የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?  ሁለተኛ ዙር፥ ቁጥር አስር

የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?  ሁለተኛ ዙር፥ ቁጥር አስር

ብርሃኑ ሁንዴ, Hagaya 4, 2019

Oromoo

ቁጥር ዘጠኝ ፅሁፍ ካቀረብኩ ወዲህ ትንሽ ጊዜው ስለረዘመ፣ ፅሁፎቼን የሚከታተሉ አንባቢዎች አንዳንድ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡልኝ ነበር። አንዱ ጥያቄ ለምን ፅሁፎችህን በየጊዜው አታቀርብ? የሚል ሲሆን፣ ሌላው ጥያቄ ደግሞ ቁጥር አስር ፅሁፍ ለመን ይህን ያህል ጊዜ ዘገየ? የሚል ነበር። ለሁለቱም ጥያቄዎች መልሴ ባጠቃላዩና ባጭሩ ከጊዜ እጥረት የተነሳ ነው የሚል ሲሆን፣ ለሁለተኛው ጥያቄ ግን ተጨማሪ መልስ፥ ቁጥር ዘጠኝ ፅሁፍ ካቀርብኩ ወዲህ አንዳንድ ፅሁፎችን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሳቀርብ ስለነበር ተከታታዩ በመሃል ሊቋረጥ ችሏል። ይህን ካልኩኝ በኋላ ያዛሬው ቁጥር አስር ፅሁፍ የሚያተኩረው በፊንፊኔ ግዳይ ላይ ይሆናል።

ኦሮሞ በፊንፊኔ ላይ ያለው የአገር ባለቤትነት ሊሰረዝ ነው?

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስፅፍ እንደነበርኩ፣ ፊንፊኔ በሕግም ሆነ በታሪክ፤ በጂኦግራፊ አቀማመጥም ሆነ በማንኛውም መንገድ የኦሮሚያ አካልና እምብርት ናት። ይህንን ታሪካዊ እውነታ የማይቀበሉት ካሉ፣ ፀረ ኦሮሞ ኃይሎችና ከምኒልክ ጋር ወደ ኦሮሞ አገር መጥተው፤ አገራችንን ይዘው በኛ ላይ ተዋልደውና ተራብተው ያሉት የነፍጠኞች ልጆች ብቻ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ከዚህች ምድር ይጠፋሉ እንጂ ፊንፊኔ ወደ እናቷ ኦሮሚያ ስር ገብታ፣ ኦሮሞ በዚህች ከተማ ላይ ያለው የአገር ባለቤትነት እንዲረጋገጥ በፍፁም አይፈልጉም። እንግዲህ የፊንፊኔ ጉዳይ የህሊውና ጉዳይ ሊሆን ነው ማለት ነው። ይህ ጉዳይ ከሚታሰበው በላይ ይህን ያህል አስቸጋሪ ነው።

የአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) የቅንጅት ኮሚቴ በሚባለው በስተጀርባ ያለው ተንኮል ምንድነው?

ከሚዲያ እንደተሰማው፣ የአዲስ አበባ የቅንጅት ኮሚቴ በሚል ስም አንድ ኮሚቴ እንደተቋቋመ ወይንም ሊቋቋም እንደሆነ ይነገራል። የዚህ ኮሚቴ ዓላማ ምን እንደሆነ ለጊዜው ግልፅ ባይሆንም፣ ሊገመት የሚችል ግን ኦሮሞ በፊንፊኔ ላይ ያለው የአገር ባለቤትነት እንዳይሳካ ወይንም ደግሞ ከተቻለ ጭራሽም እንዲሰረዝ ለማድረግ እየተሸረበ ያለ ሴራ እንዳለ ነው የሚታየኝ። ይህ ኮሚቴ አምስት አባላትን የያዝ ሲሆን፣ ከአማራ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (አዴፓ) ሁለት አባላት፤ ከኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) አንድ አባል (ይኸውም ም/ከንቲባው ኦቦ ታከለ ኡማ)፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራቲክ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) አንድ አባል፤ ከትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ሕወሃት) አንድ አባል እንደያዘ ይነገራል።

