ፕሮጀክት (አጀንዳ) 2030 አማራውን እንደገና አስተካክሎ መበየን

ፕሮጀክት (አጀንዳ) 2030 አማራውን እንደገና አስተካክሎ መበየን

CONFIDENTIAL DOCUMENT

 • ዳንኤል ክብረት (ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ)
 • ዶ/ር ዮናስ ተስፋ (አማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ)

ጥር  2012

Pastor Daniel Kibret, special adviser and confidant of Abiy Ahmed

የፕሮጀክቱ ዳራ

የሀገራችንን የቅርብ ዘመን(ከ1966 በኋላ) ፈተና ምንጩን ስንመለከት በአንድም ሆነ በሌላ በኩል በ1960ዎቹ መቀንቀን ከጀመረው የብሔር ጥያቄ (nationalist question) ጋር በእጅጉን የተቆራኘ ሆኖ እናገኛዋለን፡፡ በዚያን ወቅት ይቀነቀን የነበረው የብሔር ጥያቄ መነሻው ኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች እና ባህሎች የሚኖሩባት ሀገር ሆና ሳለ ጎልቶ የሚታየው የአንድ ወገን ባህል እና ቋንቋ ነው የሚል ቅሬታ ነው፡፡ ውሎ አድሮ ግን ይህ ጥያቄ ይዘቱ፣ መገለጫው(ቅርጹ)ና አመክንዮው እየበዛ እና የተለዋወጠ ሄዶ የኢትዮጵያን የሀገረ መንግሥት ሂደት እና ታሪክን የሚገዳደርበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህ የተነሳ የተለያዩ አሰላለፎችን ፈጥሯል፡፡

በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የአንድን ወገን ማንነት አግዝፎ የሌሎችን ማንነት በመጨፍለቅ የተከናወነ እና ብሔራዊ ጭቆናን ያነገሠ በመሆኑ ብሔራዊ ጭቆናው መሠረታዊ በሆነ መልኩ ሊወገድ እና ሁሉም የሀገሪቱ ሕዝቦች በእኩልነት ቋንቋቸው፣ ባህላቸው እና ብሔራዊ ማንነታቸው ተክበሮ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የሚኖሩበት ሥርዓት ሊፈጠር ይገባል የሚል አለ፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት የተመሠረተው ራሳቸውን ችለው ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦችን በኃይል ቅኝ በመግዛት እና ይኖሩበት የነበረውን ሀገር በማፍረስ እና ብሔራዊ ማንነታቸውን፣ ቋንቋቸውና ባህላቸውን በመጨቆን የተከናወነ በመሆኑ እነዚህ ሕዝቦች ከፈለጉ ተገንጥለው የራሳቸውን ሀገረ መንግሥት እንዲመሠርቱ ዕድሉ ሊሰጣቸው እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ መቆዬት ከፈለጉ ብሔራዊ ማንነታቸው እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው ተከብሮ ሊኖሩ ይገባል የሚል ነው፡፡

ሁለቱንም አሰላለፎች በዋናነት የሚለያዩባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ቢኖሩም በጨቋኝ-ተጨቋኝ ትርክት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸው አንድ ያደርጋቸዋል፡፡

በመጀመሪዎቹ ጊዜያት ላይ ጨቋኝ ተብሎ ይገለጽ የነበረው የፊውዳሉ ሥርዓት ቢሆንም ቅሉ ኋላ ላይ ግን ‹አንዴ የአማራ ገዥ መደብ (ከአማራ የወጡ ገዥዎች)› ሌላ ጊዜ ‹የአማራ ሕዝብ› በአጠቃላይ በጨቋኝነት እየተፈረጀ መጥቷል።

የብሔር ጥያቄንም ሆነ የፊውዳሉን ሥርዓት የነቀነቀውን የመሬት ላራሹን በተመለከተ አንድ የሚዘነጋ ጉዳይ አለ፡፡ ከእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ግንባር ቀደም አቀንቃኞቹ የአማራ ሕዝብ ልጆች እንደነበሩ ተረስቷል፡፡

