የጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ ጥረቶችና ገና የሚጠብቁት ትላልቅ ፈተናዎች, Parts III, II, I

0

የጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ ጥረቶችና ገና የሚጠብቁት ትላልቅ ፈተናዎች

ብርሃኑ ሁንዴ, Adoolessa 23, 2018

Abiy

ክፍል ሶስትና የመጨረሻ

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩት የፖለቲካና ኣይዶሎጂ ልዩነቶች፤ ስለ አንቀፅ 39፤ አሁን ስላለው በብሔር ክልሎች ላይ የተመሰረተው የፌዴራል ስርዓትና ለጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አስተዳደር ትልቅ ፈተና ሊሆኑ የሚችሉት ሌሎች ኣንዳንድ ጉዳዮች በክፍል ኣንድ ፅሁፍ ውስጥ ተነስተው ነበር። በዚህኛው ክፍል ሶስት ፅሁፍ ውስጥ በጣም ትልቅና ፈታኝ የሆነውን የኦሮሞ ነፃነት ትግልና የኦሮሞ ብሔራዊ ጥያቄን በሚመለከት ኣንዳንድ ጉዳዮችን ኣንስቼ ሀሳቤን ልሰጥበት እሞክራለሁ። ዛሬ ማንሳት ወደ ፈለኩት ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ግን ኣንድ ነገር ማለት እፈለጋለሁ።

ከተለያዩ ሚዲያዎች ማየትና መስማት እንደሚቻለው፣ ሀበሾች በተለይም ደግሞ የድሮው ያረጀ ስርዓት እንዲመለስ የሚመኙ ኃይሎች ባሁኑ ጊዜ እየተንጫጩ እንደሆነ ነው። የዚህ መንጫጫት ምክንያት ደግሞ አዲሱን የፊንፊኔ ካንቲባን በሚመለክት ሲሆን፣ ይህንን ለመቃወም የኦቦ ለማ መገርሳና የዶ/ር አብይ አህመድን አስተዳደር እየኮነኑ፣እየተቹና ዘመቻም እየደርጉበት ይመስላል። እነዚህ ኃይሎች ያኔ ዶ/ር አብይ እንደ አገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስተር ሲመረጥ ባደረገው ንግግር ውስጥ አፄ ሚኒሊክን ሲያደንቅ ሲደሰቱና እስክስታ ሲወርዱ የነበሩት ናቸው። ዛሬ ግን ፍላጎታቸው ሳይሳካ ሲቀር ፊታችውን ከዶ/ር  አብይ በማዞር አስተዳደሩን እየተቹ ነው። እንግዲህ ይኸው ዶ/ር አብይን የሚጠብቁት ፍተናዎች ከዚህ እየጀመረ ነው ማለት ነው።

በጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አስተዳደር ውስጥ የኦሮሞ ብሔራዊ ጥያቄ እንዴት መልስ ሊያገኝ ነው?

የኦሮሞ ጥያቄ ራሱ ምንድነው? ብለን ጥያቄ ብናነሳ፣ የተለያየ ትርጉምና አገላለፅ የሚሰጠው ይመስለኛል። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ለዚህ ጥያቄ ፊቺ ወይም አገላለፅ ሲሰጥ፥ የኦሮሞ ሕዝብ ወይም ብሔር በአፄ ሚኒሊክ ጦር ተወሮ በጉልበትና ጦርነት አገሩ ስለተወሰደበት ይህ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው ይላል። ኦነግ በዚህ ታሪካዊ አገላለፅና እውነታ ላይ በመመስረት፣ የኦሮሞ ሕዝብ ያጠውን ነፃነቱን መልሶ እንዲያገኝና የኦሮሚያ ነፃ መንግስት እንዲቋቋም ብሎ ነው ትግል የጀመረውና ይህንን ከግብ ለማድረስ እየታገለ ያለው። እዚህ ላይ እኔ እንደምረዳው ይህ የኦነግ የትግል ዓላማና ግብ ቢሆንም፣ ይህ ድርጀት/ግንባር እንደ ፖሊሲው ያስቀመጠው ጉዳይ ግን የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራስ የመውሰን መብቱ ተጠብቆ፤ ይህ ሕዝብ ሀሳቡን የመግለፅ ዕድል ካገኘ፣ እንዴትና ከማን ጋር መኖር እንድሚፈልግ፣ ምን ዓይነት የፖለቲካ መዋቅር መመስረት እንደሚሻ የሚወስነው ይኸው ሰፊ የኦሮሞ ሕዝብ ነው ብሎ የሚያምን ይመስለኛል።

