የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? – ሁለተኛ ዙር፥ ቁጥር አስራ ሁለት

0

የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? – ሁለተኛ ዙር፥ ቁጥር አስራ ሁለት

ብርሃኑ ሁንዴ, Hagayya 11, 2019

Oromoo
Hoggantoota ODP : Bilisoomneera, Qabasoon Oromoo galii isaa gahe, Woyaanee ari’ane, amma namni reebamu, du’u, dararamu hinjiru, misoomati dheebina fi kkf kan jedhan

በቁጥር አስራ አንድ ፅሁፍ ውስጥ ኦዴፓ እና ኢዜማን በሚመለከት አንድ አጫጭር ነገር አንስቼ ነበር። በተጨማሪም የኦሮሞ ጥያቄዎች መልስ ካላገኙ የሕዝብ እንቅስቃሴ ወይም አመፅ በድጋሚ መነሳቱ አንደማይቀር፤ በዚህ ሊነሳ በሚችለው የሕዝብ አመፅ ውስጥ ደግሞ የተለያዩ ሁኔታዎች (Scenarios) መፈጠር እንደምችሉ በመጥቀስ በአንደኛው ሁኔታ (Scenario 1) ላይ ትንሽ ለመግለፅ ሞክሬ ነበር። በዚህኛው በቁጥር አስራ ሁለት ፅሁፍ ውስጥ በእነዚህ ሊፈጠሩ በሚችሉት ሁኔታዎች ላይ ሰፋ ያለ ሀሳብ አቀርባለሁ።

የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ ወይም አመፅ ተመልሶ ከተነሳ ምን ዓይነት ሁኔታዎች (Scenarios) መፈጠር ይችላሉ?

ከባለፈው የሕዝብ አመፅ ተነስተን ካየን፣ የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ ግብ ሊመታ የሚችለው የዚህ ሕዝብ ወይም ብሔር አንድነት ሲኖር ብቻ ነው። ባለፈው የሕዝብ አመፅ ውስጥ ጠንካራ አንድነት በመኖሩ፣ ወያኔዎችን ማንበርከክ ችሏል።

ሁኔታ አንድን (Scenario 1) በድጋሚ ለማየት ወይም ለማስታወስ፥ያለፈው የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ እንደዚሁም በመሃል አገር በተቀናጀ መንገድ ሕዝብን ማሳተፍ ችሎ ነበር። ኦሕዴድም በወቅቱ የወያኔዎች ተላላኪ ቢሆንም በዚህ በሕዝብ እንቅስቃሴ ውስጥ ዕድል አግኝቶ ከተኛበት በመንቃት የተወሰነውን ያህል ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ለመቆም ተገዶ ነበር። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ የተለያዩ ስልቶችንና እስትራቴጂዎችን በመጠቀሙ የተለያዩ ልምዶችን መቅሰም ችሏል። ስለዚህ አሁን ሌላ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ከተደረገ ያለፈውን ልምድ መሰረት በማድረግ፣ ሌላ ስልትም ጨምሮ ከበፊቱ በተሻላ መልክ ድል ሊያስመዘግብና በዚህ ውስጥ ጥያቄዎቹም በቀጥታ መልስ እንዲያገኙ ማድረግ ይችላል።”

ይህ ባለፈው ፅሁፍ ውስጥ እንደተቀመጠው ነው። አሁንስ? ተመሳሳይ የሕዝብ እንቅስቃሴ ወይም አመፅ በድጋሚ ከተነሳ ምን ዓይነት ሁኔታ ነው ሊፈጠር የሚችለው?

