የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ዘጠኝ

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?
– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ, Ebla 15, 2018

Kabajaa Guyyaa Gootota Oromiyaa keessati, Ebla 15, 2018

ክፍል ዘጠኝ

በቅድሚያ ባጠቃላይ ለኦሮሞ ልጆች በተለይ ደግሞ ለኦሮሞ ብሔርተኞችና ታጋዮች እንኳን ለ2018 የታጋዮቻችንና ጀግኖቻችን መታሰቢያ ቀን ኣደረሳችሁ። ይህንን ታሪካዊ ቀን በሚመለክት በዛሬው ፅሁፌ ውስጥ የኦሮሞ የነፃነት ትግልና ግብ ምን እንደሆነ በራሴ አመለካከት ኣንዳንድ ጉዳዮችን ማንሳት እፈልጋለሁ፣

የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ዓላማና ግብ ምንድነው?

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት የኦነት ዋንኛው ዓላማና የኦሮሞ ሕዝብ ብሔራዊ መሰረታዊ ጥያቄ በኔ አመለካከት የአገር ባለቤትነትን ማረጋገጥ ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ይህንን ጉዳይ እንደ መግንጠል በመውሰድ ይህ የአገር ባለቤትነት ጥያቄ እንዳይነሳ በመሸፋፈን የኦነትን ዓላማና ግብ በሌላ መንገድ ለማብራራት ሲሞክሩ ይታያሉ።

የትግሉን ጅምርና መነሻ ለታሪክ ፀሓፊዎች በመተው፣ ነገር ግን ኣንዳንድ ሰዎች እንደሚገልፁት ኦነት የተጀመረው ካዛሬ 40 ዓመት ወይም 50 ዓመት ወይንም 3 ዓመት በፊት አይደለም። በተደራጀና በተቀነባበረ መልክ ባይሆንም ኦነት የተጀመረው የኦሮሞ ሕዝብ በጠላት ተወሮ ነፃነቱና አገሩ በኃይል ከተወሰዱበት ጊዜ ኣንስቶ ነው። ከዚህ ታሪካዊ እውነታ ተነስተን ካየን ደግሞ ባጭሩ የኦነት ዋንኛው ዓላማ በጠመንጃ የተወሰደበትን የአገር ባለቤትነትን መልሶ ማግኘት ነው። ይህ የአገር ባለቤትነት ከተረጋገጠ ደግሞ ሌሎች ጥያቄዎችም በዚህ ውስጥ ተጠቃለው መልስ ያገኛሉ ማለት ነው።

ኣንዳንድ ሰዎች የኦነትን ዓላማና ግብ ወይንም ደግሞ የኦሮሞን ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄን ሲገልፁ ይህ በሦስት ነገሮች ላይ እንደተመሰረተ ወይንም ሦስት ነገሮች እንደሆኑ ስገልፁ ይታያል ወይም ይሰማል። እነዚህም፥ ) ኦሮሞ በመሬቱ ላይ ባለ መሬትና በንብረቱ ላይ ባለንብረት እንዲሆን፤ ) ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር እና ) የማንነት ጥያቄ ናቸው። የአገር ባለቤትነት ጉዳይ ከተነሳ እንደ መገንጠል ስለሚወሰድ ይህንን ለመሸፋፈን ተብሎ ነው እንጂ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱ ጥያቄዎች በአገር ባለቤትነት ውስጥ ልጠቃለሉ የሚችሉ ናቸው። ስለዚህ ዛሬ ባለንበ ሁኔታ ውስጥ የኦነትን ዓላማና ግብ በሌላ መንገድ ለመተርጎም መሞከር ውዥንብር ይፈጥራል ብዬ ኣስባለሁ።

