“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” ይባላል።

“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” ይባላል።

Via Rundassa Eshete, August 25, 2019

ኢትዮጵያ ውስጥ በየቀኑ ብዙ የእብደት ጉዶች የሚሰሙ ቢሆንም የአሁኑን ከበድ የሚያደርገው በዚህ የመስከረም ዋዜማ መንግሥት ማበዱን አደባባይ ይዞ መውጣቱ ነው።

“ኢትዮጵያ የኩራት ቀን ልታከብር ነው” ሲባል በኃ/ሥላሴ ዘመን አንድ ሲነገር የነበረ ቀልድ ትዝ አለኝ።

ቀልዱ እንደዚህ ነው “ሃገሪቷ የገንዘብ ሚኒስቴር ስለሚያስፈልጋት መሾም አለበት” የሚል ሃሳብ ከንጉሡ ይነሳና ሹማምንት ይወያዩበታል።

ከመሃላቸው አንድ ነቃ ያለና አድርባይነት ያልተጠናወተው ይነሳና ” ሃገሪቷ ገንዘብ ሳይኖራት የገንዘብ ሚኒስቴር ምን ሊሠራ ነው የሚሾመው?” ብሎ ይጠይቃል።

ሌላው እንደ መረራ አይነት አሽሟጣጭ ይነሳና “ምን አለበት ሳውዲ አረቢያም እኮ እርሻ ሳይኖራት የእርሻ ሚንስትር ሾማ የለም እንዴ” ይላል። (ሳውዲ አረቢያ እንደ ዛሬ በቴክኖሎጂ ተደግፋ ከዋናዎቹ የስንዴ አምራቾች ተርታ ባልገባችበት ወቅት የተነገረ ቀልድ ነው።)

ዛሬ በሰባተኛው ንጉሥ ጌዜ ደግሞ ” ኢትዮጵያ የኩራት ቀን ልታከብር ነው” ተብሎ ፆሙን በሚያድር ሕዝብ ላይ ይሾፋል። ለመሆኑ የተራበና የታረዘ ሕዝብ በምኑ ነው የሚኮራው? አስተዳደሩ ተጨማልቆ ሃገሪቷ በቅራኔዎች ተወጥራ ዛሬ ትፈንዳ ነገ ትፈንዳ በማይታወቅበትና ዜጎች በሰቀቀን ውስጥ በሚኖሩበት ሃገር ውስጥ “የኩራት ቀን” ብሎ መቀለድ የአእምሮ ጤንነት ነው?

ሃገሪቷ ላለፉት 150 ዐመታት ሲንከባለል መጥቶ ባለፉት 50 አመታት መሳርያ አማዞ ደም ሲያፋስስ የኖረ የብሔር ጥያቄ መፍትሄ ከማግኘት ይልቅ በሁሉም የሃገሪቷ ክፍሎች ተስፋፍቶና ፋፍቶ ሃገሪቷን በጋለ ምድጃ ላይ በጣደበትና መንግሥት ቀድሞ እንደነበረው ከኃይል አማራጭ ውጪ ምንም ሰላማዊ የመፍትሄ ጭላንጭል ማየት አቅቶት በየቀኑ ሰዎችን በሚያስርበትና በሚገደልባት ሃገር መኖር፣ መምራት ያኮራል ወይስ ያሳፍራል?

በእውነት ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ የሚኮራ ዜጋ አለ? እኔ የአእምሮ ጤነኛ ከሆኑ ወይም hypocricy የሚባል የእይታ ችግር ካላጋጠማቸው ጠ/ሚኒስትሩ እንኳን ይኮራሉ የሚል እምነት የለኝም።

ይልቅስ ኩራቱን ትተው እንቅልፋቸውን ቀንሰው ከፊታቸው የተደቀኑ የባቱን ተራራ የሚያካክሉ የሃገሪቷ ግዙፍ ችግሮች ተደርምሰው ሳይቀብሯቸው ለመፍታት ቢተጉ መልካም ይመስለኛል። ኩራቱን ያኔ ችግሩን ከፈቱ በኋላ ቢያደርጉትም ያምርባቸዋል ሕዝብም ይቀበላቸዋል ብዬ እገምታለሁ።

አሁን ግን “ሁላችንም አልኮራንም፣ በስህተት ነው ፕሮግራሙን ያስተዋወቅነው” ብለው ያሾፉበትን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው እዚሁ ጋ ቢያቆሙ ያዋጣቸዋል የሚል የምክር ሃሳብ እለግሳለሁ።

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.