ሌሎች የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ግን የኦሮሞን ጥያቄ እንደ ዲሞክራሲና ራስን የማስተዳደር ጥያቄ አድርገው የሚገልፁ ይመስለኛል። የቅኝ ግዛት ጥያቄ በሚለው ላይ ከኦነግ ጋር የሚስማሙ አይመስለኝም ማለቴ ነው። ስለዚህ የኦሮሚያ ነፃ መንግስትን ማቋቋም አስፈላጊ አይደለም፤  ኦሮሞ ራሱን ማስተዳደር (Self Rule) ከቻለና ከሌሎች ጋር ደግሞ የጋራ አስተዳደር (Shared Rule) መፍጠር ከቻለ ጥያቄውም በዚህ ሊመለስ ይችላል የምሉ ይመስሉኛል። እዚህ ላይ ከተሳሳትኩኝ ሊያርሙኝ ይችላሉ። ይህ የሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት ከሆነ ደግሞ ኦነግም ይህንን የሕዝብ ውሳኔ የሚቃወም አይመስለኝም። በመሆኑም በመሰረቱ በኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ችግር መኖርም ኣልነበረበትም ብዬ ኣምናለሁ። ሁሉም ለኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት ከቆሙ እርሰ በርስ መቃወምን ምን ኣመጣው?

በርዕሱ ላይ ወደተነሳው ጥያቄ ለመመለስ፣ OPDOስ የኦሮሞን ጥያቄ እንዴት ያያል? እንዴት ትርጉም ይሰጠዋል? በዚህ ጥያቄ ላይ ከሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር በተለይም ደግሞ ከኦነግ ጋር መግባባት ይችላል? ኦቦ ለማና ዶ/ር አብይ ራሳቸው ይህንን ጥያቄ እንዴት ያዩታል? እንደ ኦነግ አገላለፅ ይህንን ጥያቄ  በዚህ መልኩ ተቀብለውትና መልሱንም ለማግኘት ቢሞክሩ፣ ከሀበሾች ጋር መጣላት ስለሚሆንባቸው፣ በሁለት ኃይሎች መካከል ገቡ ማለት ነው። ኣይ አይደለም ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ስሉ እንደነበረ፣ ወደ ሀበሾቹ  ወገን የሚሄዱ ከሆነ፣ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር መጣላት ይሆንባቸዋል። መጣላት ብቻ ሳይሆን በነሱ አስተዳደር ስር የኦሮሞ ጥያቄ ካልተመለሰ፣ በኦሮሞ ታሪክ ውስጥ መጥፎ ነገር ሰርተው እንዳለፉም ይታያል። ታሪክ ሁሌም ይወቅሳቸዋል። ስለዚህ ወይ ኦሮሙማን (Oromummaa) ወይንም ኢትዮጵያዊነትን (Itoophiyummaa) መመረጥ የግድ ይሆናል። ይህ ለንሱ ትልቅ ፈተና ነው።

