ፌዴራላዊ አስተዳደርና የብሄር ጥያቄ በኢትዮጵያ፣

ከባይሳ ዋቅ-ወያ

(ለውይይት መቋጫ)

*****

በቅርቡ ካንዳንድ ባብዛኛው በዲያስፖራ ከሚገኙ እንደምገምተው ከሆነ፣ የአንፋፋው ትውልድ አባላት፣ ወያኔ በኢትዮጵያ የደነገገው ፌዴራላዊ አስተዳደርና በህገ መንግሥቱ ውስጥም ያካተተው አንቀጽ 39 ለኢትዮጵያ የግዛትም ሆነ የህዝቦቿ አንድነት ጠር ነው በማለት በተደጋጋሚ የሚጽፉትን አይቼ፣ እንደው ታዝቤ ዝም ከምልና፣ ፌዴራላዊውን አስተዳደርም ሆነ አንቀጽ 39ን በህገ መንግሥቱ ውስጥ እንዲካተት ያደረጉትን አስገዳጅ ምክንያቶች ከምንጩ ለማስረዳት፣ አንድ ትውልድ ሙሉ የተወያየንበትና የተከራከርንበትን የብሄር ጥያቄ ዛሬም ማንሳቱ የችግሩን መዳፈን እንጂ መክሰም የሚያሳይ ባለመሆኑ፣ 85% ለሚሆነውና የክስተቱ ሰለባም ተጠቃሚም ላልሆነው የዛሬው ኢትዮጵያዊ ዜጋ የችግሩን ይዘት በከፊልም ቢሆን ማስረዳቱ፣ የፌዴራላዊው አስተዳደርና አንቀጽ 39 በህገ መንግሥቱ ውስጥ በተደነገገው መሰረት በተግባር ከዋለ፣ በምንም መልኩ ያገሪቱንና የህዝቦቿን አንድነት እንደማይጎዳ መሆኑን ለመሞገት ይህንን የውይይት መቋጫ ጽሁፍ ለማቅረብ ወሰንኩ። የጥያቄው እስከዛሬ ድረስ ላንዳንዶቻችን በተለይም ለ15% አባላት “ሳይገባን” መቅረቱ የሚያሳስበኝን ያህል፣ ጥያቄውን አንስተን የምንወያየው ባብዛኛው በኔ ዕድሜ ክልል የምንገኝ፣ ሶስቱንም የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሥርዓት ያየን፣ ወይ የብሄር ጭቆና ሰለባ የሆንን፣ አለያም ደግሞ የብሄር ጭቆናን ያራምድ የነበረው ሥርዓት ተጠቃሚ የነበርን አንጋፋ ትውልዶች ስለሆንን፣ ተፈጥሮ ራሱ ትውልድን ሲያሸጋሽግ ጥያቄው ባልተበረዘው አዲሱ ትውልድ በቀላሉ መፍትሄ ያገኛል ብዬ ማሰቡ ደግሞ ያጽናናኛል።

በርግጥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ባገር ቤትም ያሉት አንዳንድ የፖሊቲካ ድርጅቶች የፌዴራላዊውን አስተዳደር የሚቃወም አቋም እንደነበራቸውና ዛሬም በዚያው አቋማቸው ጸንተው የሚገኙ እንዳሉ አውቃለሁ። ያ ግን ብዙም አያሳስበኝም። ከጥቂት ዓመታት በፊት የኦሮሚያ የእግር ኳስ ቡድን ባህር ዳር ላይ የደረሰበትን መደብደብና፣ በቅርቡ ደግሞ የኦሮሞ ወጣቶች “ጣናን ኬኛ” ብለው ባህር ዳር ሲገቡ ከህዝቡ የተደረገላቸውን አቀባበል ሳስተያይ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ የኦሮሚያ ፕሬዚዴንት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ህዝብ ተወካዮችን ይዞ በሄደ ጊዜ በባህር ዳር በሁለቱ ህዝቦች ተወካዮች መካከል የተደረገውን ልባዊ የሃሳብ መለዋወጥና መግባባት፣ ቀጥሎም የኦሮሞና የአማራ ምሁራን የኢትዮጵያን ሁኔታ ለማጥናት ቀጣይነት ያለውን የምርምርና የጥናት ስብሰባ ለማዘጋጀት መወሰናቸውን ሳይ፣ በፌዴራል አስተዳደር ምንነትና ጠቃሚነቱ ዙርያ የነበረው የተለያየ አመለካከታቸው በሂደት ውስጥ ዕልባት ያገኛል የሚል ጽኑ ዕምነት አሳድሮብኛል። እስቲ ወደ ተነሳንበት ቁም ነገር እንሂድ።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አስተዳደር አመጣጥ ታሪክለማስታወስ ያህል፣

ደርግን የተካው የሽግግር መንግሥት ሙሉ በሙሉ ከብሄር ነጻ አውጪ ድርጅቶች የተውጣጣ ነበር ማለት ይቻላል። በጊዜው በኢትዮጵያ ውስጥ በትጥቅም ሆነ በትግል ልምድ ከሶስቱ የብሄር ነጻ አውጪ ድርጅቶች የተሻለ ሌላ ስላልነበር፣ የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣዋም በነሱ እጅ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። የኤርትራው ነጻ አውጪ ግንባር ደግሞ ከሁላቸውም ጠንካራና ዓለም ዓቀፋዊ ድጋፍ ስለነበረው እንኳን የኤርትራን ነጻነት ማወጅና፣ ከትግራይና የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባሮች ጋርም ጥምረት ፈጥሮ ኢትዮጵያን ሊገዛ የሚችልበት ደረጃ ላይ ነበር። ግን ኤርትራን ብቻ ይዞ ሄደ። ወያኔና ኦነግም በጊዜው የሚቀናቀናቸው ሌላ የተደራጀ ኃይል ባለመኖሩ፣ የትግራይና የኦሮሚያ ሬፑብሊኮችን መመስረት ይችሉ ነበር። ታሪክ ግን የራሱን ቦይ ስለተከተለ ያ ሳይሆን ቀረ። ሁለቱም የተቋቋሙበትን የመገንጠል ዓላማ ወደ ጎን ትተው በምትኩ የሽግግር መንግሥት አቋቋመው የብሄሮችን መብት ጥያቄ ከሞላ ጎደል ይመልሳል ብለው ያመኑበትን የፌዴራላዊ አስተዳደር ሥርዓት በኢትዮጵያ ለማስፈን ተስማሙ። የሽግግር መንግሥቱንም ቻርተር አረቀቁ፣ ወደፊት በሚታወጀው ያገሪቷ ህገ መንግሥት ውስጥም የብሄሮችን ጥያቄ ባግባቡ ለመመለሱ ዋስትና ይሰጣል ለተባለው አንቀጽ 39 መሰረት ጣሉ። በሂደት ውስጥ ግን ገና ከጅምሩ አናሳ በመሆኑ ምክንያት የበላይነት እንጂ ዕኩልነት እንደማያዋጣው የተገነዘበው ወያኔ፣ በሆነ ባልሆነ ምክንያት ኦነግን ከሽግግሩ መንግሥት ገፍቶ አስወጣና፣ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄሮችን ይወክላሉ ብሎ ጠፍጥፎ የፈጠራቸውን ኦህዴድና የመሳሰሉትን ይዞ ፌዴራላዊቷን ኢትዮጵያን በአምባገነንነትና፣ የብሄሮችን በክልል መከፋፈል ለራሱ እንደሚመች አድርጎና ህዝቡን ከፋፍሎ  ማስተዳደር ጀመረ። ከዚያ ተነስተን ነው እንግዲህ ዛሬ ያለንበት አገራዊ ቀውስ ላይ የደረስነው።

