትና ደጋፊዎቻቸው በር ስለሚከፈት በዚህ በተመቻቸ መንገድ የኦሮሞ ጉዳይ ውስጥ ገብተው ፍላጎታቸውን ለማሟላት ወይም ዓላማቸውን ለማሳካት ዕድል ያገኛሉ።

በስተመጨረሻ ለኦቦ ለማ መገርሳና ለዶ/ር አብይ አህመድ በዚህ አጋጣሚ ማስተላለፍ የምፈልገው ወንድማዊና ኦሮሙማዊ መልዕክት፥ የኢትዮጵያዊነት ሱስ አንደያዛችሁ በቻላችሁት መንገድ ለዚህች አገር መስራት መብታችሁ ነው። ይሁን እንጂ ኣንድ የማይካድ እውነታ እናንተ ለአገሪቷ ኣንድነት ለት ተቀን ስትንከራተቱ የኦሮሞ ሕዝብ ግን በየቀኑ በጠላት ቅጥረኞችና ሽፍቶች  እየተገደለና ከቤትና ንብረቱ እይተፈናቀለ ይገኛል። ስለዚህ የዚህን ሰላም ወዳድ ታላቅ ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የማትችሉ ወይም የማትፈልጉ ከሆነ፣ ብያንስ የኦሮሞ የነፃነት ትግል እስከ ዛሬ ያስገኛቸው ድሎች አንዳይነኩ ይህን መጠበቅና ማስጠበቅ የኦሮሙማ ግዴታችሁ ነው። ምንም ቢሆን ከኦሮም ሕዝብ አብራክ ስለወጣችሁ ማለቴ ነው። ይህ ሕዝብ ነው ኣብልቷችሁ፣ ኣጠጥቷችሁና አሳድጎኣችሁ ዛሬ ለደረሳችሁበት ደረጃ ያበቃችሁ። የዚህ ሕዝብ ትልቅ ውለታ ኣለባችሁ ማለት ነው። ቁቤ ኣፋን ኦሮሞን ማጥፋት ማለት የኦሮሞን ማንነት ማጥፋት ማለት ነው። ቁቤ የነፃነት ምልክትም ነችና።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.