የኦሮሞ ጥያቄ የአገር ባለቤትነት ጥያቄ ነው

በየትኛውም መንገድ ወይም መልክ ይሁን፣ የኦሮሞ ድርጅቶች ሁሉ ልስማሙበት ይገባል ብዬ የማምነው፣ የነፃነት ትግሉ ዋና ዓላማ የኦሮሞ የአገር ባለቤትነትን ማረጋገጥ  ነው። ይህ የኦሮሞ የአገር ባለቤትነት ጉዳይ ግን ከላይ እንደ ተጠቀሰው በተለያየ መንገድ ይታያል። ኣንዳንዶቹ  የኦሮሚያ ነፃ መንግስት እንደ መመስረት ሲያዩት፤ ሌሎች ደግሞ ኦሮሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ራሱን ማስተዳደር ከቻለና በንብረቱ ላይ ባለቤት መሆን ከቻለ፣ የአገር ባለቤትነትን አረጋግጧል ማለት ይቻላል የሚሉ ኣሉ። በተቃራኒው ሲታይ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ይህንን ግብ የሚቃወሙ ኃይሎች ኣሉ። እነዚህ ኃይሎች ባጭሩ የሕዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረ ሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጉዳይን የማይቀበሉና አንቀስ 39 እንዲሰረዝ የሚፈልጉ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ባጠቃላይ የኦሮሞ የነፃነት ትግልን ለማጥፋት የሚፈልጉ ናቸው። የኦቦ ለማም ሆነ የዶ/ር አብይ አስተዳደር በነዚህ ታቃራኒ በሆኑት ኃይሎች መካከል ስለሚሆን የሁሉንም ፍላጎት ለመጠበቅና ዓላማ ለማሳካት እጅግ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል።

የፊንፊኔ ጉዳይና እንደነ ድሬ ደዋ ያሉት የኦሮሚያ ከተሞች ጉዳይ ምን ሊሆን ነው?

ኦሮሚያ ነፃ ሆና የራሷን ነፃ መንግስት የሚታቋቁም አገርም ሆና በኢትዮጵያ ውስጥ ራሷን የሚታስተዳድር ብትሆንም፣ በሁለቱም መንገድ የፊንፊኔና እንደ ድሬ ደዋ ያሉት ሌሎች ከተሞች ጉዳይ በቀላሉ መፍትሄ ማግኘት የሚችሉ አይደሉም። በተለይ ደግሞ የፊንፊኔ ጉዳይ በጣም ወሳኝ በመሆኑ፣ ለዚህ ጉዳይ የመጨረሻ መፍትሄ ለማግኘት ለኦቦ ለማም ሆን ለዶ/ር አብይ ትልቅ ፈተና ነው። ቢታመንም ባይታመንም፣ ቢወሰድም ባይወሰድም፣ ፊንፊኔ የኦሮሚያ አካል ብቻ ሳትሆን የኦሮሚያ እምብርት ናት። በመሆኑም በየትኛውም መንገድ ይሁን የኦሮሞ የአገር ባለቤትነት ከተረጋገጠ ፊንፊኔ ወደ እናቷ ኦሮሚያ መመለስ የግድ ይሆናል። ይሁን እንጂ ዛሬ የፊንፊኔ ካንቲባ ኦሮሞ በመሆኑ ከዚህና ከዚያ የምንጫጩት ኃይሎች ፊንፊኔ ኦሮሚያ ስር ከገባች ምን ሊሆኑ ነው? ይህ ጥያቄ ለዶ/ር አብይ ትልቅ ፈተና ነው።

ባጠቃላይ እጅግ አስቸጋሪ የሆኑትን ጥያቄዎችና ጉዳዮችን እዚህ ኣነሳሁ እንጂ ሌሎች አስቸጋሪ የሚሆኑ ጉዳዮች ይኖራሉ። የኦሮሞ ጥያቄ በቀላሉ መልስ ሊያግኝ የሚችል ጉዳይ አይደለም። ብዙ መስዋዕትነትን ያስከፈለና አሁንም ሊያስከፍል የሚችል ጉዳይ ነው። ኣንድ መገንዘብ ያለብን ቁም ነገር ግን የመጨረሻ መፍትሄ ለማግኘት በቅድሚያ ሁሉም የኦሮሞ ድርጅቶች በኦሮሞ ጎራ (camp) በዚህ ጉዳይ ላይ መግባባት እጅግ አስፈላጊ ነው። በኦሮሞ ጥያቄ ላይ መግባባት ከሌለ በግቡ ላይ መግባባት እጅግ ያስቸግራል። ኦሮሞ ይህንን ትግል ለምን ጀመረ? የት መድረስ ነው የምፈልገው? የሚፈለገውን ግብ ለመድረስ እንዴት ይቻላል? ባጠቃላይ የወደፊታችን ዕጣ ፋንታ ምን ሊሆን ነው?  ወዘተ የመሳሰሉት ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ም ነው። እስቲ ይህን ጉዳይ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ለአሁን ግን የጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ ጥረቶችና ገና የሚጠብቁት ትላልቅ ፈተናዎች”  በሚል ርዕስ ስር በሶስት ክፍሎች ሳቀርብ የነበረውን ተከታታይ ፅሁፍ በዚሁ ኣበቃለሁ።

በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑየጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ ጥረቶችና ገና የሚጠብቁት ትላልቅ ፈተናዎች

ብርሃኑ ሁንዴ

ክፍል ሁለት

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ በቀጥታ በሕዝብ የተመረጠ መሪ ባይሆንም የሕዝብን ተወዳጅነት እንዳተረፈ፤ ስያደርግ የነበረው ጥረትና እንደዚሁም በሱ አመራር ስር የተገኙትን ኣንዳንድ ትርፎችና ለውጦች በክፍል ኣንድ ፅሁፍ ውስጥ ተነስተው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስተሩ ስያደርግ የነበሩት ጥረቶች የሚደነቁ ቢሆኑም፣ የዚህችን አገር ችግሮች ለመፍታት ገና ብዙ ፈተናዎች ይጠብቁታል። የዚህች አገር ችግሮች ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ ስር ሰደው እዚህ የደረሱ በመሆናቸው፣ በእውነት እጅግ የተወሳሰቡ ናቸው። በዚህ አይነት አገር ውስጥ የሁሉም የጋራ የሆነ መፍትሄ ማግኘትና የሁሉንም ሕዝብ ጥያቄ መመለስ እጅግ አስቸጋሪ ነው። በዚህኛው ክፍል ፅሁፍ ውስጥ የዚህችን አገር የተወሰኑ ችግሮችን ኣንስቼ ሀሳቤን ልሰጥበት እሞክራለሁ።

የተለያዩ አይዶሎጂና ፍላጎቶች በሚታዩባት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሁሉም የሚሆን የጋራ መፍትሄ ሊገኝ ይችላል?

ይህቺ ኢትዮጵያ የምትባል አገር የተለያየ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ሃይማኖት የሚታይባት የብዙ ብሔሮችና ብሔረ ሰቦች አገር መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ የፖለቲካ ዓላማዎችና ፍለጎቶች የሚታዩባት አገር ነች። በተጨማሪ ደግሞ ስመጡና ሲያልፉ በቆዩት የሀበሻ መንግስታት በጉልበት ታፍናና ተገዝታ እስከ ዛሬ የደረሰች በመሆኗ የሕዝቦችና ብሔሮች እስር ቤት (prisons house of nations) ተብላ ትጠራለች። በመሰረቱ ዲሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓትና አስተዳደር እንዲሁም ፍትህና እኩልነት ቢኖርባት ኖሮ የተለያዩ ማንነት ያላቸው ብሔሮችና ብሔረ ሰቦች በጋራ በሰላም ለመኖር ችግር አይሆንም ነበር።

ይሁን እንጂ በጉልበት የተመሰረተችና በጠመንጃ ተገዝታ እዚህ የደረሰች፥ የኣንድ ብሔር የበላይነት ስታይባት የቆየች አገር፤ የስንት ዜጎች ሕይወት የጠፋባትና ደም የፈሰሰባት፤ ዛሬም ቢሆን ይህ ያልቆመበት አገር ውስጥ የሁሉም ቁስል ድኖ፤ የሕዝቦች ጥያቄ መልስ ኣግኝቶ፤ ለሁሉም እውነተኛ እናት የምትሆን አገር መገንባት እጅግ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ የሚቻልም አይመስልም። የዶ/ር አብይ ፍላጎትና ጥረት ይህችን አገር ኣንድ ለማድረግ ቢሆንም፣ እዚህ ላይ የሚነሳ ትልቅ ጥያቄ እንዴት ይህችን አገር ኣንድ ማድረግ ይቻላል?  የሚል ይሆናል። ይህ ትልቅ ፈተና ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚጠብቀው።

