የኦሮሞ ፍልስፍና: የተግባቦት ፍልስፍናዊ ዘዴ (Ilaa fi Ilaamee Philosophic Method of Philosophy), ክፍል ፻

የኦሮሞ ፍልስፍና: የተግባቦት ፍልስፍናዊ ዘዴ (Ilaa fi Ilaamee Philosophic Method of Philosophy), ክፍል ፻

By Yoseph Mulugeta Baba, PhD, September 27, 2019

የተግባቦት ፍልስፍናዊ ዘዴ ሀገር-በቀል ሥነ-ዕውቀታዊ እሳቤ ነው። ይህንን ውስብስብ ፍልስፍናዊ ስልት (philosophical method) በግልጽ ለመረዳት፣ በመጀመሪያ ደረጃ የኦሮሞን ንጽረተ-ዓለም (Weltanschauung /World-View) በጥንቃቄ ማጠን እና መተንተን ያስፈልጋል። የኦሮሞ ሥነ-ኑባሬ (Ontology) በሦስት አንኳር አንኳር ጽንሰ-ሐሳቦች ይከፈላል። እነርሱም፡-

(ሀ) ሁማ (Uumaa—cosmology)
(ለ) ዋቃ (Waaqa—Undiffrentiated-Being) እና
(ሐ) ሳፉ (Safuu—Human – Ontology) ናቸው።

(ሀ) ሁማ (Uumaa—cosmology)

ሁማ (Uumaa) የሚለው ቃል ሁሙ (Uumuu) ከሚለው ግሥ የተገኘ ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም መፍጠር ማለት ነው። ሁማ የኦሮሞ ትእይንተ-‹‹ዓለም›› (cosmos) ፍልስፍናዊ ጽንሰ-ሐሳብ ነው። በ‹‹ዓለም›› ውስጥ ያለው ነገር በሙሉ በዚህ ሁማ ውስጥ የሚታቀፉ ሲሆን፣ ሕልውና ያለው ማንኛውንም ነገር ያጠቃልላል። (Maammoo Gadaa, 2013: 10) ስለዚህ፣ ቃሉ ሕይወት የሌላቸውን ነገሮች፣ ህያው አካላትንና መንፈሳዊ ሕላዌዎችን ሁሉ ያመላክታል። ግና በኦሮሞ ንጽረተ-‹‹ዓለም›› ፍጥረት (creation) ተሰርቶ ያለቀ እና ቋም ነገር (static) ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ነገር (a continous process) ተደርጐ ይወሰዳል። ለምን? ይህንን ጥያቄ በትክክል ለመመለስ በመጀመሪያ ደረጃ በኦሮሞ ሀገር-በቀል-እውቀታዊ-አረዳድ ውስጥ ያለውን የዋቃ ጽንሰ-ሐሳብ ቀጣይነት ካለው ሁማ ጋር ለምን እና እንዴት ፈጽሞ መለያየት በማይቻል ሁኔታ እንደተቆራኜ በጥንቃቄ እንመረምራለን።

(ለ) ዋቃ (Waaqa)

የኦሮሞ ሕዝብ ስለ ዋቃ ያለው ጽንሰ-ሐሳብ በጣም ግልጽ ነው። የሁሉም ነገር አስገኚ ዋቃ ነው። ዋቃ ምሉዕ በኩለሄ (omniscient)፣ ሁሉን ቻይ (ominipresent)፣ ዘላለማዊ (eternal)፣ ፍጹም (absoulute)፣ እና ገደብ የሌለው (infinite) ነው። ዋቃ ፍጹም አንድ ነው።  ዋቃ ፍጹም አንድ ቢሆንም ቅሉ፣ ራሱን የሚገልጸው ግን በተለያየ መንገድ ነው። በተለይ፣ ዋቃ ማንነቱን ለሁማ (Uumaa) የሚገልጸው በአያና (Ayyaana)  አማካኝነት ነው።

