የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ክፍል አስራ ስምንት

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ , Waxabajjii 5, 2018                                           

ክፍል አስራ ስምንት

የኢትዮጵያ መንግስት ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ለመነጋገር ከመፈለጉ በስተጀርባ ተንኮል መኖር እንደሚችል ባለፈው ፅሁፌ ውስጥ ሀሳቤን ለማብራራት ሞክሬ ነበር። ይህ ተንኮል ደግሞ በይበልጥ በኦሮሞ የነፃነት ትግል ጎራ (camp) ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ዓላማው በኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ኣለመግባባት እንዲፈጠር፤ የኦሮሞ ኃይል እንዲዳከምና በዚህ የተነሳ የነፃነት ትግሉ እንዲዳከም ለማድረግ ነው። ስለዚህ ይህንን ተንኮል ለማክሸፍ የኦሮሞ ብሔርተኞች ሁሉ ግዴታ መሆን ኣለበት። ይህ ተንኮል እንዳይሳካና የነፃነት ትግሉም ወደፊት እንዲራመድ ኣንዳንድ መደረግ ያለባቸውን ጉዳዮች በዚህኛው ፅሁፍ ማንሳት አሞክራለሁ።

ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለውይይት ከመቅረብ በፊት የኦሮሞ ድርጅቶች አስቀድመው መነጋገርና በኦሮሞ ጥያቄ ላይ አንድ የጋራ አቋምና አጀንዳ መያዝ ኣለባቸው

እንደ ፖለቲካ ዓላማቸውና ከሚፈልጉት የፖለቲካ ግብ አንፃር ሲታይ የኦሮሞ ድርጅቶችን በሁለት ትላልቅ ቡድኖች ክፍሎ ማየት ይቻላል። አንድኛው ቡድን፥ የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ለማስቻል የሚታገሉ ኃይሎች ሲሆኑ፥ ሌለኛው ቡድን ደግሞ፥ በኢትዮጵያ እውነተኛ ዲሞክራሲን ማምጣት ከተቻለ በዚህ ውስጥ የኦሮም ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ይችላል የሚሉና ለዚህም የሚታገሉ ኃይሎች ናቸው። ይሁን እንጂ እጅግ የሚያሳዝነው ኣንድ ዓላማና ግብ ያላቸው ድርጅቶች የትግል ሕብረት መመስረት ኣለመቻላቸው ነው። በመሰረቱ ኣንድ ላይ መጥተው ባንድ አመራር ስር እንደ ኣንድ ብቸኛ ድርጅት መወሃድ የለባቸውም። እንደ ኦሮሞ ምኞትና ፍላጎት ቢሆን ኖሮ የዓላማ ኣንድነት ወይም ሕብረት (unity of purpose) መፍጠር የኦሮሙማ ግዴታ መሆን ነበረበት። የግል ፍላጎትና ሌሎች ችግሮችም ስላሉ ይህ አንድነት ሳይሳከ ቀርቷል። ይህ ችግር በይበልጥ የሚታየው ደግሞ በውጭ አገራት በሚገኙ ድርጅቶች መካከል ነው።

ኣንዳንድ ድርጅቶች ስም ብቻ ይዘው ስቀመጡ፣ በአገር ቤት እየተደረገ ያለው ሕዝባዊ ትግል ግን እነሱን ጥሏቸው ሄዷል። እኛ እንቆምለታለን፣ እንወክላልን፣ እንመራለን የሚሉት ድርጅቶች የኦሮሞ ሕዝብ ከነሱ ቀድሞ በመሄድ ድርጅቶቹን እየመራ ነው ያለው። ስለዚህ ስም ብቻ ይዞ መቀመጥ፣ ስብሰባ በማድረግና የአቋም መግለጫ ማውጣት፣ በስራ ምንም ሳያሳዩ ኣለን ኣለን ማለት ጊዜው አልፎበታል። አሁን ከነሱ የሚጠበቀው፥ ተቀላቅለው ኣንድ ድርጅት መሆን ወይም ኣንድነት መፍጠር ካቃታቸው፣ ቢያንስ በሕዝባችን ጉዳይ ላይ መነጋገር፣ ግልፅ የሆነ ኣንድ የጋራ አቋም መያዝ፣ ድንገት ሊመጣ ለሚችል ለውጥ እንዴት ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚችሉ መወያየትና የጋራ የወደፊት ዕቅድ (road map) ማዘጋጀትና ለሁሉ ነገር ዝግጁ መሆን ነው። ከየትኛውም አካል ጋር ይሁን ለውይይትና ድርድር ከመቅረባቸው በፊት ኣንድ የጋራ አጀንዳ ሊኖራቸው ያስፈልጋል። ይህ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው።

