የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?  ሁለተኛ ዙር፥ ቁጥር አስራ ሶስት

የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነውሁለተኛ ዙር፥ ቁጥር አስራ ሶስት

ብርሃኑ ሁንዴ, Hagayya 23, 2019

Qubee Bilisummaa

በቁጥር አስራ ሁለት ፅሁፍ ውስጥ የፊንፊኔ ጉዳይ መፍትሄ ካላገኘና በዚህ ምክንያት ሕዝባዊ አመፅ በድጋሚ የሚነሳ ከሆነ፣ ምን ዓይነት ሁኔታዎች (scenarios) መፈጠር እንደምችሉ ለማብራራት ሞክሬ ነበር። በዚህኛው በቁጥር አስራ ሶስት ፅሁፍ ውስጥ ባሁኑ ጊዜ እየተሰራ ስላለውና የቋንቋን ጉዳይ በሚመለከት አንዳንድ ነገሮችን አቀርባለሁ።

ኦዴፓ(ODP) ኦሮሙማ (Oromummaa)ን የሚፃረር ስራ ከመስራት መቆም አለበት

የኦሮሞ ታሪክ እንደሚያሳየው፣ ምን ጊዜም ቢሆን የኦሮሞ ጠላቶች ኦሮሞን የምያሽነፉትና ዓላማቸውንና ፍላጎታቸውን ከግብ የምያደርሱት በኃይል፣ በእውቀትና በችሎታ ኦሮሞን በልጠው ሳይሆን፣ ኦሮሞን ራሱ እንደ መሳሪያ በመጠቀም ነው። ይህ ከጎባና ዳጬ ጀምሮ እስከ ዛሬም እየታየ ያለ ጉዳይ ነው። ከጠላቶች ጋር የምተባበሩና የምሰሩት ኦሮሞዎች በተለያዩ መንገዶች ይገለፃሉ። አንዱ ቡድን ወይም ግለሰቦች ለስልትና ለእስትራቴጂ ብለው ከጠላት ጋር ይተባባሩና ለኦሮሞ ሕዝብ አደጋ ከስከተሉ በኋላ በስተመጨረሻ ግን ለራሳቸውም ይጠፋሉ። ሌላው ቡድን ወይም ግለሰቦች ደግሞ ለራሳቸው የግል ጥቅማ ጥቅም ብለው ጠላትን በማገልገል የኦሮሞን ሕዝብ ይጎዳሉ። ያም ሆነ ይህ እነዚህ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ሁለቱም የኦሮሞ ነፃነት እንቅፋት ናቸው። አካሄዳቸው ደግሞ የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ፀር እና የኦሮሙማ ፀር ነው። ይህ እውነታ መታወቅ አለበት።

የኦዴፓ አካሄድም ከታየ፣ ከላይ ከተጠቀሱት ሁለቱ ቡድኖች ውስጥ አንዱ ወይንም ሁለቱንም ሊሆን ይችላል። እንዴት ከተባለ፣ አንደኛ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ በሚል ሽፋን፤ ሁለተኛ፣ የፖለቲካ ስልትና እስትራቴጂ ነው በማለት የኦሮሞን ሕዝብ በማታለልና በማባበል በጎን ግን እየተሰራ ያለው ፀረ ኦሮሙማ በመሆኑ ነው። እዚህ ላይ የሚያሳዝነው ግን የወያኔዎች ተላላኪ የነበረው ኦሕዴድ (OPDO) ከዚያ ከነበረበት ሁኔታ ውስጥ ወጥቶ፣ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ መገኘቱ በኦሮሞ ሕዝብ መራራ ትግልና እንቅስቃሴ በተለይ ደግሞ በቄሮ እንቅስቃሴ እንደሆነ ረስቶ፤ ለኦሮሞ ሕዝብ የገባለትንም ቃል በማፍረስ፤ የኦሮሞን ጉዳይ ወደ ኋላ በመግፋት፤ ለጠላትና ባዕድ ፍላጎት ግን ቅድሚያ በመስጠት መንከራተቱ ነው።

ይህ ፓርቲ ዛሬ በፌዴራል መንግስት ውስጥ ቁልፍ የሆነ ቦታ ያገኘው የኦሮሞ ሕዝብ በሺዎች የምቆጠሩትን ልጆቹን በዚህ ትግል ውስጥ በማጣቱ ነው። ያ ሁሉ ተረስቶ፤ የኦሮሞን ሕዝብ በመናቅ፣ ለዚህ ሕዝብ ጉዳይ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ የጠላቶችና ባዕዳን ፍላጎት ለማሟላት መጣሩ በታሪክ የሚያስጠይቅ ነው። ይህ ድርጅት ከዚህ በፊት ሲሰራ የነበረውን ስህተት በድጋሚ እየሰራ ነው። ከሁሉ በላይ የሚደንቀው ደግሞ የተወሰኑ የኦሮሞ ተወላጆች አራት ኪሎ ስለገቡ ልክ የኦሮሞ ሕዝብ ስልጣን እንዳገኘ ተደርጎ መወራት ነው። ባሁኑ ወቅት እንደሚታየው፣ አንድ ሕዝብ ስልጣን አግኝቷል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ያዳግታል። ጥያቄዎቹ ያልተመለሱለትና ፍላጉቱ ያልተሟላለት ሕዝብ፤ ሰላምና መረጋጋትን ያላገኘ ሕዝብ፤ ተርቦ የማያውቅ የኦሮሞ ሕዝብ ዛሬ ረሃብና ችግር ውስጥ እያለ፣ እንዴት ስልጣን አግኝቷል ተብሎ ይወራል?  ማጋነን አይሁንና ይህ ጉድ ነው!!