እነዚህን ሁለት ጉዳዮች አቀንቅነው መሥዋዕትነት ከከፈሉት መካከል ቁጥራቸው ቀላል የማይባለው ከአማራ ሕዝብ አብራክ የወጡ እና የተወሰኑት ደግሞ ከመኳንንቱ እና መሳፍንቱ የሚወለዱ ነበሩ። በተጨማሪም የብሔር እና የመሬት ላራሹ ጥያቄ ከመነሣቱ አስቀድሞ የዘውዳዊው እና የፊውዳሉ አገዛዝ እንዲገረሰስ እና በሀገራችን ሕዝባዊ መንግሥት እንዲመሠረት በተለያዬ መልኩ ሲወተወቱ የነበሩት የአማራ ልሂቃን እንደነበሩ ታሪክ አሌ የሚለው አይደለም።

ሆኖም ግን ከዚህ እውነታ ጋር በሚቃረን መልኩ ለባለፉት ዐርባ ምናምን ዓመታት የአማራ ሕዝብ የሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጠላት እና ሥጋት ተደርጎ እንዲሳል/እንዲታይ በጨቋኝ – ተጨቋኝ ትርክት ላይ የተመሠረተ የተቀናጀ ፖለቲካዊ እና ማኅበረሰባዊ ዘመቻ ተካሂዶበታል።

የሀገሪቱን ማኅበረ ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታትና ብሔር ብሔረሰቦችን የተሟላ መብት ለማጎናጸፍ የታገለው ሕዝብ ራሱ ችግ ሆኖ እንዲታይ ተደረገ፡፡ በዚህ የተነሣም በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የከፈለው ዋጋ እንዲሁም የፊውዳል ሥርዓቱን ለመገርሰስ በተደረገው ትግል የተጫዋተው ወሳኝ ሚና ተዘንግቶ የአማራ ሕዝብ ዛሬም በሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ፊት በተለያየ መልኩ የተሳሳተ ስም እና ስፍራ ሲሰጠው ይስተዋላል፡፡

የአማራ ሕዝብ ያለስሙ ስም እንዲሰጠው ያደረገው ዋነኛ ምክንያት ሁለት መነሻዎች አሉ፡፡

1.  አማራ-ጠል-ኢትዮጵያ-ጠል የሆኑ የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች የተቀናጀ ዘመቻ፡-

ለብዙ ዘመናት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ተነሥተው የከሸፈባቸው አካላት ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ በመከፋፈል አዳክሞ ቅኝ ለመግዛት በነበራቸው ስትራቴጂ አማራ ጠል የሆነ ትርክትን ፈጥረዋል፡፡ የእነርሱን ጽሑፎች፣ ትምህርቶችና ስብከቶች የተከተሉ የሀገር ውስጥ አንዳንድ ልሂቃን ይህን የቅኝ ገዥዎች አማራ ጠል አካሄድ ሀገራዊ መልክ ሰጡት፡፡

2.  የአማራ ልሂቃን እና ፖለቲከኞች ያደረጉት አሉታዊ አስተዋጽዖ፡-

ሀ. የሀገሪቱ ታሪክና የሥነ ጽሑፍ ቅርስ የተቀመጠው በግእዝና በአማርኛ በመሆኑ፤ በሥነ ጽሑፍ ቅርሱ ላይ የሚገኙ ሐሳቦችን ሁሉ የአማራ ሕዝብ ሐሳቦች አድርጎ የመውሰድ አዝማሚያ አለ፡፡ በሥነ ጽሑፍ ታሪኩ ውስጥ ከተለያዩ ብሔሮች የመጡ ልሂቃን መኖራቸው ተዘንግቶ ሁሉንም ስሕተት ለአማራ የመስጠት አዝማሚያ እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡

አንዳንድ የአማራ ልሂቃንም ይህን አርሞ ከመቆም ይልቅ ወርሶ የመጓዝ መንገድን ተከትለዋል፡፡

ለ. በሌላ በኩል ደግሞ ቅኝ ገዥዎችና ቅኝ ገዥ ከተል ሀገራዊ ልሂቃን የፈጠሩትን አማራ ጠል ትርክት ለመገዳደር የተፈጠሩ አንዳንድ ትርክቶች በራሳቸው ችግሩን የሚያባብሱ ሆነዋል፡፡

ሐ. በየትኛውም የዓለማችን ክፍሎች በሀገረ መንግሥት ግንባታ እንዲሁም በፊውዳልና ዘውዳዊ የአገዛዝ ሥርዓት ሊፈጸሙ የሚችሉ ስሕተቶች አሉ፡፡

