የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? 

የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? 

ሁለተኛ ዙር፥ ክፍል አንድ

ብርሃኑ ሁንዴ, Ebla 13, 2019

ማስታወሻ

“የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? – ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች “

በሚል ርዕስ የተለያዩ ፅሁፎችን በ 24 ክፍሎች ባለፈው ዓመት ሳቀርብ እንደነበር የሚታወስ ነው። የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ዛሬ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማየትና መረዳት አያስቸግርም። ይህ ትግል ብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ፤ የተለያዩ ድሎችን አስመዝግቦ ዛሬ ቢደርስም፣ ዋና ዋና የሆኑ የኦሮሞ ጥያቄዎች አሁንም መልስ አላገኙም። ኦሮሞ ነፃ ወጥቷል ብለው የሚናገሩ ብዙ ናቸው። ይሁን እንጂ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ከዚህ በፊትም እንደፃፍኩት ኢትዮጵያ ነፃ ወጣች እንጂ ኦሮሞና ኦሮሚያ ነፃ አልወጡም። ለነፃነት የሚሰጠው ትርጉም ወይም አገላለፅ እንደ ግለሰብ አመለካከት በመሆኑ፣ ይህ አከራካሪ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከእውነተኛ ነፃነት አሁንም ብዙ ርቀን እንገኛለን። ረጅም መንገድ ይጠብቀናልም።

ዛሬ ፀረ-ኦነት የሆኑት ኃይሎች በውስጥም ሆነ በውጭ እየበዙና እየጠነከሩም ናቸው። የኦሮሞና ኦሮሚያ የወደፊት ዕጣ ምን እንደሚሆን ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ኦነት እስከ ዛሬ ያስመዘገባቸው ድሎች እንኳን አደጋ ውስጥ ሊገቡ ነው ቢባል ሀሰት አይሆንም። ስለዚህየኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? የሚለው ጥያቄ አሁንም ክፍት በመሆኑ፣ ይህንን ጉዳይ የሚመለከቱ  የተለያዩ ፅሁፎችን በሁለተኛ ዙር ለማቅረብ እፈለጋለሁ።  በመጀመሪያ ዙር ሳቀርብ የነበረውን ፅሁፎች ማግኘት የምትፈልጉ Ayyaantu.org በመግባት ልታግኙ ትችላላችሁ።

መግብያ

እንደሚታወቀው የኦሮሞ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በተለይ ደግሞ የቄሮ ኦሮሞ ትግል የወያኔ የበላይነት አገዛዝ እንዲቀየር አድርጔል። ይህ ደግሞ በሺዎቹ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች መስዋዕትነት የከፈሉበት በመሆኑ፣ የኦሮሞ ድል ነው ቢባል ሀሰት አይሆንም። ይሁን እንጂ የድሉ ባለቤት የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ከዚህ ለውጥ የሚገባውን አላገኘም። የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ቤት መፈታት፣ውጭ አገር የቆዩት የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር መለስ፣ እንደዚሁም አንዳንድ ነገሮች መሻሻል በአገሪቷ ደረጃ የተደረጉ ናቸው እንጂ በተለየ መልክ ለኦሮሞ ሕዝብ የተደረጉ አይደሉም። ይህ ለውጥ ኦሮሞን ነፃ አውጥቷል የሚሉ ብዙ ብሆኑም መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ሌላ ነው።

ለውጥ መጥቷል ግን የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከግቡ ደረሰ?

የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከግቡ መድረሱ ቀርቶ፣ ወይንም ደግሞ አንዳንዶቹ  እንደሚሉት ኦሮሞ ነፃ መውጣቱ ቀርቶ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ባገሩ በሰላም ወጥቶ መግባት ኣልቻለም። እስቲ እናስታውስና፥ ቁጥራቸው የማይታወቅ በኦሮሚያ ድንበሮች ላይ በተከፈተባቸው ጦርነት ሕይወታቸውን ያጡትን እንኳን ትተን፣ ቁጥራቸው ወደ ሚልየን የሚገመት ከሱማሌ ክልል ከቀዬኣቸውና ንብረታቸው የተፈናቀሉት፤ ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉት፤ ጦርነት ተክፍቶባቸው እንደ ዛፍ ቅጠል እየረገፉ ያሉት ወዘተ በሙሉ የሆነው ይህ ለውጥ ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህና ኦሮሞ አገሪቷን እያስተዳደረ ነው በሚባልበት ጊዜ ነው። ታዲያ ለኦሮሞ ሕዝብ የተገኘው ጥቅም ምንድነው? ኦሮሞ የሆኑ ሰዎች ከፍተኛ ሹመት ስላገኙና የኦሮሞን ስም የያዘው ድርጅት ባገሪቷ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው ብቻ ኦሮሞ ነፃ ወጥቷል ማለት አይቻልም።

አገሪቷን እያስተዳደር ያለው ኦሮሞ ነው በሚባልበት ሁኔታ ውስጥ ኦሮሞ ከድሮ የባሰ እየተጎዳ እንደሆነ የሚያውቀው እግዚአብሔርና በአይኑ ያየ ብቻ ነው። በተቃራኒው ግን ይህ ለውጥ በይበልጥ እየጠቀመ ያለው ፀረ-ኦነት የሆኑትን ኃይሎች እንደሆነ ይታያል። ከኦሮሞ ውስጥ የወጣው ጠቅላይ ሚኒስተር በየሄደበት ሁሉ ስላለፉት ንጉሶች በሚያደንቅበት ወቅት፤ የኦሮሞ ልጅ የሆነው የክልሉ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው እያለ በየሚዲያው በሚያስተጋባበት ወቅት የተገኘው ትርፍ ቢኖር ፀር-ኦነት ኃይሎች በተለይም ደግሞ የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች ሞራል እያገኙ መምጣትና ራሳቸውን በደንብ አደራጅተው ሀይላቸውን ማጠናከር ነው። እነዚህ ኃይሎች ለኦሮሞ ያላቸውን ንቅትና ጥላቻ ከምንጊዜውም የበለጠ ያለምንም ገደብ በይፋ እያሳዩ ያሉት ለውጡ ለኦሮሞ ይልቅ ለነሱ መሆኑን ያሳያል።

የሚገርመው ግን ለነዚህ ለፀረ-ኦነት ኃይሎች ሞራል የሰጡት የኦሮሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንኳን ከነዚህ ኃይሎች ዒላማ ውስጥ አልወጡም። ምንም ያህል ስለ ኢትዮጵያ ፍቅር ብያወሩም ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ ከፀረ-ኦነት ኃይሎች ጥቃት አላመለጡም። ይሁን እንጂ እየተሰደቡም፣ እየተረገሙም፣ እየተናቁም፣ እየተተቹም፣ ወዘተ ሁሉንም አየሰሙና እያዩ ፀጥ ብለው ለኢትዮጵያ አንገታቸውን ለመስጠት ተግተው እየሰሩ ነው። የኦሮሞ ሞት ግን ለነሱ ምንም አይደለም። የአገሪቷ አንድነት ግን እረፍት አይሰጣቸውም። ሌት ተቀን ለአገሪቷ አንድነት ይንከራተታሉ። ከአብራኩ የወጡትን ሕዝብ ግን በኣፍ ማታለል እንጂ ለዚህ ሕዝብ የሰሩት ወይም ያስገኙት ልዩ ጥቅም አይታይም። ይህ በጣም ያሳዝናል። ከኦነት ጋር ተያይዞ ለምሳሌ ያህል የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን (WBO) ጉዳይ ካየን፣ WBO ወደ ጫካ እንዲገባ ያደረገው ኦነት ነው። ይህ ኃይል ትጥቁን ፈቶ ወደ ካምፕ እንዲገባ የሚደረገው ኦነት ከግቡ ደርሷል ለማለት ነው ወይንስ ኦነት ከግቡ መድረስ የለበትም ለማለት ይሆን? ያለንበትን ሁኔታ በደንብ ካየናን በጥልቀት ከገመገምን፣ ባጠቃላዩ ኦነት ከግቡ መድረሱ ቀርቶ እንዲያወም አደጋ ውስጥ እንደገባ ለመረዳት አያዳግትም።

በዚህ ለውጥ ውስጥ የኦሮሞ ጥያቄ መልስ አግኝቷል?

