የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? – ሁለተኛ ዙር፥ ቁጥር አስራ አንድ

0

የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? – ሁለተኛ ዙር፥ ቁጥር አስራ አንድ

ብርሃኑ ሁንዴ, Hagayya 9, 2019

Bilisummaa
Final days of Suprematism and Ku Klux Klanism (KKK) are fast approaching more than ever.

በቁጥር አስር ፅሁፍ ውስጥ የፊንፊኔን ጉዳይ በሚመለከት አንዳንድ ነገሮችን አቅርቤ ነበር። ከነዚህ ውስጥ አንዱ የአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) የቅንጅት ኮሚቴ ተብየው ሲሆን፣ በተጨማሪም አንዳንድ ጥያቄዎችን አንስቼ ግን በሚቀጥለው ፅሁፍ እንደምመለስበት አስቅምጬ ነበር። እነዚያ ጥያቄዎች የሚመለከቱት የፊንፊኔ ጉዳይ መፍትሄ ካላገኘ የኦሮሞ ሕዝብ አመፅ መነሳቱ ስለማይቀር ነገር ግን ይህ ወደፊት የሚነሳው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ከበፊቱ እንዴት ሊለይ እንደሚችል እና ሌሎች ከጉዳዩ ጋር የሚዛመዱ ጥያቄዎች ነበሩ። በዚህኛው በቁጥር አስራ አንድ እና በሚቀጥለውም ፅሁፍ ውስጥ ሌሎች ጉዳዮችን ጨምሮ በነዚያ ባነሳሁአቸው ጥያቄዎች ላይ ትኩረት በማድረግ አንዳንድ ነገሮችን ማብራራት እሞክራለሁ።

ኦዴፓ እና ኢዜማ ልጋቡ ይሆን?

ኦዴፓ እና ኢዜማ ውስጥ ለውስጥ በጋራ እንደምሰሩ ኣንዳንድ ውስጠ አዋቂዎች ሲናገሩ ይሰማል። ከዚህ ሌላም በተጨባጭ የተሰማ ነገር የኢዜማ የአመራር አባል የሆነው አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ቅርብ ጊዜ የተናገረው ይህንን ጉዳይ የሚያረጋግጥ ይመስላል። ሰውየው እንዳለው፣ ኢሕአዴግ (EPRDF) የሚሰራው ወይም እየሰራ ያለው እኛ (የቀድሞው ግንቦት ያሁኑ ኢዜማ ማለቱ ይመስላል) ባዘጋጀነው ፍኖተ-ካርታ (roadmap) ነው የሚል ነበር። ኦሕዴድ/ኦዴፓ ለኦሮሞ ጉዳይ ቅድሚያ ከመስጠት ፋንታ ለሌላ ነገር ቅድሚያ መስጠቱ ራሱ ይህንን የሚያመላክትና የኦሮሞ ሕዝብ የማያውቀው ወይንም ያልተገነዘበው አንድ ሚስጥር ስላለ ነው ብዬ አስባለሁ።  ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይ ራሱ በቢሮው ውስጥ በነፍጠኞች እንደተከበበ አንዳንድ ሾልከው የሚወጡ ወሬዎች ይሰማሉ። ኣንዳንድ የጠ/ሚኒስተሩ አማካሪዎችም ከነዚሁ ከነፍጠኛ ኃይሎች የወጡ መሆናቸውም ይነገራል። በሌላ በኩል ደግሞ ኦዴፓ አዴፓን ለማስደሰት ሌት ተቀን እየሰራ እንደሆነ ይህንን የሚያመላክቱ ብዙ ነገሮች አሉ። ይህ ደግሞ በሚስጥር ሳይሆን በግልፅ እየታየ ያለ ጉዳይ ነው።

ይህንን ጉዳይ የምነካካበት ምክንያት፣ ከዚህ በኋላ ለምፅፋቸው ጉዳዮች መነሻ ይሆናል ብዬ ስለማስብ ነው። ኦሮሞ ሲተርት እንዲህ ይላል “Waa malee manni hin aaru” ወደ አማርኛ ሲተረጎም፥ “ያላ ምክንያት አይደለም ቤት የሚጭሰው” የሚል ይሆናል። የፊንፊኔን ጉዳይ ጨምሮ ሌሎች የኦሮሞ ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙ የተጔተቱበት ምክንያት ራሱ ይህ ሚስጥር ወይም እላይ የተገለፀው አሰራር በመኖሩ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ማለት ኦሕዴድ/ኦዴፓ ሀበሾችን ለማስደስት የሚያደርገው ጥረት ያህል ለውስጥ ችግሮቹ እንኳን የሚጨነቅ አይመስልም። እዚህ ላይ ጀዋር መሃመድ ቅርብ ጊዜ በ OMN ላይ ባደረገው ቃላ ምልልስ ላይ የተናገረው ትዝ ይለኛል። እሱም እንዲህ ብሎ ነበር፥ “ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይ ሀበሾችን የሚያባብለው ያህል ቤተሰቦቹን እንኳን የሚያባብል አይመስልም” የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን (WBO)ን ሽፍቶች ብለው ማሳደድ ራሱ ከዚህ ከላይ ከተገለፀው አሰራር ጋር የሚያያዝ ይመስለኛል። ለምን ከተባለ፣ እነዚህ ሰዎች (ሀበሾች) ኦነግንም ሆነ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን የኢምፓየሯ አፍራሾች አድርገው ስለምረዱ ነው። የኛዎቹ ሰዎች (ኦዴፓ) ደግሞ ቀደም ብዬ አንዳብራራሁት ሀበሾችን ለማስደስት ሲባል የኦሮሞን ልጆች እንደ ጠላት በማየት፤ የሕግን የበላይነት ማስጠበቅ በሚል ሽፋን በወንድሞቻቸው ላይ ጦርነት መክፈት የግድ ይሆናል ማለት ነው።