ባገር ውስጥ ያሉትን የኦሮሞ ድርጅቶች ካየን፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንፈረንስ (ኦፌኮ) በትግል ዓላማ አንድ የሆኑትን ሁለት ድርጅቶችን አዋህዶ፣ ኣንድ ድርጅት ሆኗል። ይህ ድርጅት ለሌሎች ድርጅቶች ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችል ነበር። ይሁን እንጂ አቶ በቀለ ገርባ በአሜሪካ በተደረገለት የአቀባበል ስብሰባ ላይ እንደ ተናገረው፥ “እኛ በየትኛውም ድርጅት መዋጥም ሆነ ሌላ ድርጅት ለመዋጥ ዕቅድ የለንም” እንዳለው ሳይሆን ኦፌኮም በሩን ክፍት በማድረግ፤ ሌሎች ከሱ ጋር በዓላማና ግብ የሚመሳሰሉትን ድርጅቶች በመቀበል የዓላማ ኣንድነት (unity of purpose) መፍጠር አስፈላጊ ነው ብዬ ኣምናለሁ። የትኛውም ይሁን የጋራ የትግል ዓላማ ያላቸው ድርጅቶች ኣንድ ላይ መምጣት ጊዜው አሁን መሆን ኣለበት። በዚህ መንገድ ኣንድ ላይ መጥተው፣ ኣንድ ዓይነት አቋምና የጋራ አጀንዳ ይዘው በጋራ ካልሰሩ በቀላሉ መሸነፍ ይሆናል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሚያ ነፃነት ኃይሎች በአዲስ መልክ ተጠናክረው መገኘት  ኣለባቸው

እዚህ ላይ የኦሮሚያ ነፃነት ኃይሎች (Liberation Forces of Oromia) ስል የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ለማስቻል የሚታገሉ ድርጅቶች ለምሳሌ እንደ የኦሮሚያ ነፃነት ግንባር (FIO)፣  የኦሮሚያ ነፃነት ኃይሎች ኣንድነት (ULFO) እና ተመሳሳይ የትግል ዓላማና ግብ ያላቸው ሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች ማለቴ ነው።

ስለ ኦነግ ሳነሳ ግን ኣንድ መገንዘብ ያለበት ጉዳይ እኔ ስለ ኣንድ የተወሰነ ቡድን መናገሬ አይደለም። በጣም የሚያሳዝነው ነገር ዛሬ ይህንን ስም ይዘው ያሉ ድርጅቶች ወይም ቡድኖች መብዛታቸው ነው። ባሁኑ ጊዜ ይህን ማየት አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን የሚያሳፍርም ነው። ኦነግ የኦሮሞ ነፃነት ትግል ዋና መሪና አንጋፋ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍሎ መታየትን የበለጠ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነገር የለም ብል ከእውነት መራቄ አይሆንብኝም። ይህ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ እጅግ የሚወደድ ድርጅት ነው በ1991 ትላልቅ ደሎችን ያስመዘገበው። ለዛሬው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት መመስረት ከፍተኛውን ድርሻ ያበረከተው ኦነግ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር የሚያደርገው ውይይት ኦነግና ሌሎች የኦሮሚያ የነፃነት ኃይሎችን ካላሳተፈ ትርፍ የሚያመጣ አይመስለኝም።