የፖለቲካና አይዶሎጂ ልዩነቶች

በክፍል ኣንድ ፅሁፍ ውስጥ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ የአፄ ሚኒሊክ ጉዳይ ራሱ አገሪቷን በሀሳብ ለሁለት የከፈለ ይመስላል። የሰሜኑ ክፍል ሕዝቦች ሚኒሊክን እንደ ጀግናቸው ሲያወድሱት፣ ለደቡብ ሕዝቦች ግን ሚኒሊክ አደገኛ ጠላት ነበር። የሰሜኑ ሕዝቦች ሚኒሊክ በደቡብ ሕዝቦች በተለይም በኦሮሞ ላይ የፈፀመውን ድርጊት ኣምነው ተቀብለው እርቅ ካልወረደ የደቡቡ ክፍል ሕዝቦች ቁስል ሁሌም አየተነካካ ይኖራል። ይህ ታሪካዊ እውነታ እንዳለ ሆኖ የሚያሳዝነው ጉዳይ የሰሜኑ ክፍል ኣንዳንድ ኃይሎች ሚኒሊክ የፈፀመውን መጥፎ ድርጊት መቀበል ትተው ይባስ ብሎ የድሮው ስርዓት ተመልሶ እንዲመጣ መመኘታቸውና ለዚህም ለት ተቀን መስራታቸው ነው። ያ አስቀያሚውን ታሪክ እያወደሱ የደቡቡን ሕዝቦች ቁስል እየነካኩ ይገኛሉ። እነዚህ ኃይሎች ናቸው የሕዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረ ሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ለማራጋገጥ በአገሪቷ ሕገ መንግስት ላይ የተቀመጠውን አንቀፅ 39 እንዲሰረዝ የሚፈልጉት።

አንቀፅ 39 ሊሰረዝ ነው ወይንስ ምን ይሆናል?

ይህንን አንቀፅ የሚቃረኑ ኃይሎች የፈለጉትንም ምክንያት ቢያቀርቡም፤ ምንም ያህል ይህንን አንቀፅ ቢጠሉም፣ ይህ እንዲሁ በዋዛ የተፃፈ አይደለም። ይህ የብሔሮችና ብሔረ ሰቦች ትግል ያስገኘው ድል ነው። ይህንን በደም የተግኘውን ድል ማጥፋት ጭራሽ የሚቻል አይመስለኝም። የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በዓለም ላይ ተቀባይነትን ያገኘ የሰው ልጅ መብት ነው። ይህ ለኢትዮጵያ ብቻ ተብሎ የተደነገገ አይደለም። ስለዚህ ይህንን መብት መጠበቅ የግድ ይሆናል። ይህንን አንቀፅ የሚቃወሙት እንኳን ይህ ጉዳይ ተፈጥሮኣዊ መብት መሆኑን ያምናሉ። ነገር ግን ይህንን አንቀፅ የሚቃወሙት ይህቺን አገር ወደ መፍረስ ሊወስዳት ይችላል በማለት ነው አንቀፁ እንዲሰረዝ የሚፈልጉት። ህልም ተፈርቶ ኣለ እንቅልፍ አይታደርም  እንደሚባለው ይህቺን አገር ወደ መበታተን ሊወስድ ይችላል በማለት አንቀፁ እንዲሰረዝ ማድረግ ሌላ ችግር ያስከትላል እንጂ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። በነገራችን ላይ ይህ አንቀፅ ኖረም ኣልኖረ የሕዝቦች ጥያቄ ካልተመለሰ ይህቺ አገር ወደ መበታተን መሄዷ የማይቀር ጉዳይ እኮ ነው።

ይህ አሁን ያለው የፌዴራል ስርዓት ዲሞክራሲያዊ ሆኖና ተሻሽሎ ይቀጥላል ወይንስ ሊቀየር ነው?