የኦሮሞ ነፃነት ትግል ዓላማና ግብ ወይንም የኦሮሞ ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄ ለዘመድም ሆነ ጠላት በግልፅ መቀመጥ አለበት። በፖለቲካዊ ታክቲክና እስትራቴጂ ስም ነገሮችን ሸፋፍኖ ማለፍና ከእውነት የራቀ ነገር ማንፀባረቅ ሌላ ችግር ሊያመጣ ይችላል። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ መጠንቀቅ አለብን። ይህ ስንትና ስንት መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል እንደ ዋዛ የሚታይ አይደለም። ይህን ያህል መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል ደግሞ የተፈለገውን ግብ መድረስ የግድ ይሆናል። ከየት እንደተነሳን፣ ለምን እንደተነሳንና የት መድረስ እንደምንፈልግ ካላወቅን፤ ለምን እንደተነሳን፣ ወዴት እንደምንሄድና የት መድረስ እንደምንፈልግ ማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል።

የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) መቸ ነው የሚፈፀመው?

ይህንንም ጥያቄ በተመለከት የተለያዩ ሀሳቦች ይንፀባረቃሉ። እነዚህም፥ ) ትግሉ የሚፈለገው ግብ ደርሷል፤ ) ኣንዳንድ ድሎችን አስመዘገበ እንጂ አልተፈፀመም ወይም ከግብ አልደረሰም፤ ) ትግሉ በተነሳበት ቦታ ቆሞ ነው ያለው የሚሉ ናቸው። የኔ ሀሳብ ከሶስቱ ውስጥ ሁለተኛው ወይንም ) ውስጥ ቢሆንም፣ የትግሉን መፈፀም በተመለከተ ኣንዳንድ ነገሮችን ማለት እፈልጋለሁ።

አንድ ትግል ባጠቃላዩ ሲታይ፣ የነፃነት ትግልም ይሁን፣ የአገር ግንባታ ትግልም ይሁን፣ የኑሮ ትግልና የመሳሰሉትም ይሁን የሚፈፀም ወይም የሚያልቅ አይደለም። በመሆኑም ትግል ይፈፀማል የሚለው አባባል ራሱ ትክክል አይደለም። ከኦነት ጋር አያይዘን ካየን ግን ይህ ትግል የሚፈፀመው የጭቆናና ባርነት ስርዓት ሲወገድ ብቻ ነው። የጨቋኝ ስርዓት ተወገደ የሚባለው ደግሞ፣ የሕዝቦች ነፃነት ሙሉ በሙሉ ሲረጋገጥና ከዚህም ጋር በተያያዘ የአገር ባለቤትነት ሲረጋገጥ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ። የሕዝቦች አመፅና ንቅናቄም የሚቆመውና መሰረታዊ ጥያቄኣቸው የሚመለሰው ወደድንም ጠላንም፣ ኣመንም አላመንም ሕዝባችን የራሱን ዕድልና ዕጣ ለራሱና በራሱ መወሰን ስችል ነው።

ከዚህ በላይ በ )) ስር የተጠቀሱትን ሀሳቦች ካየን፣ ሁለቱም እውነት አይደሉም። ምን ማለቴ ነው? ይህ ትግል ከግቡ ደርሷል የሚሉት ሰዎች አዲሱ ጠ/ሚኒስተር ኦሮሞ በመሆናቸው ከዚህ ጋር አያይዘው አይተውት እንደሆነ ይህ ትልቅ ስህተት ነው። ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ እንደገለፅኩት አንድ ኦሮሞ ጠ/ሚኒስተር ሆኖ አራት ኪሎ ገባ ማለት የኦሮሞ ሕዝብ ብሔራዊ ጥያቄ ተመለሰ ወይንም ይመለሳል ማለት በፍፁም አይቻልም። በኔ አመለካከት ለኦሮሞ ጥያቄ መልስ መስጠት ቀርቶ እንዲያውም በዚህ በተፈጠረው ምክንያት የነፃነት ትግሉ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳይሄድ ስጋት አለኝ። ለምን ከተባለ፣ ምናልባትም ኣንዳንድ ጥቃቂን ለውጦችን  በማሳያት፤ በነዚህ ሕዝባችንን በማታለል ከዋናው የትግል ዓላማ ማዘናጋት ይሆናል የምል ግምት ስላለኝ ነው።