እነዚህን ስሕተቶች አስመልክቶ የሚነሡ ክሶችን እውነት ወይም ሐሰት መሆናቸውን በጥናት ለይቶ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ አንዳንድ የአማራ ልሂቃን ግን በነገሥታቱ ወይም ደግሞ በመኳንንቱ ተፈጸሙ ተብለው አንዳንድ ስሕተቶች ሲነሡ የአማራ ሕዝብ ተነካ ብለው ያስባሉ፡፡ ለመከላከልም ይነሣሉ፡፡ አማራውንም ያለፉት ታሪኮች ብቸኛ ተቆርቋሪ አድርገው ያቀርቡታል፡፡

መ. የአማራ ልሂቃን የአማራ ጉዳይ ሲነሣ በእልህ እና በተደፈርኩ ባይነት ስሜት ተጨፍነው የጉዳዩን ውስብስብነት እና ፈርጀ ብዙነት ባገናዘበ መልኩ በጥልቀት መርምሮ የተከፈተበትን የተቀናጀ ዘመቻ ለመመከት በሚያስችል መልኩ አለመንቀሳቀሱ።

ሠ. የአማራ ሕዝብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከየአቅጣጫው ጥትም ወቀሳም የሚሠነዘርበት የኦሪት ፍየል ሆኗል፡፡ ለዚህም በየብሔረሰቡ የሚታተሙ የታሪክ መጻሕፍትን መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ በሕዝቡና በልሂኑ ዘንድ የተጠቂነት ስሜት ፈጥሯል፡፡ በዚህም የተነሣ ሌላው የፈጸመውን ጥፋት ለመፈጸም ፉክክር ውስጥ በመግባቱ ለከሳሾቹ ራሱ ማስረጃ የሚያዘጋጅላቸው አካሄድ ፈጠረ፡፡ ይህ በመሆኑ እንኳን ሌሎች ስለ አማራ ሕዝብ ትክክለኛ

እንዲኖራቸው ማድረግ ሊችል የአማራ ሕዝብ ስለራሱ ትክክለኛ ዕውቀት እና ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ አልቻለም፡፡ ይህም የአማራን ሕዝብ ለጥቃት ተጋላጭ እንዲሆን እና በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አጣብቂኝ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል፡፡

እነዚህን ችግሮች ይሁነኝ ብሎ፣ አጥንቶና አስልቶ መፍታት ይገባል፡፡ ይህም ለአማራ ሕዝብ ምሁራኑ ሊከፍሉት ከሚችሉት ውለታ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክትም የተቀረጸው እነዚህን የዘመናት ችግሮች ስልታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ነው፡፡

1.  የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ

የዚህ ፕሮጀክት ዋነኛ ዓላማም በጨቋኝ – ተጨቋኝ ትርክት ላይ ተመሥርቶ ግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በአማራ ሕዝብ ላይ ከውጭና ከውስጥ፣ በቅድሚያና በምላሽ፣ የተካሄደውን ሕዝብን የማጠልሸት እና ሥጋት አድርጎ የመሳል ዘመቻን መቀልበስ ነው፡፡

1.1 ወሰንና ዝርዝር ዓላማዎች – የዚህን ፕሮጀክት ጊዜ የሚወሰነዉ በፕሮጀክቱ ሊፈጸሙ የታቀዱ ተግባሮችን መሠረት ባደረገ መልኩ ነዉ በዚህ ፕሮጀክት የሚከናወኑ ምርምሮችና ጥናቶች እስከ አምስት ዓመት ድረስ የሚወስዱ በመሆኑ የፕሮጀክቱ ጊዜ ቢያንስ 10 ዓመት እንዲሆን ታስቦል፡፡ ፕሮጀክቱ የሚከተሉት ዝርዝር ዓላማዎች ይኖሩታል፤-