አንቀፅ 39ን የሚቃወሙ ኃይሎች ይህንን አንቀፅ እንደ ልዩ ችግር ስለምያዩት ነው እንጂ፣ ይህ በብሔሮች ክልል ላይ የተመሰረተው የፌዴራል ስርዓትም ኣያስደስታቸውም። ይህንንም እየተቃወሙና እያወገዙ ነው ያሉት። ወደዱም ጠሉ፣ ተቀበሉም ኣልተቀበሉት ይህ የፌዴራል ስርዓትም በጭቁን ሕዝቦች መራራ ትግልና ደም ነው የተገኘው። ይህ በመራራ የነፃነት ትግል ከተገኙት ደሎች ውስጥ ኣንዱና ዋንኛው ነው። በተለይም የኦሮሞ የነፃነት ትግል ካስገኛቸው ድሎች መካከል ኣንዱና ትልቁ ነው። ኦሮሚያ በካርታ ላይ ታይታ ሊትታወቀ የቻለችው ይህ የፌዴራል ስርዓት መገንባት በመቻሉ ነው። የኦሮሞን ጉዳይ ለመናቅና ለማሳነስ ኣንዳንድ የአበሻ ኃይሎች እንደሚሉት ወያኔ ያመጣው ድል ሳይሆን በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መሪነት የኦሮሞ የነፃነት ትግል ያስገኘው ድል ነው። በመሆኑም ይህ አሁን ያለው የፌዴራል ስርዓት እጂግ ቢያንስ ዲሞክራሲያዊ ሆኖና ተሻሽሎ መቀጠል ኣለበት እንጂ መፍረሱ በጭራሽ የማይታሰብ ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ ብሔራዊ ጥያቄ በዶ/ር አብይ አስተዳደር ስር መልስ ሊያገኝ ይችላል? እንዴት?

ይህ ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ እጅግ ፈታኝ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ ኣንዱና ዋንኛው ነው። አሁን እየታየ እንዳለው የዶ/ር አብይ አስተዳደር የኦሮሞን ጥያቄ መመለስ ቀርቶ የዶ/ር አብይ አካሄድ ራሱ ከኦሮሙማ (Oromumma) ና የኦሮሞ ብሔርተኝነት (Sabboonummaa Oromoo) የራቀ ይመስላል። ለማንኛውም መጠበቅ ጥሩ ነው። ቶሎ ሌላ ድምዳሜ ላይ መድረስ አያስፈልግም። የሆነም ሆኖ፣ ዶ/ር አብይ ከዚህ አስቸጋሪ ጥያቄ ለማምለጥ ይሞክራል ወይስ ይህ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ያደርጋል? ይህንን ካላደረገ ዕጣ ፋንታዉ ምን ሊሆን ነው? የኦሮሞ ሕዝብ በተለይም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስተሩን ለዚህ ደረጃ ያደርሱት ቄሮዎች (Qeerroo) ከዶ/ር አብይ ፊታቸውን ካዞሩ ምን ሊሆን ነው?  ወዘተ የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በተመለከተ በሚቀጥለው ክፍል ፅሁፍ ውስጥ ሀሳቤን ይዤ እቀርባለህ።

ይቀጥላል

ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑየጠቅላይ ሚኒስተር / አብይ ጥረቶችና ገና የሚጠብቁት ትላልቅ ፈተናዎች

