የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስምንት

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ, Ebla 11, 2018

Oromo Nationalism continues to flourish

ክፍል ስምንት

በክፍል ሰባት ፅሁፍ ውስጥ የወያኔ መንግስት ጠ/ሚኒስተር ኦሮሞ ስለሆነ የኦሮሞ ብሔራዊ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንደማይችል፤ ምናልባትም በአዲሱ ጠ/ሚኒስተር ሊደረጉ በሚችሉት ጥቃቂን ለውጦች (ይህም ራሱ የሚቻል ከሆነ ማለት ነው?) የኦሮሞ ሕዝብ ዳግም መታለል እንደሚችል እና በዚህ ምክንያት እንደ እሳት እየተቀጣጠለ ያለው ሕዝባዊ አመፅ ለጊዜውም ቢሆን መቀዝቀዝ እንደሚችል ኣንዳንድ ነጥቦችን ኣንስቼ ለማብራራት ሞክሬ ነበር። በዚህኛው ክፍል ስምንት ፅሁፍ ውስጥ የኦሮሞ የነፃነት ትግል ጠላቶች እየሰሩ ያሉትን ኣንዳንድ ተንኮልና ደባ ኣንስቼ መግለፅ እፈለጋለሁ።

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ጠላቶች ተንኮልና ደባ ለጊዜው እንቅፋት መፍጠር ይችላሉ እንጂ፣ ትግሉን ከሚፈለገው ግብ ማስቀረት አይችሉም

እንደሚታወሰው በክፍል ሁለት ፅሁፌ ውስጥ የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ጠላቶች ማን እንደሆኑ ለመግለቅ ሞክሬ ነበር። እዚያ ያነሳሁትን እዚህ ደግሜ ማንሳት አስፈላጊ ባይሆንም፣ በዚያኛው ፅሁፍ ውስጥ ካጠቀስኳቸው ውስጥ የውጭ ጠላቶችን በመውሰድ፣ በዚህ ላይ ኣንዳንድ ነገሮች ማለት እፈለጋለሁ።

ወያኔ እየሰራች ያለችው ተንኮልና ደባ

በአስቸኳይ የጊዜ አዋጅ (SoE) ስም በመላው ኦሮሚያ በአጋዚ ወታደሮች ሕዝባችንን እየገደሉ፣ እያሰሩ፣ እያሰቃዩ፣ ከአገር እንዲሰደዱ እያደርጉ ያሉት እንዳለ ሆኖ፤ ቅርብ ጊዜ ወያኔ አንድ ሌላ ተንኮል ሰርታ ነበር። ይሀውም በኦሮሞ ሽማግሌዎች ስም የተወሰኑትን ሰዎች ከኦሮሚያ ለቃቅማ፣ በገንዘብ አታላ፣ ወደ መቀሌ በመላክ የሰላም ኮንፈረንስ በሚል የፕሮፓጋንዳ ስብስባ ላይ የተወሰኑ ጥቂት ሰዎችን ስታስጨፍርና መሪዎቿም በዚህ ላይ አብረው ስጨፍሩ ታይተዋል። ወያኔ ይህን ያደረገችው የዓለምን ማሕበረ ሰብ ላማታለልና ይሀው እኛ የኦሮሞ ሕዝብ ወዳጆች ነን፤ የኦሮሞን ሕዝብ ባህል እንወዳለን፣ እናከብራለን በማለት የሕዝቦችን ትኩረት ለመሳብ ያደረገችው ሸር ነው። ለኦሮሞ ሕዝብ ግን ይህ በቁስል ውስጥ እንጨት መስደድ እንደሚባለው ነው። በቁስል ላይ ቁስል መጨመርም ነው።

