ግብዣ፣ ውበት እና ፍቅር በወለጋ – ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

0

ግብዣ፣ ውበት እና ፍቅር በወለጋ

ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ, Amajjii 9, 2020

blank

አዎን! የወለጋ ምድር የእናት ጓዳ ማለት ነው፡፡ ከዚያ ምድር የሚፈልቁት የኦሮሞ ባህላዊ ምግቦች ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ጩምቦ፣ አንጮቴ፣ ጨጨብሳ፣ ጩኮ፣ መርቃ (ገንፎ) ሁላቸውም ጣት ያስቆረጥማሉ፡፡ የወለጋ ሴትን ያገባ እንዴት የታደለ መሰላችሁ? እጅግ ሲበዛ ሙያተኞች ናቸው፡፡

ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር በገጣሚ ሰለሞን ዼሬሳ ተጋብዞ ነቀምቴ በሄደበት ጊዜ ባየው የወለጋ ባህላዊ ቡፌ ተመስጦ ፍዝዝ ብሎ መቅረቱን ነግሮን ነበረ፡፡ በቅርቡ ያረፈው ታዋቂ ፖለቲከኛና ጠበቃ አሰፋ ጫቦ በበኩሉ የደርግ ዋነኛ ሰው ከነበሩት ኮሎኔል ደበላ ዺንሳ ጋር ወደ ወለጋ ሄዶ ያጋጠመውን ግብዣ ሲጽፍ “ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል” ነበር ያለው፡፡

እኔም በልጅነቴ “ጩምቦ-ጉልበተኛው ምግብ” የሚል ጽሑፍ ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ባነበብኩ ጊዜ በጣም ነበር የተገረምኩት፡፡ ጸሐፊው “በአንዲት አነስተኛ ሳህን የቀረበልንን ምግብ ስምንት ሆነን መጨረስ አቅቶን ነበር” ያለ ይመስለኛል (የምግቡ ዋነኛ ማሰናጃ “ቅቤ” ስለሆነ ነው ብዙ ሆነው ሊጨርሱ ያልቻሉት)፡፡ እዚህ ላይ “መሮሌ” ከተሰኘው የዘሪሁን ወዳጆ ዘፈን የተወሰኑ ስንኞችን ቀንጨብ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ዘሪሁን እንዲህ ነበር ያለው፡፡

As koottu Arjoo dhaqnee buna qalaa qalannaa
As koottu Qeellam deemnee marqaa garbuu kutannaa
ኦሮምኛውን ወደ አማርኛ ስንመልሰው እንዲህ ሊሆን ይችላል፡፡
ወደዚህ ነይ አርጆ ሄደን “ቡና ቀላን” እንቀምሳለን
ወደዚህ ነይ ቄለም ደርሰን የገብስ ገንፎ እንጎርሳለን፡፡

“ቡና ቀላ” ከቅቤ ጋር የሚቀቀል ቡና ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ቡናው በቅቤ ውስጥ ተነክሮ በምጣድ ላይ ይጠበሳል፡፡ በኦሮሞ ባህል መሠረት “ቡነ-ቀላ” የሚጋበዘው የክብር እንግዳ ወይንም የነፍስን ያህል የሚሳሱለት የቅርብ ወዳጅ ብቻ ነው፡፡ የወለጋ ሴቶች “ቡነ-ቀላ”ን ባማረ መዓዛ በማዘጋጀት ይታወቃሉ፡፡
*****
ጓዶች! የወለጋ ሴቶች በሙያቸው ብቻ አይደለም የሚታወቁት፡፡ በውበታቸውም የዘወትር ተጠቃሽ ናቸው፡፡ “ውቢት ኢትዮጵያ”ን የሚረሳ አለ? አዎን! ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን “የአስራ ሶስት ወር ፀጋ” በሚል ርእስ በሚያሳትማቸው ዝነኛ ፖስት ካርዶች ላይ የምናውቃት “ውቢት ኢትዮጵያ” የተሰኘችው ወጣት የወለጋ ልጅ ናት (የተጸውኦ ስሟ አልማዝ አመንሲሳ እንደሆነ ተነግሮኛል)፡፡

በልጅነቴ የማውቃት አንዲት ከወለጋ የመጣች ውብ ሴት ደግሞ በገለምሶ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታስተምር ነበር፡፡ ያቺ ወጣት በዚያ ዘመን በገለምሶ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት ከነበሩት ሁለት ሴት መምህራን አንዷ ነበረች፡፡ የወጣቷ ስም “ደሜ ኩምሳ” ነው፡፡ “ደሜ” በእርግጥም የተዋበች ሴት ነበረች (ደርግ ሊወድቅ በሚንገዳገድበት ሰሞን ደግሞ ደሜ ኩምሳ የታዋቂዋ የኦሮሞ መብት ታጋይ የዶክተር ኩዌ ኩምሳ እህት መሆኗን ተረድቻለሁ፡፡ ደሜ ራሷ መረጃውን ለእህቶቼ ሹክ በማለቷ ነው እውነቱን ያወቅኩት፡፡ ደሜ አሁን የአሜሪካ ነዋሪ ናት)፡፡

ይግረምህ እንግዲህ! ፈጣሪ ብሎልህ ከወለጋ ኮረዳዎች መካከል አንዷ ካንተ ጋር ከተጣመረች ከንፈር ለከንፈር እየተሞጫሞጫችሁ ማለቃችሁን እወቅ፡፡ ታዲያ ወለጊቷን ዝም ብለህ የምትስማት እንዳይመስልህ፡፡ የወለጋዋ ኮረዳ ፍቅሯ የሚጣፍጥላት “ሰው ሰው” በሚሸት ትንፋሽ ስትቀርባት ነው፡፡ የምልህ ገብቶሃል አይደለም? “ሰው ሰው” የሚሸት ትንፋሽ የሚለውን አስምርበት! “ቢኖ ቢኖ” እየሸተትክ እንዳትወሸክት! ከጎረና ትንፋሽ በጊዜ ራስህን ማፅዳት አለብህ፡፡