አያና የሁሉም ነገሮች ምንነት ወይም ንጥረ-ነገር (essence) የሚወስን፣ በአካል የማይታይ አምነ-መሠረት (immaterial principle) ነው። በኦሮሞ ፍልስፍና እሳቦት (thought) ሁሉም ነገር ከዋቃ የሚመነጨው በአያና መልክ ነው። የእያንዳንዱን ነገር ምንነት (essence) ሆነ የጋራ ባህርዮቻቸው (common properties)  የሚወስነው አያና ነው። Gudrun Dahl አያና የእያንዳንዱን ነገር ባህርይ እና እጣ-ፈንታ የሚወስን በአካል ያማይታይ አምነ-መሠረት መሆኑን በትክክል ሞግተዋል። (Gudrun Dahl, 1996: 167) የ Lambert Bartles የጥናት ግኝትም ‹‹ተራራዎች፣ ዛፎች፣ ቀናት፣ ወራት እና ወቅቶች፤ እያንዳንዱ ሰውና የዘር-ሐረጉ›› የራሳቸው አያና እንዳላቸው ያረጋገጠ ሲሆን፣ ‹‹እነዚህ አያናዎች ሕይወታችንን የሚገዙ፣ ሕልውናችንን የሚወስኑ እንድሁም የራሳቸው ሕልውና አላቸው ተብሎ ይታሰባል›› ሲል  Oromo Religion በተሰኘ የምርምር ሥራው ውስጥ አስረድተዋል። (Lambert Bartles, 1990፡ 113)   Joseph van de Loo በበኩሉ አያና ‹‹የማይታይ አካል፤ መንፈስ›› እንደሆነ The Religious Practices of the Guji Oromo በተሰኘ ጥናታዊ ሥራው ውስጥ አስገንዝበዋል። (Joseph van de Loo, 1991: 149)

አያና ጽንሰ-ሐሳብ በዋናነት የሚያመለክተው ሕልውና ያለው ማንኛውም ነገር የራሱ  ‹‹አያና›› እንዳለው ነው። አያና-አልቦ ፍጡር የለም። ያለ አያና የአንድን ነገር ምንነት ማወቅ አይቻልም፤ ጽንሰ-ሐሳቡም ሊኖረን አይችልም። አንድን ነገር ከሌላኛው ለይተን እንድናውቅ ወይም እንድንረዳ የሚያስችለን አያና ነው።  ይህንን በተመለከተ Gudrun Dahl እንዲህ ሲል ያብራራል፡-

‹‹ሀገር-በቀል የኦሮሞ ትእይንተ-ዓለም የተመሠረተው ከፊል-አፍላጦናዊ (a quasi-platonic) በሆነው በእውኑ-ዓለም (the real-world) እና በሐሳባዊ-ዓለም (the ideal-world) መካከል ነው። በቁሳዊው ዓለም ውስጥ የሚኖር እና በረቂቁ መልክ ያለው ማንኛውም ነገር ከዚህ ከማይታየው አምነ-መሠረት (Ayyaana) ጋር የተቆራኘ ሲሆን ለአንድ ነገር ባህርይ እና እጣ-ፈንታ ወሳኝነት አለው።›› (Gudrun Dahl፣ 1996፡ 167)

አያና የእያንዳንዱን ነገር ምንነት እና ዕጣ-ፈንታ የሚወስን ከሆነ የሰው ልጅ ሕልውና በአያና ኾኖ ከተገኘው ውጪ ሌላ የመሆን አማራጭ አለው ወይ? ለዚህ ፍልስፍናዊ ጥያቄ ምክንያታዊና አሳማኝ መልስ መስጠት የሚቻለው አንድ ሰው የዋቃ (Waaqa) እና የሳፉ (Safuu) ጽንሰ-ሐሳቦችን በትክክል የተገነዘበ እንደሆነ ብቻ ነው። ለምሳሌ፡- ዋቃ የሚለው የኦሮምኛ ቃል Creator ወይም God አልያም Supreme Being ወደሚለው የእንግሊዝኛ ቃል መተርጐም ትክክል እንዳልሆነ Lambert Bartles በትክክል ያሳስባል። ምክንያቱም በኦሮሞ ፍልስፍና ምንም እንኳ ዋቃ ከሰው ልጅ እውቀትና ልምድ በላይ የሆነ (transcendental) እና ከሁሉ የላቀ ነፃ ሕልውና ያለው አምላክ ቢሆንም ቅሉ፣ ከሁማ ጋር አብሮ የነበረና ያለ (immanent) እንጂ ራሱን ሙሉ በሙሉ ከተጨባጩ ዓለም ነጥሎ የሚኖር ስላልሆነ ነው። በዚህ ዓለም ውስጥ ዋቃ በብዙ መንገድ ራሱን የሚገልጽ ሲሆን እንደ ሕልውና (being) የምንረዳቸው ወይም የሚናስባቸው የተለያዩ ነገሮች ሁሉ የእርሱ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው። ስለዚህ፣ Divinity (“መለኮታዊ”?) የሚለው ቃል የዋቃን ጽንሰ-ሐሳብ የተሻለ እንደሚገልጽ Lambert Bartles ያሳስባል። ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ቃሉ በአንድ ጊዜ የአንድን ነገር ሕልውና እና የሕልውናውን ተፈጥሯዊ ባህርይ (ዓይነት) በአህምሮው እንድገነዘብ ያስችለዋል ተብሎ ስለምታመን ነው። (Lambert Bartles, 1990፡ 89)