ተንኮሉ ወይም ሴራው ከዚሁ እንደሚጀምር መረዳት አያስቸግርም። በምን ሚዛን(Criterion) እና ምክንያት (justification) ነው አዴፓ ሁለት አባላት የሚኖረው? ኦዴፓ የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስም ሆነ ለማስመለስ ደንታ የሌለው ድርጅት ቢሆንም፣ የኦሮሞን ስም ይዞ ይህንን ሕዝብ ወይም ብሔር አወክላለሁ ካለ፤ በቁጥርም ሆነ በማንኛውም ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኦሮሞ ሕዝብ ማግኘት ካለበት ቦታ አንፃር መሆን የነበረበት በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ብልጫ ያለው አባላትን መያዝ ነበረበት። በሌላ በኩል ግን ይህ ኮሚቴ በፍትሕ መልክ ቢቋቋም እንኳን የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ መመለስም ሆነ ማስመለስ አቅምም ሆነ ፍላጎት የለውም። ሴራና ተንኮል ለመሸረብ ካልሆነ በስተቀር ምን ለማቀናጀት ይሆን ይህ ኮሚቴ ያስፈለገው? በማን ፍላጎት ነው የተቋቋመው? የማንንስ ፍላጎት ለማሳካት ተብሎ ነው የተቋቋመው? የነዚህን ጥያቄዎች መልስ ወደፊት የምናየው ቢሆንም፣ አንድ ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር አሁንም አንድ ተንኮል እንደተረገዘ መገመት የሚያስቸግር አይመስለኝም።

የፊንፊኔ ጉዳይ የኦሮሞ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ/ለራስ የመወሰን መብት አካል ነው

የዚህች አገር ሕገ መንግስት ያሰቀመጠው እንዳለ ሆኖ፣ የአንድ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ/ለራሱ የመወሰን መብት የተፈጥሮ መብት ነው። በመሆኑም፣ የትኛውም የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ (የፊንፊኔን ጥያቄ ጨምሮ ማለት ነው) የተፈጥሮ መብት ጥያቄ ነው። ይህንን መብት ደግሞ እንኳንስ አንድ ኮሚቴ በዓለም ላይ ያለው የትኛውም ኃይል መቀየር አይችልም። ይህ ዛሬ እየታየ ያለው የለውጥ አየር የመጣው የኦሮሞ ሕዝብ በከፈለበት ከፍተኛ መስዋዕትነት ቢሆንም፣ በሌሎች ኃይሎች እየተጠለፈ (hijacked) እንደሆነ ሲስተዋል የቆየ ጉዳይ ነው። ይህንን የሚያመላክቱና ማስረጃ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ። ኦሮሚያ ሰላምና መረጋጋትን አጥታለች። በዚህ ላይ ደግሞ የኦሮሞ ጥያቄዎች አንድም አልተመለሱም። እነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘታቸው ቀርቶ እንዲያውም አንዳንድ የኦሮሞ ሕዝብ መብቶች አደጋ ውስጥ ገብተዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ግልፅ ነው። በውጫዊ ጠላቶች ጥንካሬ ምክንያት ሳይሆን፣ ካሃዲዎች፣ አድርባዮችና በውስጣችን ያሉ የውስጥ ጠላቶች በምሸርቡት ሴራ ነው። ኦሮሞ ይህንን በሚገባ መረዳት አለበት።

ኦሮሞ አሁንም ሌላ ከባድ መስዋዕትነት ከፍሎ የሺዎቹን ልጆቹን ሕይወት ልያጣ ነው?

የፊንፊኔ ጉዳይ መፍትሄ ካላገኘ፣ ሌላ አማራጭ የሌለው አሁንም ከባድ መስዋዕትነት እንደምጠይቀን የማይቀር ጉዳይ ይሆናል። ይሁን እንጂ ወደ ፊት የሚመጣው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ወይም አመፅ (public uprising)

  • እንዳለፈው ድል ያመጣ ይሆን?
  • ምን ዓይነት ችግሮች ናቸው የሚገጥሙት?
  • ምን ዓይነት ፈተናዎች ናቸው የምኖሩት?
  • ልዩ የሚያደርጉት ነገሮች ምንድናቸው?

እነዚህን ጥያቄዎችና ተመሳሳይ ጉዳዮችን በሚመለከት ሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ በደህና ቆዩ

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.