ጤናኛ አእምሮ ያለውና በደንብ ማሰብ የሚችል ሰው ይህ ግልፅ ተንኮል አንደሆነ መረዳት የሚያዳግተው አይመስለኝም። እስቲ ልብ በሉ፣ ባንድ በኩል ሕዝባችን በተከፈተበት የዘር ማጥፋት ጦርነት ከቀን ወደ ቀን እንደ ቅጠል እየረገፈ በሚገኝበት ባሁኑ ጊዜ፤ በሚሊዮን የሚቆጠር የኦሮሞ ሕዝብ ከሱማሌ ክልል ከቀዬና ንብረታቸው ተፈናቅለው፣ ለረሃብና በሽታ ተጋልጠው በምገኙበት ባሁኑ ወቅት፣ በአስቸኳይ የጊዜ አዋጅ ስም በሺዎቹ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ሕዝብ ወድ ጎረቤት አገር በተሰደዱበት ወቅት፣ የተወሰኑትን ሰዎች ሰብስባ ማስጨፈር በሕዝባችን ደምና አጥንት መቀለድ አይደለም? ይህ ለሕዝባችን ያላቸው ይህ ነው የማይባል ትልቅ ንቀት ነው። እነዚህ ሰዎች የኦሮሞን ሕይወት እንደ ዝንቦች ሕይወትም ማየት አልቻሉም። ታዲያ ከነዚ ጋር ነው የነሱኑ መንግስ ተብዬው የኦሮሞ ጠ/ሚኒስተር ይህንን ስርዓት ጠጋግኖ ለውጥ በማምጣት የሕዝባችን ሰላም የሚጠበቀው? ይህ ጊዜ የሚያሳየን ጉዳይ ነው።

የወያኔ ሞግዝቶችና ደጋፊዎች ተንኮልና ደባ

ኣንዳንድ ኢንፎርሜሽን አንደሚያሳየው፣ የውጭ ኃይሎች በተለይም ደግሞ በ1991 ለንደን ከተማ ተደርጎ በነበረው ኮንፈረንስ ላይ ተንኮል ሰርተው፣ ወያኔዎች ወደ ስልጣን እንዲመጡ ያደርጉትና ሞግዚት ሆነው እስከ ዛሬ ሲረዷቸው የቆዩት፤ የሕዝቦች እንቅስቃሴ በተለይም ደግሞ የኦሮሞ ሕዝባዊ አመፅና እንቅስቃሴ እየጠነከረ መምጣትንና መቆም እንደማይችል በመገንዘባቸው፤ ወዳጆቻቸው ወያኔዎች እንዳይጎዱ ሌላ ደባ እየሰሩ ነው። አሁንም እንደ 1991 ለወያኔዎች የሚመች ቅድመ ሁኔታ ለማዘጋጀት ጥረት እያደርጉ መሆናቸው ይፋ ወጥቷል።

አዘጋጅተው ልጠቀሙበት ያቀዱት ይህ ቅድመ ሁኔታ በእርቅ ስም የሽግግር መንግስት ለማቋቋም እናግዛችኋለን፤ ነገር ግን ወያኔዎች እስከ ዛሬ ለተፈጠሩት ጥፋቶች እንዳይጠየቁ ዋስትና ይሰጣቸው የሚሉ ይመስላል። ይህ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነው። በነሱ አገር አንድን ሰው የገደለ ሰው እንኳን ቶሎ በዕለቱ ተይዞ ወድ እስር ቤት ይገባና፤ ከዚያ በኋላ ሕጋዊ ውሳኔ ይሰጠዋል። በነሱ አገር የሰው ሕይወት ትልቅ ትኩረት ኣለውና። የኦሮሞ ግን አንድ ሰው ሳይሆን በሺዎች እየተገደሉ፤ በሺዎች የሚቆጠሩት ከአገር እንዲሰደዱ ሲደረጉ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከቀዬኣቸውና ቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ፤ ሺዎቹ  የት እንደገቡ በማይታወቅበት፤ ሺዎቹ በየእስረ ቤቶች እየተሰቃዩ በሚግኙበት…….. ይህ እንዴት እንደ ዋዛ ታይቶ፣ ይህን ሁሉ ጥፋት የፈፀሙት ዋስትና ይገባቸዋል ይባላል?