በተመሳሳይ መልኩ Karl Eric Knutsson ዋቃ የሚለው ቃል በምዕራቡ-‹‹ዓለም›› ነገረ-መለኮት አስተምህሮ ውስጥ የሚናውቀውን የእግዚአብሔርን አንድነት እና ነፃነት ጽንሰ-ሐሳብ የማይወክል መሆኑን ያስገነዝባል። እርሱም እንደ Lambert Bartles ሁሉ Divinity የሚለውን ቃል የዋቃን ጽንሰ-ሐሳብ ተሻለ እንደሚገልጸው Authority and Change በተሰኘ የምርምር ሥራው ውስጥ ተከራክረዋል። (Karl Eric Knutsson, 1967: 49)

የ Lambert Bartles Karl እና Eric Knutsson ነገረ-ሰባአዊ አረዳድ እና ትንተና (anthropological understanding and interpretation) እንዳለ ሆኖ Undeffrenciated-Being የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ሀገር-በቀሉን የዋቃን ጽንሰ-ሐሳብ የተሻለ ለምን እንደሚገልጸው ፍልስፍናዊ ማብራሪያ መስጠት ያስፈልጋል። ይህንን ፍልስፍናዊ እሳቤ ከሁለት ወገን ማየት ይቻላል፡-

አንድም፤ ሀገር-በቀሉ የኦሮሞ ሥነ-እውቀት ዋቃን የሚገልጽበት መንገድ ጥንቃቄ የተሞላበት ነው። በማንኛውም ጊዜና ቦታ ዋቃ የሚለው ቃል ሲጻፍም ሆነ ሲነገር ‹‹ጉራቻ›› የሚለውን ቅጽል አስከትሎ ነው። ቀጥተኛ ትርጉሙም ‹‹ጥቁር›› ማለት ሲሆን በኦሮሞ ንጽረተ-ዓለም ጥቁርነት የልዕልና ምልክት ብቻ ሳይሆን፣ የዋቃን ቀዳማዊነት (Originality) የሚገልጽ ነው። ጥቁርነት የዋቃ ምንነት በሰው አህምሮ ሊደረስበት የማይቻል እጅግ ፍጹም ምስጢር መሆኑን የሚገልጽ ጽንሰ-ሐሳብ ነው። Dahl እና Gemechu እንደሚያስረዱት ማንኛውም ነገር በአያና መልክ የሚመነጨው ከዚው ሕልውናው ሙሉ በሙሉ ‹‹ከማይታወቅ›› ዋቃ-ጉራቻ መሆኑን ይሞግታሉ። ስለዚህ፣ Undeffrenciated-Being የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የዋቃን ጽንሰ-ሐሳብ የተሻለ የመግለጽ ብቃት አለው። (Dahl, 1996: 169)