የኦሮሞ ጥያቄዎች መልስ ካላገኙ የኦሮሞ ሕዝብ አመፅ አሁንም መነሳቱ የማይቀር ነው

የሕዝብ አመፅ የሚነሳው ችግሮች እጅግ ከበዙ፤ ሰላምና መረጋጋት ከሌለ፤ ጭቆና፣ ስቃይና ጉዳት በሕዝብ ላይ ሲደርስ፤ የሕዝብ ጉዳይ ተረስቶ የሕዝቡም ትዕግስት ከወሰን ሲያልፍ እና የመሳሰሉት ሲኖሩ ነው። ዛሬ ያለውንም የኦሮሞ ሕዝብ ሁኔታ ካየን፣ የሕዝባችን ችግሮች እየበዙ በመምጣት፤ የሕዝባችን ትዕግስትም ከወሰን እያለፈ የሄደ ይመስላል። በተለይ ደግሞ የፊንፊኔ ጉዳይ ቶሎ መፍትሄ ካላገኘ ወይም ኦሮሞ በከተማይቷ ላይ ያለው የአገር ባለቤትነት ካልተረጋገጠ የሕዝብ አመፅ መነሳቱ የማይቀር ይሆናል። ይሁን እንጂ፣ ወደ ፊት ሊነሳ የሚችለው የሕዝብ እንቅስቃሴ (public uprising) እንደ ባለፈው ድል ያመጣ ይሆን? ምን ዓይነት ችግሮች ይገጥሙታል? ከባለፈው ልዩ ሊያደርገው የሚችል ምንድነው? ምን ዓይነት ፈተናዎች ናቸው የሚገጥሙት? እነዚህን ጥያቄዎች ሀሳብ ውስጥ ማስገባትና በጥልቀት ማየት አስፈላጊ ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ ወይም አመፅ ተመልሶ ከተነሳ ምን ዓይነት ሁኔታዎች (Scenarios) መፈጠር ይችላሉ?

ከባለፈው የሕዝብ አመፅ ተነስተን ካየን፣ የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ ግብ ሊመታ የሚችለው የዚህ ሕዝብ ወይም ብሔር አንድነት ሲኖር ብቻ ነው። ባለፈው የሕዝብ አመፅ ውስጥ ጠንካራ አንድነት በመኖሩ፣ ወያኔዎችን ማንበርከክ ችሏል። አሁንስ? ተመሳሳይ አመፅ እና እንቅስቃሴ ከተነሱ፣ ምን ዓይነት ሁኔታ ነው ሊፈጠር የሚችለው? አንድ ባንድ እናያለን።

ሁኔታ አንድ (Scenario 1)

ያለፈው የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ እንደዚሁም በመሃል አገር በተቀናጀ መንገድ ሕዝብን ማሳተፍ ችሎ ነበር። ኦሕዴድም በወቅቱ የወያኔዎች ተላላኪ ቢሆንም በዚህ በሕዝብ እንቅስቃሴ ውስጥ ዕድል አግኝቶ ከተኛበት በመንቃት የተወሰነውን ያህል ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ለመቆም ተገዶ ነበር። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ የተለያዩ ስልቶችንና እስትራቴጂዎችን በመጠቀሙ የተለያዩ ልምዶችን መቅሰም ችሏል። ስለዚህ አሁን ሌላ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ከተደረገ ያለፈውን ልምድ መሰረት በማድረግ፣ ሌላ ስልትም ጨምሮ ከበፊቱ በተሻላ መልክ ድል ሊያስመዘግብና በዚህ ውስጥ ጥያቄዎቹም በቀጥታ መልስ እንዲያገኙ ማድረግ ይችላል። ይህንን የሚወስነው ግን ጠንካራ የሕዝቡ አንድነት ነው። አንድነቱ ከተዳከመ ግን ሁሉ ነገር አደጋ ውስጥ የመግባት ዕድል ይገጥመዋል ማለት ነው።

ባሁኑ ወቅት ካለንበት ሁኔታ ጋር አወዳድረን ካየን ግን ባሁኑ ጊዜ የኦሮሞ ሕዝብ አንድነት ምን ያህል አስተማማኝ ነው? አንድነታችንን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡት ነገሮች ምንድናቸው? እነዚህን ጥያቄዎችና ሁኔታ ሁለትን (Scenario 2) በሚቀጥለው ፅሁፍ ውስጥ እናያለን።

ተመልሰን እስከምንገናኝ በደህና ቆዩ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.