በሌላ በኩል ደግሞ፣ አንድ ሁሉን አቀፍ ኮንፈረንስ ለማዘጋጀትም እቅድ እንዳላቸውና ከወያኔዎች ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነ ተሰምቷል። የወያኔዎችን ፈቃድ የሚጠብቁ ይመስላል። ይህ አካሄዳቸው ለኦሮሞ የነፃነት ትግል አደገኛ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም አሁንም እንደ 1991 በደንብ ሳንዘጋጅበት በሚደረገው አዲስ ተንኮል የኦሮሞ የነፃነት ትግል ወደማይሆን አቅጣጫ እንዳይሄድ ስጋት ስላለኝ ነው። የኦሮሞ የነፃነት ትግል ጠላቶች ብዙ እንደሆኑ በግልፅ እየታየ ነው። የኦሮሞ የነፃነ ትግል የውጭ ጠላቶች ይህንን ተንኮልና ደባ እየሰሩ በሚገኙበት ጊዜ፣ የውስጥ ጠላቶች ደግሞ ስተባበሩኣቸው፤ ይህ ትግል ወዴት እንደሚያመራ ለመገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም። ለነፃነት ትግላችን እጅግ ብዙ እንቅፋቶች እየበዙ በመሆኑ፤ ኦሮሞ ከምንጊዜውም የበለጠ ነቅቶ የጠላትን ተንኮልና ደባ ማክሸፍ አለበት። ይህ ካልሆነ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ልንገባ ነው ማለት ነው።

የውጭ ጠላቶች የተለያዩ ሴራዎችን ሲሸሪቡ፤ የውስጥ ጠላቶች ደግሞ ለነሱ አጋር ይሆናሉ፤ ስግብግቦችና ጥቅማ ጥቅም ኣሳዳጆች በሺዎች ብቅ ብቅ ይላሉ፤ እውነተኛ የነፃነት ታጋዮች ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ይደረጋል፤ ለነፃነት ትግሉ የመጨረሻ ግብ መስዋዕትነት እየከፈሉ ባሉት ታጋዮች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዘመቻ ይደረጋል፤ የታጋዮች ሞራል እንዲሰበር ይጥራሉ፤ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን እንቅፋት ይሆኑባቸዋል። ይህ ደግሞ በአምስተኛ ማርሽ እየሄደ ያለውን የሕዝብ ትግል በሁለተኛ ማርሽ እንዲሄድ ያደርጋል። ይሁን እንጂ የፍትሕና ነፃነት ትግል ይቆያል እንጂ ከግቡ አይቀርም። ይህ እውነታ ለጠላትም ሆነ ዘመድ ግልፅ መሆን አለበት።

እውነተኛ የኦሮሞ ብሔርተኞችና የነፃነት ታጋዮች ወደኛ እየመጣ ያለውን አደጋ በሩቅ በማየት፣ እኛ ጋ ደርሶ ሳያንቀን፣ ይህንንም ትግል ወደ ሌላ አቅጣጭ እንዳይወስድ፣  የኦሮሞና ኦሮሚያ የወደፊት ዕጣ ፋንታ ጥያቄ ውስጥ አንዳይገባ፣ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ አንድነት በመፍጠር፣ የጠላቶችን ተንኮልና ደባ ማክሸፍ የኦሮሙማ (Oromummaa) ግዴታ ነው። ይህ የነፃነት ትግል ኣንዴ በመቀዝቀዝ፣ ኣንዴ በመጠንከር ብዙ ውጣ ውረዶችን ኣልፎ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል። ካሁን በኋላ የፈለገውም ተንኮልና ደባ ቢሰራ ይህንን የፍትሕና  ነፃነት ትግል ከተፈለገው ግብ የሚያስቀር ኃይል አንደማይኖር ጥርጥር የለውም። ሌሎች የጠላት ስራዎችንና እንደዚሁም ባሁኑ ወቅት በአገራችን ኦሮሚያ እየተደረጉ ያሉትን በሚመለክት በሚቀጥለው ፅሁፍ ሀሳቤን ይዤ እመለሳለሁ።

ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

7. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሰባት
6. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስድስት
5. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አምስት
4. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አራት
3. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሦስት
2. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሁለት
1. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አንድ

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.