ሁለትም፣ በኦሮሞ ሀገር-በቀል ፍልስፍና አያናን ከዋቃ ጽንሰ-ሐሳብ ነጥሎ መገንዘብ ስለማይቻል ሁለቱም  ፈጽሞ ተቆራኙ ናቸው። ይህ ቁርኝት ከኦሮሞ የፍጥረት  ግንዛቤ የሚመነጭ ነው። Dahl እንደሚሞግተው የኦሮሞ ምልአተ-ዓለም፣ ሥነ-ምህዳር እና የሰው ልጅ ሕልውና ከዋቃ የሚመነጭ ፍሰት ነው። ይህ የሚያመለክተው ፍጥረት ቋሚ እና ተሰርቶ ያለቀ ነገር ሳይሆን ቀጣይነት ያለው መሆኑን ነው። በኦሮሞ ንጽረተ-ዓለም ፍጥረት በሆነ ወቅት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ብቻ ተከናውኖ ያበቃ ጉዳይ አድርጎ መውሰድ ስሕተት ነው። የፍጥረት ድርጊት አሁንም ቢሆን አለና። (Dahl, 1996: 167)

በዚህ መሠረት ምንም እንኳ የማንኛውም ነገር ተፈጥሯዊ ባህርይና ዕጣ-ፈንታ በአያና የሚወሰን ቢሆንም ቅሉ፣ የሁማ ወይም የአያና ሕልውና በራሱ የተመሠረተው በዋቃ ላይ ነው። ስለዚህ፣ የአያና እና የዋቃ ጽንሰ-ሐሳቦች ፈጽሞ የተቆራኙ ናቸው ሲባል፣ ሁለቱም አንድ ናቸው ማለት እንዳልሆነ በአጽንኦት ልሰመረበት ይገባል። አያና የዋቃ ‹‹ንዑስ -አካል›› ነው። Lambert Bartles ‹‹አያና ዋቃ ነው፤ ዋቃ ግን አያና አይደለም›› ሲል የሚሞግተው ይህንን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አሁንም ልብ ማለት ያሻል። ዋቃ ከሁሉም ሰዎች ጋር ግንኙነት ያለው ሲሆን፣ እያንዳንዱ ግለሰብ የእርሱን እርዳታ ይጠይቃሉ። (Lambert Bartles, 1990: 118-119)

በተቃራኒው፣ አያና የዋቃ ነጸብራቅ ነው። እርዳታውን የሚጠይቁ ግለሰቦች በምርጫ አልያም በተፈጥሮ ከእርሱ ጋራ ግንኙነት ያላቸው ናቸው። አያናዋቃ የሚፈስና ሁሉንም ፍጥረት የሚሞላ ነው። የእያንዳንዱን ፍጡር ውስጣዊና ውጫዊ ውቅረትም ይወስናል። ሆኖም አያና ለሰዎች ሳይታይ ይኖራል። ለምሳሌ፡- የሚናየው ግለሰቡን እንጂ አያና(ውን) አይደለምና። ይህ የይታየው አያና ነው የታየውን የሰው ግጽታ  የሚሠራውና የሚወስነው። (Lambert Bartles, 1990፡ 118-119) በሌላ አገላለጽ በዚህ ዓለም ውስጥ ነገሮች ማንነታቸውን ወይም ተፈጥሯቸውን ጠብቀው መኖር እንዲችሉ የሚያደርጋቸው አያና ነው፤ የራሳቸው ሕልውና እንድኖራቸውም ያደርጋል። እንደ Lambert Bartles ሁሉ ዋቃ የሚለው ቃል በጣም አጠቃላይ ጽንሰ-ሐሳብ የሚወክልና አያናን እንደሚያካትት Karl Eric Knutsson ይሞግታል። (Karl Eric Knutsson, 1967፡ 48)

እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ማለት ያሻል። አያና እንደ ሁማ በጊዜና በቦታ ሕግ አይገዛም። የሁሉም ነገሮች ምንነት አስገኝ አያና ነው። ማንኛውም ሕልውና ወደመኖር ከመምጣቱ በፊት አያና(ው) ነበር። የነገሮች መኖር ወይም የሕልውናቸው ምክንያት አያና ሲሆን የአያና የመጨረሻ አስገኝ (ultimate-cause) ደግሞ ዋቃ ነው። ዋቃ የሁሉ ነገር አስገኝ፣ የማይጠፋ፣ ማይለወጥ፣ ቋሚና ዘለዓለማዊ ነው።  ስለዚህ፣ አያና ነገሮች ማንነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው በዋቃ በኩል ብቻ ነው። በኦሮሞ ንጽረተ-‹‹ዓለም›› ጽንሰ-ሐሳብ አያና የነገሮች ሁሉ አስገኝ ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ አኳኋን አያና ሁማን እንደሚያካትት ሁሉ ሁማም አያናን ያቅፋል።