ብርሃኑ ሁንዴ

ክፍል ኣንድ

ለመግቢያ እንዲሆንና ወደኋላ ላይ ኣንዳንድ ነገሮችን ለመግለፅ እንዲረዳ፣ እስቲ ትንሽ የዚህን ጉዳይ መነሻ እንይ። እንደሚታወሰው ዶ/ር አብይ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ሚያዝያ 2 ቀን 2018 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ ተመረጠ። በዚያን ቀን ባደረገው ንግግር ውስጥ ብዙ ነገሮችን መገንዘብ ይቻላል። ይህ ንግግሩ ሰዎችን በሀሳብ ለሁለት የከፈለ ይመስላል። በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል ያሉ በተለይ ደግሞ የድሮው ስርዓት ተመልሶ እንዲመጣ የሚመኙ ይህን ንግግሩን በደስታ ሲቀበሉት፤ በደቡቡ የአገሪቷ ክፍል ያሉ በተለይ በኦሮሞ ዘንድ ማኩረፍና ወቀሳን ፈጥሯል። ለዚህ ትልቁ ምክንያት ዶ/ር አብይ ሚኒሊክን ስላሞገሰና ስራውንም ስላደነቀ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስራው ከገባ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቷ ክልሎች እየተዘዋወረ ጉብኝት ሲያደርግና ከሕዝቦች ጋር ተገናኝቶ ንግግር ሲያደርግ ነበር። ወደ አማራ ክልል በሄደበት ወቅት ባደረገው ኣንድ ንግግር ውስጥ አሁንም ኣንድ ኦሮሞዎችን ያስኮረፈ ነገር ተሰማ። ይኸውም ስለ ኦሮሞ ብሔርተኝነት ሲሆን፣ ዶ/ር አብይ እዚያ ያሉትን ሕዝቦች ለማስደስት  ይሆን ባይታወቅም የኦሮሞን ብሔርተኝነት ዝቅ ለማድረግ የሞከረ ይመስላል። የዚህ ጉዳይ ትክክለኛ ምክንያት በግልፅ ባይታወቅም የኦሮሞ ብሔርተኝነት ለአገሪቷ ኣንድነት አስጊ ሊሆን እንደሚችል ለመግለፅ ይመስለኛል። በዚሁ አካሄዱ ውስጥ ዶ/ር አብይ ብዙ ነገሮችን ብናገርም ኣንድ የሰዎችን ትኩረት የሳበ ስለ መደመር ነው። የዚህ ቃል ትርጉም በደንብ ግልፅ ባይሆንም፣ ባሁኑ ጊዜ መፈክር ሆኖ እየተሰማ ነው ያለው። እየተተቸም ነው። ምክንያቱም የዚህ ጉዳይ ትርጉምና አተገባበሩ ግልፅ ስላልሆነ ነው ብዬ ኣስባለሁ።

በሕዝብ ያልተመረጠ ነገር ግን የሕዝብን ተወዳጅነት ያተረፈ መሪ 

እኔ እንደሚታየኝ ዶ/ር አብይ ጥሩ እውቀትና ችሎታ ያለው ሰው፤ ተናግሮ ሰውን ማሳመን የሚችል፤ ለስራው ትልቅ ፈላጎትና ሞራል ያለው፤ ለዚህች ኢትዮጵያ ለምትባለው አገር ብቻ ሳይሆን ለኣፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት የሚያስብ መሪ ነው። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው ደግሞ ወደ ተለያዩ የአገሪቷ ጎረቤት አገሮች በመዘዋወር፣ ሰላምና እርቅ እንዲፈጠር ጥረት ማድረጉ ነው። በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም እንዲፈጠር ማድረጉ ትልቅ ምሳሌ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊም ነው። ለዚህም ነው ባለፉት አራት ወራት ውስጥ የሕዝብን ፍቅር ማትረፍና መጨመር የቻለው። ይህ ተወዳጅነቱ ደግሞ ለሕይወቱም ኣስጊ ሆኖ በሃምሌ ወር 2018 በፊንፊኔ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የግድያ ሙከራ ተደርጎበት ነበር።

/ አብይ ለምንድነው የሚወደደው? በማን ነው የሚወደደው? በማን ነው የሚወቀሰው? ለምን?

በአገሪቷ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ቀንድ ጭምር ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር እንደዚሁም የሕዝቦች፣ የብሔሮችና ብሔረ ሰቦች ኣንድነትና ፍቅር እንዲፈጠር ጥረት ማድረጉ፤ ኢትዮጵያ ከመፍርስ እንድትተርፍ መንከራተቱ የሕዝቦች ተወዳጅነት እንዲያገኝ ኣደርገው። ኢትዮጵያ ከመፍርስ እንድትተርፍ የሚለውን ጉዳይ እመለስበታለሁ። ይሁን እንጂ ይህ በንዲሁ አንዳለ፣ ዶ/ር አብይ የሚወቀሰው በኦሮሞ ዘንድ ሲሆን፣ ትልቁ ምክንያት በኦሮሚያ ድንበሮች ላይ በተለይም ደግሞ በምስራቅና ደቡብ ኦሮሚያ ልዮ ፖሊስ በሚባለው የሽፍቶች ቡድን በሕዝባችን ላይ ጦርነት መከፈቱና በዚህም የተነሳ በየቀኑ የወገን ሕይወት ማለፍና ይህ ነው የማይባል ንብረትም መውደሙ ነው። ወገን እንደ ዛፍ ቅጠል እየረገፈ በሚገኝበት ወቅት የዶ/ር አብይ አስተዳደር ዝምታ መምረጡ የኦሮሞን ሕዝብ እጅግ አስቆጥቷል። ይህ ችግር በእውነት አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልገው እጅግ ኣሳሳቢ ጉዳይ ነው።

/ አብይ እንደ አገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስተር ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ምን ትርፍ ኣስገኘ ወይንም ምን ለውጥ ኣመጣ?

