ይህን አይልም መምህሩ !

በዘለዓለም አበራ ተስፋ, ሔልሲንኪ, ፊንላንድ

ጠዋት ጠዋት ቀዳሹ
ቀን ቀን ተኳሹ
ጠዋት መምህሩ
ቀን ወታደሩ
ዕውቀት ከጠማው ሲጋተሩ …

“ኧረ ለመሆኑ …የዚህ …የመጻፉ ቃል
በዬትኛው ምዕራፍ በዬትኛው ወንጌል
ዝረፉ መዝብሩ ይላል?”

… ብሎ ሲጠይቅ…

“ሰውዬ… ምን ነክቶሀል?
እባክህ አትጃጃል
’’የባለጌ ሃይማኖት ከጅማት ይጠናል’’
ሲባል አልሰማህም? ጥንትም እኮ ይባላል ፣”
ብሎ ይሳለቃል።

***
እና… እንዴት ነው ነገሩ?
አልገባኝም ምስጢሩ
በእርግማን እያካለቡ
ወኔውን እየሰለቡ
ከሰማይ ታቦት እያዘነቡ
በየቦታው እያንጠባጠቡ
“እኮ እንዴት…?” ባይን ፍርሀት እየመገቡ
ሰውን አርጎ ሆደ ቡቡ
በሰማይ እያሳበቡ ፣
በሱ ሥም እየማሉ
“አንድ ነነ” ብለው እያሉ
“የተፈጠርነ በአካሉ ፣ በአምሳሉ”
በተቀባው ሥም እየማሉ
እሱ የተከለውን ሲነቅሉ
ማንነቱን እየበከሉ
ንጥር እሴቱን እዬቀብሩ
ንጥር ባህሉን እዬመዘበሩ
“ለጥበቡ እንደመካስ
በደባትር ትንታግ ምላስ”
የነግ ህይወቱን መላስ
ሥምና ግብሩን እያጣጣሉ
ይባስ ብለው ከመሰረቱ እየነቅሉ

ራስን በቦታው መትከሉ
ተጽፏል ወይ በወንጌሉ?
አስተምሯ ል ወይ መምህሩ?
ብሏል ወይ ይህን ተግብሩ?
አልገባኝም ምስጢሩ።

***
እሱ ግን…ክፋትን ከጥንቱ የገሰጸ
ሰላም ባጥንቱ የሰረጸ
ተቀበለ እንጅ አላመጸ
በቱውፊቱ ላይ ቱውፊት ቀረጸ
በባህሉ ላይ ባህል አነጸ
እንጂ…አልቀበልም አላለ
መቀበሉን በማተሙ እየማለ
ግን …የሱን ፍቅር በቋንቋዬ ብሎ ባለ
የተቀባውስ ከዚህ ወድያ ምን አለ?
ሆኖም በሱ ቦታ ራሱን የወከለ፣
“የለም! ብርሀነ ቃሉ የሚነገር
ቅዱስ ሥሙ የሚዘከር
ተአምሩ የሚወደስ የሚዘመር
በኔ ቋንቋ ካልሆነ በቀር
ከቶ አይሆንም የማይሆን ነገር !
ዘራፍ እምቡርርርር …! ጭራሽ እምቡርርርር …!”
እኮ… ምን ሊፈይድ ነገር ማክረር?
መተግበሩ ጭራሽ ላይቀር!
ታድያ በተቀባው ስም እየማሉ
እሱን ከርስቱ እየነቀሉ
ራስን በይዞታው መትከሉ
ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው በሉ?

“መጽሀፉን ከጥግ ጥግ የሰለቅነ
በቃሉ ትርጉም የረቀቅነ
በግብረገብ የመጠቅነ
በረቂቃን ረቂቅነት የረቀቅነ
አህዛብን ያሳመነ ያጠመቅነ
ሉሲፈርን ያዋረድነ ያበሸቅነ
በአረመኔ የተከበብነ
ብጹዕ ወ ቅዱሳን ነነ።

ብለው ላለም ሁሉ ያሳበቁ
ታቦት ከሰማይ እያወደቁ
ጠበል ከጅረት እያፈለቁ
መሬት ከድሀ ሲነጥቁ
“ጉድ ፈላ!” አልነ “አትስረቁን” ሲሰርቁ።

***
“ያመነ ይድናል” ሲሉት “ያመነ ይድናል” ብሎ
“እግዚኦ” በል ሲሉት “እግዚኦ አድነነ” ብሎ
ለነብስና ለስጋው ብርሀነ ቃሉን ተቀብሎ
ታድያ ሰነባብቶ አድሮ ውሎ
ከቄዬውና ከማሳው ከነበረበት ተደላድሎ
በ“ታቦት ወረደ” በ“ጸበል ፈለቀ” ተሸንግሎ
ሌላው በሱ መሬት ሲተከል እንዴት ይጣል ተነቅሎ?
ይህን ሁሉ መከራ ችሎ
ውሎ አድሮ አድሮ ውሎ
ነገር ነገርን አብሰልስሎ
ለጊዜው ስንዱ መልስ ቢጠፋ

ውሎ አድሮ ግን ቅጥፈቱ ሲሆን ይፋ
“ለኔ የዘነበው ታቦት ምነው ለነሱ አላካፋ?
ይህ ጸበል ከኔ ደጅ ካጋተ ከፈለቀ
ከሌላው ደጅ ምነው ነጠፈ ደረቀ?
ታቦት ከሰማይ ወድቆ
ጸበል ከደጄ ፈልቆ
አይነቅለኝም መሬቴን ነጥቆ”

ብሎ ቆርጦ ከእምነቱ ቢሸሽ
ማን ሊሆን ነው ተወቃሽ?

