“ዓመቱ የውሳኔ ነው!”  ዶ/ር ደብረጽዮን;

ዓመቱ የውሳኔ ነው!”  ዶ/ር ደብረጽዮን;

ምርጫ በዚህ ዓመት የማይካሄድ ከሆነ የትግራይ ክልል የራሱን ውሳኔ እንደሚወስን ም/ር/መስተዳድሩ ገለጹ፡፡

 

TPLF Chairman Debretsion (Ph.D.) press briefing (Amharic) on the occasion of 45th Lekatit 11 anniversary – Mekelle Feb 20, 2020.

የትግራይ ክልል ም/ር/መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካዔል የህወኃት 45ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበርን አስመልክተው ትናንት የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም በጽህፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫን ሰጥተዋል፡፡
በዓሉ የተለየ ትርጉም ባለው መልኩ በስኬት መከበሩን ደብረጽዮን በመግለጫቸው ወቅት ተናግረዋል፡፡ ህወኃት ለግማሽ ምዕት ዓመት የተቃረበ እድሜን አስቆጥሮ የምስረታ በዓሉን ማክበሩ ብቅ ብለው በቶሎ እንደሚጠፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች አለመሆኑን እና ተቋማዊ ቅርጽ መያዙን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ይህ የካበተ ያሉት ልምድ ለጦርነት የሚጋብዙ ጸብ አጫሪ ድርጊቶች በፌዴራል መንግስቱ ሲፈጸሙ እንኳን በትዕግስት ለማስቆምና ህግና ስርዓት እንዲከበር ጠይቆ ለማለፍ እንዳስቻላቸውም ነው የገለጹት፡፡ ለዚህም ወደ መቀሌ መጥቶ ነበር ያሉትን የታጠቀ የፌዴራል ኃይል በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ይህ ወደ ውጊያ ለመግባት በቂ ምክንያት ቢሆንም ከክልሉ እውቅና ውጭ የገባውን ታጣቂው ኃይል ከኤርፖርት እንዳይወጣ በመክበብ ተልዕኮው እንዳይሳካ አድርገናልም ነው ያሉት፡፡ አሁንም ሊጣሱ የማይገባቸው ቀይ መስመሮች አሉ ብለዋል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዘለግ ያሉ ሰዓታትን በወሰደው ጋዜጣዊ መግለጫቸው የተለያዩ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ አጀንዳዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ህጋዊነት የለውም ባሉት የኢህአዴግ ውህደት በህዝብ ያልተመረጠ ፓርቲ ስልጣን መያዙን ገልጸዋል፡፡ እስከ ምርጫ ድረስም ስልጣኑ የኢህአዴግ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

”ችግሩ መዋሃዱና ፓርቲ መመስረቱ ሳይሆን የስልጣን ወራሽ ነኝ ማለቱ ነው፤ ይህም በአቋራጭ ስልጣን መያዝ ነው ክልሎች ተቀጽላ ሆነው በብልጽግና መቀጠል አይችሉም“ ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ተቋም የሚገነባበት አንዱ መንገድ ነው ባሉት ምርጫ ይህ ችግር ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

ሆኖም በፌዴራል የተወከሉ የህወኃት አባላት ከምርጫው በፊት ከኃላፊነት ሊነሱ እንደማይገባና በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተው የተመደቡ ሰዎች እንዳሉና ጥያቄው ይመለሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ነገር ግን ገና እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
“የውሳኔ ነው” ባሉት በዚህ ዓመት ሊካሄድ የታሰበው ምርጫ ከነጉድለቱም ቢሆን እንዲካሄድ እንደሚፈልጉ፤ የማይካሄድ ከሆነ ግን ለውሳኔ የሚያበቋቸው አማራጮች በእጃቸው ላይ እንደሆኑ የውሳኔያቸውን ምንነትም በጊዜው እንደሚያሳዩ አስታውቀዋል፡፡
በምርጫው የተሻለ ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴን ለማድረግ የሃሳባቸው ደጋፊ የሆኑ የፌዴራሊስት ኃይሎችን እንደሚያሰባስቡና አሁንም ጥምረቱን የሚቀላቀሉ አዳዲስ ኃይሎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ደብረጽዮን በህዳሴው ግድብ ጉዳይ እጅግ አዝኛለሁ ብለዋል፡፡ ግድቡን በራስ አቅም በመገንባት የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት እግረ መንገድንም የኃይል ምህንድስና ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም ተይዞ የነበረው ሀገራዊ ውጥን መጨናገፉንም ነው የገለጹት፡፡

ሊስተካከሉ የሚችሉ አስተዳደራዊ ስህተቶች በግንባታ ሂደቱ እንደነበሩ ግን አልሸሸጉም፡፡

ሆኖም በአመራር ክፍተት ምክንያት ተጽዕኖ መምጣቱንና መሄድ የማይገባው የራስ ጉዳይ ወደ ዋሽንግተን መሄዱ ለበለጠ ጫና ማጋለጡንም ጠቁመዋል፡፡

የትግራይንና የኤርትራን ህዝብ ወደ ቀደመ ሰላማዊ ግንኙነቱ ለመመለስ ከአሁን ቀደም የተጀመሩ የግንኙነት ስራዎችን የማስቀጠል ፍላጎት አለን ያሉ ሲሆን የሚደረጉ ግንኙነቶች ግልጽ ሊሆኑና ተቋማዊ መልክ ሊኖራቸው እንዲሁም በሚደረጉ ስምምነቶች ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

”ባድመ እንዲሰጠን ፌዴራል መንግስቱ ቢወስንም ወያኔ እንዳይሳካ እያደረገ ነው“ በሚል ከሰሞኑ በመሪዎች ተሰጠ የተባለውን ንግግር ኮንነዋል፡፡ “የባድመ ጉዳይ የሃገር እንጂ የትግራይ አይደለም ፤ የማይመለከተው መሪ በእኛ ሃገር ጉዳይ አያገባውም፤አደገኛ ጣልቃ ገብነት እየተደረገ ነው” ሲሉም ተችተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባሌ አደረጉት የተባለውን ንግግር በማስተርጎም ማድመጣቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ”የተናበበ ሴራና የውጭ ጣልቃ ገብነት አለ“ የምንለው ለዚህ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መንግስት ይህን ማስቆም እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ኤርትራውያን ስደተኞች እንዳይመጡ መከልከሉና እና ካምፑ ይፍረስ መባሉም ተገቢ እንዳይደለ ተናግረዋል፡፡ ይህ መፍትሄ አይሆንም ያሉም ሲሆን፣ ስደተኞችን ካምፑ ባይቀበል እኛ እንቀበላለን ብለዋል፡፡

ምንጭ ፡ አል-ዐይን ሚዲያ

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.