ሁኔታ ሁለት (Scenario 2)

ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ ከገመገምን፣ ባሁኑ ወቅት የኦሮሞ ሕዝብ አንድነት ምን ያህል አስተማማኝ ነው? አንድነታችንን ጥያቄ ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ነገሮች ምንድናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች በደንብ ማየት አስፈላጊ ነው። በቅድሚያ፣ ወደ ጉዳዩ ከመግባቴ በፊት አንባቢዎች እንድገነዘቡ የምፈልገው እኔ በግሌ ከኦዴፓ ችግር የለብኝም። እነሱም የኛው ወንድሞች ስለሆኑ ማለት ነው። የሰፊው የኦሮሞን ሕዝብ ብሔራዊ ፍለጎት (Oromo National Interest) የሚያሟላ ነገር ከሰሩ ይደገፋሉ። ተቃራኒውን ከሰሩ ግን ይተቻሉ፣ ይወገዛሉ። በነገራችን ላይ ይህ ሁሉንም የኦሮሞ ድርጅቶችን ይመለከታል። በመሆኑም ኦዴፓን የሚተች ጉዳይ ካነሳሁ እነሱም ከስህተት እንዲማሩ እንጂ በነሱ ላይ ፕሮፓጋንዳ ለማድረግ እንዳልሆነ ግልፅ መሆን አለበት። ይህ ዓላማዬም ፍላጎቴም አይደለም። ይህ በዚህ መልክ እንዲታይ እፈለጋለሁ።

የኦሮሞ ሕዝብ አንድነት ባሁኑ ጊዜ ምን ያህል አሰተማማኝ ነው?

እንደሚታወሰው የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት፣ ንቃት ያለው ማንኛውም ኦሮሞ ባጋራ ስለተሳተፉበት፣ ያ እንቅስቃሴ ግብ እንዲመታ አስችለውታል። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉት የኦሮሞ አክቲቪስቶች በዚያ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። የኦሮሞ ሕዝብም በዚያን ወቅት በውስጣቸው የምከፋፍላቸው ባለመኖሩ ለጋራ ጉዳይ ባንድነት ቆመው ነበር። ዛሬ ግን ብዙ ነገሮች እየተቀየሩ ነው። ለምሳሌ፣ አንዳንድ ወሳኝ ሚና ስጫወቱ የነበሩት የኦሮሞ አክቲቭስቶች በግል ጥቅም የተሳቡ ወይም የተታለሉ ይመስላል። ሌሎቹ ደግሞ ቀድሞውኑ ማለትም በዚያ በሕዝባችን እንቅስቃሴ ወቅት ሲሳተፉ የነበሩት ለአድርባይነትና ልዩ አጋጣሚን ለመጠቀም ስሰሩ የነበሩ ናቸው። ከነዚህ አክቲቪስቶች ውስጥ ኣንዳንዶቹ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ከፈተኛ ቦታ ያገኙ አሉ። የነዚህ አክቲቪስቶች ቡድን የኦሮሞ ሕዝብ ነፃነቱን አግኝቷል፤ አሁን የቀረን በኢኮኖሚና እድገት ላይ መስራት ነው እያሉ ሕዝቡን ስያወናብዱ ይሰማል፣ ይታያል። ባጭሩ ለማስቀመጥ እነዚህ አክቲቪስቶች የኦዴፓ ፕሮፓጋንዲስቶች (mouthpiece) ሆነው ቁጭ አሉ ማለት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮሚያ ውስጥ ዛሬ ያለውን ሁኔታ ካየን፥

blank
Hoggantoota WBO: Jijjiramni dhufe tokko hin jiru. Jijjiramni jiru aangoon warra afaan biro dubbatani irraa gara warra afaan Oromoo dubbataniti darbuu qofaa dha. Ummata Oromoo irraa duuni, hidhamuun, saamamun fi kkf hin dabbanne.  Qabsoon mormi Abbaa Biyyummaa Oromoo hanga xummuraa argatuti itti  fufa.

አንደኛ፣ ኦዴፓ ቄሮን ከጎናቸው ለማሰለፍ ጥረት እያደረጉ ስለሆነ፣ በዚህ ምክንያት ቄሮዎች በተለያዩ ቡድኖች የተከፋፈሉ ይመስላሉ። የነፃነት ቄሮ፣ የእድገት ቄሮ እና የለውጥ ቄሮ ወዘተ በማለት በቄሮ መካከል መከፋፈልን የመሞከር አዝማሚያ እንዳለ ይሰማል። ይህ ማለት ባጭሩ ኦዴፓን በሚደግፉትና ያዚህን ድርጅት አካሄድ በሚቃወሙት መካክል የመከፋፋል ሁኔታ እንደሚታይ ነው።