***
የአቻምናው ሹምባሽ
የትላንቱ ቡሉቁባሽ
የነሙንጣዝ ኑሮ ሲመሽ
ከደም ጉማ ሮጦ ሲሸሽ
ቤተ መቅደስ ገብቶ ይምነሸነሽ?
ሌሎችን አደናበሮ
ዩኒፎርሙን ቀይሮ
አንዴ እንደ ጸጋዬ ቢራቢሮ
ወይ እንደ ጉድጓድ ከርከሮ
አንዴ እንደ ጫካ ቀበሮ
ደግሞ እንደ ገመሬ ዝንጀሮ
ከትላንት ተሰውሮ
ልብስና እምነት ቀይሮ
ሰታት ስለቆመ አቀርቅሮ
ለሱም ክፍት ነው በሩ?
እኮ እንዴት ነው ነገሩ?
አልገባኝም ምስጢሩ።

***
ወይም…
እንደ ብርችምችም* እንደ ጠንፍየለሽ*
እንደ ሰናይት እንደ ብዙነሽ*
በልጅነት ዳንኪራ ደንካሪ
የአራዳዋ ኮማሪ
ህይወት ሲሆንባት ቅራሪ
ትላንት ሆይ ሆይ
ዛሬ እማሆይ
መነኩሴ የደብሩ ዘማሪ
የገበዙ ልዩ አማካሪ
“አታመንዝሩን” ደጋግመው የሰበሩ
በጭናቸው ወዝ የከበሩ
ምነው እነሱ አልተነቀሉ?
ደግሞስ በስለት መልክ ከገቢያቸው ካቀበሉ
መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ?

***
የሰው ነብሰ በላ በራሪ
ወይ የትላንቱ ቀላማጅ ቀባጣሪ
ዛሬ ሲሆን አስተማሪ
ተርጓሚና መስካሪ
የነብስ አባት አማካሪ
ሲሆን የላይኛው ቤት አጋፋሪ
አባሆይ የአቡኑ አማካሪ
አይሆንም ወይ አነጋጋሪ?
እኮ እንዴት ነው ነገሩ?
አልገባኝም ምስጢሩ
ይበጃል መጠርጠሩ
ይህን አይልም መምህሩ።

***
ትላንት ባርያ ፈነገሉ
ዛሬ ለአምላክ አገለገሉ
በልጅነት ባሪያ ነገዱ
በመጻፉ ቀልድ ቀለዱ
ዛሬ በአምላክ ፍቅር አበዱ
ሀብት አፈሱ መዘበሩ
ትላንት በግፍ ከበሩ
ዛሬ ለአምላክ ዘመሩ
እኮ እንዴት ነው ነገሩ?
አልገባኝም ምስጢሩ።
ለነሱም ክፍት ነው በሩ?
አይመስለኝም ይበጃል መጠርጠሩ
ይህን አይልም መምህሩ።

*ብርችምችም በጅማ ፣ ጠንፍየለሽ፣ ሰናይት፣ እና ብዙነሽ በነቀምቴ ከተማ ኮማሪቶች ነበሩ።

ዘለዓለም አበራ ተስፋ
14.10. 2019
ሔልሲንኪ ፊንላንድ

Similar Articles

Comments

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

OMN: ODUU GALGALAA (GURRAANDHALA 20, 2020)

OMN: ODUU GALGALAA (GURRAANDHALA 20, 2020)

Ethnic cleansing continued in Oromia Regional State by Abiy Ahmed

Ethnic cleansing continued in Oromia Regional State by Ethiopian government lead by Dr. Abiy Ahmed, Prime Minister of Ethiopia July 10, 2020 The Right Honourable Justin...

New Book: የተጠለፈ ትግል (The hijacked revolution) in pdf

Book: የተጠለፈ ትግል (The hijacked revolution) in PDF Via Aba Orma, September 3, 2019 የተጠለፈ ትግል (The hijacked revolution) Author: Mudhin Siraj Pages: 152 Language: Amharic Year: July 2019 To...

21 million Chinese died of coronavirus – US intelligence officials intercept data

21 million Chinese died of coronavirus – US intelligence officials intercept data By James Alami (Web Archive) -- A new data intercepted by the United States...

BBC Afaan Oromoo: ODUU Owwituu, Amajjii 27, 2020

BBC Afaan Oromoo: ODUU Owwituu, Amajjii 27, 2020