 •  የአማራ ሕዝብን ታሪክና ማንነት በተመለከተ ጥናትና ምርምር ማካሄድ፣
 • የአማራ ሕዝብን ማንነት በተመለከተ በጥናት ላይ በመመርኮዝ ብያኔ በመስጠት ወጥ የሆነ አረዳድ በአማራ ሕዝብና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ እንዲዳብር ማድረግ፣
 •  በሀገራችን ሀገረ መንግሥት ግንባታ ዙሪያ የአማራ ሕዘብ ያደረገዉን አስተዋጽዖ መረጃን መሠረት አድርጎ በመመርመርና በመተንተን በአማራ ሕዝብ ላይ የተመሠረቱ የተዛቡ ትርክቶች ላይ ግንዛቤን በማሳደግ ተገቢዉን ማስተካከያ ማድረግ፣
 •  በአማራ ሕዝብና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ያለዉን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር የሚያሳዩና የሚያሳድጉ ምርምሮችን ማከናወን፣
 •  የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ያበረከታቸውን አስተዋጽዖዎች በመረጃና በማስረጃ ማሳየት
 •  በአማራ ሕዝብና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ያለዉን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያግዙ የተለያዩ
  የማህበራዊና የኢኮኖሚ ቅንጀት የሚፈጥሩ ስልቶችን መቀየስ፣
 •  የአማራ ሕዘብን በተመለከተ በተለያዩ ሰነዶች ማለትም በሥርዓተ ትምህርት፣ በመጻሕፍትና በጆርናሎች የታተሙ መረጃዎችን በማጥናት መሰተካከል ያለባችዉን መረጃዎችና ሰነዶች በመለየት ትክክለኛዉ መረጃ እንዲካተት ወይንም እንዲሠራጭ ማድረግ፣
 • በተለያዩ ዓለማት የአማራን ሕዝ በተመለከተ ከቀድሞ ጀምሮ የተያዙ አዎንታዊ ምስሎችን ማበርታት አሉታዊ ምስሎችን ደግሞ ማስተካከል፤
 •  የአማራን ሕዝብ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወዘተ ጉዳዮች በተመለከተ በተለያዩ አካላት ለሚነሡ ተገቢ ያልሆኑ ትችቶች፣ መረጃ አልባ ክሶችና ወቀሳዎች እንዲሁም ተገቢ ያልሆኑ ገጽታዎች አፋጣኝና በቂ ምላሽ የሚሰጥ ተቋም መፍጠር፤

2. የፕሮጀክቱአደረጃጀት

2.1  ፕሮጀክት ጽ/ቤት – የፕሮጀክቱ ጽ/ቤት በአማራ ምሁራን መማክርት ሥር የሚቁቁም ይሆናል፡፡ ጽ/ቤቱም በአስተባባሪና በግብረ ኃይል የሚመራ ሲሆን ከተግባራቱ ጋር ቀጥተኛ ተዛማጅ ያላቸዉ ጊዜያዊና ቋሚ ባለሞያዎችን እያወዳደረ ይሠራል፡፡

በፕሮጀክቱ ትግበራ ላይ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ፣ ዕውቀትና ብቃት ያላቸው፣ የተሰጣቸው ሥራ ደረጃው ጠብቀው በተገቢ ጊዜ ማከናወን የሚችሉ የክልሉንና ሌሎችን ምሁራን ጽ/ቤቱ በመብራት እየፈለገ እንዲያገለግሉ ያደርጋል፡፡

2.2  የፕሮጀክቱን አስተባባሪና ግብረ ኃይል ስየማ የፕሮጀክቱን አስተባባሪና ግብረ ኃይል ለመሰየም አደራጅ ኮሚቴ በክልሉ መንግሥትና በምሁራን መማክርት ኮሚቴ ይመረጣል፡፡ አደራጅ ኮሚቴዉ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችና ከሥራዉ ጋር አግባብ ካላቸዉ አካላት በተመረጡ አባላት ይዋቀራል፡፡

2.3  የፕሮጀክቱ ተግባራት – ፕሮጀክቱ የአጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ተግባራት ይኖሩታል

2.3.1  የአጭር ጊዜ ተግባራት

 •  የፕሮጀክት ጽ/ቤቱን በሰው ኃይል፣ በቢሮ፣ በቁሳቁስና በበጀት ማደራጀት
 •  የአማራ ሕዝብን ማንነትና ታሪክ በተመለከተ ለተለያዩ የሀገራችን ሕዘቦች ግብዐት የሚሆኑ፣ ውጤታቸው ተቆጥሮ የሚለካ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ማካሄድ፣
 •  የክልሉን ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ የሚዳስስ ለተለያዩ አካላት ተደራሽ የሚሆን ሰነድ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የዉጭ ቋንቋዎች ማዘጋጀት፣
 •  የዉጭ ድርጅቶችንና የተመረጡ ሀገራት ኤምባሲዎችን በአማራ ሕዝብ አጀንዳዎች ዙሪያ ግንኙነት በመፍጠር መረጃ መስጠት፣
 •  ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች፣ ለኪነ ጥበብ ባለሞያዎች፣ ለታሪክ ምሁራን፣ ለተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ወዘተ. በተዘጋጀው ሰነድ መነሻነት፣ የአማራ ሕዝብን ትክክለኛ ገጽታ በተመለከተ ሦስት ሴሚናሮችን ማካሄድ፣