በጊዜው የነበረውን ያገሪቷን የፖሊቲካ ሁኔታ በትክክል የገመገመ ሰው፣ የያኔዋ ኢትዮጵያ በአደባባይ አሓዳዊ በተግባር ግን የብሄሮች ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጎልቶ የታየባት ነበረች። በጊዜው ተቀናቃኝ ያልነበራቸው ነጻ አውጪ ግንባሮች በድል አዲስ አበባ ገብተው ስለ ኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ሲወያዩ፣ አገሪቷን ከመገነጣጠል ሊያድናት የሚችል፣ ከፌዴራላዊ አስተዳደር የተሻለ ሌላ ሥርዓት ሊያመጡ ይችሉ ነበር ብሎ መገመት አንድም በጊዜው የነበረውን የኢትዮጵያን ሁኔታ ካለመረዳት፣ አለያም ደግሞ የብሄሮችን ጥያቄ ምንጭና መልሱን አለማወቅ ነው። ለዓመታት ስንኖረው የነበረውን የማስመሰል አሓዳዊአስተዳደር ያኔ መልሶ ለማቋቋም ተፃራሪ ሙከራ ቢደረግ ኖሮ፣ ወያኔም ትግራይን፣ ኦነግም ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ ከመገንጠል የሚያቆማቸው ኃይል በቦታው ስላልነበረ፣ የኢትዮጵያ የግዛትና የህዝቦቿ  አንድነት ትልቅ አደጋ ውስጥ እንደሚገባ ግልጽ ነበር።

ይህ ማለት የፌዴራላዊው አስተዳደር ስለተመሰረተና በህገ መንግሥቱ ውስጥ ደግሞ አንቀጽ 39 ስለተካተተ፣ ብሄሮች ያነሱት  የነበረው የብሄር ጥያቄ ላንዴና ለመጨረሻ የተሟላ መልስ አገኘ ማለት ሳይሆን፣ ችግሩን በሂደት ለመቅረፍ መሰረት ተጣለ ለማለት ያህል ነው። አለበለዚያማ፣ ገና ከመሰረቱ የክልሎቹ አወቃቀር ራሱ ብዙ ችግር ነበረበት፣ ለምሳሌ ሃረሪና አፋር፣ ጉሙዝና ጋምቤላ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች ሲሆኑ፣ በህዝብ ብዛትና በቆዳ ስፋት ከነሱ በብዙ የሚበልጡት የሃዲያና ከምባታ፣ የወላይታና የሲዳማ ብሄሮች ለምን በክልል ደረጃ እንዳልተዋቀሩ ዛሬም መልስ ያላገኘሁለት ጥያቄ ነው። ይባስ ብሎም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩትን እነዚህን ከሃምሳ በላይ የሚሆኑትን በደቡብ ኢትዮጵያ የሚኖሩትን ብሄሮችን አንድ ላይ ጨፍልቆ የደቡብ ህዝቦች” የሚል የአቅጣጫም ስም ሰጥቶ የፌዴራሉ አካል ማድረግ፣ በቁስላቸው ላይ ጨው የመጨመር ያህል እንደሆነም ይገባኛል። በጽንሰ ሃሳብ ደረጃም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦችን በምን መስፈርት ገሚሱን ብሄር የቀረው ደግሞ ብሄረ ሰብ ወይም ህዝብ ተብለው እንደተሰየሙ ዛሬም የማይገባኝ ጉዳይ ነው።

የፌዴራላዊ አስተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ የብሄር ጥያቄን በሂደት ለመቅረፍ መሰረት ጣለ ብዬ ስሞግት፣ ጥያቄዎቹ በሙሉ መልስ አግኝተው ዲሞክራሲ ሥርዓት ሰፈነ ማለቴ አይደለም። ለምሳሌ የኦሮሞን ህዝብ በተመለከተ፣ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደዚህ ጊዜ ብዙ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ፣ ህገ መንግሥታዊ መብቱን ለማስጠበቅ በሚያቀርበው የማንነት ጥያቄ ብቻ ተወንጅሎ የተገደለበት ወይም ለእስር የተዳረገበት ዘመን ያለ አይመስለኝም። ከነአቶ ስዬ ወይም አቶ ሃብታሙ ምስክርነት እንደሰማነው፣ በእስር ቤቶቻችን ከሚማቅቁት ኢትዮጵያውያን መካከል አብዛኛው ኦሮሞ እንደሆነ ነው። ያም ሆኖ ግን እና ዝቅ ብዬ ለማስረዳት እንደምሞክረው፣ የዚህ ሁሉ ጥፋትና ወንጀል መንስዔ ከአፈጻፀሙ ላይ እንጂ ከፌዴራላዊው አስተዳደር መሪህ ወይም ከራሱ ከህገ መንግሥቱ አይደለም ባይ ነኝ። በህገ መንግሥቱ እንደተደነገገው ብሄሮች ያለወያኔ ጣልቃ ገብነት በየክልላቸው ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው ቢጠበቅላቸው ኖሮ፣ ይህ ሁሉ ሰላማዊ ዜጋ ባልታሰረና፣ ህዝባዊ ዓመጹም ባልተከሰተ ነበር። ለማንኛውም፣ የፌዴራል ሥርዓት ለኢትዮጵያ የግዛትም ሆነ የህዝቦች አንድነት ጠንቅ ነው በማለት አጥብቀው የሚከራከሩት ወገኖቻችን ከሚያነሷቸው ነጥቦች ጥቂቱን ብቻ ላንሳና እስቲ ውሃ ይቋጥር እንደሆነ እንፈትሽ።

1) የኢትዮጵያ ህዝብ ተከባብሮና ተፈቃቅሮ በእኩልነት ይኖር የነበረ፣ አንድ የጋራ ታሪክ ያለው አንድ የኢትዮጵያ ህዝብ ነበር ይላሉ፣ የፌዴራሉ ሥርዓት ግን ይህንን ያፈርሳል ይላሉ።

) ኢትዮጵያ ከሰማንያ በላይ ለሚሆኑት ብሄሮች መናኸርያ ናት። ያም ሆኖ ግን የደርግ መንግሥት መጥቶ ትንሽ ዕውቅና ከመስጠቱ በፊት፣ የብዙዎቹን የኢትዮጵያ ብሄሮች እስከነመፈጠራቸው እንኳ የምናውቅ ኢትዮጵያውያን በጣም ጥቂት ነን። ስለዚህም ነው “ተዋዶና ተፈቃቅሮ አንድ ላይ ይኖር የነበረ የሚለው አባባል ለብዙዎቻችን ባይዋጥም፣ ያው በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እንዳለን ያለመግባባት አቋም እዚህም ላይ “ላለመስማማት ተስማምተን” ጉዞ መቀጠሉ የሚሻለው። ለማንኛውም የራሴን አመለካከት ብቻ አምጥቼ “እመኑኝ” ከማለት ልንክዳቸው የማንችላቸውን አንዳንድ በመረጃ የተደገፉትን ለአብነት ብጠቅስ ምናልባት አንዳንዶቻችሁን ላሳምን እችላለሁ ብዬ እገምታለሁ። በ1953 ዓም ከተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ንጉሡ “መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ” ለምን ታማኝ ወታደሮቻቸው እንዳመጹባቸው ጥናት ተደርጎ እንዲቀርብላቸው ባዘዙት መሠረት በወቅቱ ታዋቂው አማካሪያቸው አቶ ሃዲስ ዓለማየሁ ለንጉሱ የሚከተለውን ምክር አዘል ጽሁፍ አቅርበው ነበር፣