ኦሮምኛ ማደግ ባለበት ጊዜ በዚህ ቋንቋ ላይ ሴራ መስራት የኦሮሞ ሕዝብ ንቀት ነው

የኦሮሞ ሕዝብ ስያነሱ ከነበሩትና ካሉት ጥያቄዎች ውስጥ አንዱና ዋንኛው ኦሮምኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን ነው። ይህ ቢደረግ፣ ቋንቋውም የማደግ ዕድል ይኖረዋል። ይህ ቶሎ መልስ ማግኘት ያለበት ጉዳይ ሆኖ እያለ፣ ፀረ ኦሮሙማ የሆነ ዕቅድ ተግባር ላይ ለማዋል፤ አማርኛን በኦሮሞ ልጆች ላይ ለመጫን ማቀድ በጭራሽ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው። ይህ አካሄድ የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) እስካሁን ያስመዘገበውን ድል ወደ ኋላ እንደ መመለስ ነው። ይህ የኦሮሙማ ጠላት ነው፤ ፀረ-ኦነትም ነው። ይህን ተንኮል ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ አጥብቆ መቃወም አለበት። ጠንካራ ተቃውሞ ማሳየትም የግድ ይሆናል። የኦሮሞ ጠላቶች በተለይም ደግሞ የኦነት ፀር የሆኑ ኃይሎች በኦዴፓ በመጠቀም ፍላጎታቸውንና ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሆነ ሕዝባችን ማስተዋል አለበት።

እውነት ለመናገር የኦሮሞን ሕዝብ ንቆ ጠላቶቻችን ተንኮል እንድሰሩብን የሚያደርገው ኦዴፓ ነው። በመሆኑም የኦሮሞ ሕዝብ ለኦዴፓ የመጨረሻ ዕድልና ማስጠንቀቂያ መስጠት አለበት። ይህ ካልሆነ፣ ይህ ፓርቲ ትልቅ ችግር ሊያመጣብን እንደሆነ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ይህ ለፕሮፓጋንዳ ሳይሆን በመሬት ላይ እየታየ ያለው ሀቅ በመሆኑ ነው። የምገርመው በምን ሞራል ወይም በየትኛው አሳማኝ በሆነ ምክንያት ነው ይህ ፀረ ኦሮሙማ የሆነ ፍኖተ ካርታ (roadmap) ተዘጋጅቶ፣ አማርኛን በኦሮሞ ልጆች ላይ ለመጫን የሚታሰበው፧ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አፋን ኦሮሞን ለማቀጨጭ ተብሎ በደንብ የታሰበበትና ለረጅም ጊዜ ሲሰራበት የቆየ በመሆኑ፣ ይህንን ተንኮል በንቃት ማየት ወሳኝ ነው። ይህ ፍኖተ ካርታ በስራ ላይ ከዋለ፣ ተከትሎ የሚመጣው ምን እንደሚሆን መገመት የሚያስቸግር አይመስለኝም። እየመጣ ወይም እየተቃረበ ያለውን አደጋ በሩቅ ማየት መቻል አስፈላጊና ወሳኝም ነው።

የባዕድን ቋንቋ በሕዝባችን ላይ መጫን ቀርቶ፤ ኦሮምኛ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን ለማድረግ ጊዜው ደርሷል። የኦሮሞ ሕዝብ ትዕግስትም ከወስን እያለፈ ስለሆነ፣ ኦዴፓ ከጠላቶቻችን ጋር የሚያሴረው ድርጊት በጥሞና መከታተልና መቆጣጠር የግድ ይሆናል። ይህ ድርጅት ለኦሮሞ ሕዝብ እንዳልቆመና የዚህን ሕዝብ ፍላጎት እንደማይጠብቅ በተደጋጋሚ ሲያሳይ ቆይቷል። እየተሰራ ያለውን ተንኮል ለማክሸፍ የኦሮሞ ሕዝብ ባንድነቱና በንቃት መነሳት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ብሔራዊ ፍለጎት (Oromo People’s National Interest) ሳይሟላ ከሚቀር፣ ይህቺ ኢትዮጵያ የምትባል አገር በመቶ ቦታ ብትበታትን ይሻላል። ለኦሮሞ ጉዳይ ትኩረት የማይሰጥ አካሄድና አሰራር ካሁን በኋላ በዝምታ መታለፍ የለበትም። የኦሮሞን ሕዝብ መብትና ፍለጎት የማይጠብቅ የአገሪቷ አንድነትም እውነተኛ አንድነት መሆን አይችልም። እውነተኛ ላልሆነ አንድነት መንከራተት ደግሞ አስፈላጊ አይደለም። ኦዴፓም በእሳት መጫወትን ማቆም አለበት።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ ቸር እንሰንብት

1 Comment

  1. I would like to remind Oromos what former Minster of Haile Sellasie Aklilou Habte Wold told General Tadesse Biru ” Oromo bebizat ketmarree lenjaa adegga neuw ” meaning if many Oromos get good education it will be dangerous for us(meaning for Amhara). Aklilou also threatened Ato Emmanul Abarham for promoting education in Oromo regions although at the time most of the schools were established in Amhara region . At Emmanul challenge him by providing accurate statistical evidence to th Emperor. I invite Oromo people to read Ato Emmanul Abraham’s book entitled ” Reminiscences of my Life”. I agree with Admi that the same thing is going on in Finfine although the PM is a nominal Oromo and ODP leaders are no different from Aklilou Habte Wold . Fact is Fact but the Quebbee generation is not going to accept neither should any Oromo .

Leave a Reply to Bontu Biyya Cancel reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.