ለዚህ ፍቱን መድኃኒቱ ደግሞ “ኮረሪማ ማኘክ” እንደሆነ ገጣሚ ሰለሞን ዼሬሳ ነግሮናል፡፡ “ሰለሞን ዼሬሳ ወልለቱ ዘኢትዮጵያ ዘብሄረ ኦሮሞ ወ-ዘምድረ ወለጋ”ን ታውቁት የለምን?! ነፍሱን ይማረውና በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ል. ያረፈው ጎምቱ ባለቅኔ ማለታችን ነው፡፡ ያ “ልጅነት”ን እና “ዘበት እልፊቱ”ን የደረሰው ቱባ ገጣሚ!

ሰለሞን የተወለደው “ጨታ” በተባለች የወለጋ መንደር ነው፡፡ በዚያች መንደሩ እስከ ጉርምስናው ድረስ ኖሯል፡፡ ታዲያ ሰለሞን “ዘበት እልፊቱ” በተሰኘችው የወለሎ መጽሐፉ እንዳጫወተን ከሆነ የወለጋ ሸበላዎች ኮረሪማ ማኘክ የሚጀምሩት የጉርምስና ምልክት ሲመጣባቸው ነው፡፡ ሸበላው የራሱን ተጣማሪ እስኪያገኝ ድረስ ኮረሪማውን እያኘከ እና ትንፋሹን እያሳመረ በተስፋ ይቆያል፡፡ መለሎዋን ሲያገኝ ደግሞ መሳሳም ይጀምራል፡፡

ታዲያ የወለጋው ሸበላ ኮረዳዋን የሚስመው እንዲሁ ከመንገድ ላፍ አድርጎአት አይደለም፡፡ ጉብሊቷ ለእንጨት ሰበራ እና ውሃ ለመቅዳት ወደ መስክ ስትወጣ ይመጣና ውበቷን እያደነቀ ይዘፋፍንላታል፡፡ ከዚያም በራሱ ላይ እንደ ሻሽ አድርጎ የጠመጠመውን ነጠላ በማውረድ ከልጅቷ ጋር ይከናነበዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሁለቱ ወጣቶቹ የሚሳሳሙት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶቹ ለኢያሴ እና ለሌሎች ጨዋታዎች ተቀጣጥረው በሚገናኙበት ወቅት በጨዋታው መሃል የአፍታ እረፍት ወስደው ሊሳሳሙ ይችላሉ፡፡

ጥብቅ ማሳሰቢያ! የወለጋው ደርገጌሳ (ሸበላ) ፍቅረኛውን ከመሳም ባለፈ ለሌላ ነገር አይጋብዛትም፡፡ በየትኛውም የኦሮሚያ ዞን ባሉት ገጠሮች ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ወጣቶች ፍቅራቸውን የሚገልጹበት የመጨረሻው ድርጊት መሳሳምና መተቃቀፍ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ለወሲብ መገባበዝ በባህላቸው ውስጥ የለም፡፡ በኦሮሞ ባህል ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸም በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡
—–
የወለጋ ምድር ሰፊ ነው፡፡ እዚህ የቀነጨብኩት የባህር ጠብታ ያህል ነው፡፡ ህዝቡን ልትጎበኙት ብትሄዱ በፍቅር ይቀበላችኋል፡፡

አንዳንድ ስም አጥፊዎች ይህንን ህዝብ የሚያዩበት የተንሸዋረረ መነጽር እኛ ዘንድ አይሰራም። ወለጋን የምናውቀው ዛሬ ሳይሆን ድሮ ነው። ለምሳሌ የአምስተኛ እና ስድስተኛ ክፍል የሂሳብ መምህራችን የነበረው የወለጋው ጋሽ ኩማ ባይሳ ደመወዙን ይጨርስ የነበረው ችግረኛ ተማሪዎችን ምሳ በማብላት ነበር። ካደግኩ በኋላ እንዲያ ዓይነት ባህሪ ከየት እንዳዳበረው ሳጣራ ከተወለደበት የወለጋ ኦሮሞ ህዝባችን ባህል የወረሰው እንደሆነ ደርሼበታለሁ።

የወለጋን ስም የሚያጠፉት፣ “ሽፍታ” የሚሉት፣ “የአክራሪ ብሄርተኝነት ምንጭ” የሚሉት በዘመቻ የሚያስፈራሩት እና በጦር ዝም ሊያሰኙት የሚያደቡት ሁሉ ዓላማቸው የኦሮሞን አንድነት መበተን እና በጎሳና በክፍለ ሀገር መከፋፈል ነው፡፡ ህዝቡ ከእነርሱ በላይ ነቅቷል፡፡ በመሆኑም ድሉን በቀላሉ እንደማያስነጥቅ ሊያውቁት ይገባል፡፡ የወለጋ ጉዳይ የመላው የኦሮሞ ህዝብ ጉዳይ ነውና፡፡
—-
blank(አፈንዲ ሙተቂ፡ ከመጨረሻዎቹ ሁለት አንቀጾች ውጪ የተቀረው “ቦረና እና በሬንቱ” ከተሰኘው መጽሐፌ የተቀነጨበ: ገጽ 56-58)

1 COMMENT

  1. Hori Buli!!
    Yaa jaalee kiya, kitabakee kan attamit afaan English iti hinee biyya lafa waa’ee Oromoofi waa’ee adaa Oromoo kana barsisuu dandenya? Mee yaada iti kena.

    GLTM

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.