የጠ/ሚ ኃይለማርያም ንግግር ያስከተለዉ ቁጣ

የጠ/ሚ ኃይለማርያም ንግግር ያስከተለዉ ቁጣ

(DW) — የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአገሪቱ የፖለቲካ ይዞታዉ አሳሳቢ ሁኔታ ዉስጥ እንደሚገኝ በትላንትናዉ ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክተዋል። በተለይም በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰቱት ግጭቶች የሰው ህይወት እንደጠፋ፣ ሰዎች ከቀያቸዉ እንደተፈናቀሉ እና ንብረት እንደወደመም አሳዉቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትላንት ምሽት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ይተላለፍ በነበረዉ የወጣቶች ዝግጅት መሃል ብቅ ብለዉ ነበር ስለአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ የሰጡት። አስር ደቂቃ ባልሞላዉ ንግግራቸዉ አሁን በኦሮሚያ፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በአማራ እና ትግራይ ክልል የፖለቲካ ቀዉስ ለሰዉ ሕይወት መጥፋት፣ ንብረት መዉደም፣ መፈናቀል እና የትምህርት መስተጓጎል ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በንግግራቸዉ የሁለቱም ክልል ተወላጆች ላይ የተደረሰዉን ጥቃት አንዱን «የጅምላ ግድያ»፣ ሌላዉን ደግሞ «የሞትና መቁሰል አደጋ» በማለት መግለፃቸዉ በመግለጫቸዉ የሚዛናዊነት ጥያቄ አስከትሏል።

Ethiopia: የኢፌዲሪ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሀገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች በደረሰው የዜጎች ህይወት ማለፍ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለፁ፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊት በኦሮሚያ ክልል በጨለንቆ ከተማ ሜታ አካባቢ ከ15 ሰዎች በላይ በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት መገደላቸዉን የክልሉ ባለስልጣናት አሳዉቀዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎችን ወደ አካባቢዉ እንዳልጋበዘ የገለፁት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ፤ የክልሉ የፀጥታ አስከባሪዎች ከማህበረሰቡ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ «ሐሰተኛ እና የተጋነኑ መረጃዎችን» የሚያሰራጩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ካልተቆጠቡ ርምጃ እንደሚወሰድባቸዉም አሳስበዋል። አቶ ተማም ግጭቱን የቀሰቀሰዉም፤ እያባባሰ የሚገኘዉም መንግሥት ያስታጠቃቸዉ ኃይል ነዉ ይላሉ።

የተለያዩ የዶቼ ቬለ ተከታታዮች የጠቅላይ ሚኒስትሩን መግለጫ በተመለከተ በዶይቼ ቬሌ የፌስቡክ ገፅ እና በዋትስአፕ አድራሻችን አስተያየታቸዉን ልከዉልናል።  አንድ የፌስቡክ ተከታታይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ «መፍትሔ ለመስጠት የሕዝቡ ጥያቄ ምንድነው? ማለት ሲገባ እርምጃ ምን ለውጥ አመጣ? ብሎ ማመዛዘን አለበት ሀገር በብልሀት፣ በሰከነ አመራር እንጂ በወኔ በርምጃ አይመራም» ሲል፤ ማሂር ማሂር የተባለ ግለሰብ ደግሞ «ይህ እኮ የ27 አመት ዉጤታቸዉ ነዉ፣ አሁን ህዝብ ነቅቷል። ሥልጣኑን ያለማቅማማት ለህዝብ ማስረከብ ብቻና ብቻ ነዉ መፍትሄዉ» በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.