 “በፖሊቲካ የኢትዮጵያ ህዝብ የምንለው ከአማራ ከትግሬ ከጋላና ከሌሎችም ልዩ ልዩ ቋንቋ፣ ልማድ፣ ዘር ወይም ሃይማኖት ካላቸው ክፍሎች አንድ ላይ ሆኖ በኢትዮጵያ ዘውድ ሥር የሚተዳደር ነው፥ ነገር ግን እነዚህ ልዩ ልዩ ቋንቋ ልማድ ዘር ወይም ሃይማኖት ያላቸው ክፍሎች ምንም እንኳ ባንድ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ  የሚል ስም ቢሰጣቸውና ባንድ ዘውድ ሥር ቢተዳደሩም፣ በደስታም ሆነ በመከራ፣ በመልካም ይሁን በክፉ ጊዜ አንድ ላይ የሚያስተሳስረውና ህዝብን አንድ የሚያሰኘው የህብረት ማሰርያ ያላቸው ናቸው ለማለት አያስደፍርምካሉ በኋላ፣

በዚህ አኳኋን የሕይወት ዓላማቸው የተለያየ ክፍሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚባለው ስምና ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የጦር ኃይል በቀር ሌላ የሚያስተባብራቸውና አንድ ላይ የሚያስተሳስራቸው የፖሊቲካ ድርጅት ስለሚጎድሏቸው በእውነተኛው የፖሊቲካ ትርጉም የኢትዮጵያ  ሕዝብ አንድ ነው ለማለት ያስቸግራል በማለት በአሃዳዊዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ባንድ ዘውድ ሥር ይተዳደሩ የነበሩት የተለያዩ ብሄሮች፣ አንድ የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያሰኝ የሚያስችል ደረጃ ላይ እንዳልነበሩ በግልጽ ለንጉሠ ነገሥቱ አሳውቀው ነበር።

ይህንን የህዝቦችን አንድነት አለመኖሩን ለማሳወቅና አንድነቱ ለምን እንዳልነበረ፣ ብሎም ችግሩ መፍትሄ አግኝቶ አንድ “የኢትዮጵያ  ህዝብ” እንዲፈጠር መሰረት ለመጣል ከማሰብ ነው ያኔ የነቁ የተማሪው እንቅስቃሴ አባላት፣ ለምሳሌ ያህል እንደነዋለልኝ መኮንን ዓይነት ጥያቄውን አንስተው ለህዝቡ ለማስተዋወቅ የሞከሩት። ዋናው ዓላማቸው የችግሩ መኖር ታውቆ መፍትሄ እንዲገኝለትና የኢትዮጵያ ብሄሮች በእኩልነት አብረው እንዲኖሩና በሂደቱም ውስጥ “የኢትዮጵያ ህዝብ” የሚባለው እንዲፈጠር ከማሰብ እንጂ አንዳንድ “የዘመኑ የፖሊቲካ ልሂቃን” እንደሚሉት፣ ብሄሮች እንዲገነጣጠሉ አልነበረም።

) ወደድንም ጠላንም ባለፈው ሃያ ስድስት ዓመት ውስጥ ከዚህ በፊት ባገራችን ታሪክ ውስጥ ታይቶም ተሰምቶም ባልታወቀ መልኩ የብሄርን ጭቆና አስመልክቶ ታላቅ መሰረታዊ ለውጥ ተደርጓል። ለምሳሌ የኦሮሞን ህዝብ በተመለከተ፣ ለመጀመርያ ጊዜ ኦሮሚያ የምትባል፣ ቅርጽና ይዘት፣ እንዲሁም የራሷ ድንበር ያላት አንድ የፌዴራል አካል ሆና መፈጠሯ፣ ለማንነታቸው መገለጫና ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄሮች ጋር ተከባብሮ በእኩልነት ለመኖር ማስተማመኛ ያገኙበት ጉዳይ ነው። ኦሮሞዎች ዛሬ፣ ምስጋና ለአንጋፋዎቹ የኦሮሞ ታጋዮችና የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ አባላት ይድረሳቸውና፣ ለመጀመርያ ጊዜ ዛሬ በክልላቸው ውስጥ በመንግሥታዊ ድርጅቶችና በፍርድ ቤቶች ያለምንም ችግር ብሶታቸውን በገዛ ቋንቋቸው ይገልጻሉ። በትምህርት ቤቶችም፣ እነ ኃይሌ ፊዳን ለመሳሰሉ ብርቅዬ ልጆቿ ዘላለማዊ ምስጋና ይድረሳቸውና፣ በቁቤ ይማራሉ፣ ያስተምራሉ፣ ይጽፋሉ፣ ይመራመራሉ። እኔ ተማሪ ሆኜ የተነፈግሁትን በራስ ቋንቋ መማርና ማስተማር ዛሬ እነሱ ዕድለኛ ሆነው የዚህ መብት ተጠቃሚ ሆነዋል። በኔ ጊዜ፣ ማለትም “በአሃዳዊ” “የጠቅላይ ግዛት” ዘመን፣ በግል ቋንቋ ለመማርና ለመናገር ይቅርና ማሰቡ ራሱ “የኢትዮጵያን ህዝቦች አንድነት ያደፈርሳል” ተብሎ በኢትዮጵያ ውስጥ በህግ በተከለከለበት ዘመን፣ የኦሮምኛን ዘፈን እንኳ እንሰማ የነበረው በሳምንት አንድ ቀን ከሞቃዲሾ ሬድዮ ለሰላሳ ደቂቃ በኦሮምኛ ቋንቋ በሚተላለፈው ብቻ ነበር። ዛሬ ያ ሁሉ በታሪክ ብቻ የሚወሳ ሆኗል። ዛሬ የኦሮሞ ልጆች ቤታቸው ቁጭ ብለው ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ በገዛ ቋንቋቸው የሚተላለፍላቸውን የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ፕሮግራም ሲከታተሉ፣ ፍርድ ቤት ሄደው በራሳቸው ቋንቋ ብሶታቸውን ሲገልጹ፣ በትምህርት ቤት በራሳቸው ቋንቋ ሲማሩና ሥነ ጽሁፋቸውን፣ ባህላቸውንና ሙዚቃቸውን ያላንዳች መሰናክል እያጎለበቱ ማየቱ ብዙ ርቀት እንደተጓዝን የሚያሳይና፣ ለዚህም ያበቃን የፌዴራል ሥርዓት ደግሞ በትክክል ሥራ ላይ ከዋለ ምንኛ ፍቱን እንደሆነ አመላካች ነው ባይ ነኝ።

) ፌዴራላዊ አስተዳደር ላገርና የህዝቦች አንድነት ጠንቅ የሆነበት አንድም በታሪክ የተወሳበት ጊዜ የለም። ባገራችንም ለምሳሌ የኤርትራን ህዝብ ለመገንጠል የገፋፋው ያኔ የነበረው ፌዴራላዊ አስተዳደር በንጉሱ በመገርሰሱና ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ስላዋሃዱ እንጂ፣ ፌዴራላዊው አስተዳደር እንዳለ ቢቀጥል ኖሮ ኤርትራ ምናልባት ዛሬ አስረኛው የፌዴራል ኢትዮጵያ ክልል እንጂ ጎረቤት አገር አትሆንም ነበር። የኢትዮጵያ አሃዳዊ አስተዳደርም ኤርትራን ከኢትዮጵያ ከመገንጠል አላዳነም። ስለዚህ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ የምትተዳደርበት የፌዴራል ሥርዓት በትክክል ህገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት ሥራ ላይ ከዋለና ብሄሮች (ክልሎች) ራሳቸውን በራሳቸው ካስተዳደሩ፣ የመገንጠል ጥያቄው የሚነሳበት ምክንያት አይኖርም። በተቃራኒው ግን አንዳንድ አፍቃረ-ጠቅላይ ግዛት ጓደኞቼ እንደሚመኙት፣ ኢትዮጵያ ካሁን በኋላ አሃዳዊ መሆን ቀርቶ ለመሆን እንኳ ሙከራ ብታደርግ፣ ለዘመናት ሞክረነው ያላዋጣንና ለአንድነታችን ጠንቅ የሆነ ሥርዓት በመሆኑ፣ ዛሬ በክልል ደረጃ ከሞላ ጎደል ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳደሩ ህዝቦች ያለምንም ጥርጣሬ የመገንጠልን ጥያቄ ያነሳሉ ባይ ነኝ።