በዶ/ር አብይ አስተዳደር ስር ባለፉት አራት ወራት ከተገኙት ትርፎችን ለውጦች ውስጥ ኣንዳንዶቹ ከዚህ በላይ ተጠቅሰዋል። ሌሎቹን ለመጥቅስ ያህል ኣሁንም እስር ቤት ያሉት ዜጎች ቁጥር ትልቅ ቢሆንም፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) መሪዎችን ጨምሮ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ሰዎች ከእስር ቤት ተለቀዋል። ይህ እንደ ኣንድ ለውጥ ይታያል። ሌላ ደግሞ የፖለቲካ ማህደርን ለማስፋት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚናቅ አይደለም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጥቂት የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች ወደአገር ቤት ገብተዋል። ሊገቡ ዝግጅት ላይ ያሉም እንዳሉም ይሳማል። የቀሩትም ወይይት ላይ እንዳሉም ይነገራል። በእውነት የፖለቲካ ማህደር ሰፍቶ፣ የሚፈለገው ሽግግርና ለውጥ ስለመደረጉ ገና የምናየው ይሆናል።

ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ታውጆ የነበረው የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳም ተደርጔል። የፀረ ሽብርተኝነት ሕግም ሊቀየር ወይም ሊሻሻል እንደሆነ የዶ/ር አብይ መንግስት ኣስታውቆ ነበር። ሌላው ደግሞ አካሄዱ ለጊዜው አጥጋቢ ባይሆንም፣ ኣንዳንድ ሰዎች ከስልጣናቸው እንዲነሱና ኣንዳንዶቹ ደግሞ ቦታቸው እንዲቀያየር ተደርጔል። ይህ እንደ ለውጥ ባይታይም እንደ ኣንድ ትርፍ ሊታይ ይችላል። ነገር ግን ይህ ያለውን ችግር ሊፈታ ይችላል? የሚለውን ጥያቄ እመለስበታልሁ።

እንግዲህ በዶ/ር አብይ አስተዳደር ስር የተገኙት ትርፎችና ለውጦች እነዚህ ሲሆኑ፣ ባጠቃላይ ግን እስካሁን መልስ ያላገኙ ጥያቄዎችና ያልተፈቱ ብዙ የኢትዮጵያ ችግሮች ስላሉ፣ እነዚህ ዶ/ር አብይን የሚጠብቁ ትላልቅ ፈተናዎች ናቸው። የዚህች አገር ችግሮች ብዙ ብቻ ሳይሆኑ እጅግ የተወሳሰቡም ናቸው(complex and complicated).

ዶ/ር አብይን ወይም አስተዳደሩን ገና የሚጠብቁ ትላልቅ ፈተናዎች የሆኑት ጥያቄዎች፥ 1) የተለያዩ አይዶሎጂዎችና ፍላጎቶች የሚታዩባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ለሕዝቦች ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ተገኝቶ፤ ሕዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረ ሰቦች በእኩልነትና በሰላም አብረው መኖር ይችላሉ? 2) በይበልጥ ደግሞ የኦሮሞ ብሔራዊ ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ይችላል? 3) የፖለቲካ ዓላማና ግብ የሚቃረኑባት አገር ውስጥ ምን ዓይነት ስርዓት ሊፈጠር ነው? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህ ናቸው ለዶ/ር አብይና አስተዳደሩ እጅግ ፈታኝ ሊሆኑ የሚችሉት። እነዚህን በተመለከተ በሚቀጥለው ክፍል ፅሁፍ ውስጥ ሀሳቤን ይዤ እቀርባለሁ።

ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.