ከዚህ በላይ እንደተገለፀው፣ ኦነት ከግቡ መድረሱ ይቅርና ዋና ዋና ከሆኑት የኦሮሞ ጥያቄዎች ውስጥ እስካሁን አንድም መልስ አላገኘም። ለጥያቄዎቹ መልስ መስጥት አስቸጋሪ ሆኖ ነው ወይንስ ለመመለስ ፍላጎትም ስለሌለ ነው? ኦሮሞ ነው አገሪቷን እያስተዳደር ያለው ወይንም ኦሮሞ ስልጣን አግኝቷል ከተባለ ለምንድነው አንድም ጥያቄ መልስ ያጣው? የአንድ ሕዝብ ስልጣን እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ ነው እንዴ? የአንድ ሰፊ ሕዝብ የስልጣን ባለቤት መሆን የሚያስገኘው ትርፍ እኮ እጅግ ብዙ ነው። ታዲያ የኦሮሞ ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ከሆነ ለምን ጥያቄው አይመለስም? አስቲ ከኦሮሞ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱን እንደ ምሳሌ እንውሰድና፣ የፊንፊኔን ጉዳይ እን ይ። ፊንፊኔ በታሪክም፣ በሕግም፣ በአቀማመጥም በሁሉ መንገድ የኦሮሚያ አካልና የኦሮሞ ሕዝብ መሬት ናት። በመሆኑም የፊንፊኔ ጥያቄ ያለምንም ማወላወል የኦሮሞ የአገር ባለቤትነት ጥያቄ ነው።  የድሮ ስርዓት ናፋቂውች ግን ፊንፊኔ ጭራሽ የኦሮሞ መሬት አይደለችም አስከማለት ደፍረዋል። ምን ያድርጉ ሞራል የሰጣቸውም ሆነ ሁኔታዎችም እንዲመቻችላቸው ያደረጉት በስጋና ደም ኦሮሞ ሆነው ግን በኢትዮጵያዊነት ሱስ የሰከሩ የኦሮሞ ባለስልጣናት በመሆናቸው አይደንቅም።

አሁን ያለው የፌዴራል ስርዓት ምን ሊሆን ነው?

በብሔሮችና ብሔረሰቦች ክልሎች ላይ ተመስርቶ የተቋቋመው አሁን ያለው የፌዴራል ስርዓት የኦሮሞ የነፃነት ትግል ካስገኛቸው ድሎች ውስጥ አንዱና ዋናው ነው። ይህ ደግሞ በወያኔ የተሰጠን ስጦታ ሳይሆን ስንት የዜጎች ሕይወት የጠፋበት፣ ደም የፈሰሰበትና የጭቁን ሕዝብ ልጆች አጥንት የተከሰከሰበት ነው። ዛሬ በካርታ ላይ ታይታ በዓለም የምትታወቅ ኦሮሚያ በዚህ በተከፈለው መስዋዕትነት ውስጥ ነበር የተረጋገጠች። አሁን ያለውን የፌዴራል ስርዓት ማፍረስ ማለት ኦሮሚያን ማጥፋት በመሆኑ፣ ከባድ መስዋዕትነት ይከፈልበታል እንጂ ይህ ዘመቻ አይሳካም። ይህንን ጉዳይ በሚቀጥለው ፅሁፍ በሰፊው እመለስበታለሁ።

ተመልሰን እስከምንገናኝ በደህና ቆዩ

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.