) ፌዴራላዊ ሥርዓት ዲሞክራሲያዊ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ዲሞክራሲያዊ አሰራር ባልተለመደበት አገር ውስጥ ፌዴራላዊ ሥርዓት በትክክል ሥራ ላይ ሊውል አይችልም። ለዚህ ደግሞ አገራችን የዓይነተኛ ምሳሌ ናት። ከዘመናት የፊውዳልና አስራ ሰባት ዓመታት ጥራዝ-ሶሺያሊስታዊ ሥርዓት በኋላ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል አለመቻላችን ብዙም ላይደንቅ ይችላል። የሆነውም ይህ ነው። ምንም እንኳ በዛሬው የፌዴራላዊው ህገ መንግሥታችን ውስጥ የብሄሮች መብት በዕኩልነት እንደሚጠበቅ የተደነገገ ቢሆንም፣ በተግባር ግን ክልሎቹ የይስሙላ እንጂ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸውን ተነፍገዋል። የያንዳንዱን ክልል ፖሊቲካም ሆነ ኤኮኖሚያዊ ህይወት የሚመራው ወያኔ ብቻ ነው፥ ይህንን በመቃወም ነው እንግዲህ ዛሬ ክልሎች ተነስተው ራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር ሀገ መንግሥታዊ መብታችን ይጠበቅ፣ የወያኔ በክልላችን የፖሊቲካና የኤኮኖሚያዊ ህይወት ገብቶ ማዘዙ ይቁም ብለው በሰላማዊ መንገድ ያቀረቡት ጥያቄ ሰሚ ጆሮ ባለማግኘቱ፣ ለህዝባዊ ዓመጽ የተነሳሱት። ስለዚህ ዛሬ ወደተዘፈቅንበት የቀውስ መቀመቅ ያመራን የወያኔ በጉልበቱ ተማምኖ በየክልሉ ጣልቃ እየገባ የክልሎቹን ህዝቦች ህገ መንግሥታዊ መብት መጣሱ ብቻ እንጂ የፌዴራላዊው አስተዳደር ያመጣው ችግር አይደለም ለማለት ነው። በመሆኑም፣ ለዚህ ቀውስ ዓይነተኛና ቀላል የሆነ መፍትሄው ደግሞ የፌዴራል ህገ መንግሥቱን ቃላትና መንፈስ (letters and spirits) በትክክል ሥራ ላይ ማዋል ብቻ ነው የምለው። ሌላ ምንም የሚያሳስብ ነገር የለውም። ክልሎች በህገ መንግሥቱ በተደነገገላቸው መሰረት ያላንዳች ሌላ ብሄር ጣልቃ ገብነት ራሳቸውን ቢያስተዳድሩና፣ በማዕከላዊው መንግሥት መዋቅርና ፓርላማ ውስጥ ደግሞ፣ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸው ቢወከሉ፣ ያገሪቷም ሆነ የህዝቦቿ አንድነት አንዳችም ዓይነት ጥያቄ ውስጥ አይገባም ባይ ነኝ። የሚያሳስበኝ ግን፣ የዛሬው የወያኔ መንግሥት፣ ይህንን ህገ መንግሥታዊ መብት አላከብርም፣ “ጉልበቴን ተጠቅሜ በያንዳንዱ የክልል ፖሊቲካና ህይወት ገብቼ ማዘዙን አላቆምም” ካለና፣ ሌሎች ብሄሮች ደግሞ በጋራ ሆነው በህዝባዊው ዓመጽ በመሳተፍ ይህንን የወያኔ  አካሄድና ግምት ለማስቀየር ካልቻሉ፣ እውነትም የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና የህዝቦቿ በጋራ የመኖር ጉዳይ ትልቅ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል ባይ ነኝ።

ለየእያንዳንዱ አገር የአፈጣጠር ታሪክና በውስጧም የሚኖሩ ህዝቦች ግንኙነት፣ ብሎም አገሪቷ የምትገኝበት የዕድገት ደረጃ ፣ ለህዝቦቿ  አብሮ ለመኖር ወይም ለመፋታት ትልቅ ሚና አለው። ህብረተሰብ አንድ ቦታ ላይ ረግቶ የሚቆም ግዑዝ ነገር ሳይሆን ተቀሳቃሽና አዳጊ ስለሆነ፣ አንድ ሥርዓት ሁሉም አገር ላይ በትክክል ይሰራል፣ ወይም ደግሞ ዘላለማዊ መፍትሄ  ይሰጣል ለማለት አይቻልም። ለዚህም ነው ህዝቡ ባንድ ወቅት ላይ ትክክል ነው ብሎ አምኖበት ወይም መስሎት የተቀበለውን የአስተዳደር ሥርዓት በሌላ ጊዜ ደግሞ ሲቀይር የምናየው። በኢትዮጵያችንም ለብዙ ዓመታት በህዝቦቿ ፈቃደኝነት ሳይሆን ከላይ ተጭኖብን የተቀበልነውና የኖርነው “አሃዳዊ” ሥርዓት የተለያዩ የኢትዮጵያን ብሄሮች ጥያቄ ለመመለስ ባለመቻሉ ነበር ከያቅጣጫው የብሄር ነጻ አውጪ ድርጅቶች መፍለቅ የጀመሩት። (በነገራችን ላይ፣ በታሪካችን ውስጥ የታዩት የብሄር ነጻ አውጪ ድርጅቶች በሙሉ የተፈጠሩት በዚህ አሃዳዊዘመን ነበር። ፌዴራላዊው አስተዳደር ሥራ ላይ ከዋለ በሩብ ምዕት ዓመት ውስጥ ግን አንድም የብሄር ነጻ አውጪ ድርጅት አልተፈጠረም) በሌላ አነጋገር፣ ነጻ አውጪ ድርጅቶቹ የብሄሮችን የመብት ጥያቄ አሃዳዊው ሥርዓት ሊመልስ ባለመቻሉ፣ ከኢትዮጵያ ተገንጥለው ለመኖር የትጥቅ ትግል ጀመሩ፣ ሁኔታዎች ሲቀየሩና አብሮ ለመኖር የሚያስችል አጋጣሚ ሲገኝ ደግሞ፣ በ1991 ዓም “አሃዳዊውን” አስተዳደራዊ ሥርዓት ገርስሰው በፌዴራላዊ አስተዳደር ለወጡትና ኢትዮጵያን ከመገነጣጠል አዳኗት።