ይሁን እንጂ፣ የአያና እና ሁማ ልይይት አንድ መሠረታዊ የፍልስፍና ጥያቄ እነድናነሳ ያስገድደናል፡- ከሁማ ነጥለን ከቶ ማሰብ የማንችለው የሰው ልጅ ሕልውና (ነፃነት፣ ህልና፣ ሐሳብ) ታስረዋል ወይንስ ነፃ ናቸው? አንድ ግለሰብ በአያና ኾኖ ከተገኘው ውጪ ሌላ የመሆን አማራጭ (ነፃነት) አለው ወይ? በጊዜና ቦታ ከማይወሰነው አያና መሳ-ለ-መሳ መሄድ የሚችሉት እንዴት ነው? የሰው ልጅ ሕልውና የራሱ ወይንስ ማንቱን የሚወስንለትና ከእርሱ ቁጥጥር ውጪ የኾነ አያና? ለኦሮሞ ሀገር-በቀል ቃሉዎች ምስጋና ይግባውና የሳፉ ጽንሰ-ሐሳብ ለዘህ ፍልስፍናዊ ጥያቄ አጥጋቢና ጥልቅ ፍልስፍናዊ ትንተና ይሰጣል።

ክፍል 2 ይቀጥላል

ቸር እንሰንብት
ዋቢ-መጽሐፍት

References

– Baxter, P. T. W., Hultin, J., and Triulzi, A. eds. Being and Becoming Oromo: Historical and Anthropological Enquires. Asmara: The Red Sea Press, Inc., 1996.
– Dirribi D. B. Oromo Wisdom In Black Civilization. Finfinnee: Finfinne Printing and Publishing S. C., 2011.
– Geleta K. Hirkoo: English-Afan Oromo-Amharic Dictionary. Aster Nega Publishing Enterprise, 2008.
– Knutson, K. E. Authority and Change: A Study of the Kallu Institution Among the Macha Galla of Ethiopia. Gӧteborg: Etnografiska Museet, 1967.
– Lambert, B. Oromo Religion: Myths and Rites of the Western Oromo of Ethiopia: An Attempt to Understand. Berlin, 1990.
– Leus, Ton. Aadaa Boraanaa: A Dictionary of Borana Culture. Addis Ababa: Shama Books, 2006.

– Loo, J. V. D. The Religious Practices of the Guji Oromo. Addis Ababa, 1991.
– Sumner, Claude, Oromo Wisdom Literature. Vol.1 Addis Ababa: Gudina Tumsa Foundation, 1995

===============

*Yoseph Mulugeta Baba is a qubee generation born in Konchi/Nekemte, Ethiopia. He holds a B.A, M.A, and Ph.D. degrees in Philosophy from The Catholic University of Eastern Africa (CUEA), Nairobi-Kenya. He also holds a B.D, in Sacred Theology (Magna Cum Laude Probatus) from Pontifical Urbaniana University, Rome. His research interests involve: Metaphilosophy, Oromo Philosophy, Continental Philosophy, Post-colonial African Philosophy, Sage Philosophy, and Post-modernism. His publications include, Metaphilosophy or Methodological Imperialism? (2015); Philosophical Essays (2016); The Oromo Concept of reality: Epistemological Approach (2016); የኢትዮሮፒያንስ የአስተሳሰብ ቅሬ፤ ‹አበበ በሶ በላ› vs ‹ጫላ ጩቤ ጨበጠ› (2017); KANA DUBBIIN (2017); Negritude As The Recovery of Indigenous African Political Leadership፡ The Case of Gadaa Oromo Political Philosophy (2017); Remembering Great African Thinkers (2018). His book titled, African Philosophical Hermeneutics, is forthcoming. Currently he teaches African philosophy at CFIPT. He can be reached at:  kankokunmalimaali@gmail.com

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.