ትግሉ በተነሳበት ቦታ ነው ያለው የሚሉትም የወቅቱን ሁኔታና እየተደረግ ያለውን አልተገነዘቡም ማለት ነው። ይህንን ሀሳብ የሚያንፀባርቁት ምናልባት ከ1991 በኋላ ለውጥ የለም ብለው አስበው ከሆነ ይህ ትንሽ ተቀባይነት የሚያገኝ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ኦነት የተፈለገውን ግብ ባይደርስም በ1991 ትላልቅ ድሎችን አስመስግቧል። ከዚያ በኋላ ግን ያገኘናቸው ድሎች እነዚህ ናቸው ብለን ለመናገር አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ብዙ ለውጦች እንደታዩና እየታዩም እንደሆነ የማይካድ ነው። ስለዚህ ይህ ትግል እዚያው በተነሳበት ቦታ ቆሟል ማለት ትክክል ስላልሆነ፣ በዚህ ጉዳይ የሕዝባችንን እና የታጋዮቻችንን ሞራል መስበር ትክክል አይደለም። ኣንድም ይሁን ሁለት፣ ይነስም ይብዛ ይህ ትግል ባስመዘገባቸው ድሎች መደሰትና በዚህም መኩራት አለብን እንጂ ጀግኖቻችንና ታጋዮቻችን የወደቁለትን ድል አሳንሶ ማየት ተገቢ አይደለም።

ሌላው እንኳን ቢቀር ማለትም የኦሮሞ ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄ መልስ ሳያገኝ ቢቀርም እንኳን በአገር ውስጥና በውጭ አገር የተደረጉት ሕዝባዊ እንቅስቋሴ በተለይም ደግሞ በቄሮ ኦሮሞ (Qeerroo Oromoo) የተደረጉት ፊልሚያና የተገኙት ድሎች እንደ ዋዛ መታየት የለባቸውም። ኦሕድድ (OPDO) እንኳን የሚመካበትም አዲሱ የኦሮሞ ጠ/ሚኒስተር ራሱ የዚህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ውጤት ነው። ሌላም መረሳት የሌለበት ጉዳይ የዓለም ማህበረ ሰብና የውጭ መንግስታት ለኦሮሞ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ትኩረት መስጥት መጀመራቸውም ራሱ አንድ ትልቅ ድል ነው። እንደ ልዩ ምሳሌ ከወሰድን የአሜሪካ መንግስት እስከ ዛሬ ድረስ ወያኔዎችን ተንከባክበው አሳድገው እዚህ ደረጃ ያደረሱት እንኳን ቀስ በቀስ ከወያኔዎች ፊታቸውን እያዞሩ በመሆናቸው፣ ይህ ራሱ የሕዝባችን አመፅና እንቅስቃሴ ውጤት ነው።

የዛሬውን ፅሁፍ ለማጠቃለል፣ የኦሮሞ ሕዝብ ብሔራዊ ጥያቄ መልስ ማግኘት የሚችለው የአገሪቷ ጠ/ሚኒስተር ኦሮሞ በመሆናቸው እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። ባንዳንድ ጥቃቅን ለውጦች ሕዝባችንን አታለው፤ እንደ እሳት እየነደደ ያለው ሕዝባዊ ንቅናቄ እንዳይበርድ፤ የነፃነት ትግሉም ከተፈለገው ግብ አንዳይቀር፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን እስከሚችልበት ይህ ትግል በተጠናከረ መልክ መቀጠል አለበት። ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትግሉን ማፋፋም ጊዜው አሁን ነው። የመጨረሻው ድል የጭቁን ሕዝቦች ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎትም እንደሚሟላ ጥርጥር የለውም። በዚህ ትግል ውስጥ የወደቁት ጀግኖቻችን ሁሌም ታሪክ ያስታውሳቸዋል። እነሱ የወደቁለት ዓላማም ከግብ ይደርሳል።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

8. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስምንት
7. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሰባት
6. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ስድስት
5. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አምስት
4. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አራት
3. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሦስት
2. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል ሁለት
1. የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አንድ

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.