ሁለተኛ፣ በኦሮሚያ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ ያለበት ሁኔታ ይለያያል። ባንዳንድ የኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ ለምሳሌ በጉጂና በምዕራብ ኦሮሚያ በየትኛውም ምክንያት ይሁን በጣም መጥፎ ሁኔታና እጅግ በሚያሳሳብ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። ምናልባትም በሀሳብ ለሁለት (ኦሮሞ ነፃነት አግኝቷል በሚሉና ኣይ ገና ከነፃነት ብዙ ርቀን እንገኛለን በሚሉት መካከል) በመከፈሉ የተነሳ ይሆን ባይታወቅም፣ ባንዱ የኦሮሚያ ክፍል ሕዝባችን ስስቃይ፣ በሌሎች ክፍሎች ያሉት ዝምታ የመረጡ ይመስላል።

ሶስተኛ፣ ይህ እየመጣ ነው ከሚባለው ለውጥ ጋር በተያያዘ ኣንዳንዶቹ የኦሮሞ ሕዝብ ስልጣን ተጎናፅፏል፤ የኦሮሞ መንግስትም ተመስርቷል ሲሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ይህ ሁሉ እውነት አይደለም፤ የኦሮሞ ሕዝብ ዛሬም የተለያዩ ችግሮች ውስጥ ገብቶ ነው ያለው፤ ይህ መንግስት በኦሮሞዎች ተመራ እንጂ የኦሮሞ መንግስት አይደለም የሚሉ አሉ። እንግዲህ ይህ ሕዝባችንን የሚያወናብዱና አንድነታችንን አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ናቸው።

ይሁን እንጂ እኔ ምንጊዜም የኦሮሞ ሕዝብ ባንድ የጋራ ጉዳይ ላይ ልዩነት ይኖራዋል ብዬ አላስብም። ነገር ግን ከላይ እንደ ተገለፀው፣ ባሁኑ ወቅት እየታየ ካለው ሁኔታ አንፃር ሲታይ ብዙ የሚያሳስብ ጉዳይ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሕዝብ አመፅ ቢነሳ፣ እንዴትና ባማን ይቀናጃል? የሚል ጥያቄ ትኩረት ማግኘት ያለበት ወሳኝ ጥያቄ ነው።

እዚህ ላይ ለነዚህ ለተፈጥሩት ሁኔታዎች ወደ ኦዴፓ ብቻ ጣት መቀዘር ተገቢ አይመስለኝም። የቀሩት የኦሮሞ ድርጅቶችም ራሳቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዚህ ውስጥ ሚና አላቸው። እነሱም ካለፈው ስህተታቸው የተማሩ አይመስሉም። እነሱም ቢሆኑ ዛሬ የምሰሩትና የምናገሩት አንዳንዶቹ የኦሮሞን ሕዝብ የምከፋፍል እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ለምሳሌ፣ ተዋህደናል፣ አንድ ሆነናል ወይንም ተስማምተናል አያሉ መግለጫ ከማውጣትና አብረው ፎቶ ከመነሳት ባሻገር አንድነታቸውን በሚመለከት በመሬት ላይ ተሰርቶ የሚታይ የለም። ይህም ራሱ ባለው ሁኔታ ላይ ተጨምሮ የሕዝባችንን ሁኔታ በይበልጥ የተወሳሰበ ያደርገዋል። ጠላቶቻችን የሚሸርቡትን ሴራና ተንኮል ሳይጨምር ማለት ነው። ይህንን መጥፎ ሁኔታ እንዴት ማሻሻል ይቻላል? ይህንን ጥያቄ ሁሉም ኦሮሞ ማንሳትና መልሱንም ማግኘት ያለበት ትልቅና የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። ፅሁፌን ለማጠናቀቅ፣ ሁኔታ ሁለት (Scenario 2) ምን መሆን እንደሚችል የሚረዳው ይረዳል። ዋቀዮ/እግዚአብሔር/አላህ ከመጥፎ ነገር ይጠበቀን።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ ቸር እንሰንብት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.