2) ብሄር ተኮር በሆነ የክልሎች አስተዳደር አገሪቷን መከፋፈል፣ ላገሪቷ የግዛትና የህዝቦች አንድነት ጠንቅ ነው።

ሳያድለን ቀርቶ ከምናየው ይልቅ የምንሰማውን የምናምን ህዝብ ሆነን ነው እንጂ፣ የኢትዮጵያ በክልሎች መዋቀርና የየክልሉን አስተዳደር ለየብሄሮቹ መስጠት በሌላው ብሄር ተወላጆች ላይ ጉዳት የሚያስከትልና ብሎም ለህዝቦች  አንድነት ጠንቅ አድርጎ ማቅረብ፣ ሆን ተብሎ ዓይኖችን በመረጃ ላይ ተክሎ አንብቦ ከመረዳት ይልቅ ጆሮን ቀስሮ ካንዳንድ ጽንፈኞች የሚወረወረውን መሰረት የሌለውን ወሬ ለመስማት ከመምረጥ የተነሳ እንጂ፣ የየክልሎቹን ህገ መንግሥት ለግማሽ ሰዓት እንኳ ጊዜውን ወስዶ ላነበበ ሰው፣ ያገሪቷ በክልሎች መዋቀር በህዝቦች ተከባብሮ በእኩልነት ለመኖርም ሆነ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት አንዳችም ዓይነት አደጋ እንዳላመጣ መረዳት ይቻላል። ባለፉት ሁለት መንግሥታዊ ሥርዓትና ዛሬም በፌዴራላዊው አስተዳደር የኦሮምያ ህዝብና መንግሥት የሌሎችን ብሄር ተወላጆችን መብት ሲጋፋ ወይም ተከባብሮ ባንድ ላይ ለመኖር ተቃውሞ ያነሳበት ጊዜ ፈጽሞ አልነበረም። ይህን ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄር ተወላጆች ጋር ባንድ ላይ ተከባብሮ ለመኖር ዋስትና ማረጋገጫው ህገ መንግሥት ነውና እስቲ ለመረጃ ያህል ከኦሮሚያ ክልላዊ ህገ መንግሥት አንዳንድ አንቀጾችን ጠቅሼ ፍርዱን ለናንተ ልተው።

በነሐሴ 1987 በታወጀው የኦሮሚያ ክልል ህገ መንግሥት ከተካተቱት ውስጥ አንዳንዶችን ብጠቅስ፣ ህገ መንግሥቱን አንብቦ ለመረዳት ለማይችሉ ወይም ለማይፈልጉና እንደው በግምት “የፌዴራላዊው አስተዳደራዊ መዋቅር ለህዝቦች አንድነት ጠንቅ ነው“ የሚሉት የዕድሜ ዕኩዮቼ በተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ የተሳሳተ ግምታቸውን ያስተካክላሉ ብዬ እገምታለሁ።

  • ኢትዮጵያውያን የሆኑ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች በዚህ ክልል ውስጥ እንደማንኛውም የዚህ ክልል ተወላጅ ሰርቶ የመኖር፣ ከስፍራ ስፍራ የመዘዋወር፣ ሃብትና ንብረት የማፍራትና የመያዝ መብት አላቸው” (አንቀጽ 34/1)
  • የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም የክልሉ መንግሥታዊ ሥራ ውስጥ ተመርጦ ወይም ተመድቦ የመሥራት መብት አለው፣ (አንቀጽ 34/2)
  • ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ ወይም በሕጋዊ መንገድ በክልሉ ውስጥ የሚገኝ ሰው በመረጠው የክልሉ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖርያ ቤት የመመስረት መብት አለው፣ (አንቀጽ 33)
  • ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ በቀለም፣ በዘር፣ በብሄረሰብ፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖሊቲካ ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት…. በቀጥታና በነጻነት በማንኛቸውም የመንግሥት ደረጃ የመምረጥና የመመረጥ መብት አለው፣ (አንቀጽ 39/1)።
  • ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ ወይም በክልሉ ለመኖር የሚፈልግ ሌላ ኢትዮጵያዊ በማንኛውም የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደርያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው፣ (አንቀጽ 41/1)።
  • የክልሉ ነዋሪዎች ሁሉ በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው፣ (አንቀጽ 41/3)።

በዚህ ህገ መንግሥታዊ ዋስትና መሰረት ነው ለምሳሌ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የአማራና የሌሎች ብሄር ተወላጆች ዛሬ በኦሮሚያ ውስጥ የመኖርና የመሥራት፣ ብሎም ቋንቋውን እስከቻሉ ድረስ በከልሉ መንግሥት ያላንዳች አድልዖ የመሥራትና አልፎ ተርፎም የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው ተጠብቆላቸው የሚኖሩት። ይህ ዕውኔታ እንግዲህ የማይታየን እንደኔ ዓይነቱ አብሮን ያደገውን የጭቆና ጠባሳ ይዘን ለምንጓዝና፣ በወዲያኛው ጫፍ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የጨቋኙ ሥርዓት ተጠቃሚ የሆኑት የዕድሜ እኩዮቼ ካልሆንን በስተቀር፣ የክልል መዋቅሩ ለህዝቦች ተፈቃቅዶ አንድ ላይ ለመኖር ህገ መንግሥቱ ምንም ዓይነት አሉታዊ ጎን እንደሌለው ግልጽ ነው። ኢትዮጵያ አንድ ቋንቋ የሚናገር ያንድ ወጥ ብሄር አገር ብትሆን ኖሮ፣ እዚህ ሁሉ መናቆር ውስጥ ባልገባን ነበር። ብትሆን ኖሮ! ግን ደግሞ ዛሬ ያለውን ዕውኔታ በቅንነት ተገንዝበን አንድ ላይ በሰላም ብንጓዝ፣ ልክ ሌሎች አገሮችም በሂደት ውስጥ አንዱ ብሄር አንዱ ውስጥ በመቅለጥ አንድ ወጥ ህዝብ እንደፈጠሩት ሁሉ፣ የልጅ ልጆቻችንም ከረጅም ጉዞ በኋላ አንድ ቀን ዕድሉ ገጥሟቸው አንድ ብሄር የሚሆኑበት አጋጣሚ ይፈጠር ይሆናል። የዚያን የብዙ ሺህ ማይሎች ጉዞ የመጀመርያውን እርምጃ ግን ዛሬ አገሪቷ የምትደዳርበት የፌዴራላዊው ሥርዓት ጥሩ ጅምር ነው ብሎ ከማመን ይመስለኛል። በተግባር ደግሞ፣ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የየክልሉ ብሄር፣ ከራሱ ቋንቋ በተጨማሪ የሌላውን ብሄር ቋንቋ መርጦ በየትምህርት ቤቱ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ማስተማር ቢጀምር፣ የህዝቦችን ቀስ በቀስ የመዋሃድ ዕድል ያሰፋል ባይ ነኝ።

3) የብሄር ጥያቄ ማርክሲስቶች ያመጡብን መጤ ችግር ነው እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረ መንግሥታዊ ፖሊሲ አልነበረም፣

የብሄርን ጥያቄ፣ አንዳንዶቹ “የግራ አስተሳሰብ የነበራቸው” ግለሰቦች ያመጡብን ነው እንጂ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ተዋዶ ተዋልዶና ተካባብሮ ለዘመናት አብሮ የኖረ ነው ይሉናል። ይህ ከዕውነት የራቀ አባባል ነው። በመጀመርያ ደረጃ በማርካሳዊ አስተሳሰብ ይመሩ የነበሩ የኢትዮጵያ ተማሪዎች  ህብረተሰቡ ውስጥ የነበረውን ችግርና ላገሪቷ የግዛትና የህዝቦች አንድነት ያሰጋል ያሉትን ማህበረሰባዊ አደጋ ለህዝብ አሳወቁ እንጂ አልፈጠሩትም። ያኔ አንድም የፖሊቲካ ፓርቲ በሌለበት አገር ውስጥ ነው የመሪነትን ሚና በመጫወት፣ በብሄር ጥያቄ ምንነት ሰውን አሳምነውና አሰልፈው ያካሄዱ በነበረው መራራ ትግልም፣ በአገሪቷ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እንኳ ሥር ነቀል ተብለው ከተመዘገቡት የሰፊው ህዝብ ድሎች መሃል አንዱና ዋነኛው የሆነውን የየካቲት 1975 ዓም የመሬት ዓዋጅ በማሳወጅ ለብሄር ጭቆና ዋነኛ መሳርያ የነበረውን መሬትን ከፊውዳሉ እጅ አላቅቆ መላውን የደቡብን ህዝብ ()ባርነት ነጻ ያወጡት። ምስጋና ለዚያ ታሪካዊ ትውልድ ይሁን!