2.3.2 የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ተግባራት

 •  በአማራ ሕዝብ ታሪክና ማንነት ዙሪያ ምርምሮችን ማካሄድ፣ በተለያዩ መድረኮች የጥናት ዉጤቶችን ማሠራጨት፣ በጆርናሎች በተለያዩ የኅትመት መንገዶች በተለያዩ የሀገር ዉስጥና የዉጭ ቋንቋዎች እንዲታተሙ ማድረግ፣
 •  በሀገራችን ሀገረ መንግሥት ግንባታ ዙሪያ የአማራ ሕዘብ ያደረገዉን አስተዋጽ መረጃንና ማስረጃን መሠረት አድርጎ በመመርመርና በመተንተን ከሀገር ግንባታዉ ሂደት ጋር በተያያዘ የሚነሡ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ትርክቶች ላይ ዉይይትና የሐሳብ ልዉዉጥ በማድረግ በሀገራችን ሕዝቦች መካከል የጋራ መግባባት እንዲዳብር መሥራት፣
 •  በአማራ ሕዝብና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ያለዉን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር የሚያሳዩና የሚያሳድጉ ምርምሮችን በማከናወን፣ በሕዝቦች መካከል ያለዉን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያግዙ የተለያዩ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ቅንጀት የሚፈጥሩ ስልቶችን መቀየስ፣
 •  የአማራ ሕዘብን በተመለከተ በተለያዩ ሰነዶች ማለትም በሥርዓተ ትምህርት፣ በመጻሕፍትና በጆርናሎች የታተሙ መረጃዎችን በማጥናት መስተካከል ያለባችዉን መረጃዎችና ሰነዶች በመለየት ትክክለኛዉ መረጃ እንዲካተት ወይንም እንዲሰራጭ መሥራት፣
 •  በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በሚዘጋጁ የትምህርት መርጃዎች የአማራን ሕዝብ ማንነት በተመለከተ ትክክለኛው መረጃ እንዲቀመጥ በጋራ መሥራት፣ አስፈላጊን የገንዘብ፣ የሰው ኃይል፣ የሞያና የመረጃ ድጋፍ ማድረግ፤
 •  የአማራ ሕዝብን ማንነትና ታሪክ የሚያሳዩ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን ማሠራት፣ ለሚሠሩ ድጋፍ ማድረግ፣ እንዲሠሩ ማበረታታት፣
 •  የአማራ ሕዝብን ማንነት የሚያሳዩ ሥራዎችን አወዳድሮ መሸለም፣ የተዘጋጁት እንዲታተሙ፣ ፊልሞቹ እንዲቀርቡ፣ ሙዚቃዎቹ እንዲታተሙ፣ ጥናቶች እንዲሠሩና እንዲታተሙ አስፈላጊን ማበረታቻ መስጠት፤
 •  የአማራ ሕዝብን በተመለከተ እስከዛሬ በመላው ዓለም የተዘጋጁ በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምጽ፣ በዳታ፣ የተዘጋጁ መረጃዎችን ማሰባሰብና በአንድ ማዕከል እንዲደራጅ ማስቻል፤
 •  የተለያዩ ክልሎች ተማሪዎችና ወጣቶች ወደ አማራ ክልል መጥተው የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ባህል፣ እምነት፣ ተፈጥሮና እንቅስቃሴ እንዲመለከቱ፣ ትክክለኛውንም ግንዛቤ እንዲይዙ ዕድሎችን ሁሉ ማመቻቸት፤
 •  ከተለያዩ ሞያዎችና ሕዝቦች የተውጣጡ የአማራ ሕዝብ የባህል፣ የታሪክና የቅርስ አምባሳደሮችን መሰየም
 •  የተለያዩ ብሔረሰቦች ተወላጆች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች የአማራ ክልልን ሕዝብ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ የሚያዩበትን፤ ከሕዝቡ ጋር የሚወያዩበትንና ትክክለኛ ገጽታውን የሚውቁበትን ዕድል መፍጠር፤
 •  የአማራን ሕዝብ ዕሴቶች የሚያሳዩ የተረት መጻሕፍትን፣ የልጆች መጻሕፍትን፣ የልጆች ፊልችን፣ ካርቱኖችንና የመሳሰሉትን በሀገር ውስጥና በውጭ ቋንቋዎች አዘጋጅቶ ማሠራጨት፤
 •  የተለያዩ ክልሎች ወጣቶች ስኮላርሺፕ አግኝተው በክለሉ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ በማድረግ የሕዝቡን ማንነት በቅርብ እንዲረዱ ማስቻል፤
 •  የሀገራችንን ብሔሮችና ብሔረሰቦች ታሪኮች፣ ባህሎች፣ ቅርሶች፣ የወግ ዕቃዎች፣ አልባሳት፣ ምግቦች፣ ወዘተ የሚያሳዩ ባዛሮች፣ ዐውደ ርእዮች በክልሉ ልዩ ልዩ ከተሞች እንዲካሄዱ ማስቻል፤
 •  ለብሔር ብሔረሰቦች ወይም በዚያ ማኅበረሰብ ለሚታወቁ ጀግኖችና ኩነቶች መታሰቢያ የሚሆኑ መንገዶች፣ ጎዳናዎች፣ ፓርኮች፣ ደኖች፣ ድልድዮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ወዘተ በአማራ ክልል እንዲሰየሙ ማድረግ፤
 •  የተለያዩ ብሔረሰቦች ቋንቋዎች በክልሉ በትምህርት መልክ እንዲሰጡ ማመቻቸት፤
 •  ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች የሚመጡ ባለሀብቶች፣ ኢንቨስተሮችና ነጋዴዎች በአማራ ክልል እንዲሠሩ
  ማበረታታት፣ የሕግ ማሕቀፍ ማዘጋጀት፣ ጥበቃ ማድረግ፣ ከክልሉ ተወላጆች ጋር በጋራ እንዲያለሙ ማስቻል፤