በሌላ በኩል ደግሞ ኦነግ የሚለውን ስም ይዘው የሚገኙ የተለያዩ ድርጅቶች ወይም ቡድኖች ኣንድ ላይ ተመልሰው እንደ አንድ ኦነግ ባንድ አመራር ስር ባይወሃዱም እንኳን ኣንድ ላይ መጥተው ተመካክረው ወይም ተወያይተው ኣንድ የጋራ አቋም ካልያዙ እና ለብቻ ለብቻ ሄደው ከመንግስት ጋር ውይይት ማድረግ የሚፈልጉ ከሆነ ከሚያመጣው ትርፍ ይልቅ የሚያስከትለው ጉዳት ይበልጣል የምል እምነት ኣለኝ። የዚህ አይነት አካሄድ የፖለቲካ ኪሳራን ሊያመጣ ይችላል። በኋላ መስተካከል የማይችል ስህተት ሊሰራ ይችላል በዬ ኣስባለሁ። አሁን ባጣም ወሳኝ የሆነ ጊዜ ውስጥ ስላለን እጅግ መጠንቀቅን ይጠይቃል።

ለሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ትርፍ ለማምጣት የሚፈልጉ ማንኛውም የኦሮሞ ኃይሎች ጠላትን ለማሸነፍም ሆነ ለወደፊታችን ጥሩ መሰረት ለመጣል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በኦሮሞ ጥያቄ ላይ ተመካክርው የጋራ አቋም መያዝ ጊዜ የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ ነው። ድሮ እንደተለመደው ሁሉም ለየብቻ የምሯሯጡ ከሆነ ታግለው ጠላትን ለማሸነፍም ሆነ ለውይይት ቀርበውና ተደራድረው ለኦሮሞ የሚበጅ መፍትሄ ማግኘት በፍፁም አይቻልም። የተለያየ ዓላማ ያላቸው የኦሮሞ ድርጅቶች ኣንድ የጋራ አቋም መያዝ ባይችሉም  አንድ ወይም ተመሳሳይ የትግል ዓላማና ግብ ያላቸው ድርጅቶች የዓላማ አንድነት ፈጥረው ኣንድ አቋም መያዝ አስፈላጊ ብቻም ሳይሆን እንደ ግዴታ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው ብዬ ኣምናለሁ።

በስተመጨረሻ፣ ኣንድ መረሳት የሌለበት ጉዳይ ነፃ የሆኑ የኦሮሞ ድርጅቶች ተግባብተው የጋራ አቋም ይዘው፣ የሰፊውን ኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት በኣንድነት ወይም በሕብረት ካልሰሩ የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዲድ) እንደ ኣንድ ዋንኛና የኦሮሞን ሕዝብ ሊወክል እንደሚችል ድርጅት ራሱን ኣቅርቦ፣ ሁሉንም ለመወሰን የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ኣለኝ። ይህ ድርጅት ደግሞ አሁንም ነፃ ያልሆነ በመሆኑ፣ ሌሎች የኦሮሞ ነፃ ድርጅቶች ባልተሳተፉበት የፖለቲካ መድረክ በዚህ ድርጅት ስር የኦሮሞ ጥያቄ መልስ ሊያገኝ አይችልም። የኦሮሞ ጥያቄ መልስ ማግኘቱ ቀርቶ ዜጎች እየተገደሉ ባሉበትና ባጠቃላይ የሕዝባችን ሰላምና ደህንነት በልተጠበቀበት ባሁኑ ወቅት ይኸው እንደሚሰማው ነፃ አወጣናችሁ፣ ከዚህ ሌላ ምን ትፈልጋላችሁ እያሉን አይደለም?

በነገራችን ላይ፣ ለመሆኑ በኦቦ ለማ መገርሳም ሆነ በጠ/ሚኒስተር አብይ አህመድ አማራር ስር ሌት ተቀን የኢትዮጵያን አንድነት ከመዝፈን ውጪ ለኦሮሞ ሕዝብ የተገኘ ለውጥ ምን ኣለና ነው ይህን ኣደረግንላችሁ እያሉ የሚፎክሩት? ስለዚህ ጉዳይ በሰፊው እመለስበታለሁ።

ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.