4) የአንቀጽ 39 በህገ መንግሥቱ ውስጥ መካተት የብሄሮችን የመገንጠል ጥያቄ ያበራታል።

) በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ውስጥ እንደ አንቀጽ 39 በክፉም ሆነ በደግ እየተነሳ ውይይት የተደረገበት አንቀጽ የለም ብል ማጋነን አይሆንብኝም። እንደ እውነቱ ከሆነ ከዚህ አንቀጽ የበለጠ በኢትዮጵያ ውስጥ በመከሰተት ላይ ላሉት አንዳንድ ችግሮች ጠንቀኛ የሆኑ ብዙ የህገ መንግሥቱ አንቀጾች አሉ። ለዚህም ነው ዛሬ በወያኔ መንግሥት የጭቆና አገዛዝ ተንገፍግፈው ለሰላማዊ ሰልፍ የሚወጡ የኦሮሞና የአማራ ክልል ህዝቦች አንግበው ከሚወጡት ደርዘን መፈክራት መካከል፣ የአንቀጽ 39ን ጎጂነት የሚጠቁም አንድም መፈክር የሌለው። ችግሩ ሌላ ቦታ ነው። ብዙዎች በ1990ዎቹ መጀመርያ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያና የዓለም ዓቀፍ የፖሊቲካ ሁኔታ የገመገሙ የፖሊቲካ ሊቃውንትና ዲፕሎማቶች እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ አስተዳደርና ይህንን የብሄሮችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያረጋገጠውን አንቀጽ 39 በህገ መንግሥቱ ውስጥ ማካተት አማራጭ የሌለው እርምጃ ነበር ብለው የደመደሙት። የኔም ድምዳሜ ተመሳሳይ ነው። ያኔ ባገሪቷ በግንባር ቀደምነት የደርግን መንግሥት ይታገሉ የነበሩና ብሎም ለመገርሰሱ ምክንያት የሆኑት የብሄር ነጻ አውጪ ድርጅቶች በመሆናቸው፣ የኢትዮጵያን የግዛትና የህዝቦቿን አንድነት ለመጠበቅ ሲባል በአንድ ፌዴራላዊ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄሮች ራሳቸውን እያስተዳደሩ ግን ደግሞ ባንድ ፌዴራላዊ ባንዲራና መንግሥት ሥር እንዲተዳደሩ ማድረግ ብቸኛው ምርጫ ነበር ባይ ነኝ።

) የአንቀጽ 39 በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ውስጥ መካተትም የኢትዮጵያ ብሄሮች ከኢትዮጵያ እንዲገነጠሉ ሳይሆን፣ ባንድ ላይ እንዲኖሩ፣ ነገር ግን ደግሞ የአንድ ብሄር ህዝብ፣ ”ለብቻዬ መኖር እፈልጋለሁ” ብሎ ካመነበት በህገ መንግሥቱ ውስጥ በተደነገገው መሰረት፣ ከኢትዮጵያ ተለይቶ የራሱን መንግሥት ሊያቋቋም እንዲችል ዋስትና ለመስጠት ታስቦ ነው። ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ውስጥ አንቀጽ 39ን ጠቅሶ የመገንጠል ጥያቄ ያቀረበ አንድም ብሄር የለም። ባለፉት ሶስት ዓመታትም በግልጽ በአደባባይ የወያኔን አገዛዝ በመቃወም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለውን የህዝባዊው ዓመጽ ተካፋዮች እያነሱት ያለው ጥያቄ ከመልካም አስተዳደርና እጦትና በህገ መንግሥቱ ውስጥ የተደነገገው ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው በተግባር አልተተረጎመም ከማለት ሌላ፣ አንድም ቦታ አንቀጽ 39 ጠቅሰው ከኢትዮጵያ ተገንጥለን የራሳችንን የኦሮሚያ አገር ለመፍጠር እንፈልጋለን የሚል መፈክር ይዘው አልታዩም። ዛሬ የኦሮሞ ብሄር፣ ህዝባዊ አመጽን ተጠቅሞ የወያኔ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን እንዲያውጅ ያስገደደ ትልቅ ህዝብ፣ የመገንጠል ዓላማ ቢኖረው ኖሮ የሚያቆመው ምድራዊ ሃይል ያለ አይመስለኝም። የኦሮሞ ሕዝብ፣ ኢትዮጵያዊነቱን ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ መሰረትና ያንድነቷም ዋናው ምሰሶና ማገር መሆኑን አጥብቆ ስለሚያምንበት፣ እየጠየቀ ያለው፣ የወያኔን አምባገነንነት አልፈልግም፣ ህገ መንግሥቱ በሚፈቅድልኝ መሰረት ራሴን በራሴ ላስተዳድር ነው እንጂ ልገንጠል እያለ አይደለም።

መደምደምያ፣

በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የኦሮሞና የአማራ ህዝብ “በማንነታችን እየተበደልን ነው፣ በክልላችን ውስጥ በህገ መንግሥቱ የተደነገገውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብታችንን ለመጠቀም አልቻልንም፣ የወያኔ  የበላይነት መቆም አብቅቶ በዕኩልነት የመኖር መብታችን በተግባር ይተርጎም” በማለት ህዝባዊ አመጽ ያወጁበትን የማንነት ጥያቄ፣ የፌዴራላዊው ሥርዓት ያመጣብን አደጋ ነው ብሎ መደምደም ትክክል አይመስለኝም። በበኩሌ የሚሻል መስሎ የሚታየኝ፣ አንድ ብሄር በማንነቴ ጥቃት ደርሶብኛል ካለ፣ የለም ጥቃት አልደረሰብህም ብሎ ፋይሉን ከመዝጋት ይልቅ፣ ለመራራው ዕውኔታ ዕውቅና ሰጥቶ መፍትሄ በመፈለጉ ላይ መትጋት ይመረጣል። “የፌዴራላዊው ሥርዓት ጎጂ ነው” ወይም “የኢትዮጵያ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ተከባብሮና ተዋዶ በእኩልነት የኖረ በመሆኑ ላገሪቷ የሚበጃት አሃዳዊ ሥርዓት ነው” ብሎ መሞገት፣ አንድም በብሄሮች እኩልነት አለማመን፣ አለያም፣ ጭቆናው በዘመናዊ መልኩ እንዲቀጥልበት ከመፈለግ ሌላ ትርጉም የለውም ባይ ነኝ። ዛሬ ያገራችን ሁኔታ በቅንነት መመልከት አቅቶን ሁኔታዎችን ልክ የዛሬ አርባና ሃምሳ ዓመት በፊት በነበሩበት ቆመው የቀሩ የሚመስለን የዕድሜ እኩዮቼ እያለቃቀስን ያለነው “ለኢትዮጵያ  የግዛትና የህዝቦቿ አንድነት አደጋ ላይ መውደቅ” በሚል ሰበብ የምናራምደው ጽንፈኛ ሃሳብ፣ ላገሪቷ አንዳችም ዓይነት ጥቅም የማያስገኝና እንዲያውም በማስመርያው ሌላኛው ጫፍ ያለውን ተቃራኒ የሆነ ጽንፈኛ አስተሳሰብን ሊያጎለብት ስለሚችል፣ ከልባችን ላገራችንና ህዝባችን ህልውና የምንቆረቆር ከሆነ፣ ዓይናችንንና ልባችንን በመክፈት፣ የችግሩን መኖር አምነን መቀበልና በጋራ መፍትሄ  በመፈለጉ ላይ ብንተባበር የሚሻል ይመስለኛል።