2 Comments

 1. የአምሀራ ህዝብ ከባቢሎን ዘመነ መንግስት ጀምሮ ከኩሻዊ ወንድሙ ኦሮሞ ህዝብ ጋር የጋራ ታሪክ አለዉ።ይሁን እንጅ የታሪክ ሰነድ ሳይኖር የዛሬውን እማራ እና አማርኛ ተናጋሪ ከጥንታዊው የግእዝ ቋንቋ ተናጋሪ የአምሀራ ህዝብ ጋር እንደ አንድ መቁጠሩ ትውልድን ለማደናገር ካልሆነ ጠቃሚ ስራ አይደለም።
  የዛሬዉ አማርኛ ተናጋሪ አማራ እንደ ጥንታዊው ግእዝ ቋንቋ ተናጋሪ አምሀራ ሁሉ ከኦሮሞ ጋር የጋራ ታሪክ አላቸው።
  ዛሬ የማንነት መቃወስ በሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ዘንድ ያለ ችግር ነው።ማንም የአማራ ምሁር አማራ ስለመሆኑ ሳይሆን አማራ ማለት በራሱ ከመላምት ባለፈ እውቀቱ የለውም።ኦሮሞውም እንዲሁ ነው።በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችም ችግሩ ተመሳሳይ ነው።
  በመሆኑም እነ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሆኑ ሌሎች ሌላ የታሪክ ስህተት የማይፈፅሙ ስለመሆኑ በምንም ማረጋገጥ ይቻላል? በፍፁም አይታሰብም።
  ስለዚህ ዜጎች የሚያምኑበትን እና የሚተማመኑበት ታሪክ በምኞት ሳይሆን ከሁሉም የሀገራችንና የውጭ ሀገራት የተውጣጣ ነፃ እና ገለልተኛ የታሪክ፣የአርኪዎሎጂ፣የቋንቋ፣የአንትሮፖለጂ፣…ወዘተ ምሁራን የጋራ ሙያዊ የምርምር ስራ ውጤት እንጅ አንዱ አንጃ የፈበረከዉን ልበወለድ ከእውቀት የሚቆጥር እና ይህንኑ እየቀባጠረ የሚታረክ ትውልድ ትርፋማ አይሆንም።ቸር ይግጠመን።

 2. The newly appointed acting Mayor of Addis Ababa Dr. Menilik Alemayehu
  should condemn the trend of demolitions of historical heritage sites that are taking places in the city such as the Legehare 100+ years old historical building along with Woinshet’s adjacent home at the historical train station Babur Tabiya which currently is being demolished to be replaced with Dubai’s architecture .

  The city of Pompelli in Italy is a good example of a well kept historical city which Addis Ababa should aspire to imitate under the newly appointed Addis Ababa’s acting Mayor Menilik Alemayehu’s leadership .

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.