ዛሬ የኦሮሞ ህዝብ በፌዴራላዊው ሥርዓት ውስጥ በህግ የተደነገገልኝ ራሴን በራሴ የማስተዳደር መብት በትክክል ሥራ ላይ አልዋለም በማለት የሚያቀርበውን ህጋዊ ጥያቄ “ባንዳንድ የመገንጠል ዓላማ ባላቸው ግለሰቦች የተጠነሰሰ ሴራ ነው እንጂ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ አይደለም” ማለት በሳሎን ቤታችን መሃል የቆመን ትልቅ ዝሆን ያለማየት ያህል ነው። ጥያቄው ዕውኔታ ነው፣ ግምት ወይም ህልም አይደለም። ከላይ ደጋግሜ እንዳልኩት፣ የብሄር ጥያቄ የማንነት ጥያቄ ነው። ፍቅር ባለበት ትዳር ውስጥ የፍቺ ጥያቄ የማይነሳውን ያህል፣ ጭቆናው ከሌለ የማንነት ጥያቄም አይነሳም። የመደብ ጥያቄን የምርት ማምረቻዎችን በመውረስና ሰርቶ አደሩ እንዳይበዘበዝ ህግ በመደንገግ ሊፈታ ይቻላል። ብሄር ነክ ጥያቄዎች ግን እጅግ በጣም ስስ በመሆናቸውና ስሜትን በቀላሉ ሊነኩ ስለሚችሉ በተራ ዓዋጅ ሊፋቁ የሚችሉ አይደለም። ይህን ስሜት ደግሞ ከሁሉም ሰው በላይ የሚሰማው መብቱ የተነካበት ብቻ ነው። ይህ ምንም ሂሳባዊ ወይም ሳይንሳዊ ፎርሙላም ምክንያት የሌለው፣ ግን ደግሞ የማይታበል ሃቅ ነው። ምጥ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በትክክል ለመረዳት ሴት ልጅ ሆኖ መፈጠር ብቻ ሳይሆን አምጦ መውለድን ይጠይቃል። አለበለዚያ አምጠን ላልወለድን ሰዎች፣ በተለይም ለወንዶች፣ የምጥ ወርድና ስፋቱ በትክክል ሊገባን አይችልም። የብሄር ጥያቄንም ሰለባ በቅጡ ለመረዳት ከዚያ ብሄር መወለድና ገፈቱን መቅመስ ያስፈልጋል። አለበለዚያ የብሄርና የመደብ ጭቆናን እያማታን የጥያቄውን ዕምብርት አውቀነውም ሆነ ሳናውቀው ለማንጋደድ መሞከር ቅንነት የጎደለው ከመሆኑም በላይ ከፊታችን ለተደቀነው ከባድ ችግር አንዳችም መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም።

ከመሰናበቴ በፊት ግን በዲያስፖራ ለምንገኝና “ደጉን የጠቅላይ ግዛት አሃዳዊ ዘመን” ሲንድሮም ላጠቃን፣ እዚህ ባህር ማዶ ሆነን ገንቢ ሃሳብ እያቀረብን ወጣቱን ትውልድ መክሮ ለብሩህ ነገ ከማዘጋጀት ይልቅ፣ የወያኔን የግፍ አገዛዝ ሰበብ በማድረግ፣ የፌዴራሊዝም አስተዳደሩንና የክልል መዋቅሩን አሉታዊ ጎኖች ብቻ በመጥቀስ ህዝቡን ከወያኔ ባልተናነሰ መልኩ በመከፋፈል ላይ ለምንገኝ የአንጋፋው ትውልድ አባላት፣ እንደ አንድ የዕድሜ ባለፀጋ ኦሮሞ አዛውንት የሚከተለውን ምክር ለመለገስ እሻለሁ።

) የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት ተጭኖት የነበረውን የብሄር ጭቆና፣ የብዙ ብርቅዬ ልጆቹን ህይወት ከፍሎበት፣ ቀስ በቀስ ደምስሶ በመጣል የራሱን ዕድል በራሱ ለመወሰን የሚያስችል ሥርዓት አስደንግጎ ፍሬውን መመገብ ጀምሯል። ዘላለማዊ ምስጋና ለዚያ ላንጋፋው ትውልድ ይድረሳቸውና ዛሬ ያለው የቁቤ ትውልድ በብሄረ ኦሮሞነቱና በኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ኮርቶ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚኖር፣ በራሱ ቋንቋ የሚማርና የሚጽፍ፣ ፍርድ ቤት ሄዶ ያለአስተርጓሚ ብሶቱን የሚገልጽና የሌሎች ኢትዮጵያውያንን መብት ሳይነካ በመከባበርና በዕኩልነት አብሮ የሚኖር ህዝብ ነው። እዚህ ደረጃ ለመድረስ ግን የብዙ ሰው ነፍስ መሰዋት ነበረበት፣ ብዙዎቹ መታሰርና መሰቃየት ነበረባቸው። ባጭሩ፣ የተጓዝነው ርቀት፣ ያቋረጥናቸው ሸለቆዎች፣ የተሻገርናቸው ድልድዮችና የወጣነው ዳገት ይህ ነው አይባልም። ዋናው ነገር ግን ዛሬ በከፍታው ላይ ቆመን ያለፍናቸውን መሰናክሎች እያስታወስንና እየገመገምን፣ ባንድ በኩል አዲሱ ትውልድ እኛ የተጓዝነውን የመከራ ጉዞ ተመልሶ እንዳይጓዝ፥ ሌሎች ስለጉዞው ብዙም ያልሰሙ ዜጎች ደግሞ ሰምተው እንዲረዱት እየጣርን እያለን፣ አንዳንድ የዕድሜ ዕኩዮቼ ባለፈው ሥርዓት ምንም ዓይነት በደል እንዳልደረሰብን በማስመሰል፣ እኛ የወደፊቷን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት መሰረቱን ለመጣል የሚያስችል ሲሚንቶ ለማቡካት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጋር ሽር ጉድ በምንልበት ቀውጢ ሰዓት ላይ፣ ከሞቀ ቤታቸው በረንዳ ወይም ስታር ባክስ ካፌ ተቀምጠው፣ “የፌዴራሉ ሥርዓት ለኢትዮጵያ አንድነት መጥፎ ነው” “የክልሎች አስተዳደር አፓርታይዳዊ ነው” “የጎሣ ፖሊቲካ” ወዘተ እያሉ አንድ እርምጃ ወደፊት ስንራመድ ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ መጎተት፣ እጅግ በጣም አሳሳቢና ወዳልታሰበ አደገኛ አቅጣጫ ሊመራን ስለሚችል እስቲ ሰከን ብለን እናስብበት እላለሁ።

) የኦሮሞ ህዝብ የማንነቱ ንቃተ-ኅሊና ከመቼውም ጊዜ በላይ የበሰለና ሊቀለበስ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶአል። ዲን ዳንኤል እንዳሉትም፣ አሁን ጊዜው “የቀንድ ጊዜ” ስለሆነ ጥጆቹን “በጆሮ ዘመን” እንደለመድነው ጎትተን በጉልበት የናታቸውን ጡት ለማስጠባት አንሞክር። ብዙዎቻችን በተለይም በኔ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምንገኝ የኦሮሞ ልጆች፣ ያኔ ቆስለን የነበረው ዛሬ ግን ድኖልን ለማስታወሻ ብቻ ይዘን የምንዞረው ጠባሳ አለን። ዛሬ የቆሰልንበትን ምክንያትና ዘመን እንደ ታሪክ ማጣቀሻ እንጠቀምበታለን እንጂ አያመንም። ስለዚህ እባካችሁ ይህንን ጠባሳ እየነካካችሁ ለማቁስል አትሞክሩ። በብሄር መጨቆኑ በኛ ትውልድ ላይ ያብቃ፣ አሁን ያለውና ካሁን በኋላ የሚመጣው ትውልድ ደግሞ ማንም ኢትዮጵያዊ በማንነቱ የማይጨቆንበትና ኢትዮጵያም ህዝቦቿ በፍቅርና በመከባበር አብረው የሚኖሩባት ዲሞክራሲያዊት አገር እንድትሆን እንጣር።

) ከ85% በላይ የሚሆነው የዛሬው የኢትዮጵያ ትውልድ፥ ኢትዮጵያን የሚያውቃት እንደ ፌዴራላዊ አገር ነው። ለነሱ “አሃዳዊ ሥርዓት” “ጠቅላይ ግዛት” ወይም “ክፍለ ሃገር” እንግዳ  ነገር ነው። ስለዚህ አይመኙትም፣ ተመልሶ  እንዲመጣም የሚፈልጉበት ምክንያት አይኖርም። የሚያውቁት ይህንን የፌዴራል አስተዳደር ብቻ ነውና። አዎ በቁጣ ገንፍለው በየቀኑ ሰልፍ እየወጡ ቅሬታቸውን ያሰማሉ፣ ቅሬታቸው ግን በፌዴራላዊው ሥርዓት ላይ ሳይሆን የፌዴራላዊው ሥርዓት ህገ መንግሥታዊ ዋስትናዎች በትክክል ሥራ ላይ ባለመዋላቸው ነው። ይህ 85% የሚሆነው ህዝባችን የሚበጀውን አያውቅም ማለት ደግሞ አይቻልም። ታድያ እኛ ከ 15% የምናንስና ባብዛኛው ደግሞ የአሃዳዊው ሥርዓት ሰለባ ወይም ተጠቃሚ የነበርን አንጋፋ ትውልድ፣ ይህን ያህል ህዝባችን እስከነጉድለቱ የተቀበለውን ፌዴራላዊ አስተዳደር፣ እኛ ከዚህ ከሞቀ ባህር ማዶ ቤታችን ሆነን “ፌዴራላዊ አስተዳደር ላገራችን ጠንቅ ነውና አሽቀንጥረህ ጣለው” ብሎ “ለመምከር” የሞራል ብቃቱስ አለን?

) እንዲታወቅልኝ የምፈልገው አንድ ዓቢይ ጉዳይ አለ፥ በህይወት ዘመኔ ምንም እንኳ ፌዴራላዊ አስተዳደር በነበራቸው አገራት ለምሳሌ በሶቪዬት ህብረትና በዩጎዝላቪያ ኖሬም ሰርቼም ባውቅም፣ ፌዴራላዊ አስተዳደርን በተመለከተ ያደረግሁት ሳይንሳዊ ጥናት የለም። ስለዚህ ፌዴራላዊ አስተዳደር ለባለብዙ ብሄሮች አገራት ብቸኛው መፍትሄ  ነው የሚል ድምዳሜ ላይ አልደረሰኩም። በርግጠኝነት ግን ከራሴ ልምድ ተነስቼ ለማለት የምችለው፣ ኢትዮጵያ ትተዳደርበት የነበረው አሃዳዊ ሥርዓት ለኢትዮጵያ የግዛትም ሆነ የህዝቦች አንድነት ጠንቅ እንደነበረ ነው። ይህንን ደግሞ የምለው እንደው በስሜት ተገፋፍቼ ወይም በወሬ ተመርቼ ሳይሆን በራሴ እንደ አንድ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ከደረሰብኝ፣ በማንነቴ የተነሳ ብዙ ችግር ያየሁበት ስለሆነ ማንም የፖሊቲካ ሳይንስ ሊቅ ወይም “አፍቃረ አሃዳዊ” ሊያሳምነኝ የማይችል መሆኑን ስለማውቅ ነው። ስለዚህ የፌዴራላዊው አስተዳደርና የብሄሮች በክልል መዋቀር ለኢትዮጵያ የግዛትና የህዝቦቿ አንድነት ጎጂ ነው የምትሉ ወገኖቼ፣ አንገፍግፎንና  አሽቀንጥረን የጣልነውንአሃዳዊ ሥርዓትሳትጨምሩ፣ ሌላ የተሻለ የብሄሮችን መብት ጠብቆ ላገሪቷ ህዝቦች አንድ ላይ በዕኩልነትና በሰላም የመኖር ዋስትና ይሰጣል ብላችሁ የምትተማመኑበት የአስተዳደር ሥርዓት ካለ አምጡና እንወያይ።

ለመቋጨት ያህል፣ ዛሬ ባገራችን ውስጥ በመካሄድ ያለው ህዝባዊ ዓመጽ እዚያው በሚገኙ ብሩህ ልጆች እየተመራ ስለሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በዲያስፖራ ያለነው “መካሪ” ሁሉ ዋጋ እንደምናጣ ዕሙን ነኝ። ስለዚህ እዚህ ውጭ አገር ለሌላ መንግሥትና ህዝብ ጥቅም እየሰራንና እያገለገልን የድሎት ኑሮ የምንኖር የቀድሞ ኢትዮጵያውያን፣ ያለን ምርጫ ባገር ቤት ህዝባዊውን ዓመጽ የሚመሩትን ቢያንስ ቢያንስ “እንደኛው የተማሩ” ወይም የነቁ ዜጎች መሆናቸውን ተገንዝበን፣ ያካበትናቸው የፖሊቲካና ያስተዳደር ልምዶች ካሉን ማካፈል፣ ከሌለን ደግሞ አፋችንን ዘግተን መቀመጥ ብቻ ነው። ህዝቡ ራሱ የወያኔ የጭቆና አገዛዝ በቃኝ ብሎ በተነሳና በአግዓዚ ጥይት በተቆላ፣ እኛ እዚህ ዳር ቆመን የነሱን መቃጠል የምንሞቅበት የሞራል ብቃት የለንምና ቢቻል፣ ገንቢ የሆኑ ሃሳቦችን በማቅረብ የድርሻችንን እናዋጣ፣ አለበለዚያ ደግሞ፣ እያዩ ፈንገስ እንዳለው “የመናገር ብቻ ሳይሆን ዝም የማለት መብትም አለንና ዝም እንበል”።

*******

በቸር ይግጠመን

ጄኔቫ፣ ዴሴምቤር 25 ቀን 2017 ዓም

Similar Articles

Comments

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

BBC Afaan Oromoo: ODUU Owwituu, Amajjii 27, 2020

BBC Afaan Oromoo: ODUU Owwituu, Amajjii 27, 2020

OMN: ODUU GALGALAA (GURRAANDHALA 20, 2020)

OMN: ODUU GALGALAA (GURRAANDHALA 20, 2020)

21 million Chinese died of coronavirus – US intelligence officials intercept data

21 million Chinese died of coronavirus – US intelligence officials intercept data By James Alami (Web Archive) -- A new data intercepted by the United States...

Ethnic cleansing continued in Oromia Regional State by Abiy Ahmed

Ethnic cleansing continued in Oromia Regional State by Ethiopian government lead by Dr. Abiy Ahmed, Prime Minister of Ethiopia July 10, 2020 The Right Honourable Justin...

New Book: የተጠለፈ ትግል (The hijacked revolution) in pdf

Book: የተጠለፈ ትግል (The hijacked revolution) in PDF Via Aba Orma, September 3, 2019 የተጠለፈ ትግል (The hijacked revolution) Author: Mudhin Siraj Pages: 152 Language: Amharic Year: July 2019 To...